ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ የሚቃጣን የሕልውና አደጋ ለዘመናት በአንድነት ቆመው በመመከት ኢትዮጵያን አንድ አድርገው አቆይተዋል። የአሁኑም ትውልድ በእናት አገሩ ሕልውና ላይ የሚደቀኑ ሳንካዎችን በኅብረት በመሰለፍ ጠራርጎ ለመጣል እስከሕይወት መስዋዕትነት እንደሚከፍል በተግባር እያሳየ ነው።
ኢትዮጵያ ካላት ጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታ አንጻር የውጭ ኃይላት ምንጊዜም ትኩረት ያደርጉባታል። እነዚህ ኃይላት በተለያዩ ጊዜያት በቅርብ ሆነው ሊያስተዳድሯት ሙከራ ቢያደርጉም ጥረታቸው በተባበረ ክንድ ተመክቷል። ይህ ሙከራቸው ያልተሳካው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመነሳቱ መሆኑን ስለተረዱ፣ የተጠናከረች አንድ ኢትዮጵያን ላለማየት የልዩነት መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን ተግባራት ሁልጊዜ ይጠቀማሉ። እነዚህን ተግባራት የሚያስፈጽሙት በአገር ውስጥ ባሉ እነሱ ባደራጇቸው ባንዳ ቡድኖች ነው። ቡድኖቹ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ለአገራቸው ሕልውና ሲሉ ልዩነታቸውን ከመፍታት ይልቅ የውጭ ኃይላት የሚሰጧቸውን አጀንዳ ተከትለው የማይሳካላቸውን አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ሲውተረቱ ይታያሉ።
አሸባሪው ሕወሓት አገር የማፍረስ እንቅስቃሴውን የሚያከናውነው በእነዚህ የኢትዮጵያን አንድነት ማየት በማይፈልጉ ኃይላት የዲፕሎማሲና የቴክኖሎጂ እገዛ በመጠናከር ነው። እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሆ ብሎ በአንድነት በመውጣት የሕልውና አደጋውን ቀልብሶታል። የሕልውናው አደጋ ከተቀለበሰ በኋላ እነዚሁ የውጭ ኃይሎች በጦር ሜዳው ያጡትን ድል ለማካካስ፣ ሆ ብሎ በአንድነት የወጣውን ሕዝብ ሊከፋፍሉ ይችላሉ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በባንዳዎች በኩል ለኅብረተሰቡ ያነሳሉ። አጀንዳዎቹን ካነሱ በኋላ ኅብረተሰቡን ስሜታዊ በማድረግ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዲያመሩ ለማድረግ ሲሞክሩም ይስተዋላል።
በዚህ ጽሑፍ ኢትዮጵያውያን ከስሜታዊነት ወጥተው ለአገር ሕልውና እና ደህንነት እንዲሁም ለሕዝብ ሰላም ሲሉ የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ፤ በአገሪቱ አንድነት ላይ እያንዣበቡ ያሉ አደጋዎች ምን እንደሆኑ ፤ በሰበብ አስባቦች ከመነታረክና ከመጨቃጨቅ መውጣት የሚቻልባቸው መንገዶች እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች በማንሳት ምሑራን አነጋግረናል።
በኢትዮጵያ ላይ እያንዣበቡ ያሉ የአንድነት አደጋዎች (እንከኖች) በሁለት መልኩ ሊታዩ ይገባል የሚሉት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካና ዓለም አቀፍ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ዶክተር ቃለወንጌል ምናለ ናቸው። እነዚህን የአንድነት እንከኖች ሲገልጹ አንደኛው የግዛት (የሉዓላዊነት) አንድነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብሔራዊ (ሕዝባዊ) አንድነት ነው ይላሉ።
እንደሳቸው ገለጻ በአሁኑ ሰዓት በግዛት አንድነት ላይ የሚያንዣብቡ እንከኖች ተብለው የሚባሉት በሰሜኑ አካባቢ እና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶች ናቸው። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የማንስማማባቸውና የሚያጨቃጭቁን ጉዳዮች አሉ፤ እነዚህ ጉዳዮች ሕዝባዊ አንድነት ላይ የሚያንዣብቡ አደጋዎች ናቸው። ለምሳሌ ባንዲራ ላይ እንዲሁም የግለሰብና የቡድን መብት ምን መሆን ይገባዋል ? የሚሉት ላይ የሚነሱ አለመግባባቶች ሲያነታርኩ ይስተዋላል። ሕዝባዊ አንድነት ላይ እንከን ሲከሰት ሰከን ባለ መንፈስ በማስተዋል ተከታታይ ውይይት በማድረግ ተገቢ የሆነ ምላሽ በወቅቱ መስጠት ካልተቻለ ፣ ወደ ግዛት አንድነት አደጋ ሊለወጥ እንደሚችል ያስረዳሉ።
ዶክተር ቃለወንጌል እነዚህ የአንድነት አደጋዎች ሲከሰቱ ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ በፊት ያሉት የኢትዮጵያ መሪዎች በጋብቻ በማስተሳሰር፣ በመሾም፣ ቅሬታ ያለውን ወገን ጥላቻ ባለማሳየትና በማቅረብ፣ ደም በማድረቅ (የእርቅ ሥነሥርዓት በማድረግ) እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ቴክኒኮች እና ታክቲኮች በመጠቀም የአንድነት እንከን እንዳይሆኑ ያደርጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ግን የሚነሱ ቅሬታዎች የአንድነት እንከን እንዳይሆኑ መንግሥታት የሚወስዱት መፍትሔ ከበፊቶች በተለየ ኃይል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ፣ አዲስ ርዕዮተዓለም መከተል፣ አዲስ የብሔራዊ መንግሥት አወቃቀር ማምጣት፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ እንዲሁም ተሐድሶና ጥልቅ ተሐድሶ በማለት የአንድነት አደጋ እንዳይሆኑ ሲከላከሉ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ ደግሞ በመደመር ዕሳቤ አዲስ አይነት አተያይ በማውረድ፣ በመንግሥትና በኅብረተሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት የማጠናከር እንቅስቃሴ ታይቷል ይላሉ። በዚህም የአገረ መንግሥቱንም ሆነ የብሔረ መንግሥቱን አንድነት ለማስቀጠል ጥረት ሲደረግ ተስተውሏል። ይሄ ተጠናክሮ ኅብረተሰቡ በአንድነት ተሳስሮ እንዲቀጥል፣ ያሉ ቁርሾዎችን የማረምና የማጥፋት ሥራዎች በተከታታይነት ሊተገበር ይገባል በማለት አበክረው ይመክራሉ።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እያዣንበበ ያለው እንከን ዋነኛው መነሻ ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦ ፖለቲካ ከባቢ ሁኔታ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን ተፈራ ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ናቸው። እንደሳቸው አባባል በመካከለኛ ምስራቅ አካባቢ እየተራመደ ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ሄዶ ሄዶ ወደ ምስራቅ አፍሪካ የሚያርፍበት አጋጣሚ አለ። በተለይ አሜሪካ በአካባቢው የጦር ኃይሏን የማደራጀትና የማከማቸት እንቅስቃሴ ስታደርግ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረቷን ታደርጋለች። አሜሪካ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንደፈለጋት እንድትንቀሳቀስ ደግሞ ለእሷ የሚመቻት መንግሥት ማቋቋም ትፈልጋለች። የማይመቻት መንግሥት ካለ ደግሞ የአገሪቷን አንድነት የሚንድ ተግባራት በውጭ አገራት ትብብርም ሆነ ከውስጥ የምታገኛቸውን ባንዳዎች በማደራጀት ታከናውናለች። ምዕራባውያኑም የአሜሪካ ተባባሪ ሆነው ይሰለፋሉ። ስለሆነም በአገር አንድነት ላይ የሚቃጣን ጫና እና ጥቃት ለመመከት የውስጥ አንድነትን በማጠናከር በራስ አቅም ኢኮኖሚን መገንባት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
በመቀጠልም ኢትዮጵያውያንን በጦር ሜዳ ገጥመው ማሸነፍ ያቃታቸው ጠላቶች ፣ ከሽንፈታቸው በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት መጠናከሩ ስለሚያስፈራቸው ልዩነት የሚፈጥር የሚመስላቸውን አጀንዳ በየጊዜው እንደሚፈጥሩ ተመራማሪው ይገልጻሉ። በተለይ አሁን በአሸባሪው ሕውሓት የተቃጣው የሕልውና አደጋ ከተቀለበሰ በኋላ ‹‹ድሉ የአንተ ነው፣ የአንተ ነው›› እያሉ የልዩነት መነሻ እንዲሆን ይሠራሉ። የልዩነት መነሻ እንዲሆን ለሚሠሩ አካላት ከጥንት ጀምሮ ከድርቡሾች እና ከጣሊያኖች ጋር የተደረገው ጦርነት ድል እንዲሁም የካራማራው ድል የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ድል ሆኖ እንደሚወሳው ሁሉ፣ የአሁኑም ድል ሽሚያ ውስጥ ሳይገባ የሕዝቦች የጋራ ድል እንደሆነ ትኩረት ሰጥቶ በመንገር ማሳፈር እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ዶክተር ቃለወንጌል ድሉ የጋራ ድል መሆኑ ላይ ከአቶ ሰለሞን ሀሳብ ጋር የሚስማሙ ቢሆንም ‹‹ድሉ የእኔ ነው፤ የእኔ ነው›› የሚለው ለምን መጣ ? ብሎ ግን በቅንነት ማየትና መፍትሔ መስጠት ይገባል ይላሉ። አስተያየታቸውን በመቀጠል፤ ‹‹ይሄ የሚያሳየው ዕውቅና እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ነው። መንግሥት ድሉ የመጣበትን ሁኔታ በተመለከተ ከሚመለከታቸው ጋር ተከታታይ ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል። ለተገቢው ኃይል ተገቢውን ዕውቅና በተገቢው ጊዜ የሚሰጥበት መንገድም መዘርጋት ይገባዋል። የግጭት መንስዔ እንዲሆን ለሚሠሩ አካላት ደግሞ አግባብ ባለው ሕጋዊ አሠራር መፍትሔ ሰጥቶ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስፈልጋል›› በማለት ያስገነዝባሉ።
ዶክተር ቃለወንጌል ያነሱትን ለተገቢው ኃይል ተገቢውን ዕውቅና በተገቢው ጊዜ መስጠት የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ሰይድ አሕመድ ኢትዮጵያውያን በታሪክ አጋጣሚዎች የተከሰቱባቸውን የአንድነት አደጋዎች በሁለት መልኩ በመመከት ሲመልሱ እንደቆዩ ይናገራሉ። በአገር ውስጥ የሚከሰትን የአንድነት አደጋ በአገራዊ ልማዶች ይፈታሉ። የውጭ አደጋን ደግሞ ጠላትን በማሸነፍ ፣ ሉዓላዊነት በማስከበር እና ጠላትን አንገት በማስደፋት ሲፈቱ መኖራቸውን ያስታውሳሉ። በተለይ የአድዋ ድል የአገር አንድነትን ለማስከበር ሕዝብ በአንድነት ሆ ብሎ በመሰለፉ የተገኘ ድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ድሉን የአፍሪካውያንም ድል የሚያደርገው የነጮችን የበላይነት ከሥሩ የናደና የበታተነ መሆኑ እንደሆነ ይገልጻሉ።
የአድዋ ድል በቅኝ አገዛዝ ስር ላሉ አገራት ነጻ መውጣት መነሻ ቢሆንም ፣ ምዕራባውያን አፍሪካን ቀበሌያት በሚደርስ በትናንሽ አገራት በመከፋፈልና በማዳከም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማስተዳደር ለሌላ ዙር ሲዘጋጁ ኢትዮጵያን ተተኳሪ እንድትሆን እንዳደረጓት ዶክተር ሰይድ ይናገራሉ። ሀሳባቸውን በመቀጠል ሲያብራሩ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ለመሸርሸር ካቀዱት እቅድ ውስጥ አንደኛው ብሔር ተኮር እሳቤን በማምጣት ሕዝቡ ትኩረቱ ወደ ቀበሌው እንዲሆን ማድረግ ነው። ይሄን በተለይ ላለፉት ሶስትና አራት አስርተ ዓመታት ሲሞክሩት ቆይተዋል፤ ሙከራቸው ግን አልተሳካም። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ የሚከሽፍ ነው። ኢትዮጵያዊነት ቢገዘገዝ የማይበጠስ፤ ቢቀጥን የማይሰበር፤ በትልቅ አለት ላይ የተገነባ ነው። የኢትዮጵያ አንድነት በየትኛውም መስፈርት፣ በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ሁኔታ የማይላላ ነው። በታሪክ እንደታየው የኢትዮጵያውያን አንድነት ተሸርሽሯል ባሉበት ጊዜያት ፣ ጠላቶች ያደረጓቸው ትንኮሳዎቻ በሙሉ የኢትዮጵያን አንድነት ያጠናከሩ ናቸው። እነዚህ ተሞክሮሞች ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም በወሳኝነት የሚታዩ ሆነዋል›› በማለት ያስረዳሉ።
መንግሥት ለኢትዮጵያ ህልውና ቀጣይነትና ለዘላቂ ሰላም እንዲሁም ሁሉን አካታች ለሆነ ብሔራዊ ውይይት በማሰብ በሚወስናቸው ውሳኔዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች የተቻኮሉ አፍራሽ ምላሾች ሲሰጡ ይስተዋላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምሑራኑ ያላቸውን ሀሳብ እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸዋል። ዶክተር ቃለወንጌል የክስ መቋረጥ ውሳኔን በአብነት አንስተው ሲናገሩ፤ የተቻኮለ አፍራሽ ምላሽ የሚሰጡት ሰላምን ለማስፈን እና ፍትሕን ለማስፈን በሚወሰኑ ውሳኔዎች መካከል ባለው ተቃርኖነት ምክንያት ነው በማለት ይጀምራሉ።
ጉዳዩንም ምሳሌ በመስጠት ሲያብራሩ፤ ፍትሕን ለማስፈን አንድ ሰው በፍርድ አደባባይ በሠራው ወንጀል ልክ ውሳኔ ማግኘት ይገባዋል የሚለው ጽንሰ ሀሳብ እና አጠቃላይ ሰላምንና መረጋጋትን ለማግኘት በፍርድ አደባባይ ባልሆነ አግባብ ውሳኔ መስጠት ተቃርኖነት አላቸው። ተቃርኖነት ይኑራቸው እንጂ ተደጋጋፊነትም አላቸው፤ ለዘላቂ ሰላም ሲባል የሚወሰን ውሳኔ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚከፈል ዋጋ ነው። ፍትሕ ለማስፈን ተብሎ የሚወሰን ውሳኔ ይሻላል ወይስ ሰላምን ለማስፈን ተብሎ የሚወሰን ውሳኔ የሚሉ ጉዳዮች በተለያዩ ጊዜያት ክርክር የሚያስነሱ ናቸው። ለዘላቂ ሰላም ሲባል የሚወሰን ውሳኔ በዓለም ላይም እንደ ኢትዮጵያ አይነት ሁኔታ የገቡ አገራት የሚወስኑት ውሳኔ ነው ይላሉ።
ዶክተሩ የእነ አቶ ስብሃት ከእስር መፈታትን በተመለከተ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተነሳው ተቋውሞ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው ባይ ናቸው። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ እነዚህ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ክፍሎች ወደ ሰላም ለመምጣት ጫና ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። የተነሳውን ተቃውሞ ለማርገብና በኅብረተሰቡ ዘንድ ውሳኔው ተቀባይነት እንዲኖረው ለማስረዳት፣ ለማብራራት እና ግልጽ ለማድረግ የተከናወኑ ድርጊቶች ላይ ግን ድክመት እንደሚታይ ይናገራሉ።
አያይዘውም ውሳኔው ምን አይነት አገራዊ ጥቅም ለማግኘት እንደሆነ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይዞ የሚመጣውን ፋይዳ ማብራራቱ ላይ ክፍተት እንዲታይ ካደረጉ ጉዳዮች አንዱ ውሳኔው በካቢኔ ታይቶ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገሩንና ለማስረዳት የሞከሩ ቢሆንም ሌሎቹ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ግን ውሳኔው የጋራ እስከሆነ ድረስ በፍጥነት የማብራራቱን ሥራ ባለመጋራታቸው ነው ይላሉ። ማብራራቱና ማስረዳቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ኅብረተሰቡ ላይ የተከሰተው ብዥታ እንዲከሰት ሆኗል በማለት ገልጸው ውሳኔው ግን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ለሚከታተል አካል ድንገተኛ እና አስደንጋጭ እንዳልሆነ እንዲሁም ሲጠበቅ የቆየ ነው በማለት ያስረዳሉ።
አገር ሲመራ ከግላዊ ስሜት ወጣ በማለት ሕዝብን ሊጠቅም ወደሚችል እንዲሁም የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያስቀጥል ውሳኔ ላይ ማተኮር ስለሚገባ መንግሥት የሚወስናቸውን ውሳኔዎች በተረጋጋ መንፈስና በአስተዋይነት መመልከት ይገባዋል የሚሉት ደግሞ ዶክተር ሰይድ አሕመድ ናቸው። እንደሳቸው አባባል መንግሥት ለሚወስናቸው ውሳኔዎች ትችት ለመስጠት መንግሥት የቆመበት ቦታ ላይ ሆኖ ፣ የመንግሥትን ጫማ አጥልቆ ማየት ይጠይቃል። የሰላም አማራጮች በሰፉ ቁጥር ግን እንደአሸባሪው ሕውሓት ያሉ ቡድኖች መሸሸጊያ ያጣሉ። ምክንያቱም ሰላም ሲኖር የጦርነት ቀዳዳ ይጠባል። አሣ በውሃ ውስጥ ይኖራል፤ ከውሃው ውስጥ ከወጣ ግን መኖር አይችልም። ጦርነት የሚፈልግ አካልም ሰላም ሲመጣ መኖር አይችልም፤ ለእሱ መጥፎ ዜና እና ኪሳራ ነው። ሰላማዊ መፍትሔው በተለይ አሸባሪው ሕውሓትን ከትግራይ ሕዝብ የሚለይ ነው።
መንግሥት ሁሉን አካታች ሰላም እንዲመጣ በማሰብ የወሰነውን ሆደ ሰፊ ውሳኔን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዘነብሉ መሆናቸውንም ጠቅሰው ለኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካና አገራዊ ምክክርም የሚበጅ ሆኖ ይታያል ብለዋል። መንግሥት በወሰነው ውሳኔ በተቻኮለ ሁኔታ ማኩረፍና ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ማድረግ ሳይሆን፣ ደጋግሞ የአገር ሕልውናን እና ሰላምን በዘላቂነት ማስቀጠል ላይ ማሰብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አገር ስትኖር ነው ማኩረፍም ሆነ ሌላ ነገር ማድረግ የሚቻለው በማለት ምክረ ሀሳባቸውን ይሰጣሉ።
የፖለቲካ ተመራማሪው አቶ ሰለሞን ደግሞ ውሳኔዎች ሲወሰኑ በዋነኛነት ትኩረት ሊደረግ የሚገባው አገራዊ ጥቅም ማስገኘቱ ላይ ነው ይላሉ። ብሔራዊ ምክክር ወይም እርቅ ሲደረግ በሀሳብ ከሚመስል ጋር ብቻ ሳይሆን በሀሳብ ከማይመስል እንዲሁም ከጠላት ጋር ስለሆነ መንግሥት የወሰነው ውሳኔ ለአገር አንድነት እንደሚጠቅም የውጭ አገራት ተሞክሮን በማንሳት ያስረዳሉ። አብነት ሲጠቅሱም በደቡብ አፍሪካ በነጮችና ጥቁሮች መካከል የተካሄደውን የምክክርና የእርቅ ሥነ ሥርዓት ያነሳሉ። ከዚህ የእርቅ ሥነ ሥርዓት በፊት በጣም ብዙ ሰው መገደሉን፤ የአካልና የአዕምሮ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሲባል ግን በጋራ መመካከር የቻሉበትና ሰላም ያመጡበት ተሞኩሮ መኖሩን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥትን እኔን ወክለህ ለአምስት ዓመት በሙሉ ኃላፊነት ሥራ ብሎ መርጦታል፤ መንግሥት መሰል ውሳኔዎችን ሲወስን በስሜታዊነት ለመቃወም ከመቸኮል ይልቅ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የሚጠቅም መልካም ጎኑን በትዕግስት መጠበቅ እንደሚገባ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ። የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ መከናወኑ እና የአፍሪካውያንን ድምጽ ማግኘት መቻሉ ውሳኔው ያስገኘው መልካም ጎን መሆኑ በጊዜ ሂደት ታይቷል በማለት በተረጋጋ መንፈስ ውሳኔዎችን መመልከት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ሲደፈር ሕዝብ ሆ ብሎ በአንድነት ይነሳል። የሕልውናው አደጋ በድል ከተቀለበሰ በኋላ ግን ጥቃቅን ሁኔታዎች እየተነሱ የልዩነት መንገድ ሆነው እንዲካረሩ የሚሆኑበት አግባብ ይስተዋላል። ይህ ከምን እንደሚነሳ እንዲሁም መፍትሔው ምን እንደሆነ ምሑራኖቹ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
በሕልውና ላይ አደጋን የሚጋርጥ ጦርነት ሲኖር ሕዝቡ በአንድነት ሆ ብሎ መነሳቱ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ስለሆነ እንዲሁም የጦርነት ባህሪ በመሆኑ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ቃለወንጌል ናቸው። በጦርነት ጊዜ በአንድነት የተነሳው ሕዝብ አደጋው ከተቀለበሰ በኋላ በሰላማዊ ሁኔታ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ግላዊ ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ይፈልጋል። በዚህ ሂደት የሀሳብ ልዩነት መፈጠሩ አይቀርም። የሀሳብ ልዩነቶች በራሳቸው ችግር አይደሉም። ልዩነቶች አብረው የሚኖሩና ተፈጥሯዊ ናቸው፤ ወደፊትም የሚቀጥሉ ናቸው። የሀሳብ ልዩነቶች ችግር የሚሆኑት ልዩነቶቹ በሚተላለፉበትና በሚያዙበት መንገድ እንደሆነ ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተሩ አባባል የሀሳብ ልዩነቶች በመቀራረብና ሰጥቶ በመቀበል መርሕ በውይይት ከተያዙ ችግር አይሆኑም። ችግር የሚሆኑት ልዩነቶች ከውይይት ወጥተው ወደ ግጭት ሲያመሩ ነው። አንደኛው ሌላኛውን ዝቅ ወደ ማድረግና ወደ ማጥቃት የሚያመራ ከሆነ ልዩነቶቹ ችግር ከመሆን አልፈው ለአገር አንድነት አደጋ እስከመሆን ይደርሳሉ። ስለሆነም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት፣ በአገረ መንግሥት ግንባታ የታሪክ ሂደት ውስጥ የተከሰቱ ክስተቶችና ቁርሾዎችን በመነጋገር ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋቸዋል። ይህ የሚሆን ከሆነ ታሪክን መነሻ በማድረግ የመነታረኪያ ርዕሰ ጉዳይ ማፈላለግ አይኖርም። በተለያዩ ጉዳዮች ልዩነቶች ወደፊት መከሰታቸው አይቀርም። ለአገር አንድነትና ሰላም ዘላቂነት በማሰብ ልዩነቶች ችግር እስከመፍጠር ደረጃ እንዳይደርሱ፣ በውይይትና በመግባባት መንፈስ በመነጋገር መፍታት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ዶክተር ሰይድ አህመድ በተነሳው ጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ሲገልጹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ ሲሆኑ የማይወዱ የውስጥም የውጭም ኃይላት መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። እነዚህ ኃይላት በጦርነት ሲሸነፉ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት የሚያለያይ ጉዳይ እንዲኖር በየጊዜው ጉድጓድ መጫራቸውን እንደማይተዉ በታሪክ የታየ ጉዳይ መሆኑንም ይናገራሉ። አስተያየታቸውን በመቀጠልም የመነታረኪያ አጀንዳዎች እንደሚፈበርኩ በማወቅ ቅድሚያ ለአገር ሕልውና እና ለሕዝብ ጥቅም በመስጠት፣ ገመድ መጓተት ለጠላት በር መክፈት መሆኑን በመገንዘብ ተቀራርቦ መወያየትና መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል ይላሉ።
ዋና ትኩረታችን አንድነታችንን አስጠብቀን እንዴት ከተረጅነት እንላቀቅ ? እንዲሁም እንዴት ከድህነት እንውጣ ? የሚለው ላይ መሆን እንዳለበት ዶክተሩ ያሳስባሉ። ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ብዙ የቤት ሥራ አለባት። ከዚህ በፊት በየዓመቱ ስንዴ ስንረዳ ነበር ፤ አሁን በቆላማ አካባቢዎች ሰፋፊ መሬቶች ላይ ስንዴ እየተመረተ ነው። ይሄ እድገት ያመጣል። ልዩነትን በመመካከርና በመቻቻል በመፍታት እንደነዚህ አይነት ልማታዊ ተግባራት ላይ ማተኮር ለሁሉም ሕዝብ ይጠቅማል ይላሉ።
አቶ ሰለሞንም በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ በኢኮኖሚ ራስን መቻል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማውሳት ኢትዮጵያውያን አንድ የጋራ አገር ነው ያለን፤ ይቺንም አገር የበለፀገች ለማድረግ ከስሜታዊነት በመውጣት ሰከን ብሎ በመረጋጋት ማሰብ ይጠይቃል በማለት የዶክተር ሰይድ ሀሳብን ይጋራሉ። የኢትዮጵያን አንድነትና እድገት የማይፈልጉ ኃይሎች የመነታረኪያ ጉዳይ በየጊዜው እንዲኖረን በማድረግ ወደልማት ፊታችንን አዙረን በትኩረት እንዳንሠራና ድህነትን ታግለን እንዳናሸንፍ የመከፋፈያ አጀንዳዎች ቀርፀው ያቀርቡልናል። አጀንዳዎቹ ሲራገቡ ደግሞ የሰው ኃይልና ፋይናንስ ተመድቦላቸው ነው። ስለዚህ ስለኢትዮጵያ ደህንነትና አንድነት እንዲሁም እድገት በተረጋጋ መንፈስ በማሰብ፣ ከግል ስሜታዊ ፍላጎት እና ከግል የፖለቲካ ትርፍ በመውጣት፣ የአጠቃላይ ሕዝብን ፍላጎት በማክበር ከፋፋይ አጀንዳቸውን ማክሸፍ ይጠብቅብናል በማለት ይመክራሉ።
እኛም በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያን የሰከነ መንፈስና ማስተዋል ይዘው ቢንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ያስጠብቃሉ፤ ልማት እንዲሳለጥ ያደርጋሉ እንዲሁም የውጭ ጣልቃ ገብነትንም ያስቀራሉና ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ብሔራዊ ውይይት መድረክ ይበል የሚያሰኝ ነው እንላለን።
ስሜነህ ደስታ
ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም