ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አገር እንደመሆኗ በጊዜያት ውስጥ በርካታ አስገራሚ፣ አስደሳች፣ አስደንጋጭ፣ አሳዛኝ …ወዘተ ክስተትና ሁነቶችን ሳታስተናግድ አላለፈችም። እነዚህም በተለያዩ ወራትና ቀናት እንደሚሆኑም የሚጠበቅ ነው። ዘመናዊ በሚባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ግን የየካቲትን ያህል ታሪካዊ ክስተትና ሁነቶችን ያስተናገደ ወር ያለ አይመስልም። ከክስተትና ሁነቶች መካከል አንዳንዶቹ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ያገኙ፣ በአገር ውስጥ ማኅበረ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸውን እናገኛለን።
ከእነዚህ መካከል ጉልሆቹን በዚህ መጣጥፍ መዘከር እንሻለን። ጉልህ ሲባልም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ሁኔታዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የነበራቸው ማለታችን ነው።
የካቲት 23
በኢትዮጵያውያን ዘንድ እጅግ የሚያኮራ፣ ኢትዮጵያንም እንደ አገር በእጅጉ ያጸና ታሪካዊ ጉዳይ በየካቲት 23 ተከስቷል።
ለኢትዮጵያ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የታቀደባትን የቅኝ ግዛት ወረራ በመቃወም ውጤት ያስመዘገቡበት ወር የካቲት ነው። የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ኃይል ባሕር አቋርጦ አፍሪካዊቷን የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነችውን አገር ለመቆጣጠር ጎምዥቶ በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከቷል። በጊዜው የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ምኒልክ ሕዝባቸውን ይዘው ለነጻነታቸው ለመዝመት ተንቀሳቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን በየጦር አዝማቾቻቸው በኩል በውጊያው ተሳታፊ ለመሆን ወደ ዓድዋ ዘምተዋል። ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ንጉሥ ሚካኤል፣ ራስ ወሌ፣ ራስ አባተ ቧ ያለው፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ራስ ወሌ፣ ራስ መኮንን፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መንገሻ አቲከም ….. የሚጠቀሱ የጦር መሪዎች ነበሩ።
ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት ዘማች እጅግ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በባዶ እግሩ ተጉዞ መስዋዕትነት ሊከፍል ነው። ከዘማቾች አብዛኞቹም ገበሬዎች ነበሩ። በእነዚህ ጀግና መሪዎቹ ጥሪ ተሰለፈ። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ሸልዶ፣ ማርያም ሸዊቶ፤ አዲ ተቡን፤ ረቢ አርእየኒ በተባሉት የአድዋ ግርማ ሞገስ በሆኑ ተራሮች ላይ ጠላትን በእጅጉ በሚያስደነግጥ የመስዋዕትነት መንፈስ የተቆጡ ተናዳፊ ንቦች ጣሊያኖችን እየበረሩ ወረሯቸው። በእነዚያ ተራሮች ተተግነው ባሉ እጅግ በሚያስፈሩ ዘመናዊ መድፎችና ልዩ ልዩ የነፍስ ወከፍ ጦር መሣሪያዎች በታጠቁ የጣሊያን ወራሪ ወታደሮች በመደፈራቸው የተቆጡ የሃበሻ ጎበዛዝት በድንገት እየፎከሩ በየመድፎቻቸው ላይ ሲወድቁ፣ ያለመሳሳት ለሚወዱት ወገንና ተከብራ በነጻነት ለቆየችው አገራቸው ሲሉ ሕይወታቸውን በወኔ ገበሩ። ጣልያኖች ታላቅ ቁጣ በድንገት ወረደባቸው።
የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እስከ 7 ሺህ ጣሊያኖች ሲሞቱ ሁለት ሺህ ያህሉ ደግሞ ቆሰሉ። ሦስት ሺህዎቹ ደግሞ ጦርና ጎራዴ ለያዙ ጀግና ወታደሮች እጅ ሰጡ። ሌሎች ደግሞ ወደመጡበት ‹‹እግሬ አውጪኝ›› ብለው ሸሹ። ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፤ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ሸሽቷል። ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በብዙ ሺዎችና በመቶ ሺዎች
ከሚቆጠሩ ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል። በዚህች ቀን ዓለም የተገረመበት፣ ኢትዮጵያውያንም ቀጣይ ትውልዳቸው በነጻነት እንዲኖር ዋጋ የከፈሉበት ታላቅ የድልና የመስዋዕትነት ቀን ነበረች። እንደ የካቲት 23 በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ደማቅና አስደሳች ተጽእኖ የነበረው ቀን አልነበረም።
የካቲት 26
ከአድዋ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከምትዘክራቸው ነጻነትን ካጎናጸፏት የድል ቀኖች አንዱ በዚሁ በየካቲት ወር የሚዘከር ነው። የካቲት 26/ 1970 ዓ.ም ወሳኝ የኢትዮጵያውያን ድል የተመዘገበበት ቀን ነው።
የኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥን ተከትሎ ወያኔን የመሰለ ሾተላይ በኢትዮጵያ ውስጥ መብቀሉ ብቻ ሳይሆን የውጪ ኃይሎችም ዕድሉን ተጠቅመው ለመውረር ተንቀሳቅሰዋል። በ1970 ዓ.ም የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያ ላይ በምሥራቅ በኩል 700 ኪሜ.፣በደቡብ በኩል ደግሞ 300 ኪሜ. የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቷል።
ኢትዮጵያ በወቅቱ በብዙ የውስጥ ችግሮች (የመሐል አገር የሥልጣን ሽኩቻ፣ የነጻነት ጠያቂዎች በአገር ቤት፣ የተለመደው ድህነትና ረሀብ …) ተወጥራ የነበረ ቢሆንም ለዚያድባሬ ወረራ ግን ምላሽ ከመስጠት አልቦዘነችም። 300ሺ የሚሆን ሕዝባዊ ሠራዊት በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ ለውጊያ የተሰለፈ ሲሆን ፤የኩባና የደቡብ የመን መንግሥታት ጦራቸውን ይዘው ከኢትዮጵያ ጎን ተሰለፉ። ሶቭየት ኅብረትም በጀኔራል ፔትሮቭ የሚመሩ ወታደራዊ አማካሪዎቿን ለኢትዮጵያ ላከች።
የኢትዮጵያውያን ዘመቻ በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም ተጀመረ። ኢትዮጵያውያን በምድርና በአየር አስደናቂ ድል ተጎናጸፉ። ዘመቻው እስከ የካቲት ወር 1970 ዓ.ም ቆይቶ የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያ ሰራዊት ተከቦ መፈናፈኛ አጣ። በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ ገብቶ ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ድንበር ጥሳ እንዳትገባ ተማጽኖ በማቅረቡ የተከበበው የሶማሊያ ጦርም ወደ ሶማሊያ በ24 ሰዓታት እንዲወጣ በመደረጉ የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ካራማራ ተራራ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተውለበለበ። ይህ ቀን ለሶማሊያ ቅጥረኛ መሪዎች ትምህርት የሰጠ፣ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ክብር ያጎናጸፈ ሆኗል።
እጅግ በጣም አስገራሚ ሌላው የየካቲት የድል ዜና የኢትዮጵያ ሠራዊት በኤርትራ ወራሪ ሠራዊት ላይ የባድመን ድል የተቀዳጀው በየካቲት ወር ውስጥ በ1991 ዓ.ም ነበር።
የካቲት 12
በየካቲት ከተከሰቱ ነገሮች ሁሉም በአስደሳች አጋጣሚነት የሚዘከሩ ብቻ ሳይሆኑ በአሳዛኝ አጋጣሚዎች የሚዘከሩ ነገሮችም ሆነዋል ለዚህም የካቲት 12 በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ቀን ነው። ዓመቱ 1929 ዓ.ም ነበር። በአዲስ አበባ ሰማይ ስር የሆነውን ለማመን ይከብድ ነበር። የቅኝ አገዛዝ እና የአውሮፓ ፋሺስቶች የጭካኔ አካሄድ የተጋለጠበት አጋጣሚ ሆኗል። ይህን በተመለከተ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ በታሪክ መጽሐፋቸው ባወሱበት ቃል እናውሳው።
‹‹የኢጣሊያ ፋሺዝም ፅልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12/1929 ነው። አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት። ‹ጥቁር ሸሚዝ እየተባሉ የሚታወቁት የፋሺስት ደቀመዛሙርት በፋሺስቱ አገዛዝ አይዞህ ባይነት አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት። የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ። ቤቶች ከነዋሪዎቻቸው ጋር ጋዩ። እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ። የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ። ይህ የምሁራን ጭፍጨፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም በአገሪቱ ፖለቲካና ምሑራዊ ታሪክ ላይ የማይሻር ቁስል ጥሎ አለፈ። ይህ የፋሺስት ጭፍጨፋ በሌላ መልኩ በወራሪና ተወራሪ መካከል ያለውን ቅራኔ መካረር በማመልከት የጸረ ኢጣልያ ተቃውሞውም ከመጀመሪያው ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመደበኛ ወይም ከፊል መደበኛ ጦርነት ወደ ሽምቅ ውጊያ መሸጋገሩን አረጋገጠ።›› ባሕሩ ዘውዴ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 179።
በአጠቃላይ ሲታይ የካቲት 12 /1929 በአዲስ አበባ የሆነው አሳዛኝ የፋሺስት ሥራ ለኢትዮጵያውያን መራር የነጻነት ትግል መቀስቀሻ ለኢጣልያ ፋሺስቶች መጋለጫ ሆኗል ማለት እንችላለን።
ከዚሁ የካቲት ወር የሰማዕታት መታሰቢያ ሳንወጣ ያንን ተከትሎ ጣሊያኖች ከፍተኛ የኢትዮጵያን ጀግና አርበኛ አመራሮች የገደሉበትም ወር ነው። የካቲት 16/1929 ዓ/ም በግራዚያኒ የሚመራ የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት በዝዋይ አካባቢ የጦር አዝማቾቹን የራስ ደስታ ዳምጠውን እና የደጃዝማች በየነ መርዕድን አርበኞች በመምታት የእነዚህ ሁለት ታላላቅ ሰዎችን ሕይወት የነጠቀበትም ወር ነው። በተለይ ራስ ደስታ በትግራይ ተወላጁ በደጃዝማች ተክሉ መሸሻ ተይዘው በፋሺስት ኢጣልያ እጅ በመውደቃቸው በጥይት ደብድበው እንደገደሏቸው ሲታሰብ ምን ያህል በጭካኔ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር እንደተንቀሳቀሱ መረዳት ይቻላል።
የካቲት 11
የካቲት ወር አሳዛኝ አስደሳች ብቻ ሳይሆን መልካምም ክፉም ውርስና ቅርስ ያስከተሉ ነገሮችም ሆነዋል። ከእነዚህ ወሳኝ ክስተቶች አንዱ የካቲት አብዮት ፍንዳታ ነው። የአብዮት ፍንዳታ የካቲት ወርን ሙሉውን የሸፈነ ነበር። ኢትዮጵያውያን በጊዜው የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሣዊ መንግሥት የነበረበትን የፖለቲካ ሥሪት፣ የመልካም አስተዳደር ችግርና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በየካቲት ወር ውስጥ ከቀን ወደ ቀን እየሰፋና እያደገ የሚሄድ የሕዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን በ1966 ዓ.ም አስተናግዷል።
ይህ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ፍንጭ ማሳየት የጀመረው ከየካቲት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በሠራዊት ውስጥ በተነሡ የደሞዝ/የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ቢሆንም የካቲት 11/1966 የተደረገው የአገሪቱ መምህራን ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ ሲመታ አንዳች ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መፈንዳቱ ታወቀ። በግራ ዘመም ፖለቲከኞች እየተገፋ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የነበሩ የመከላከያ ሠራዊቱ አካላት በየካቲት ወር በተለያዩ ቀናት የተቃውሞ እንቅስቃሴው አካል መሆናቸውን ያውጁ ነበር። ያንንም ተከትሎ ሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች በተደራጀ መንገድ የሥርዓት ለውጥ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቁን በመቀጠሉ የካቲት ወር በኢትዮጵያ የነበረውን የዘውድ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወገደው አብዮት የፈነዳበት ወር በመሆኑ በልዩ ሁኔታ የሚዘከር ነው። አብዮቱ ድንገት የፈነዳ በመሆኑም ያልተቀናጀ ያልተደራጀ ነበር። የለውጥ ጥያቄው እየተጠናከረ ሲሄድ የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በዚያው በየካቲት ወር ካቢኔ ከመቀየር
ጀምሮ ሕገ መግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ኮሚቴ እስከ መሰየም የሄደ እርምጃ እየወሰደ ነበር። ይሁን እንጂ የአብዮቱ እንቅስቃሴ ያመጣው ውጤት ልዩ ልዩ ትርጉም የሚሰጠውና አንዳንዶች በጸጸት ሌሎች በኩራት አሁን ድረስ የሚዘክሩት ሆኗል።
ሌላው ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ያስከተለ ክስተት የታየው የካቲት 11/ 1967 ዓ.ም የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካል ሆኖ መወለዱ የታወጀበት ቀን መሆኑ ነው። ወያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ዘርን ማዕከል ያደረገ ጠባብ ብሔርተኛ የፖለቲካ ቡድንነትን አስተዋወቀ።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የሥርዓት ለውጥ ሂደት ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ ከትግራይ ተወላጅ የሆኑ የተማሩ ወጣቶች የትግራይን ነጻነት የሚጠይቅ ፖለቲካ እናካሂዳለን በሚል ደደቢት በሚባል በረሃ ውስጥ የትጥቅ ትግል በማድረግ ከኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ፍልሚያ የጀመሩበት ወር ነበር።
የወያኔ መወለድ በኢትዮጵያ አዲስ የጠባብ ብሔርተኞች እንቅስቃሴን የሚያስፋፋ አማራን ብሔርን በጠላትነት ፈርጆ በጥላቻ እያሳዩ የሚካሄድ የፖለቲካ ስልትን አስተዋውቋል። በመሆኑም ከማስማማት፣ ከማስታረቅ፣ ከማስተባበር፣ የተሻለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ኢትዮጵያን የሚያላላ፣ ተገንጣይነትን የሚሰብክ፣ ጥላቻን የሚያነግሥ ፖለቲካን አስፍነዋል። በኋላም አብዮቱን ተከትሎ ሥልጣን የያዘውን ደርግን በትጥቅ ትግል በመጣል ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላና ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ እስከአሁን ድረስ የተፈጠረው ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅል ከዚህ የሕወሓት መወለድ ተከትሎ የመጣ በመሆኑ ምን አልባትም እንደ የካቲት 12 በርካቶች ኢትዮጵያውያን ካለቁበት የሰማዕታት ቀን ሳንለይ ኢትዮጵያን የሚቀስፍ ኃይል የተወለደበት አሳዛኝ ቀን አድርገን ልናስታውስ እንችላለን።
ሌሎች
አነሰም በዛም በኢትዮጵያ ወሳኝ ፖለቲካዊ ለውጦች ያስከተሉ ክስተትና ሁነቶችን ስናስብ መረሳት የሌለባቸው ሌሎችንም መጥቀሱ ይጠቅማል። የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ጀማሪ ተደርገው የሚታሰቡት ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ደርስጌ ማርያም ላይ፣ አቡነ ሰላማ ቀብተዋቸው፣ ዘውድ ጭነው ዓፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተባሉት በዚሁ በየካቲት ወር 1847 ነበር። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ንግሥተ ነገሥታት በመሆን ዘውዲቱ ምኒልክ የተሾሙትም በየካቲት 4/1909 ዓ.ም ነበር።
ኢትዮጵያ በኦጋዴን ግምቱ 76 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የሆነ ሰፊ የተፈጥሮ ነዳጅ (ጋዝ) እንዳላት ቴኔኮ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ በኦጋዴን እንዳገኘ ያስታወቀው አብዮቱ ከመፈንዳቱ አንድ ዓመት በፊት የካቲት 15/1966 ዓ.ም ነበር። ይሁን እንጂ ነገሮች ወደፊት እንዳይራመዱ የሚያደርግ የአብዮት እንቅስቃሴ አሰናክሎት ቆይቷል።
በመጨረሻም የካቲት 13/2014
ከበርካታ አስደሳችና አሳዛኝ የየካቲት ክስተቶች በኋላ፣ የዘንድሮ የካቲትም አስደሳች ታሪክ አርፎበታል፡
ኢትዮጵያ የብዙ ዘመን በዓባይ ተፋሰስ የመጠቀም ሕልሟን በይፋ እውን ማድረግ የጀመረችበት ዕለት የካቲት 13/2014 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውጣ ውረድ ያየችበት አሁንም እያየችበት ያለችው ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመረችበት ዕለት ሆኗል። ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ጉዳይ አድርጎ እስከሚያየው ድረስ ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ውጥረት ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የተደረገው ትግል ድል የተመዘገበበት መሆኑን ፍንትው አድጎ የሚያሳይ የኤሌክትሪክ ኃይልና ብርሃን የተገኘበት ነው።
በአጠቃላይ የካቲት በርካታ ታሪካዊ ሁነትና ክስተቶች በኢትዮጵያ የከተቱበት ወር ነው ማለት እንችላላን።