ድምጽ አልባው የጦርነት ጓዝ

 ዮርዳኖስ ፍቅሩ

የሰው ልጅ በተለያዩ ሁኔታዎች በሚፈጠሩ አስከፊ ክስተቶች ሕይወቱ ሊመሰቃቀል ይችላል። በግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና አገር ላይ በዘመናት መካከል የሚፈጠሩ ትላልቅ አሰቃቂ ኹነቶች አንዴ ተከስተው ከመረሳት ይልቅ፣ ለረጅም ጊዜ በልቡና ውስጥ ተሸሽገው አንዳች ዓይነት ጫናን ያሳድራሉ። በውጤታቸውም የቀደመ ማንነትን ያመሰቃቅላሉ። አሰቃቂ ኹነቶቹ በስሜት ወይም አእምሮ ላይ የሚያሳርፉት ጉዳት በህክምናው ዘርፍ “ትራውማ” ተብሎ ይጠራል።

“ትራውማ” የግሪክ ቃል ሲሆነ “wound” ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አቻ ትርጉም አለው። በአማርኛ “ ቁስል” የሚል ፍቺን ይሰጣል። ቃሉ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው የአእምሮ ቁስልን ለመግለጽ ነው። በውጫዊው የአካል ክፍላችን ላይ የሚከሰት ቁስል ለእይታ ግልጽ ሲሆን፣ የአእምሮ ቁስል ግን በግልጽ በአይናችን የማናየው ጉዳቱ ግን በሚታየው አካል ላይ ከሚፈጠረው ቁስልና ጠባሳ ይልቅ የሚቆጠቁጥና በባህሪና በድርጊት የሚገለጥ ነው።

የሥነ ልቡና አጥኚዎች ጉዳዩን አስመልክቶ በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል። በተካሄዱ ጥናቶች፣ የአእምሮ ቁስል ወይም ትራውማ በአንድ ሰው ቀጣይ ሕይወት ላይ ተጽእኖ ካሳደረና ጥላ እያጠላ ከዘለቀ ግለሰቡ ለድኅረ ሰቀቀን ጭንቀት (Post Traumatic Stress Disorder (PTSD)) እንደሚዳረግ ተረጋግጧል። የተጠቂውን ማንነት ከማወክ አልፎ የማኅበረሰብን ነባር እሴት የሚያናጋ፤ የማኅበረሰብ የኅልውናው መሠረት የሆኑ የማንነት መገለጫዎችን በመግፈፍ ለእሴቶቹ የነበረውን ዋጋ የሚያወርድ፤ የሕይወትን ጣዕም የሚያሳጣ እና ዛሬን በቅጡ መኖር ትቶ ወደ ቀደሙ መልካም ጊዜያቱ በትዝታ ተጓዥ የሚያደርገው መሆኑም ተመላክቷል። በተጨማሪም፣ የስሜት ጉዳት ሰለባው በመልካም ቀናቱ ትዝታ መጽናናትን እንዳያተርፍ እንኳ፣ የአሰቃቂው ኹነት ትውስታ መሰናክል እየሆነ ደስታውን የሚነጥቀው መሆኑንም ማየት ተችሏል።

ለአእምሮ ቁስል መከሰት ምክንያት የሚሆኑት እንደ ጦርነት፣ የመኪና አደጋ፣ ባልንጀራን በሞት መነጠቅ፣ ተገዶ መደፈር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና የመሳሰሉት ያልተጠበቁ አሰቃቂ ክስተቶች ናቸው። በዚህ ክስተት የስሜት ጉዳት የሚደርስበት የመጀመሪያው ተጠቂ ወይም ጉዳቱን በአካል የተጋፈጠው ሰው ብቻ ሳይሆን፣ አሰቃቂ ክስተቱን በማየት ወይም በመስማት ጉዳቱን በስሜት በተጋራው ሰውም ጭምር ነው። ለአእምሮ ቁስል መከሰት እነዚህ አሰቃቂ ክስተቶች መንስዔ ናቸው ሲባል አደጋዎች ሲደርሱ የነበረው እያንዳንዱ ትዕይንትና አደጋው በተከሰተበት ቅጽበት በተጎጂው ላይ የተፈራረቁበትን በቅጡ የማያስታውሳቸውን ስሜቶችን ሁሉ የሚያካትት ስለመሆኑ Geoffrey H. Hartman፣ On Trau­matic Knowledge and Literary Studies፣ (1996:540). በተሰኘው መጣጥፋቸው ላይ ያስረዳሉ።

የአእምሮ ቁስል ተገቢውን ህክምና ካላገኘ በቀደመው ዘመን የተከሰቱና የተከናወኑ ኹነቶች አሻራ በመጪው ዘመንም/ በቀጣይ ትውልድም ላይ ያርፋል። ይህንን የተረዱ አገራት ለምሳሌ – አፓርታይድን በመቃወም በደቡብ አፍሪካ ለተደረገው እንቅስቃሴ፣ በጀርመኑ የናዚ ጦርነት እና ለተፈጥሮ አደጋዎች ለአእምሮ ቁስል ለተጋለጡ ሰዎች እንደ “Center for victims of Torture” ፣ “Trauma and PTSD treatment and Re­habilitation center” እና “Trauma survi­vors center” የመሳሰሉ ከትራውማ ማገገሚያ ማዕከላትን ያቋቁማሉ። ይህ አገራት የሰጡት ትኩረት የትራውማን አሳሳቢነትና ሊታከም የተገባው ህመም መሆን ያረጋግጣል።

ተገቢውን ህክምና ያላገኘ ተጎጂ ወደ አጥቂነት ወይም ተበቃይነት በመቀየር ሌላ ተጠቂ እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። Maercker (2004) “Revenge after Trauma” በሚል ርዕስ ባቀረቡት መጣጥፍ ‘በቀል’ መልካም ያልሆኑ ገጠመኞችን ተከትሎ የሚሰጥ ምላሽ እንደሆነ ገልጸው፣ ከአሰቃቂ ክስተቶች በኋላ የሚፈጠሩ የቁጭት፣ ምሬት፣ እልህ እና እነዚህን መሰል ስሜቶች ወደ በቀል ስሜት፣ ስሜቱም አስከፊ ውጤትን የሚያመጣ እርምጃን ወደ መውሰድ የሚመራ እንደሆነ ያስረዳሉ (ገጽ፣ 41- 69)። ከዚህም የተነሳ በተለያዩ ዘመናት የነበረው ትውልድ/ ማኅበረሰብ ላይ ላዩን ሲታይ ጤናማ መስሎ ፤ ዳሩ ግን በአንዳንድ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የቀደመው ህመሙ እየተገለጠ የከፉ አለመግባባቶችንና ጦርነትን እያስተናገደ መሆኑ በየጊዜው በግልጽ የሚታይ እውነት ነው።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው፣ በቅዱስ አማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአእምሮ ስፔሻሊስት ሀኪምና የምርምርና ስልጠና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ንጉሤ፣ ትራውማ ከድንገተኛ አሰቃቂ ክስተት (melancholic event) በኋላ የሚከሰት የአእምሮ ችግር መሆኑን ጠቁመው፣ ዋናውና ህክምና የሚያሻው ህመም ተደርጎ የሚወሰደው ክስተቱ ካለፈ በኋላ በአእምሮ ላይ የሚፈጠረው “ድህረ ሰቀቀን ጭንቀት” መሆኑን ይገልጻሉ። እርሳቸው እንደሚያስረዱት፣ ይህ የሥነ ልቡና ጭንቀት የሚፈጠረው ብዙውን ጊዜ በራሳችን ወይም በሌላ የቅርብ ሰው ላይ ለሕይወት አስጊ ሁኔታ ሲከሰት ነው። ውጤቱም በተጎጂው የወደፊት ሕይወት ላይ የሚታይ ዓይነት ሲሆን ከግለሰቡም አልፎ አካባቢው ባሉ ሰዎችም ላይ ሊዛመት ይችላል።

የድህረ ሰቀቀን ጭንቀት (PTSD) መሠረታዊ ባህርይው ኹነቱ በተፈጠረ ቅጽበት ጉዳቱን ማየት የማይቻል መሆኑ ነው የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪና ትራውማ በማኅበረሰብ ላይ የሚያሳድረውን ተሻጋሪ የሥነ ልቡና ቀውስ መነሻ ያደረጉ የጥናት ሥራዎችን የሰሩት ኢየሩሳሌም ዳኜ ናቸው። ክስተቱ ያስከተለውን ጉዳት ወደኋላ በሚኖር ቀጣይ ሕይወት፣ ምናልባትም ምክንያቱን ይህ ነው ብለን አስታውሰን ልናገናኝ በማንችልበት የጊዜ ርቀት ላይ የሚገለፅ ሊሆን ይችላል። የዚህ ምክንያት ደግሞ ኹነቱ በተፈጠረበት ቅፅበት የሰው አእምሮ ድንጋጤና ፍርሃቱን ሊቋቋመውና ሊጋፈጠው ስለሚሳነው እንደማንኛውም አጋጣሚ በመደበኛ መልኩ መዝግቦት የማያልፈው በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደ ኢየሩሳሌም ማብራሪያ፣ የአሰቃቂ ኹነቶች ትውስታ ከመደበኛው ትውስታ በተለየ መንገድ በኢ ንቁ አእምሮ ክፍል ተሸሽገው የሚቀመጡ ናቸው። እንደማንኛውም ገጠመኞች ባሻን ሰዓት አስታውሰን ለራሳችንም ሆነ ለሌላ ሰው የምንተርካቸው አይነት አይደሉም። ትውስታው በእጅጉ ህመም አዘል ስለሚሆን ያንን ተቋቁሞ እያንዳንዱን ኹነት በቅደም ተከተል እያስታወሱ፣ በምክንያትና ውጤት እያስተሳሰሩ ትርጉም ወዳለው ትርክት ለመቀየር አቅም ያጥራል። ኹነቱ ከቀደመው የማኅበረሰብ ወግና ሥርአት ጋር የማይሰምር ወይንም ያፈነገጠ በመሆኑ፣ ትርጉም ለመስጠትና ለመግለጽ እንኳ የሚያዳግት ይሆናል። የጉዳቱን ጥልቀት ሲገልጹም፤ “ተጎጂው ለሰው ልጅና ለሚኖርባት ዓለም ያለውን እምነት ይሸረሽረዋል። ክስተቱ የተፈጸመበት ጊዜ ቢያልፍም፣ ያስከተለው ቀውስ ግን አያልፍም፣ ልርሳህ ቢሉትም አይረሳም፤ ማስታወሱም ጤና አይሰጥም። የስሜትና የባህርይ መናወጥ ያመጣል። ተጎጂውን ራሱን የገዛ ፣ ከቀልቡ የታረቀ፣ አመዛዛኝና ታጋሽ እንዳይሆን ያደርገዋል። ለተጎጂው ትላንቱ ጥያቄ፤ ዛሬው ስሜት አልባ፤ ነገው ተስፋ የለሽ ስለሚሆንበት ለዓለም፣ ለሕይወት፣ ለራሱም ሆነ ለሌሎች ያለው አመለካከት ይለወጣል። በውጤቱም፣ ከማህበረሰቡ ባህል፣ እምነትና ልማድ ያፈነገጠ ሲያደርገው፣ እንደ ማህበረሰብም እርስ በርስ የሚያስተሳስረውን ሰንሰለት ያላላዋል። ባስ ሲልም ይበጥሰዋል” ይላሉ። አያይዘውም ይህ ደግሞ በማኅበረሰብ መካከል አለመተማመንን እንደሚያሰፍን ፤ ለአለመግባባትና ማቆሚያ ለሌላቸው ግጭቶችም መነሻ እርሾ እያስቀመጠ እንደሚዘልቅ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ህክምና ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና የጥቁር አንበሳ የጤና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ በቅርቡ ከሸገር የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፣ በተለይ በጦርነት ወቅት በሚፈጠር የሥነ ልቡና ቀውስ ተጎጂ የሚሆነው ጉዳት የደረሰበት ሰው ብቻ ሳይሆን ጉዳት አድራሹም ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል። በአካል ላይ የሚወጣ ቁስል ተገቢ ህክምና ካገኘ በኋላ ሲድን ቁስልነቱ ጠፍቶ ጠባሳ ብቻ ይሆናል፤ ጠባሳው ደግሞ ምልክትን ብቻ ትቶ የሚሄድ እንጂ የህመም ስሜት አይኖረውም። ልክ እንደዚሁ የማኅበረሰብ የሥነ ልቡና ቀውስን በአግባቡ ማከም ከተቻለ አሰቃቂ ክስተቱ የፈጠረውን ስጋት፣ ፍርሃት እና በሰውም በፈጣሪም ላይ እምነት ማጣት የመሳሰሉ የድኅረ አሰቃቂ ክስተት ወይም ጦርነት የሥነ ልቡና ቀውስ መገለጫዎችን ማጥፋትና ትውስታውን ብቻ ማስቀረት ይቻላል የሚሉት ዶክተር ዳዊት፣ ነገር ግን ለማኅበረሰብ የሥነ ልቡና ችግር ትክክለኛ መፍትሔ እየሰጠን የቀውስ ፋይሎችን እየዘጋን ባለመሄዳችን ያልተፈወሱ ያመረቀዙ ብዙ ቁስሎች ለማያቋርጡ ቀውሶች እየዳረጉን እንዳሉ ተናግረዋል።

ጦርነትና የሥነ ልቡና ቀውስ በኢትዮጵያ

በአገራችን በተለያዩ ዘመናት ማኅበረሰብን ለጋራ የሥነ ልቡና ቀውስ የዳረጉ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ከ1966ቱ አብዮት መፈንዳት በኋላ የተለያየ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ባላቸው ቡድኖችና መንግሥት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት በወለደው ግጭት የተከሰተው የእርስ በእርስ እልቂት አሳዛኝ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። በዘመኑ የተፈጸሙ የብዙዎችን እልቂት ያስከተሉ ግድያዎች እንግዳና ለአእምሮ የከበዱ እርምጃዎች፣ ፈጣንና እጅግ አስደንጋጭ መቅሰፍቶች በዘመኑ በነበረው ማኅበረሰብ ላይ የስሜት ጉዳትን እንዲሁም የሥነ ልቡና ጫናን አስከትለዋል።

ይህ ጉዳት በዚያን ጊዜ ብቻ ተከስቶ ስላለመክሰሙ ወይም ጠባሳ ሆኖ ስለመቀመጡ በዘመኑ በነበረውና “ያ ትውልድ” በሚል በሚጠራው ትውልድ ዛሬም ድረስ ጊዜውን ተንተርሰው የሚጻፉ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ማሳያዎች ናቸው። ይህንንም ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ “ፍካሬ ልቡናና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ምንና ምን ናቸው፤ ጌታና ሎሌ? መጻተኛና ቤተኛ? ወይንስ አቻ ለአቻ?” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት “ከ2000 ዓ.ም. በኋላ በ “ያ ትውልድ” አባላት ተጽፈው እየታተሙ ከሚወጡ ባዮግራፊ ነክ ድርሰቶች መሃል ጥቂት የማይባሉት – ለምሳሌ የቆንጂት ብርሃኑ ምርኮኛ፣ የሕይወት ተፈራ ማማ በሰማይ ፣ የካሕሳይ አሲምባ – እጅጉን የዘመናቸው ሕማም ቅኝቶች ናቸው።” በማለት ዘመኑ ጥሎት ያለፈውን ሥነ ልቡናዊ ቀውስ ህመም አመላክተዋል።

እነዚህ ባለታሪኮች፣ በጽሑፎቻቸው ተስፋ አድርገው የታገሉለት ርዕይ አለመሳካቱ የሚያንገበግባቸው፤ በዘመኑ የተፈጸመውን እልቂት እንደ ሰመመን የሚያስታውሱ እና ከዚህ ትውስታም መውጣት ያልቻሉ ናቸው። በእነርሱ መኖርና አብረዋቸው ታግለው ሕይወታቸውን በከፈሉ ወዳጆቻቸው መሐከል ያለው ድንበር ምንድነው እያሉ ግራ ሲጋቡ የሚስተዋሉ እና የሕይወት ትርጉም ሲጠፋበቸውና የባዶነት ስሜት ውስጥ ሲገቡ የሚታዩ ናቸው። ዘመኑ አንድ ፈውስ የሚሻና ከደረሰበት የሥነ ልቡና ቀውስ የተነሳ አብዝቶ ወደኋላ የሚጓዝ ቆዛሚ ትውልድ ማፍራቱን በመጽሐፍቱ ላይ ከተደረጉ ጥናቶች እናስተውላለን።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት የደረሰው ዘግናኝ ጥፋት፣ ጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ መኖሪያ ቤት ማቃጠል፣ ማፈናቀል እና ሌሎችም የተፈፀሙ ወንጀሎች ሁሉ ያለፈው ዘመን ትራውማ ውጤት መሆናቸውን ኢየሩሳሌም ይናገራሉ። በጦርነቱ የደረሰው የገንዘብና የቁስ ጉዳት እንዳለ ሆኖ፣ ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ግን ወዲያው ልናየው የማንችለው ነገ ከነገ ወዲያ ከመሰል አዙሪት እንዳንወጣ የሚያደርገን ሥነ ልቡናዊ ጉዳቱ ነው ሲሉም ያክላሉ። እንደ እርሳቸው ሐሳብ፣ በአገራችን እየታዩና እየተሰሙ ያሉ ያልተለመዱና በምንኖርበት ባህልም ሆነ እምነት ተቀባይነት የሌላቸው ድርጊቶች ቀጥታ ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑትን ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን፣ በሩቅ ሆነን በምንሰማውም ላይ ሳይቀር ሥነ ልቡናዊ ጉዳት ያስከትላሉ። ከዚህም የተነሳ እንደ ማኅበረሰብ፣ በተለይም እንዲህ ካለው ምስቅልቅል በኋላ በሚኖር ቀጣይ ጊዜ ለሚገለጠው ለድኅረ ሰቀቀን ጭንቀት (PTSD) ለመጋለጥ በጣም ምቹ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ይከትታል።

የሥነ ልቡና ቀውስ የደረሰበት ተጠቂ፣ ጉዳቱ በማኅበረሰብ መካከል በሚኖረው ተግባቦት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖን የሚያሳድርበት መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር መሀመድ፣ ለአእምሮ ቁስል ወይም ከአስደንጋጭ ክስተት በኋላ ለሚፈጠር ድኅረ ሰቀቀን ጭንቀት የተጋለጠ ሰው ከባልንጀሮቹ፣ ከቤተሰቡና ከአጠቃላይ ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረው ግንኙነት እንደ ቀደመው እንደማይሆንና ችግሩ ወደ ጎን በመስፋፋት በማኅበረሰብ ጤና ላይም ከባድ ጫናን እንደሚያሳርፍ ይገልጻሉ።

ጫናው በይበልጥ በተፈጥሮ ስስ ስሜት ባላቸው ህጻናትና ሴቶች ላይ ይበረታል የሚሉት ዶክተር መሀመድ ከደረሰባቸው ጉዳት ለማገገም አጠገባቸው ረዳት በሌላቸው ወይም እርዳታ ማግኘት በማይችሉበት ስፍራና ሁኔታ ውስጥ ያሉና በሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦችም ለሥነ ልቡና ጉዳት ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ይላሉ። አያይዘውም ይህ የአእምሮ መታወክ የገጠመው ሰውና ለሥነ ልቡና ቀውስ የተዳረገ ማኅበረሰብ ቀጣይ ማንነቱ ላይ ክፉ አሻራን እያሳረፈ ሊዘልቅ፣ ጫናውንም ይበልጥ እያበረታ ሊሄድ እንደሚችል ሲገልጹ “ለሥነ ልቡና ጉዳት የተጋለጡ ልጆች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንደቀድሞው ለመከታተል ይቸገራሉ። ይህም የነገ ሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። አንዲት የአስገድዶ መደፈር የደረሰባት ልጅም የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ፤ የትዳር ሕይወት ለመመስረትና ለመምራት ትቸገራለች” በማለት በምሳሌ ያስረዳሉ።

የሥነ ልቡና ቀውስ ህክምና

የሥነ ልቡና ቀውስን ማከም መቻሉ ጥሩ ዕድል መሆኑን የሚገልጹት ኢየሩሳሌም፣ እንደ ሁልጊዜው ችግሩን ሸፋፍነን እንለፍ ማለት ግን፣ ቀን ቆጥሮ የሚፈነዳ ቦምብ ቀብሮ እንደመሄድ ነው ይላሉ። የፈውስ ሂደቱ ጥንቃቄና ዝግጅት እንደሚፈልግ ሲገልጹም የባለሙያዎች ስራ መሆኑም መዘንጋት እንደሌለበት፣ አካሄዱ ፖለቲካዊ ብቻ መሆን እንደማይገባው ወይንም የፖለቲካ ሰዎች አጋዥ የሚሆኑበት እንጂ በእነርሱ መካከል ብቻ የሚከወን እንዳልሆነ ያስረዳሉ። የፈውስ መንገዱ አንድ ብቻ ላይሆን ይችላል። ሌላ ቁስልና ህመም እንዳይፈጥር ግን፣ ሕግና ስርአት በተበጀለት መንገድ በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት መከወን አለበት። አላማውን የልቦና ማንፃት ብቻ አድርጎ ቀጥታ ተጎጂዎቹ ላይ መስራትም ያስፈልጋል። በሌሎች አገራት፣ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ በእውነትና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን የተሰሩ ስራዎች አሉ። ያንን ማጤንና ለእኛ እንዲስማማ አድርጎ መተግበር ይቻላል። ሆኖም ግን መጀመሪያ ይህን ማሰብና ማከናወን የሚያስችል የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አገርና ሥርዓትን ማበጀት ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ። በሥነ ልቡና

ሕክምና በታካሚው ዘንድ የደህንነት ስሜትና እምነት ማሳደር ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ በመጠቆምም ይህ በሌለበት ሁኔታ ከፍረጃና አድልዎ ነፃ ሆኖ የእኔንም ጉዳትና ቁስል አድምጦ እውቅና ይሰጠዋል፣ ህመሜን ይጋራኛል ብሎ ራሱን ለሂደቱ ዝግጁ የሚያደርግ አይኖርም። እንደ ማኅበረሰብ ሥነ ልቡናዊ ፈውስን ለመስጠትና ለማግኘት፣ አስፈላጊውን አመኔታ በመፍጠር የትላንት እጦትና ሰቆቃችንን ወደ ኩራትና ቤዛነት ትርክት መለወጥ መቻል በማለት ያሳስባሉ።

ዶክተር መሐመድም በበኩላቸው፣ የአእምሮ ቁስል ወይም ድህረ ሰቀቀን ጭንቀት ህክምና እንዳለውና ጉዳቱ የሚያስከትለውን ውጤት በማክሰም ትውስታውን ብቻ ማስቀረት እንደሚቻል፤ ነገር ግን ረጅም ጊዜን ሊወስድ እንደሚችል ይናገራሉ። በአእምሮና ሥነ ልቡና ጤና ላይ የሚሠሩ የህክምና ተቋማትና ባለሙያዎች የሥነ ልቡና ተጠቂዎችን ለማከም የተለያዩ ሳይንሳዊና ባህላዊ ወይም ማኅበረሰባዊ የሕክምና መንገዶችን እንደሚከተሉ ጠቅሰው፣ ለፈውሱ መገኘት ቀዳሚውንና ዋነኛውን ሚና መጫወት የሚችለው ማኅበረሰብ መሆኑን ይጠቁማሉ።

እንደ ዶክተሩ ማብራሪያ፣ ጉዳት የደረሰበትን ግለሰብ እያስተናገደ ያለ ማኅበረሰብ ተጎጂው ከጉዳቱ ጥልቅ ስሜት ወጥቶ የተሻለ ነገን እንዲያስብ፤ ለሥነ ልቡና ቀውስ የተዳረገው በሰው ከሆነም፣ ሁሉም ሰው ክፉ እንዳልሆነ በተግባር በማሳየት ሥነልቡናውን እንደ አዲስ ለመገንባት ቢያግዘው ተጎጂው ፈጥኖ ከተጠቂነት ስሜት እንዲወጣ ይረዳዋል። የሥነ ልቡና ቀውሱ በማኅበረሰብ ላይ የተፈጠረ ከሆነም፣ ማኅበረሰቡ ጉዳቱን በግልጽ ቢያወራው፤ እርስ በእርሱ ሐሳቡን ቢከፋፈል እና ባሕላዊ እሴቶቹን መከባበሩንና ሐይማኖቱን መልሶ በመገንባት ከቀውሱ ፈጥኖ ነጥሮ ለመውጣት ቢጠቀምባቸው እንደ ማኅበረሰብ ፈውስን ማምጣት ይቻላል። ባሳለፍነው ጦርነት በርካቶችን ለሥነ ልቡና ቀውስ የዳረጉ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የሚያወሱት ዶክተር መሀመድ፣ በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት ከግለሰቦች ሥነ ልቡና አልፎ ወደ ማኅበረሰብና አገር የሚሻገር መሆኑንም ይገልጻሉ።

ኢየሩሳሌምም “የእኛ አኗኗር ትስስራዊ እንደመሆኑ ግለሰብን ከማኅበረሰብ ነጥሎ ማየት ብዙም አያስኬድም። ግላዊ የምንለው አመለካከት፣ ባህርይ ወዘተ ከሞላ ጎደል ካደግንበት ማኅበረሰብ ባለን ጥብቅ ትስስር የተሰራ ነው። ግለሰባዊ ጉዳታችን ዞሮ ዞሮ ከማኅበረሰብ ይያያዛል፣ አንዱን ከሌላው ነጥሎ ማየት ብዙ አያስጉዝም። አሁን ያለንበት ወቅታዊ ምስቅልቅልም በግለሰብም ሆነ የማኅበረሰብ ስነ ልቡና ላይ ጫና ማኖሩ የማይቀር ነው።” በማለት የግለሰብ ሥነ ልቡናዊ ጉዳት ወደ ማኅበረሰብ የማኅበረሰብም ወደ ግለሰብ የሚጋባ እንጂ ተነጣጥሎ የሚቀመጥ አለመሆኑን ያስረዳሉ።

ማኅበረሰብን ከሥነ ልቡና ቀውስ ማውጫ መንገድ

እንደ ዶክተር ዳዊት ሐሳብ፣ ለመፍትሔው ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት እንደ አገር መጎዳታችንን መረዳት፤ ጉዳታችንም አብሮን የዘለቀ መሆኑን ማወቅ ነው። አሁን ባለንበት የጦርነት ወቅት ሊሠሩ የሚገባቸው የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችና ሰዎች እንዲያገግሙ የማድረጉ ተግባር እንዳለ ሆኖ የአሁኑ ጦርነት ብቻ ነው የጎዳን ብለን የምናስብ ከሆነ መፍትሔ አናመጣም፤ ቁንጽል የሚባል መፍትሔም የለም። ትራውማ ፈጣሪ ሁነቶችን በጥልቀትና በዝርዝር በማስታወስ ትርጉም ሊበጅላቸው ይገባል። አገራችን ከህመሟ እንድታገግም ተስማምተን፣ የዛሬው የአገራችን ሁኔታ መነሻው ዛሬ አለመሆኑንና በዘመናት ውስጥ ሲጎነጎን የቆየ መሆኑን መቀበል አለብን። ከጦርነትና ሥነ ልቡና ችግር አዙሪት ውስጥ ለመመላለስ የዳረገን ምንድነው? ብለን ችግሮቻችንን መለየት ይኖርብናል። በዚህ ሂደትም መጣራት ያለበት ተጣርቶ፤ መነገር ያለበት በይፋ ተነግሮ እና ወቃሹ ተወቅሶ ተጎጂው መጎዳቱ ታምኖ ይቅርታ ተጠይቆና ፍትህ አግኝቶ ልቦናው እርፍ እንዲል ማድረግ ይገባል።

ችግሩን መሸሽ ወይንም እንዳይነገሩና እንዳይወጡ መደበቅ ህመሙንና ታማሚነት ስር እንዲሰድ ከማድረግ ባለፈ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ነው የሚሉት ዶክተር ዳዊት በቀጣይ ይደረጋል የተባለው አገራዊ ምክክር ቁንጽል የሆኑ የፖለቲካ አለመግባባትን ብቻ በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ከማለፍ ይልቅ፣ የማኅበረሰብን የሥነ ልቡና ችግርና ያመረቀዘ ቁስል ለመፈወስም መጠቀም ያለብን ሊያመልጠን የማይገባ መልካም አጋጣሚ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ኢየሩሳሌም በበኩላቸው፣ የሥነ ልቡና ቀውሱን ለመፈወስ በጦርነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ማኅበረሰቦች በልባቸው የተቋጠረ ሐዘናቸውን፣ መናገሪያ መንገድና አድማጭ አጥተው እህህ ሲያሰኛቸው የኖረ ጉዳታቸውን እና በፍርሃትና ሽብር ታጅቦ የሚያሳድድ ክፉ ትውስታቸውን ማውጣት፣ ማደመጥ እንዲሁም እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ሰቆቃዊ ኹነቱን ህመማዊ ትውስታውን የሕይወታቸው ክፍል፣ እነሱነታቸው የተሰራበት አንድ ግብአት እንደሆነ አድርገው የእኔነት ወይንም እኛነት ትርክታቸውን እንዲሰሩ መታገዝ አለባቸው። “ሀዘንህ ሀዘኔ ነው” ብሎ አብሮ ማልቀሱ የሚያስገኘው ሥነ ልቡናዊ ጥቅምም ቀላል እንዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል ብለዋል። ይህም በጽሑፎች፣ በሙዚቃዎች፣ በሌሎች ባህላዊ ውጤቶች፣ ሐውልቶችን በማቆም፣ የመታወሻ ቀኖችን በመሰየምና ታሪክን በሙዚየሞች በማስቀመጥ ሊፈጸም እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ግለሰቦችንም ለማገዝም ሆነ ማኅበረሰብን ለመፈወስ እርዳታ ስንሰጥ፣ እርዳታውን እንዴት መሥጠት እንዳለብን ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል የሚሉት ደግሞ ዶክተር መሐመድ ናቸው፡፡ የእርዳታ አሰጣጥ መንገድን በሚገባ ካለማወቅ የተነሳ እናግዝ ብለን የጀመርነው የህክምና አሰጣጥ አይነት እንዲያውም ችግሩን የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል ሲሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻሉ። የሚሰጠው ህክምና የማኅበረሰብን እሴት፣ ልማድ ጥንካሬውንና ሌሎችንም ጉዳዮች ታሳቢ ባደረገ መንገድ መሆን እንዳለበት የሚያሳስቡት ዶክተሩ፣ እርሳቸው የሚሰሩበት የቅዱስ አማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጦርነት ምክንያት የስነ ልቡና፣ የስነ አእምሮ እና ማኅበራዊ ቀውስ የደረሰባቸውን አካላት ለማከምና ድጋፍ ለመስጠት የሚሰሩ የተለያዩ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ወደ ተግባር እየገባ እንደሚገኝ በመግለጽ ህክምናው ሙያዊ መንገዶችን ተከትሎ በባለሙያ መሰጠት እንደሚገባው ያስገነዝባሉ።

ዘመን መጽሔትም አገራችንን ለማያቋርጥ ጦርነትና አለመግባባት አዙሪት የዳረጋት ዘመናትን የተሻገረ የሥነ ልቡና ችግር በመፍታት መጪው ትውልድ ጤናማ ሥነ ልቡናና ሰላማዊ አገር እንድትኖረው ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣ ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

Recommended For You