ወራሪ እፅዋት በኢትዮጵያ

 መግቢያ

ወራሪ (መጤ) እፅዋት አገር በቀል ያልሆኑና፣ ነባር ከሆኑበት አገር ወደ ሌላ አገር ወይም አካባቢ በታወቁና ባልታወቁ መንገዶች ገብተው በፍጥነት በመዛመት በምጣኔ ሃብት፣ በአካባቢ፣ በሰው እና በሌሎች እንስሳትና እፅዋት ደሕንነት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ እፅዋት ናቸው። ወራሪ እፅዋት ከሰው ይዞታ ወይም ክትትል ቁጥጥር ውጭ ሲሆኑ፣ ከተወሰነ አካባቢ፣ ቦታ ወይም ድንበር በማለፍ ባልታሰበና ባልተገመተ ፍጥነት በብዙ አካባቢዎች ሊንሰራፉ ይችላሉ። በተለያዩ ዘመናት በፍላጎትም ሆነ በድንገት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሠላሳ አምስት ገደማ የሚሆኑ ወራሪ የእፅዋት ዝርያዎች ተመዝግበዋል። በመጤ እፅዋት መወረር ዓለም አቀፍ ተግዳሮት ነው። ለምሳሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተለያየ ብዛት ያላቸው ወራሪ እፅዋት ዝርያዎች ወደ አፍሪካ አህጉር እንደገቡ ተመዝግቧል (ደቡብ አፍሪካ 81፣ ሞሪሽዬስ 49፣ ስዋዚላንድ 44፣ አልጀሪያ፣ ኬንያና ማዳጋስካር እያንዳንዳቸው 37፣ ግብፅ 28፣ ጋናና ዚምባብዌ እያንዳንዳቸው 26፣ ወዘተ)። የወረራዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ ይታወቃል።

የዘርፉ ጠበብቶች ስለ ወራሪ እፅዋት መረጃዎችን በተለያዩ ጽሑፎች አበርክተዋል:: ለአብነት ያህል ደምል ተከታይ፣ ረዘነ ፍስሃዬ፣ ታዬ ተሰማ፣ ደምሰው ሰርፀ፣ ዋቅሹም ሽፈራው፣ ሰብስቤ ደምሰው፣ ታምራት በቀለ እና ጌዲዮን ታምሩን መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም በሳይንሳዊ መንገድ በጽሑፎች የሚያበረክቷቸው መረጃዎች፣ ጠቀሜታቸው የጎላ የሚሆነው በሙያው ለተሰማሩ ጠበብት ነው። በአንጻሩ ከዘርፉ ውጭ ላሉ ሰዎች በይዘታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው አመች ባለመሆናቸው ለብዙኃኑ የመረጃ ምንጭ የመሆን አቅማቸው ውስን ነው። በመጤ ወራሪ እፅዋት መንስዔነት የሚከሰቱት ችግሮች ጉዳት የሚያስከትሉት በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ላይ ስለሆነ፣ በመጠኑም ቢሆን ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጭበጥ በሚያስችል መንገድ መረጃዎችን ማበርከት ጠቀሜታ አለው ብለን በማመን ይህችን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ወሰንን። ይህች ጽሑፍ ሳይንስን የማለዘብ ዓላማ አንግባለች።

የወራሪ እፅዋት ባህርያት

ወራሪ እፅዋት የሚጋሩዋቸው የወራሪነት ሁኔታን የሚያደላድሉ ባህርያት አሉዋቸው። ዋና ዋናዎቹ ከፍተኛ የመራባት ባህርይ (በአጭር ጊዜ በስፋት የማንሰራራት ችሎታ)፣ ለእንስሳት ምግብነት ተስማሚ ሆኖ አለመገኘት (በብዛት የእንስሳት የምግብ ግብዓት አለመሆን)፣ በየብስ ላይ ሌሎች እፅዋት በማይበቅሉባቸው በተጎሳቆሉ አካባቢዎች በቀላሉ ለመራባት መቻል፣ ከተለያዩ የአካል ክፍሎች (በዘር /seed፣ ካለ ዘርም፣ በእፃዊ ተዋልዶ ወይም በኢ-ሩካባዊ መራቦ /Asexual reproduction/Vegetative reproduction/ በግንደ ወይም በስር) ራስን የመተካትና የመራባት ባህርይ ስላላቸው ነው። ስለሆነም ወራሪ እፅዋት፣ በወረሩት አካባቢ በአጭር ጊዜ መስፋፋት ይችላሉ።

ምንም እንኳን ከወራሪ (መጤ) እፅዋት ጥቃት ሊያመልጡ የሚችሉ መልክአምድሮች ባይኖሩም፣ ተጋላጭነታቸው ግን ይለያያል። ሁኔታዎችን በሦስት ዓቢይ ከፍሎች ለይቶ ማየት ይቻላል። (ሀ) የእፅዋት አዳባሪ ውህዶች ክምችት የበዛባቸው ወንዞች፣ ህይቆችና እርጥበታማ ቦታዎች፤ (ለ) የብስ ላይ ሞቃታማ፣ ዝናብ አጠር፣ በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት የደርሰባቸውና ደህንነታቸው የተዛባ ቦታዎች፤ (ሐ) የእፅዋት ሽፋናቸው የተመናመነና አዝጋሚ እድገት ያላቸው አገር በቀል የእፅዋት ዝሪያዎች የበዙባቸው አካባቢዎች ናቸው።

ወራሪዎች አገር በቀል ከሆኑበት ቦታ ወደ አዲስ ቦታ ሲዘምቱ፣ ሲያጠቋቸው ወይም ሲቆጣጠሯቸው ከነበሩ ጠላቶቻቸው (ግብዓቶችን ከሚሻሟቸው፤ ከሚበሏቸው እንስሳት፣ ተባዮችና ከሚያጠቋቸው በሽታዎች) ነጻ ይሆናሉ። ይህ አጋጣሚ በወረሩቡት ቦታ ባሉ አገር በቀል እፅዋት ላይ የበላይነትን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። አጠር ብሎ ጠሎ ሲታይ፣ የመጤ እፅዋት ወረራ ሊሳካ የሚችለው የዘር አቅረቦት ሲኖርና ሥነምህዳሩ ለመጤ እፅዋት ቅበላ ዝግጁ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው።

ወራሪ (መጤ) እፅዋት በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በጣም የተለያዩ ሥነምህዳሮች ባለቤት ስለሆነች (በቆላም በደጋም)፣ በምድር ወገብ አካባቢም ሆነ፣ ከዚያ ውጭ ነባር የሆኑ የእፅዋት ዝርያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ሊሰራጩ ይችላሉ። እነዚህ መጤ የእፅዋት ዝርያዎች የወረሩዋቸው አካባቢዎች በድምስሱ ሲፈተሹ፣ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ የረግረግ ቦታዎች፣ የመንገድ ዳርዳሮች፣ ከተሞች፣ በእፅዋት ያልተሸፈኑ አካባቢዎች እና በከብት መሰማሪያ አካባቢዎች ናቸው።

ከላይ እንደተጠቀሰው በተለያዩ ዘመናት በፍላጎትም ላይ ተመስርቶ ሆነ በድንገት (በአጋጣሚ) ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሠላሳ አምስት ገደማ የሚሆኑ ወራሪ እፅዋት ተመዝግበዋል። አንዳንዶች የአካባቢ ስሞችን ተጎናጽፈዋል። ከተግዳሮት አንፃር ስማቸው ብዙ ጊዜ የሚወሳው ጥቂቶች ናቸው። ከእነሱም እምቦጭ (Water hyacinth – Eichhornia crassipes)፣ ወያኔ ወይም ደርጊ ሃራ (Mesquite – Propsopis juliflora)፣ የወፍ ቆሎ (Lantana camara)፣ ሽምቤሮ (ኦሮሚፋ) ቡርካቲ (ሱማልኛ)፣ ዳንዳሮ (Mexican poppy – Argemone ochroleuca -)፣ ኮሸሽላ (ትግርኛ)]፣ ፋራሚሲሳ (ኦሮሚፋ) (Whitetop weed-Parathenium hysteropho­rus)፣ ሃራማ ዲህምብል (ሱማልኛ)፣ ስትራይጋ (purple witchweed – Striga hermonthica )፣ የቆቅ ድንች (Bean broomrape -Orobanche crenata) እና ኩሰኩታ (Field dodder- Cuscu­ta campestris) ናቸው።

ችግር ለመፍታት በሚደረግ ጥረት ተዛምዶ ያለታሰበ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ፓራቴኒዬም (Parathenium hysterophorus)፣ እንዲሁም ደረጊ ሃራን እንደ ተምሳሌነት ልንወስድ እንችላለን። ፓራቴኒዬም በመሠረቱ በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በሜክሲኮ አካባቢ ነባራዊ (አገር በቀል) እፅ ሲሆን ፣ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአጋጣሚ (በድንገት) ነው። ይህም በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረ ረሃብ መንስዔ ነበር። አረሙ ከእርዳታ እህል ጋር እንደገባ ይወሳል፣ በመጀመሪያም አገር ውስጥ እንደገባ የታወቀው (የታየው) ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በደሴ ዙርያ እና በትግራይ አካባቢዎች ነበር።

ወያኔ ወይም ደርጊ ሃራ የመሬት መጎሳቆልን (የአፈር መከላትን) ለመታደግ በባለሙያዎች ወደ አገር ቤት እንዲገባ የተደረገ እፅ ነው። ሲያጌጡ ይመላለጡ ዓይነት ችግር የተነሳው የወፍ ቆሎ (በላንታና ካማራ – Lantana camara) መንስዔ ነው። የዚህ እፅ አበቦች የሚያምሩ ስለሆኑ እና እፁም በአጭር ተከርክሞ ለግቢ/ጓሮ ማስዋቢያነት ስለሚያገለግል ነው ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አካባቢዎች ለመስፋፋት የበቃው። አሁን ይህ እፅ በብዙ አካባቢዎች እንደ አረም ነው የሚታየው። ያም ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች፣ ለተለያዩ ተውሳኮች መፈወሻ መድኃኒት በመሆን ያገለግላል። ለምሳሌ ለቁርጥማት ፣ ለጉንፋን፣ ለወባ፣ ለአስም መድኃኒትነት ጥቅም ላይ ይውላል በተጨማሪ ለአፈር ጥበቃም (በተለይ በነፋስ መንስዔ ለሚከላ አፈር) እንደ መከላከያ ሆኖ ያገለግላል።

የወራሪ እፅዋት ተግዳሮቶች በሁለት እፅዋት ማሳያነት እምቦጭ (Water hyacinth – Eich­hornia crassipes)

 የእምቦጭ መነሻ በምድር ወገብ ንፍቀ ክበብ ዙሪያ ከሚገኙ የላቲን አሜሪካ አገሮች ነው። እፁ በውሃ ላይ በመንሳፈፍ ወይም እርጥባማ ቦታዎች ላይ በመብቀል ሊራባ የሚችል ነው። የአካባቢ ሙቀታቸው በአማካይ 25–30 °C (77–86 °F) የሆኑና ከፍተኛ ሙቀታቸው ከ33–35 °C (91–95 °F) የማይበልጡ ቦታዎች ለእምቦጭ መስፋፋት የተመቹ ናቸው። እምቦጭ ከ19ኛው ምዕተ ዓመት በኋላ በአፍሪካ እንደተመዘገበ ይነገራል።ሆኖም ይህ አረም በ1790 (በዚህ ጽሑፍ ዓ.ም የሚል ካልታከለበት የሚጠቀሰው ዘመን የግሪጎርያን ዘመን አቆጣጠር ነው) ገደማ በአንድ የፈረንሳይ የእፅዋት ምሁር ወደ ግብፅ እንዲገባ እንደተደረገ ይወሳል። እምቦጭ በአፍሪካ በተለያዩ የውሃ አካላት፣ በተለይ በሃይቆች (ለምሳሌ ቪክቶሪያ፣ ማላዊ) እንዲሁም በወንዞች (ለምሳሌ ዛምቤዚ) በሰፊው ተሰራጭቷል። ከ1880 እሰከ 1990 ይህ አረም በብዛት የአፍሪካ አካባቢዎችን አዳርሷል (ለምሳሌ በ1937 ዚምባብዌ ፣1946 ሞዛመቢክ፣ 1950 ረዋንዳ ቡሩንዲ፣ 1956 ኢትዮጵያ፣ 1960 ታንዛንያ እና ዛምብያ፣ 1968 ማላዊ፣ 1982 ኬንያ፣ 1990 ቪክቶርያ ሃይቅ)።

እምቦጭ እስከ አሁን በ50 አገሮች ውስጥ ተስፋፍቶ አንደሚገኝ ተመዝግቧል። ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በ 1965 ዓ.ም ቆቃ ሃይቅ ዳርቻ ነው ተብሎ በሰፊው ቢነገርም፣ ከዚያ በፊት ግን በጋምቤላ ባሮ ወንዝና በአካባቢው ባሉ ረግረጋማ ቦታዎች በስፋት ይገኝ እንደነበረ ይታወቃል። ምናልባትም ነጭ ናይልን ተከትሎ ከታላቁ ቪክቶርያ ሃይቅ ወይም ከሱዳንና ከግብፅ የታላቁን ናይል ዳርቻ ተከትሎ ወደ ባሮ ወንዝ ተዛምቶ ሊሆን ይችላል። አሁን እምቦጭ ጋምቤላ ውስጥ በሚገኙ ወንዞችና ረግረጋማ ቦታዎች፣ በቆቃ ሃይቅ፣ በአንዳንድ አዋሽ ወንዝ ኩሬ አካባቢዎች እና አለም ጤና አጠግብ በምትገኝው ኤለን ሃይቅ ይገኛል። እምቦጭ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙት ሃይቆች አልፎ አልፎ የሚታይ ቢሆንም፣ የውሃ አካላቱ በውሃ ባህሪያቸው (በጨዋማነታቸው) ምክንያት ለወረራ እምብዛም የተጋለጡ አይደሉም። በዘመናችን እምቦጭ ከሱዳን እስክ ግብፅ ባለው አባይ ወንዝና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በጣና ሃይቅ እንዳንሰራራ ይታወቃል። ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር በወረራ መልክ ሰፊ ቦታ የያዘውና አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰው ግን በጣና ሃይቅ ነው። ምንም እንኳን ወረራው አሁን መጠነኛ መቀነስ ቢያሳይም፣ በአንድ ወቅት የእምቦጭ ወረራ በጣና ሃይቅ ላይ እስከ 197 ካሬ ኪሎ ሜትር ደርሶ ነበር። ይህ አደገኛና ፈጣን ወረራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሦስት ሚሊዮን ሰዎችን ኑሮ ያዛባና ለጉዳት የዳረጋቸው መሆኑ ተደርሶበታል።

የእምቦጭ መስፋፊያ መንገዶች

እምቦጭ ከስሩ እንደኳስ በአየር በተሞላ አካል በመታገዝ ከተንሳፈፈበት የውሃ አካል ከአንድ ሜትር በላይ ከፍ ለማለት በሚስችለው ግንዱ ላይ ከስምንት እስክ አሥራ አምስት የሚደርሱ ሃምራዊ ቀለም ያላቸው በጣም የሚያምሩ አበቦች ያወጣል። እንደፀጉር በበዙ ስሮቹ አማኻኝነት ከሚንሳፈፍበት ውሃ ውስጥ የሚያስፈልጉትን ውህዶች፤ ውሃና ኦክስጅን በማግኘትና በአንጸባራቂና ወፍራም ቅጠሎቹ ደግሞ እንደማንኛውም እፅ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ከአየር ውስጥ በመውሰድ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ባለማቋረጥ ለመራባትና ለመስፋፋት ይችላል። እምቦጭ መደበኛ የመራቢያ መንገዶቹ ሁለት ናቸው። ከስሩ ብዙ ተገንጣዮች በማውጣትና እያንዳንዱ ተገንጣይ በአጭር ጊዜ ራሱን የቻለ ግለ-እፅ በመሆን ነው። በተጨማሪም እያንዳንዱ የእምቦጭ አበባ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ለሠላሳ ዓመታት ገደማ ሳይበላሹ ሊቆዩ የሚችሉ ጥቃቅን ዘሮችን (seeds) ሊያፈራ ይችላል።

ሁሉም ዘሮች (seeds) በአንድ ጊዜ ቢበቅሉና ከዚያም የውሃው አካሉ ለእምቦጭ አመቺነቱ ቢቋረጥ የእምቦጭ መስፋፋት ሊገታና ዝርያውም ሊከስም ይችላል። ይህ እንዳይከሰት ግን የእምቦጭ ፍሬዎች ለሠላሳ ዓመታት የመብቀል ችሎታቸው ሳይቀንስ ለመቆየት ከመቻላቸውም በተጨማሪ፣ በዚህ ረጅም ዘመን ውስጥ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመብቀል እንዲችሉ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው። የዘሮችን የመብቀል አደረጃጀት፣ ምናልባት ሁኔታዎች ቢቀየሩ አመቺ ጊዜ እስከሚመለስ ድረስ ዘሮቹ ከውሃው በታች በሚገኘው ጭቃ ውስጥ (የዘር ባንክ) አድፍጠው ይጠባበቃሉ። ይህ የማድፈጥ ስልት ሁሉም ወራሪ እፆች በተግባር (በሥራ) የሚያውሉት ተፈጥሯዊ ዘዴ ነው። እምቦጭ በፍጥነት በማደግ ከሚታወቁት እፅዋት አንዱ ሲሆን፣ አመቺ ሁኔታ ሲያጋጥመው አንድ የእምቦጭ ዘለላ በአንድ ወር ውስጥ እስከ ሃያ ዘለላዎች ድረስ ሊባዛ ሲችል፣ በክብደት ደግሞ ከ160 ግራም መነሻ እስከ 1700 ግራም (1063% እድገት) ድረስ ጭማሪ ሊያሳይ ይችላል።

እምቦጭ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች

እምቦጭ በሃይቆች፣ በግድቦችና በወንዞች ውሃ ላይ ትነትን በማስከተል የውሃው መጠን በፍጥነት እንዲቀንስ ያደርጋል። የእምቦጭ መስፋፋት ለቀንዳአውጣዎችና ለቢምቢዎች አመቺ የመራቢያ አካባቢ ስለሚፈጥር ቢልያርዚያና ወባ እንዲስፋፉ ሁኔታውን ያመቻቻል። የፀሃይ ብርሃን ወደ ውሃ ውስጥ ዘልቆ እንዳይገባ ስለሚከለክል በፀሃይ ብርሃን አመካኝነት (እንደ እፅዋት) የራሳቸውን ምግብ ሊያዘጋጁ የሚችሉ ጥቃቅን ነፍሳትን (አልጌዎች) የሕልውና ተግባር ያስተጓጉላል። በዚያ መንስዔ እነዚህን ነፍሳት የሚመገቡ ሌሎች የውሃ ውስጥ ጥቃቅን እንስሳት ደግሞ ምግብ ለማግኘት ይቸገራሉ። በውሃ ውስጥ የሚገኘውን ኦክስጅን ከሚፈለገው መጠን በላይ ስለሚቀንስም ተጨማሪ ችግርን ያስከትላል።

በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳትን የሚመገቡ አዕዋፍ ለምሳሌ የተለያዩ የዳኪዬና የቆልማሚት (ፊላሚንጎ) ዝርያዎችና አሳ በል አዕዋፍና ለሎች እንስሳት ምግብ ስለሚያጡ ቁጥራቸው ይቀንሳል ወይም አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ይገደዳሉ። በዚህም ምክንያት የውሃ ውስጥና የአካባቢው የምግብ ሰንሰለት ይዛባል (ይበጠሳል)። የውሃ ውስጥ የምግብ ሰንሰለት መበጥስ፤ አሳዎች ምግብ ለማደን እንደልብ መንቀሳቀሻ ቦታ ማጣት፤ በእምቦጭ በተሸፈነው ውሃ ስር የውሃው ሙቀት መቀነስ፤ የአሳ ማስገሪያ ቦታዎች በእምቦጭ መሸፈን እንዲሁም ሌሎች ቀጥተኛ ያልሆኑ ምክንያቶች ስለሚከሰቱ የአሳ ምርት ይመናመናል (ያሽቆለቁላል)።

በውሃ ላይ የሚያንሰራራው እምቦጭ የጀልባዎችንና የሌሎች የመጓጓዣ መሳሪያዎችን እንቅስቃሴን ያውካል፤ የመስኖ ቦዮችን ይዘጋል፤ በኃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ያስከስታል እንዲሁም የውሃ አካላትን በስፋት በመሸፈን ውበታቸውን ይቀንሳል። እምቦጭ መርዛማና ጎጂ ውህዶችንና ንጥረነገሮችን ከውሃ ውስጥ የማስወገድ ባህሪው ከፍተኛ ስለሆነ ሕይወት አልባ ከሆነ በኋላ ሲበሰብስ፣ መርዙ በውሃው ወለል ባለው ጭቃ ውስጥ ስለሚጠራቀም ከፍተኛ የውሃ መበከልን ሊያስከትል ይችላል። በአጠቃላይ ሲታይ እምቦጭ በብዝሃ ሕይወት ደህንነትና በሰዎች ጤና ላይ ከባድ አሉታዊ ተፅእኖ ያደርሳል።

የእምቦጭን ወረራን መቆጣጠርያ ዘዴዎች

የእምቦጭ መቆጣጠርያ ዘዴዎች በተወረሩ ቦታዎች ነባራዊ ሁኔታዎች ለምሳሌ በወረራው መጠንና ስፋት፣ በአካባቢው የአየር ጠባይ እና ለሰዎች መኖሪያና ለጥብቅ ቦታዎች ቅርበት ይወሰናል። ዘዴዎቹም የጸረ-እፅዋት መርዞችን ርጭት (chemical methods) ፤ በሰው ኃይል ወይም መሳሪያዎችን በመጠቀም እምቦጭን ሰብስቦ ማስወገድ (mechanical methods) እና ተፈጥሯዊ ዘዴዎችን (Biological methods) ጥቅም ላይ ማዋል ሊሆኑ ይችላሉ።

ሀ. የጸረ-እፅዋት መርዞች ርጭት

ጸረ-እፅዋትን መጠቀም አነስተኛ ወጪና የሰው ኃይል ሊያስከትል ቢችልም ውጤታማነቱ ግን ውስን ነው። ምክንያቱም በሰፊ ቦታዎች ላይ የተጠቀምን እንደሆነ እምቦጭ ጸረ-እፅዋትን የመቋቋም ችሎታው ከፍተኛ ስለሆነ የተበጣጠሱ የእምቦጭ አካላት በውሃ ውስጥ ተበትነው እንደገና ሊያቆጠቁጡ ስለሚችሉ፣ ተጨማሪ መስፋፋትን ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም ጸረ-እፅዋቱ ኬሚካላዊ ውሁዶች እምቦጭን ብቻ መርጦ ስለማያጠቁ፣ ለሎች ጥቃቅን ነፍሳት (አልጌዎች) ትላልቅ እፅዋት አብረው ስለሚጎዱ የተፈራው የውሃ ውስጥ የምግብ ሰንሰለት መቃወስ፣ የምግብ መረብ መበጣጠስና በሰዎች ላይም የጤና እክል ሊያደርስ ይችላል።

ስለዚህ የጸረ-እፅዋት መርዞች ርጭት በሰፊ የውሃ አካላት ላይ የመጀመርያ አማራጭ አይደለም።

ለ. የሰው ኃይልና መሳሪያዎችን መጠቀም

የሰው ኃይልንና የተለያዩ እምቦጭን ከውሃ ውስጥ የሚያስወግዱ መሳሪያዎችን በሥራ ላይ በማዋል የእምቦጭን መስፋፋት ለመቆጣጠር መሞከር ለረጅም ጊዜ ችግር የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊሆን ይችላል። በ2003 በ3,000 ኪሎ ሜትር ካሬ በታላቁ ቪክቶሪያ ሃይቅ ላይ የተስፋፋውን እምቦጭ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአሥራ ሁለት ወራት ለማስወገድ ተችሏል። በወቅቱ የመጀመሪያው የማስወገድ ሥራ እስከ ሃያ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ አስከትሏል። ይህ አሠራር ዘላቂና አስተማማኝ ውጤት ለማስገኘት ሳይቋረጥ (በቀጣይነት) መተግበር ይኖርበታል። ስለሆነም ከፍተኛ ወጪ ሊያስከትል ስለሚችል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የኢኮኖሚ ውስንነት ላለባቸው አገሮች ትግበራው ከአቅም በላይ ሊሆንባቸው ይችላል።

ሐ. ተፈጥሯዊ ዘዴዎች

አንዳንድ ተመራማሪዎች የጸረ-እፅዋትን ጎጂነትና የእምቦጭ ማስወገጃ መሣሪያዎችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያከትለውን ወጪ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተፈጥሯዊ ዘዴ ፅንሰ ሃሳቦችን እንደአማራጭ አቅርበዋል። እነዚህ ፅንሰሃሳቦች በአሜርካ እምቦጭን ሊመገቡ የሚችሉ የተለያዩ ጢንዚዛ ዝርያዎች በሉዚያና፣ ሜክሲኮና ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኙ ሃይቆች ላይ ከ1970ቹ ጀምሮ በመሞከር በ10 ዓመታት ውስጥ የእምቦጭን ሽፋን በ 33% (ሰላሳ ሦስት በመቶ) ለመቅነስ ተችሏል። እነዚህ ጥንዚዛዎች የእንቦጭን ግንድ እየቦረቦሩ ስለሚመገቡ ፣ ተንሳፋፊነቱን በመቀነስ ወደ ውሃ ውስጥ እንዲሰጥምና ሕይወትአልባ እንዲሆን ያደርጉታል። በተጨማሪም ጥንዚዛዎቹ በእምቦጭ ላይ የተለያዩ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎችን ያስተላልፋሉ። ሆኖም የጥንዚዛዎቹ አማካይ እድሜ ከዘጠና ቀናት ስለማይበልጥ በዚህ ዘዴ የሚገኘውን ውጤት ውስን ያደርገዋል።

ምንም እንኳ ከጥንዚዛዎች የሚገኘው ውጤት ውስን ቢሆንም እስካሁን ይህ ዘዴ በ20 አገራት በጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ጥንዚዛዎችን እንደእምቦጭ መቆጣጠሪያ ዘዴ መጠቀም ሌላ ያልታሰበ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ጥንዚዛዎቹም መጤ ስለሆኑ፣ እምቦጩ ከተወሰነ መጠን ሲቀንስ ወደ ሌላ አገር በቀል እፅዋት እንደማይዘምቱ ምንም ዋስትና የለም።

የተወገደ እምቦጭን ጥቅም ላይ ማዋል

አንድ የውሃ አካል በስፋትና በአስጊ ሁኔታ በእምቦጭ ከተወረረ አዋጩ የመቆጣጠሪያ ዘዴ አቅምና ቴክኖሎጂው በፈቀደው ሁኔታ ወራሪውን መሰብሰብና ማስወገድ በመሆኑ ከተስማማን የተወገደውን ምርት የአካባቢን ጤንነት ለመጠበቅ በሚያስችል ሁኔታ ለመጠቀም የተለያዩ አማራጮችን መፈተሽ ያስፈልጋል። የአፈርን ለምነት ለማሻሻል ብስባሽ (compost) ማዘጋጀት ይቻላል። የናይትሮጅን ውህዶች ከበዙባቸው የውሃ አካላት የተሰበሰበ የእምቦጭ ክምችት የከብት ፍግ መጨመር ሳያስፈልግ ኮምፖስት በመደበኛ መንገድ ተዘጋጅቶ አፈር ላይ በመጨመር ምርት እንዲጨምር ማድረግ ይቻላል። ይኸም እውን ሊሆን የሚችለው እምቦጭ ለእፅዋት እድገት አስፈላጊ ውሁዶችን ከውሃ ውስጥ ለይቶ በማውጣት በሕዋሳቱ ውስጥ ስለሚያከማች የተዘጋጀው ኮምፖስት የአፈርን ካርቦን፣ ናይትሮጅን፣ ፎስፎረስና ፖታሽየም መጠን ያሻሽላል። የአፈር ኮምጣጥነትንም (acidi­ty) እንዲቀንስ ያደርጋል።

የእምቦጭ ኮምፖስት በተለይ ኮምጣጣ ወይም አሲዳማ አፈር ላይ የበለጠ ውጤት ያስገኛል። አሲዳማ የአፈር አይነት በባሕር ዳር ዙሪያ ባሉ ደጋማ ቦታዎች ስለሚበዛ፣ የእምቦጭ ኮምፖስት ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሄ ሊሆን ይችላል። ከውሃ ውስጥ ተለይተው በእምቦጭ ሕዋሳት ውስጥ የሚከማቹት ውህዶች መርዛማና ከባድ ማዕድናትን (heavy metals) ሊጨምር ስለሚችል ኮምፖስት ከመዘጋጀቱ በፊት ለጥንቃቄ ያህል ውሃው ውስጥ የሚገኘው የከባድ ማዕድናት መጠን ከሚፈቀደው መጠን በላይ አለመሆኑ መረጋገጥ (መታወቅ) ይኖርበታል።

ከእምቦጭ ባዮጋዝ ማምረት ይቻላል። ብዛት ያለው እምቦጭ ከውሃ አካል ተወግዶ በአቅራቢያው ሲከመር በክምሩ፣ ውስጥ የኦክሲጂን እጥረት ሊደርስ ስለሚችል፣ ባዮጋዝ ይፈጠራል። ይህ በካይ ጋዝ ሚቴን በመባል የሚታወቀው የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያመጡት ጋዝ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚሰደር ነው። ስለዚህ በራሱ መንገድ ጋዙ መፈጠሩ ካልቀረ፣ የእምቦጩን ክምር በመደበኛ ማምረቻ መንገድ በመጠቀም ባዮጋዝ ተመርቶ ጥቅም ላይ ቢውል ለአካባቢ ክብካቤና እምቦጩን ከውሃ ውስጥ ለማውጣት የዋለውን ወጭ ማካካስ ይቻል ይሆናል።

ከውሃ የተከላው የእምቦጭ ክምር ለወረቀት ምርት እንደአንድ ግብዓት መጠቀም ይቻላል። አንዳንድ የምርምር ውጤቶች የደረቀ የእምቦጭ ክምችት ከባሕርዛፍና ቀርከሃ ውጤቶች ጋር በመቀየጥ ጠንካራነቱ የላቀ ወረቀት ለማምረት የሚቻል መሆኑን ያመላክታሉ። ንጣቱ የወረቀትን መስፈርት የማያሟላ ቢሆንም፣ ካርቶንና ችፕውድ ለመስራት ግን በቂ መሆኑን ጥናቶቹ ያሳያሉ። ከእምቦጭ ለማገዶ የሚውል ብሪኬት ማምረት ይቻላል። ትርፋማነታቸው አጠራጣሪና ውስብስብ በሆኑ ሂደቶች ከእምቦጭ ክምር ባዮጋዝና ወረቀት ከማምረት ይልቅ ክምሩን በሰፊ ሜድ ላይ በማስጣትና በፀሃይ ሙቀት ብቻ በማድረቅ በወጭ ቆጣቢ መሳያዎች ብሪኬት አምርቶ ለማገዶነት በጥቅም ላይ ቢውል በትንሹም ቢሆን የእንጨት መተኪያ ሊሆን ይችላል። እንጨትን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በእምቦጭ መተካት ለአካባቢ ደህንነትና ለአየር ንብረት ለውጥ መቀነስ የሚሰጠው አስተዋጽኦ ከፍተኛ  መሆኑ አያጠያይቅም።

እምቦጭን ለመቆጣጠር ወይም ለማስወገድ ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይገባታል?

እስከ አሁን ድረስ በጥቅም ላይ ከዋሉት ዘዴዎች ይልቅ በተለያዩ መንገዶች ወደ ውሃ አካላት የሚገቡትን የእፅዋት አልሚ ኬሚክ ውህዶችንና (fertilizers) ከከተሞች የሚለቀቁ ዝቃጭ ፍሰቶችን መቆጣርና በሕግ መወሰን እንዲሁም የእምቦጭን መስፋፋት ከወዲሁ ለመከላከል የሚሻሉ ዘዴዎች እንዲሆኑ ይመከራል። እምቦጭ እንዳይስፋፋ የሚወሰዱት ቅድመጥንቃቄዎች ሳይተገበሩና የእምቦጭ መስፋፋት በቂ ትኩረት ሳይሰጠው ቀርቶ ጉዳት የማድረስ ደረጃ ላይ ከደረሰ ግን አይቀሬውን የኢኮኖሚ ጫና በመሸከም፣ በሰው ኃይልና በመሣሪያዎች በመታገዝ እምቦጭን በቀጣይነት ማስወገድ የተሻለና አማራጭ እርምጃ ነው። የተወገደውን የእምቦጭ ክምችት ሃይቁ ዳር ቢከመር፣ የሚቀጥለው የክረምት ዝናብ እንደገና ወደ ሃይቁ ጠራርጎ ሊመልሰው ስለሚችል፣ ወድያውኑ አድርቆ ከላይ የተጠቀሱትን እምቦጭን ጥቅም ላይ የማዋል ዘዴዎችን በፍጥነት መተግበር ያሻል።

የእፅዋት አልሚ ኬሚክ ውህዶች ፍሰትን መቆጣጠርና መከላከል የማያቋርጡ ሥራዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆን ለመብቀል ያደፈጡት ፍሬዎች አመቺ ሁኔታ እስኪመጣ ድረስ ሲጠባበቁ ተፈጥሮ የወሰነላቸውን ዕድሜ ይጨርሳሉ፣ ብሎም ወረራው ያከትማል። የተወገደውን እምቦጭ ግን የአጭር ጊዜ ገቢ ምንጭ በማግኘት ለማስወገድ ያስከተለውን ወጪ በትንሹም ቢሆን ማካካስ ይቻላል። ‘እምቦጭን በማጥፋት ጣናን እንታደገዋለን’ የሚለውን መፈክር ደግሞ ደጋግሞ በመዘመር ቆራጥነቱ ከሰው አዕምሮ ውስጥ እንዳይጠፋ ማድረግ ይገባል። ለዚህም የክልሉ መንግስት፤ የአካባቢው አርሶአደር፤ የልማት አጋሮችና ዩኔስኮ የመጀመሪያ ተጠሪዎችና ቀዳሚ ደራሾች መሆን አለባቸው። ጣና ሃይቅ የዩኔስኮ ጥብቅ ቦታ (Biosphere re­serve) ሆኖ መመረጡና ደንብና ግዴታውን በመከተል ጥብቅነቱን የማስከበር ሥራ የተጀመረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ወያኔ ወይም ደርጊ ሃራ – ፕሮሶፒስ (Prosopis juliflora)

ፕሮሶፒስ (Prosopis juliflora) በሜክሲኮ፣ ካሪቢያንና፣ መሃከላዊ አሜሪካ አገር በቀል እፅ ሲሆን በኢትዮጵያ በተልም አጠራር ወያኔ ሃራ ወይም ደርጊ ሃራ በመባል የሚታወቅ አስቸጋሪ መጤ ወራሪ እፅ ነው። ከፍተኛ ችግር እንዳስከተለ የሚወሳው ግን በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ባሉ አከባቢዎች ላይ ነው። የዚህ እፅ ቅጠሎቹ ዓመቱን ሙሉ የለመለሙና አረንጓዴነታቸውን ጠብቀው የሚቆዩ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ለፕሮሶፒስ በብዙዎች የቆላ ዛፎች ላይ የአሸናፊነት ባህርይ ያጎናጽፉታል። ብዙ የቆላ ዛፎች በድርቅ ወራት ውሃ ለመቆጠብ ቅጠሎቻቸውን ያረግፋሉ። ፕሮሶፒስ ልክ እንደ እምቦጭ በፈጣን እድገቱ የታወቀ ሲሆን በዚህ ጠባዩ በብዙ ቦታዎች የእፅዋት ሽፋናቸው በተራቆተ፤ አፈራቸው በጎርፍ በተሸረሽረ ወይም ማዕድናት ከተመረቱባቸው በኋላ በተረሱ ቦታዎች ላይ የእፅዋት ሽፋናቸውና የአፈራቸው ለምነት በፍጥነት እንዲመለስ በተመራጭነት ሲተከል ቆይቷል።

ፕሮሶፒስ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1965 ዓ.ም ጎሮ- ድሬዳዋ ችግኝ ጣቢያ ሲሆን፣ 1970ዎቹ ገደማ በዓለም የምግብ ለሥራ ፕሮግራም በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲስፋፋ ተደርጓል። አሁን በአፋር፣ ሱማሌ፣ ድሬዳዋ፣ አንዳንድ ኦሮሚያ አካባቢዎች፣ አማራ እና በደቡብ ቆላማ ቦታዎች የሚገኝ ቢሆንም በአፋር ክልል ግን የአዋሽን ወንዝ ተከትሎ ሰፊ ቦታ በመውረር የከፍተኛ ችግር መንስዔ ሆኗል።

ፕሮሶፒስ ምንም እንኳ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እየጎላ የመጣ ቢሆንም፣ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ያመጡት ሰዎች መልካም ጎኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደነበር ብዙ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ፕሮሶፒስ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ በወቅቱ ተከስቶ የነበረው ከባድ ድርቅና እሱን ተከትሎ የተስፋፋው በረሃማነትና የምግብ እጥረት እንደሆኑ ይገመታል።

በዚያን አስቸጋሪ ጊዜ ፕሮሶፒስን ተመራጭ የሆነው በድርቅ የተጎዱና የተጎሳቆሉ አካባቢዎች እንዲያገግሙ፤ ለከብቶች ጥላ እንዲሆን፤ የአፈር ልምላሜ እንዲሻሻል፤ ለከብቶች መኖ በፍጥነት ለማግኘት፤ የማገዶ እንጨት በቀላሉ ለሁሉም ለማቅረብ እና በረሃማነትን ለመዋጋት በማስቻሉ ነበር። ፕሮሶፒስ እንደየአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጉዳት ሊያደርስና ጥቅምም ሊሰጥ ስለሚችል “ትክክለኛ ዛፍ በተሳሳተ ቦታ” በመባል ይታወቃል።

የፕሮሶፒስ የመራቢያና የመስፋፊያ መንገዶች

ፕሮሶፒስ በዘርና (seeds) በግንጣይ ሊራባ ይችላል። ግንጣዩ እርጥብ ቦታ ካገኘ ወዲያውኑ ስር ሊሰድና ሊያቆጠቁጥ ይችላል። ዘሩ የተመቸ ሁኔታ ሲያጋጥመው በስድስት ሰዓታት ውስጥ ለመብቀል ይችላል። አንድ የፕሮሶፒስ ችግኝ በሦስት ዓመታት ውስጥ ማፍራት ሲችል፣ የፍሬው መጠን ግን በዕድሜውና በአካባቢው ተስማሚነት ይወሰናል። አንድ የፕሮሶፒስ ዛፍ በፍጥነት በማደግና ብዙ ቅርንጮፎችን ወደ ጎን በመዘርጋት ስሮቹን ደግሞ እስከ ስድሳ ሜትር ድረስ ወደታች በመስደድ በአካባቢው ይንሰራፋል። አንድ የፕሮሶፒስ ዛፍ እስከ አሥራ ሁለት ሜትር ርዝመትና አንድ ነጥብ ሁለት ሜትር (1.2 ሜትር) የወገብ ስፋት ድረስ ሊያድግ ይችላል የፕሮሶፒስ ዛፎች በአንድ ቦታ በብዛትና ተጠጋግተው ያደጉ እንደሆን፣ የአንዱ ዛፍ ቅርንጭፎች ከሌላው ዛፍ ቅርንጫፎች ጋር ስለሚነካኩ፣ የፀሃይ ብርሃን ወደመሬት ወለል እንዳይደርስ ይከለክላሉ። ስለሆነም በተጠለለው አካባቢ ሌሎች እፅዋት ለማደግ አይችሉም።

የፍሬው ግልፋፊና ገለባው ስኳራማ ጣዕም ስላለው የዱር እንስሳት፣ ግመሎች፣ ፍየሎችና የዳልጋ ከብቶች በጣም ይወዱታል። ደረቅ የፕሮሶፒስ ዘር (seeds) በቀላሉ ሲለማይቆረጠምና በእንስሳቱ ሆድ ውስጥ ስለማይፈጭ በቀላሉ ለመብቀል በሚያስችል ሁኔታ በበጠጣቸውና እበታቸው አማኝነት በወደቀበት ቦታዎች ሁሉ ይሰራጫል። እበት የሚያድበልብሉ ጥንዚዛዎችም ተጨማሪ የፍሬ ስርጭት ያከናውናሉ። አርብቶአደሮች ለከብቶቻቸው ማደሪያ አጥር ለመስራት ዛፉን ቆርጠው ሲጎትቱ ፍሬውን በየቦታው ያሰራጫሉ። እንዲሁም ከሰል አክሳዮችም ለፍሬው ስርጭት የተወሰነ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በክረምት ወቅት የሚከሰተው ጎርፍና የወንዞች ሙላት በተለያዩ አጋጣሚዎች በየቦታው የተበተነውን ዘር በፍጥነት ወደሚበቅልበትና ወደሚስፋፋበት ቦታ ያጓጉዙታል።

ፕሮሶፒስ የሚያደርሰው ጉዳት

ከላይ እንደተጠቀሰው ፕሮሶፒስ የተለያዩ የመሰራጫ መንገዶች ስላሉትና በተለያዩ የአየር ጠባዮችን መቋቋም እንዲሁም በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ለማደግ የሚችል ስለሆነ በማንኛውም ቦታ በመንሰራፋት ለሌሎች የአካባቢው አገርበቀል እፅዋት በአካባቢው የመኖር ዕድል እንዲያጡ ያደርጋል። ከስሩ የተለመዱ የእንስሳት መኖ እፅዋት በብርሃንና በእርጥበት እጦት ምክንያት እንዲጠፉ (እንዲወሰን) ያደርጋል። ከራሱ ዘር በስተቀር የሌላ እፅዋት ዘሮች እንዳይበቅሉ የሚከለክል ውህድ ወደ አካባቢው በመርጨት አንዳንድ እፅዋት እስከነአካቴው እንዳይበቅሉ ይገታል። ፕሮሶፒስ ግንዱና ቅርንጫፎቹ ላይ በረጃጅምና ጠንካራ እሾሆች የታጀበ ስለሆነ፣ እንዲሁም ጥቅጥቅ ያለ አስተዳደግ ስላለው እንስሳትና ሰዎች በፕሮሶፒስ ጫካ ውስጥ ለመተላለፍ ይቸገራሉ።

አንድ የፕሮሶፒስ ዛፍ በቀን መጠነ ብዙ ውሃ ስለሚወስድ (ስለሚምግ) የማገውን ውሃ ብዙውን እጅ ወደትነት ይቀይራል። በውሃአጠር ቦታ ያደገ የፕሮሶፒስ ዛፍ በረጅም ስሮቹ ከከርሰምድር ውሃ በማግኘት የውሃ ፍላጎት አሟልቶ የተረፈውን በሙሉ ዘወትር ልምላሜያቸውን ጠብቀው በሚኖሩ ቅጠሎቹ አማካኝነት በትነት እንዲባክን ያደርጋል። በፕሮሶፒስ በተወረሩ የአፋር አካባቢዎች በዝናብ ከሚገኘው ውሃ ከግማሹ በላይ በፕሮሶፒስ ምክንያት ይባክናል። በዚህም ምክንያት የአካባቢው የውሃ በጀት ስለሚቃወስ ለሌላ የተፈጥሮ አገልግሎቶች ሊውል የሚችለው የውሃ መጠን ይመናመናል። እነዚህ ኩነቶች ፕሮሶፒስ በአካባቢና በብዝሃ ሕይወት ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሲሆኑ በምጣኔሃብትም ላይ ተመሳሳይ ጉዳቶችን ያደርሳል።

ወራሪው እፅ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ እስካሁን በአፋር ክልል ብቻ 120,000.00 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ ሸፍኗል። በፕሮሶፒስ በተወረረው የአፋር ክልል ብቻ በቀን እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ሊትር ውሃ በትነት እንደሚጠፋ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። የመስኖ ቦዮችን ይዘጋል፤ የወንዞችን የፍሰት አቅጣጫዎች ይቀይራል፤ የግጦሽ መሬቶችን በመውረርና ከተግባር ውጪ በማደርግ የአርብቶአደሩን ኑሮ ያቃውሳል እንዲሁም የአርብቶአደሩን የአሰፋፈር ስብጥር በማዛባት በጎሳዎች መሃከል ያልተጠበቀ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል። በአሚባራ የጥጥ እርሻ፣ የመስኖ እርሻ መሰናዶዎችን የውሃ መስመር፣ ፓምፕዎችን ወዘተ ከጥቅም ውጭ አድርጓል። በእርሻዎች ውስጥ የመኪና መገናኛ መንገዶችን ጥቅምአልባ አድርጓቸዋል።

ፕሮሶፒስ የሚሰጣቸው ጥቅማጥቅሞች

ፕሮስፒስ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ሊሰጥ የሚችል እፅ እነደሆነም ይታወቃል። በተለያዩ አገሮች ፕሮሶፒስ ለሰው ምግብ፣ ለከብቶች መኖ፣ ለመድኃኒት ቅመማ ግብዓትነት፣ ለማገዶ፣ ከሰል ለማምረት፣ ለአጥር መሥሪያ፣ ለወረቀት ፋብረካ ግብዓት እና ለቅርጻቅርጽ ሥራዎች እንደሚውል መረጃዎች ያሳያሉ። የፕሮሶፒስ እሸት ልክ እንደባቄላ፣ አተርና ሽምብራ እሸት ጥሬው ወይም ተቀቅሎ በመጠኑ ሊበላ ይችላል። የእስፓኛ ቅኝ ገዥዎች ሜክሲኮን በወረሩ ጊዜ፣ ይህንን ፍሬ የሜክሲኮ ሕዝቦች ሲበሉ አይተው እነሱም እንደበሉና አልኮልም እንዳመረቱበት በታሪክ ተመዝግቧል። በተጨማሪም ከፕሮሶፒስ ዛፍ የሚገኘውን ሙጫ የመክሲኮ ሕዝቦች ለትኩሳት ማስታገሻና ለሆድ ሕመም መፈወሻ ይጠቀሙበት ነበር። የፕሮስፒስ ሙጫ መጠን ከጋም አራቢክ ሙጫ መጠን ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ቢሆንም በጥራቱ ግን አይተናነስም። የፕሮሶፒስ ግንድ በምስጥ በቀላሉ ስለማይጠቃ እርጥበትን ስለሚቋቋምና ስለማይበሰብስ ለባቡር መንገድ አግዳሚነት በጥቅም ላይ ዉሏል።

በሕንድ አገር የፕሮሶፒስ ፍሬ ፍየሎችንና ጥገቶችን ከሌላ የከብት መኖ ግብዓቶች ጋር ቀይጦ በመመገገብ አመርቂ ውጤት ተገኝቶበታል። በሕንድ እንዲሁም በሜክሲኮ በምግብ እጦትና በፕሮቲን እጥረት ለከሱና ለተጎሳቆሉ ህፃናት ከፕሮስፒስ ፍሬ ዱቄት የተዘጋጀ ምግብ በመስጠት በፍጥነት እንዲያገግሙ እንደሚያደርግ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የፕሮሶፒስን ወረራ ለመቆጣጠር ምን ማድረግ ይገባል?

የፕሮሶፒስ ወረራ በኢትዮጵያ ብዙ አካባቢዎችን የሸፈነ ስለሆነ ወረራውን ለመቆጣጠር ስልታዊ ዕቅድ ማውጣት ያስፈልጋል። ዕቅዱ ፕሮሶፒስን በጥቅም ላይ እያዋሉ መጠኑን መቀነስና በኅብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤን መፍጠር ብሎም ማዳበር ቢያካትት ጥረቱ በአጭር ግዜ ውጤታማ መሆን ይችላል ብለን እንገምታለን። የፕሮሶፒስ ዛፍ ግንዱ አጭርና የተወላገደ ስለሆነ ለግንባታ ሥራ ወይም ለጣውላ ምርት በፍጹም ተመራጭ አይደለም። ስለሆነም ለሌላ የበለጠ ጥቅም ለሚሰጥ ጉዳይ ማዋል ያስፈልጋል። አንዱም አማራጭ ከፕሮሶፒስ ግንድ ከሰል ማምረት ነው። የፕሮሶፒስ ከሰል ጥራት በጣም ተመራጭ ስለሆነ በአሜሪካ የምግብ ሱቆች ውስጥ በውድ ዋጋ ይሸጣል። ስለዚህ የግራር ዛፎችን ከማክሰል ይልቅ የሚታየውን የማገዶ እጥረት ለመቀነስና የግራር ዛፎችንም ከጥፋት ለመታደግ ይረዳል። የፕሮሶፒስ ከሰል ለማምረት የተደራጁ አክሳዮች መጠን በተመናመነ ጊዜ ወደሌላ አገርበቀል እፅዋት ዛፎች እንዳይዞሩ ሌላ አማራጭ የሥራ ዕድሎችን መፍጠርና አክሳዮችን ለአዲሱ አማራጭ ከመጀመሪያው ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

ሁለተኛው የፕሮሶፒስ ግንድ ለወረቀት ፍብረካ ተጨማሪ ግብዓት እንዲሆን ማድረግ ነው። የፕሮሶፒስ ግንድ ጠንካራ ስለሆነ ጥራት ያለው የወረቀት ፍብረካ ግብዓት ሊሆን ይችላል። ሆኖም የፕሮሶፒስን ዛፍ ጥቅም ላይ ለማዋል ተብሎ የወረቀት ፋብሪካ ከማቋቋም ይልቅ በወረቀት ምርት ላይ የተሰማሩትን ፋብሪካዎች በፕሮሶፒስ እንዲጠቀሙ መጋበዝና ማበረታታት አግባብነት አለው። በወረቀት ሥራ ላይ ቀደም ብሎ የተሰማራ ፋብሪካ ፕሮስፒስ ከአካባቢው ሲያልቅ ወይም መጠኑ ሲመናመን ፕሮሶፒስን ከመጠቀሙ በፊት፣ ለወረቀት ፍብረካ ይጠቀምባቸው ወደነበሩ ግብዓቶች በቀላሉ ይመለሳል እንጂ ፋብሪካውን ለመዝጋት አይገደደም።

የተቆረጡ ዛፎች እንደገና እንዳያቆጠቁጡና ወረራው እንዳያገረሽ ጉቶዎቹን ናፍጣ ወይም በጥቅም ላይ የዋለ የሞተር ዘይት በመቀባት ማቃጠል ያስፈልጋል። ወረራ ለመቆጣጠርና ለማሸነፍ ዛፎቹን ለተለያዩ ጥቅሞች በሚቆረጡበት ጊዜ ለፍሬ ያልደረሱትን ችግኞንም አብሮ ማስወገድና እዚያው ማቃጠል ይገባል። ይህ ሁሉ ጥረት ውጤት ሊኖረው የሚችለው የኅብረተሰቡ ይሁንታና የማያቋርጥ ተሳትፎ ሲኖረው ብቻ ነው። ተሳትፎው ደግሞ ከጥቅም፣ ተከፋይነትና ከንቃተ ሕሊና ጋር መያያዝ አለበት። የነቃና የጥቅም ተከፋይ የሆነ ኅብረተሰብ ለፕሮሶፒስ መከላከልና ማጥፋት ተግባር በማደራጀት “ፕሮሶፒስን በመቆጣጠር የአፋርን የግጦሽ መሬት ወደነበረት እንመልሰዋለን” የሚል መፈክር እንዲያነግብና ለሥራው ግንባር ቀደም ተዋናይና እንዲሁም ከተግባሩ ዋነኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይገባል።

በሌሎች ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በሚገኙ ለፕሮሶፒስ ወረራ ተጋላጭ የሆኑ ከተሞች ለምሳሌ አዋሽ ፣ መተሃራ፣ ንጂ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ባቱ፣ ሃዋሣና አርባ ምንጭ እንዲሁም ሌሎች ያልተጠቀሱ ከተሞች በዘመቻ መልክ የተለያዩ የወጣቶች ክበቦችን በመጠቀምና ፕሮሶፒስን እንዴት ማስወገድ እንዳለባቸው ስልጠና በመስጠት የፕሮሶፒስን የመስፋፋትና የወረራ አደጋ መከላከል ያስፈልጋል። የከተሞቹ መስተዳድር ፕሮሶፒስን ለአካባቢ ማስዋቢያና ለጥላ መትከል እንዲከለክሉና የተተከሉትንም ዛፎችን አግባብ ባለው ሁኔታ እንዲያስወግዱ ደንብና ግዴታ ማውጣት ይኖርባቸዋል።

መደምደሚያ

ወራሪ እፅዋት አንድን አካባቢ ከወረሩ በኋላ ወራሪዎችን ለማስወገድ የሚያስፈለገው ጉልበት/ወጭ ከፍተኛ ስለሆነ፣ በመጀመሪያ ወረራው አንዳይከሰት መጣሩና መከላከሉ ተገቢ አማራጭ ነው። በየትኛውም አካባቢ ወረራ እንዳይከሰት ለመከላከል የሚረዱ የቁጥጥር (ቀሳ/Plant quarantine) መሰናዶዎች አሉ። መከላከል የሚጀምረው ስለ ወራሪው እፅዋት በቂ መረጃዎችን በማግኘት ሲሆን፣ መረጃዎች ከተለምዶ የተቀሰሙ ወይም በሳይንሳዊ ስልቶች የተገኙ ሊሆኑ ይችላሉ። የመረጃ ማሰባሰቡ ተግባር በተመሳሳይ ሁኔታ ችግር ከደረሰባቸው አገሮች/አካባቢዎች መረጃ ማሰባሰብንም ያካትታል። መረጃዎች በአካባቢው ብሎም በማኅበረሰቡ የኑሮ ዘዴ ላይ ሊደርሱ በሚችሉት ጉዳቶችና ተግዳሮት ዙሪያ ያጠነጠነ ሊሆኑ፣ ከዚያም ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው የማኅበረሰቡ አባላት መረጃው እንዲደርሳቸው ማድረግ ይገባል።

የማኅበረሰቡ አባላት በአካባቢዎቻቸው ያሉ ሁኔታዎች በየጊዜው እየቃኙና እየተገነዘቡ አዳዲስ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ለተግባሩ ኃላፊዎች ለሆኑ ግለሰቦች ወይም ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች መረጃዎች እንዲደርሱ ማድረግ ይገባቸዋል። በተለይ ጉብኝት በሚደረግባቸው አካባቢዎች (የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ አካባቢዎች) መጤ እፅዋት ለመቆጣጠር በቂ ዝግጅት/መሰናዶ እንዲኖር ያሻል። ወረራው ከተከሰተ በኋላ እንደወራሪው ባህርይ የተለያዩ የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች አሉ። ወራሪው አረም ከሆነ፣ በግብርና ተግባራት አማኻኝነት እንዳያንሰራሩ ለማድረግ መሞከር ነው። በመጀመሪያ የእርሻ ማሳውን ደጋግሞ በማረስ ወራሪው ስር ሰዶ እንዳያንሰራራ ብሎም በፀሃይ ኃይል ለድረቀት እንዲጋለጥ ማድረግ ነው። መጤ አረሞችን በኬሚካላዊ ዘዴዎች የማስወገድ ተሞክሮም አለ።

ወራሪው አንደ እምቦጭ ያለ ከሆነ ከሁሉም በላይ ተመራጭ የሆነው የመከለከያ ዘዴ ከመጀመሪያው የእፅዋት አልሚ ውህዶች ፍሰት እንዳይኖርና አረሙ ወደ ውሃ አካል እንዳይገባ መከላከል ነው። ይህን አረም የመቆጣጠር ተለምዶ ብዙ አገሮች ያካበቱ መሆኑ ቢታወቅም፣ አረሙን ጨርሶ የማስወገድ አቅም ያጎለበተ ታዳጊ አገር ያለ አይመስልም። አረሙን ለመቆጣጠሩ ፊዚካላዊ (physical) ኬሚካላዊ (chemical) እንዲሁም ባዮሎጅካዊ (biological) ስልቶች [እምቦጭን የሚመገቡ/ የሚበሉ ጢንዚዛዎችን/ (Weevils/ beetles/) እና የእሳት ራት ዝርያ (moth) የሆኑ ሦስት አፅቄዎች በሃይቁ እንዲሰራጩ በማደረግ (ወደ ሌላ እፅዋት የማይዘምቱ መሆኑን ከተረጋገጠ በኋላ) ነው። ይህ ዘዴ በብዙ ቦታዎች ተግባር ላይ ውሎ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። በዛ ባሉ አካባቢዎች የሚተገበረው አረሙን በማሽን እገዛ ወይም በእጅ ማስወገድ ነው። የኬሚካላዊ ስልት አካባቢውን ስለሚበክል በብዙ አካባቢዎች ጥቅም ላይ አይውልም። በየብስ ላይ ያለው ወራሪ እንደ ወያኔ ሃራ ወይም ደረጊ ሃራ ግንደ ያለው ከሆነ ግንዱን ለጎጆ ቅለሳ፣ ለወረቀት ፋብሪካዎች ግብዓትነትና አክስሎም ሆነ ሳያከስል በማገዶነት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።

ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም

Recommended For You

About the Author: wendimagegn