ለምክክር መድረኩ ስኬት ማን ምን ያድርግ ?

ሰው በተፈጥሮው የኔ ብሎ የያዘው አቋም በሌሎች ዘንድም ይሁንታን እንዲያገኝ ይሻል፤ ፍላጎታችን ለየቅል ነውና የኔ ብለን የያዝነው አቋም በሌላውም ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ቀርቶ ተቃውሞን ልናስተናግድ እንችላለን። ፍላጎታችንን ለማሳካት የምናደርገው ጥረት መደማመጥና መቀባበል ከጎደለው፣ የሐሳባችንን ተቃዋሚ በኃይል የመጫን ፍላጎት ካሳየን የሀሳብ ልዩነታችን ወደ አለመግባባት ይወስደናል፤ አለመግባባትም ሲከር ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል። ራሳችንን ከግጭትና ግጭት ከሚያስከትለው ኪሳራ መጠበቅ የምንችለው አለመግባባትን መደማመጥ በሰፈነበት ውይይት መፍታት ስንችል ብቻ ነው። የውይይት ዓላማ ምንጊዜም የሐሳብ ልዩነትን ወደ አንድ ማምጣት ብቻ አይደለም፤ ይልቁኑም የሚበጀውን ሐሳብ ለመውሰድ፣ በመደማመጥ ውስጥ መከባበርን ለማዳበር፣ አቋሜ ብለን አጥብቀን የያዝነውን ለአብሮ መኖራችን ስንል ለመተውና ከእኔ ይልቅ ያንተ ለመባባልም ጭምር እንጂ።

ጥንታዊነቷን ታሪክ የሚዘግብላት አገራችን ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ነች፤ ስልጣኔና የኢኮኖሚ ከፍታም የታሪኳ አካል ነበሩ። በርካታ ዘመናትን በጦርነት ማሳለፏም እሙን ነው። በየዘመናቱ ከውጭና ከውስጥ የገጠሙን ጦርነቶች በኢኮኖሚ ወደፊት ከምናደርገው ጉዞ ብዙ ርቀት ወደኋላ አስቀርተውናል። አገራት ጠግበው ከመብላት አልፈው የቴክኖሎጂ ቅንጦት ውስጥ በገቡበት በዚህ ዘመን እንኳ፣ አገራችን ከጦርነት አልተላቀቀችም፤ ሙሉ ትኩረታችንንም ልማት ላይ ብቻ ማድረግ አልቻልንም። የውስጥ አለመግባባታችንን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ፈጥነን ለግጭት መንደርደራችን ኢኮኖሚያችንን ከመብላቱም በላይ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው ትልቅ ሐብት የነበሩ፣ የማይተኩ ዜጎቻችንን አሳጥቶናል። የቅርብና የሩቅ ባላንጣዎቻችንም አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ሊያጠቁን ያቆበቁባሉ፤ የድንበር ትንኮሳን ጨምሮ የቻሉትን ያህል ጫና ያሳድራሉ። ከዚህ የጦርነት አዙሪት ለመውጣት ደግሞ፣ ያለን ብቸኛ አማራጭ ልዩነቶቻችንን ወደ ጠረጴዛ ማምጣትና መምከር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፤ ያለፉ ዘመናትን ጨምሮ አሁን ባለንበትም ሥርዓተ መንግሥት ለውይይት የነበሩንን እድሎች በአግባቡ ባለመጠቀማችን ብዙ ኪሳራ ውስጥ እንደከተተን በቁጭት የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።

በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲከኞች መካከል የሚስተዋለውን ልዩነት ወደ አንድ ለማምጣትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ቁልፉ መፍትሔ ምክክር መሆኑ ታምኖበት፤ ወደ ተግባር ለመግባት፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የማቋቋምና ገለልተኛ ኮሚሽነሮችን የመምረጥ ጥንስስ ደረጃ ላይ እንገኛለን። የሌሎች አገራትን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ይካሄዳል ተብሎ የሚታሰበው አካታች አገራዊ ምክክር ዋነኛ ግብ “በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃን መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው እንዲነጋገሩና ገንቢ የሆነ አገራዊ አቋም እንዲይዙ ማድረግ” ሲሆን፣ ምክክሩ አለመግባባትን ያረግባል፣ መተማመንን ይፈጥራል ወደ ሠላምም ያመጣናል በሚል ብዙዎች ተስፋን ጥለውበታል፤ ለስኬታማነቱም ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም ብዙዎች ይስማማሉ።

በተለይ በ2010 ዓ.ም አዲስ መንግሥት ሲመሰረት፣ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን “ባለን ሙያና እውቀት ለአገራችን ምን ማድረግ እንችላለን? አገራችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?” በሚል መነሻ የተቋቋመው፣ በኢትዮጵያ መሪዎችና እና ፖለቲከኞች ዘንድ የውይይት ባህል አለመዳበሩ ለተደራራቢ ችግር እንደዳረገን ያስተዋለውና የፖለቲካ ልሂቃንን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲወያዩ በማድረግ ለአገራዊ መግባባት ሰፊ ሚናን ሲጫወት የቆየው የ “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” መስራችና ሰብሳቢ አቶ ንጉሡ አክሊሉ፣(አቶ ንጉሡን ያነጋገርናቸው የምክክር ኮሚሽን ተጠቋሚ አባል ከመሆናቸው ቀደም ብሎ መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱልን በትህትና እንጠይቃለን) መድረኩ የተለያዩ የፖለቲካ ሰዎችን በመምረጥና በተደጋጋሚ እንዲገናኙ በማድረግ በአገራችን እጣ ፈንታ ላይ እንደመከረ ይናገራሉ። ይህንን ሲያደርጉ ሌሎች አገራት በእርስ በእርስ አለመግባባት አጣብቂኝ ውስጥ በገቡባቸው ጊዜያት ከገቡበበት አጣብቂኝ መውጣት የቻሉት ምን ምን ነገር አድርገው ነበር? የሚለውን ተሞክሮ በማየት እንደነበር ጠቅሰው፤ እነዚህ አገራት ካደረጓቸው ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው የአገራቸው የወደፊት እጣ ፈንታዎች ላይ በመምከር፣ እጣ ፈንታዎቹን ካወቁና ከለዩ በኋላ የትኛውን ብንከተል ነው የሚያዋጣን የሚለውን በሚገባ መክረውበት ወደ ተሻለው እጣ ፈንታ የሚያደርሳቸውን መንገድ መምረጥ እንደነበር ያወሳሉ። ለዚህም አቶ አክሊሉ፡ ደቡብ አፍሪካን ኮሎምቢያን፣ ጓቲማላን፣ አየር ላንድና ካናዳን ማሳያ አድርገው ይጠቅሳሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡና ከመሪውና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉምቱ ጉምቱ 50 ፖለቲከኞችን በመምረጥ ለአንድ ዓመት ያህል በየጊዜው እየተገናኙ እንዲመክሩ ካደረገ በኋላ፣ ምን አይነት ኢትዮጵያን መገንባት ትፈልጋላችሁ? የኢትዮጵያ እጣ ፈንታስ ምን ላይ ያርፋል? የሚል ጥያቄ አቀርቦ፣ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ “የፉክክር ቤት”፣ “ሰባራ ወንበር”፣ “አጼ በጉልበቱ” እና “ንጋት” በተሰኙ አራት አማራጮች ላይ እንደሚወድቅ ተወያይተው ከወሰኑ በኋላ፣ ከሶስቱ አማራጮች ይልቅ “ንጋት” በእጅጉ የተሻለ አማራጭ ነው ተብሎ “ንጋትን እውን ለማድረግ ሁላችንም ተግተን እንሰራለን!” ብለው ትልልቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች ውሳኔ ላይ ደርሰው መለያየታቸውን አውስተዋል።

“ለእኔ፣ እንደ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ መስራችና አስተባባሪ፣ በመንግሥትም፣ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ አሁን ደግሞ በመላው ህዝብ ሊባል በሚችል ደረጃ አገራዊ ምክክር ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ደስታ የሚሰጠኝ ነው” ያሉት አቶ ንጉሡ፣ አያይዘውም፣ ንጋት የሚመጣው በአገራዊ ምክክር እንደሆነ በዴስቲኒ ኢትዮጵያ የውይይት ሂደት ወቅት ተወያዮቹ አመላክተዋል ብለዋል።

አገራችን ኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነቶችን በማስተናገድ ከሌላ አገር የተለየች እንዳልሆነች የተናገሩት አቶ ንጉሡ፣ ሌሎች አገራትንም በብዙ አለመግባባት ውስጥ ማለፋቸውን ታሪክ እንደሚናገር ያነሳሉ። ነገር ግን፣ በአገራችን ሁኔታ ሁሌም የሚያጨቃጭቁን፣ አንዳንዴም የምንታኮስባቸውን አለመግባባቶች የፈታንባቸው መንገድ ዘላቂ ሰላምን በሚያመጣ መልክ ባለመሆኑ የግጭት ዑደት ውስጥ ከተውናል ይላሉ። “ያለፉትን 100 ዓመታት ታሪክ በአጭሩ ብንመለከት እንኳ፣ በአማካይ በየ15 ዓመቱ ቀውስ ውስጥ እንገባለን፤ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ መንግሥትም ሆነ ሌላ ኃይል አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚሞክሩት በጠብመንጃ አፈ ሙዝ ወይም በጦርነት ነው። አልፎ አልፎ የመነጋገርና የመመካከር ነገር ይጀመርና ምክክሩ አሳታፊና አካታች ሳይሆን የይስሙላ ዓይነት ይሆንና፣ እድል ያልተሰጠው አካል እንዳኮረፈ እንዲቀር ያደርጉታል፤ ያኮረፈውና እድል ያልተሰጠው አካልም ታፍኖ ይቆይና፣ አጋጣሚውን ሲያገኝ ይፈነዳል በማለት ሐሳባቸውን ይገልጻሉ።

ይህ አይነቱ አካሄድ ጥፋትን እያስከተለ እንደሚቀጥል አቶ አክሊሉ የቅርብ ጊዜ ታሪኮችን በማስታወስ ያስረዳሉ። “ለምሳሌ፡- በ1950ዎቹ የጀመረው የጭቁኖችን ፍትህ የሚፈልገው የመሬት ላራሹ እንቅስቃሴ በሚገባ ስላልተስተናገደና በበቂ ሁኔታ ምክክር ተደርጎበት ስላልተፈታ ጊዜ ጠብቆ ከ10 ዓመታት ገደማ በኋላ 1966 ዓ.ም ሲፈነዳ፣ ገዢውን መንግሥት ይዞት ሄደ፣ ሌላ የቀውስ ዑደት ውስጥ ከተተን ፣ ከዚህ በኋላም የመጣው ሥርዓተ መንግሥት የመሬት ላራሹና የከተማ ቤቶች ጥያቄን ለመመለስ ሙከራ ቢያደረግም፣ በተለይም ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ በመቅረታቸው፣ ከአስራ ሰባት አመታት በኋላ የእርስ በእርስ ጦርነት ተቀስቅሶ አገር እንደገና ሌላ ቀውስ ውስጥ ገባች፣ በዚህ ቀውስ ገዢው መንግሥት ተሸንፎ አንድ የአገራችንን ክፍል አጥተን ጨረስን።” ይላሉ። በጥሩ መንፈስ ተቀስቅሶ ጥሩ ባልሆነ መንፈስ የተጠናቀቀው አብዮት በአገርና በጊዜው በነበረው ወጣት ትውልድ ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ማለፉን በትውልዱ አባላት የተጻፉ መጻሕፍት ምስክር መሆናቸውን ያነሱት አቶ ንጉሡ፣ በ1983 ዓ.ም አዲስ መንግሥት ሲመጣም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የነበረው የመመካከር ሙከራ አካታች ባለመሆኑ፣ “የኔ ሃሳብ አልተደመጠም” ይሉ የነበሩና በነበረው የፖለቲካ አካሄድ ያልተስማሙ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ አካላት አድፍጠው ቆዩና የወጣቶች አመጽ እንዲቀሰቀስ መንስኤ ሆነ፣ ይህ የወጣቱ አመጽም ገፍቶ ገፍቶ በ2010 ዓ.ም ገዢውን ፓርቲ ይዞት ሄደ፡፡” በማለት የገባንባቸውን የቀውስ አዙሪቶች ያወሳሉ፤ ያሳለፍነው ታሪክ የገጠሙንን አለመግባባቶቻችንንና ልዩነቶቻችንን ስንፈታ የነበረባቸው መንገዶች ትክክል እንዳልሆኑና ለሌላ ቀውስ ሲዳርጉን እንደቆዩ በግልጽ የሚያሳዩ እንደሆኑም ይናገራሉ።

አሁንም ችግራችንን ፈትተን እንዳልጨረስን የሚናገሩት አቶ ንጉሡ፣ ካሳለፍነው ታሪክ ተነስተን ውይይትንና ምክክርን እንደ ተራ ነገር ማየት እና ለሌላው ጆሮ አለመስጠት፣ አንድን የቀውስ ጊዜም በኃይል ለማሸነፍ መሞከር፣ ያለፍንበትን መሠረታዊ ስህተት መድገምና ተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት ውስጥ መግባት ነውና አገራዊ ምክክር ያስፈልገናል የሚለውን መልካም አመለካከት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ያሳስባሉ።

እኛ ባልተግባባንበት፣ ግጭት ውስጥ በገባንበትና በደከምንበት ጊዜ ሁሉ ከኢትዮጵያ ተጻራሪ ፍላጎት ያላቸው የውጭ አካላት ጣልቃ መግባታቸው የማይቀር ነው ያሉት አቶ ንጉሡ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው፣ እኛ ስንፎካከር ባልዘጋነው በር ሌሎች በቅርብም በሩቅም ያሉ አካላት ጣልቃ እየገቡ ኢትዮጵያን እያደከሟትና እያደቀቋት ነውና፣ ለኛ ከመመካከርና ከመቀራረብ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም የሚል ሐሳብም ያክላሉ። ስለዚህ፣ ይህ አገራዊ ምክክር ለኔ ስር የሰደዱና ለረጅም ጊዜ የቆዩ የዞሩ ድምሮች ከመፍታት በተጨማሪ አላስፈላጊ ለሆኑ ጣልቃ ገብነቶች በር የምንዘጋበት በጣም ጥሩ አማራጭ ይሆንልናል ብለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጋበዝናቸው የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ሌንጮ ለታ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ “ውይይት” ስር የሰደደ ባህል አለመሆኑን አንስተው “ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሻገር እድል አግኝተን አነኚያን እድሎች በትክክል አልተጠቀምንባቸውም” ይላሉ። ይህንንም፡- የንጉሡ ሥርዓት ፈርሶ ወደ ወታደራዊ ሥርዓት ስንሻገር የነበረንን የውይይት እድል እንዳልተጠቀምንበት፣ በ1983ዓ.ም የደርግ ሥርዓት ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝም ተወያይተን፣ ተስማምተን ሳንሻገር መቅረታችንን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። አቶ ሌንጮ፣ “በጦርነት ሞክረነዋል፣ አላዋጣንም! በክርክር ሞክረነዋል አላዋጣንም! ለኢትዮጵያ መፃዒ እድል ወሳኝ ነው ብዬ የማስበው ይህ ምክክር የመጨረሻ እድላችን ነው! እንደ አገር፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካ ባህል መልመድ አለብን በውይይቱም ይሕ መሠረቱ ይጣላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት አገራዊ ምክክሩን በተገቢ ሁኔታ ልንጠቀምበት እንደሚገባና ተቀራርቦ የመወያየት ባህልን ለመገንባት መሠረት ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ። “እነዚያን ያልተጠቀምንባቸው እድሎች ምን ምን አጥፍተን ነው የከሸፉት ብለን ብንመረምርና ለአገራዊ ምክክሩ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ቢቀርብ ብዙ ትምህርትን እናገኛለን ብዬ አምናለሁ” የሚል ሐሳብም አክለዋል።

ሌላዋ ያነጋገርናቸው፣ በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ብቸኛዋ ሴት አባል የሆኑት የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ ደስታ ገብሩ በበኩላቸው፣ አገራችን ካሳለፈችውና ካለችበት ሁኔታ አኳያ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋም አስፈላጊነት ላይ ይስማማሉ። በህብረተሰቡ መካከል ቅሬታ ፈጥረው የግጭት እርሾ ሆነው የተቀመጡና የተከማቹ ነገሮች አሉ ያሉት ወ/ሮ ደስታ፣ አሁን ላይ ትንሽ የዲሞክራሲ ትንፋሽ የማግኘት ሁኔታ ሲፈጠር ገንፍለው የወጡ የከረሙ ችግሮቻችንን ለይተን አገራዊ መቀራረብና መግባባት ለመፍጠር የኮሚሽኑ ሚና ትልቅ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። እነዚህ ላለመግባባታችንና ለአገራችን ሠላም እጦት መንስዔ የሆኑ ነገሮች ምንድናቸው? ምንስ እናድርግ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘትና በህዝብ መካከል ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር የምንችለው በአገራዊ ምክክር ነው ብለዋል።

ለምክክሩ ስኬታማነት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ከተለያዩ አካላት ብዙ ነገር ይጠበቃል ያሉት አቶ ንጉሡ፣ “እንደ ህዝብ የሀሳብ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ አምጥተን ለመነጋገር መፍቀድ አለብን። በምክክሩ ሂደት አንዳንድ ሙጭጭ ብለን የያዝናቸውን ነገሮችና አቋሞች ለሌላኛው ወንድሜ ወይም ለሌላኛዋ እህቴ፣ ለአንድነታችንና ለህልውናችን በአጠቃላይ ለአገራችን መረጋጋትና ደህንነት ስንል ብንተወው ብለን የምንመክርበት ሊሆን ይገባል፤ ምክክሩ አሸንፌ እወጣለሁ ብለን የምንገባበት ሳይሆን፣ አሸንፈን እንወጣለን ብለን የምንጀምረው መሆን አለበት” ይላሉ።

አቶ ንጉሡ፣ አገራዊ ምክክሩ ላይ ህብረተሰቡን ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡ የተወሰኑ አካላት የሚሳተፉ ቢሆንም፣ ህዝቡ የአገሩን ጉዳይ የእነዚህ ሰዎች ብቻ ጉዳይ ሳያደርግ በየመሥሪያ ቤቱና መሰብሰብ በቻለባቸው ቦታዎች ሁሉ የተለየ የፖለቲካ አመለካከትና ሐሳብ አላቸው ከሚላቸው ሰዎች ጋር እየተቀራረበ፣ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መደማመጥ መቻል አለበት በማለትም ይመክራሉ። “የማዳመጥ ባህልን ማዳበር ከህዝቡ የሚጠበቅ መሠረታዊ ነገር ነው፤ እኛ ቁጭ ብለን በረጋና በቀና መንፈስ የመነጋገርን ልምድ ባላዳበርንበት ሁኔታ እላይ ያሉ ሰዎች መክረው፣ የሆነ ውጤት ይዘው ቢመጡም ውጤቱን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አንችልም፤ ስለሆነም ሁላችንም ለምክክሩ ስኬት ልባችንን ዝግጁ ማድረግ ይኖርብናል” የሚለውንም አክለዋል።

ወ/ሮ ደስታም በተመሳሳይ፣ “የተወሰነ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የተወሰነ የህብረተብ ክፍል፣ የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ወይም የሥራ ኃላፊዎች ብቻ በሚያደርጉት ውይይት አገራዊ መግባባትን እንፈጥራለን ማለት ያስቸግራል፤ የሰላሙ ባለቤት ህዝቡ ስለሆነ፣ ሃሳቦችም በብዛት የሚንሸራሸሩት ታች ያለው ህዝብ ጋር በመሆኑ፣ ምክክሩን የሚመራው አካል ለህዝብ ሃሳብ ዋጋ መስጠትና ማንንም ያላገለለ ምክክር እንዲካሂድ ማድረግ ይኖርበታል።” ብለውናል።

ምክክሩ የተቻለውን ያህል አካታች መሆን አለበት የሚለውን ሐሳብ የሚጋሩት አቶ ሌንጮ፣ አገራዊ ምክክሩ በፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ሳይወሰን፣ ሠራተኛውን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን የሐይማኖት መሪዎችን የተማረ ያልተማረውን ሁሉ አካቶ መካሄድ እንዳለበት ያሳስባሉ።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የመንግሥትን ዝግጁነትና በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ እየታየ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አቶ ንጉሡ፣ ተስፋ ሰጪ ነው በማለት ይገልፁታል። “እነዚህ ነገሮች በዚህ መልኩ ቢስተካከለሉ የምንላቸውና መንግሥትን የምንተችባቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ገለልተኛ በሆነ አካል ለማቋቋም ማሰቡ፣ የኮሚሽኑን ኮሚሽነሮችም ‘በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ጠቁሙ’ ብሎ ለህዝቡ እድል መስጠቱና ኮሚሽነሮችን የመሰየምና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ከሥራ አስፈጻሚው ወደ ህግ አውጪው ኃላፊነቱን ማሻገሩ በጣም አበረታችና ዋጋ ልንሰጠው የሚገባ ነው፤ አሁን ያለው መንግሥት ቀደምት መንግሥታት እንዳደረጉት፣ ‘የጨዋታውን ህግ እኔ ፅፌዋለሁ፤ ይህን የምትከተል ከሆነ ተከተል የማትከተል ሂሳብህን ታገኛለህ’ ሳይል፣ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ለአገራዊ ምክክር መደላድል መፍጠሩን ቀላል ነገር አድርገን ልንቆጥረው አይገባም” ብለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ለምክክሩ በተዘጋጀ መንፈስ እስረኞች መፈታታቸውም ለምክክሩ ስኬታማነት የመንግሥትን ዝግጁነት የሚያሳይ ነው። እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ፍርድ ቤቶች ያሉ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ከፊት ይልቅ ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ያሳየው ቁርጠኝነትም መልካምና አበረታች ነው፤ እነዚህ ተቋማት ከመንግሥት ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ ያለው ዝግጁነት፣ ምክክሩ በተሻለ ሁኔታ ሊካሄድ እንደሚችል የሚያሳይ ተስፋ ሰጪ ተግባር ነው።

“በመንግሥት በኩል አገራዊ ምክክርን ለማካሄድ እጁን መዘርጋቱ፤ ቅድመ ዝግጅቶችንም እያካሄደ መሆኑ ለምክክሩ ስኬታማነት ያለውን ፍላጎት ያሳያል። ከዚህ ቀደም የነበሩንን የውይይት እድሎችና የተዘረጉ የሠላም እጆችን በይሁንታ አለመቀበላችን ለበርካታ ችግሮች ዳርጎናል፣ ዳግመኛ ላለመሳሳት፣ መንግሥት አገራዊ ምክክር እንዲደረግ መስመሩን ሲዘረጋ፣ ‘እንመካከር፤ መፍትሔ እናምጣ’ በሚልበት ጊዜ፣ የተዘረጉ የሰላም እጆች እንዳይታጠፉ ሠላም የሚፈልግ ሁሉ ተባባሪ መሆን አለበት።” ያሉት ደግሞ ወ/ሮ ደስታ ናቸው።

 አቶ ሌንጮም፣ ለምክክሩ መንግሥት ያሳየው ዝግጁነት መልካም መሆኑን አንስተው፣ በሂደቱም የመንግሥት ሚና ለምክክሩ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠርና እንደ አንድ የምክክሩ ተሳታፊ ከመመካር ያለፈ ተግባር ውስጥ ሳይገባ ለኮሚሽኑ ገለልተኛነት ለምክክሩም ስኬት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ለምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው የሚናገሩት አቶ ንጉሡ፣ “የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች የምክክሩ ተሳታፊዎች የሌላውን ፓርቲ አመለካከት ያለ ምንም ብያኔ ቁጭ ብለው በማዳመጥ፣ ለህዝቡ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፤ በምክክሩ የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መምጣታቸው ስለማይቀር የምንሰማቸው ነገሮች የሚቆረቁሩ የጫማ ውስጥ ጠጠር ሊሆኑ ይችላሉና ልበ ሰፊነት እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

“ፖለቲካ” ፈረንጆቹ እንደሚሉት “The art of possible” ወይም የተለያዩ አመለካከቶች ወደ ጠረጴዛ መጥተው የተሻለውን መቀበል በመሆኑ፣ ፖለቲከኞቻችን ሰጥቶ መቀበልን መልመድ አለባቸው ያሉት አቶ ንጉሡ፣ ከዚሁ ጋር አያይዘው ፖለቲከኛና አክቲቪስት ለየቅል መሆናቸውን በመጥቀስ፣ “አክቲቪስቶች” የእኔ አጀንዳ በማንኛውም አይነት መንገድ ተቀባይነት ማግኘት አለበት የሚሉ ሲሆኑ፣ “ፖለቲከኛ” ግን በባህሪው ዲፕሎማት ወይም፤ ሰጥቶ በመቀበል የሚያምን ነው በማለት ያስረዳሉ። አክለውም፣ ይህ ምክክር የፖለቲካ አመራሮቻችን ህዝብን የሚያከብር፣ ሀገርን የሚያስቀድም እውነተኛ አመራር የሚሰጡበትን እድል የሚሰጣቸው ነው ብለዋል።

አቶ ሌንጮም ለምክክሩ ስኬት፣ ሁሉም አካል ከተናጠል አሸናፊነት ስሜት መውጣት እንዳለበት “በኢትዮጵያ ሁኔታ ክርክር አደገኛ ነው፤ የሚያስፈልገንም አንድ ቡድን ብቻ በአሸናፊነት የሚወጣበት ክርክር ሳይሆን ሁሉም የሚያሸንፍበት ውይይት ነው። እስከዛሬም፣ አንድ ቡድን በኃይል የሚመጣበት፣ ስልጣን የሚቆጣጠርበትና መንግሥት የሚያዋቅርበት፣ በህዝብ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን በገዥው ኃይል ላይ ግን ተፈጻሚ የማይሆን ሕገ-መንግሥት የሚባል ጽሑፍ የሚያዘጋጅበት ሥርዓት ችግር ፈጥሮብናል፤ ስለሆነም የምናደርገው ውይይት ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርገን፤ በፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል።” በማለት አብራርተዋል።

ታሪካችንን ያበላሸነው፣ የራሳችንን ንብረት በራሳችን ክብሪት ያቃጠልነው፣ በርካታ ዜጎቻችንን ያጣነው፣ ዓላማችንን ባለመለየታችን፣ ረጋ ብለን ማሰብና “እንወያይ፤ እንምከር” የሚሉ ግብዣዎችን መጠቀም ባለመቻላችን ነው በማለት በቁጭት የሚናገሩት ወ/ሮ ደስታ ቁጭ ብለን ባለመነጋገራችን እንጂ፣ ሠላማችንን የሚነሱ የትኞቹም ጉዳዮች በውይይት የማይፈቱ አልነበሩም ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱንና የመንግሥት አሰራሮችን ከመቀየር ጀምሮ ሌሎች በርካታ የማያግባቡንና በየጊዜው ሠላም የሚነሱን ጉዳዮች ላይ እርስ በእርስ በመነጋገርና በመመካከር ልንፈታቸው የሚችሉ እንደሆኑም ይናገራሉ። ዋናው የህዝቡ ፍላጎት ሠላም ነው፤ ህዝቡ ምን ትፈልጋለህ? ቢባል የሚያስቀድመው ሠላሙን ነውና፣ የውይይታችን የመጨረሻ ግብ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና ለአገራችን ሠላምን ማስገኘት መሆን ይኖርበታል፣ ውይይታችንንም በቅንነት ልናደርገው ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የህዝብ ፍላጎት፣ አገሩ የተረጋጋች ሆና፣ ከአገሩ ሳይሰደድ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ ሠላማዊ ኑሮን መኖር ነው በማለት አቶ ንጉሡ፣ የወ/ሮ ደስታን ሐሳብ ያጠናክራሉ። ፖለቲከኞች ቅድሚያ ለሕዝቡ ፍላጎት፤ ቅድሚያ ለሠላም መስጠት አለባቸው በማለት፣ ይህን ሐሳባቸውን የሚያስረዳ የሚከተለውን ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡-

“ሶስት ጎረቤታሞች በጣም ጥሩና የሚያምር በሬ ያዩና ይወዱታል፤ ብር ስላልነበራቸው ከገዛን በኋላ እንከፍላለን ይሉና በዱቤ ይገዙና ያርዱታል። በሬው ከታረደ በኋላ ግን፣ ሶስቱም በሬው ይመለስ አንፈልግም ይላሉ። እነዚህ ሰዎች በሬው ከታረደ በኋላ አንፈልግም ያሉበት ምክንያት፡-

አንደኛው፡- ለካ በሬውን የፈለገው ቆዳው ለአንድ ሌሎቹ ለማያውቁት ዓላማ ይፈለግ ስለነበረና የበሬው ቆዳም ከበሬው ዋጋ ስለሚበልጥ ነበር፣ ነገር ግን ቆዳው ብዙ ቦታ ስለተበሳሳና እንደፈለገው ስላልሆነለት በሬውን አልፈልግም አለ፣

ሁለተኛው፡- አካባቢው ላይ ያሉ ከብቶች ሆዳቸው ውስጥ ወርቅ ይገኛል የሚል ነገር ስለሰማ ወርቅ አገኛለሁ ብሎ ጠብቆ ነበር፤ ነገር ግን በሬው ሆድ ውስጥ ምንም ዓይነት ወርቅ ስላልነበረ በሬውን አልፈለገም፣

ሶስተኛው፡- የበሬው ጉበት ለአንድ ክፉኛ ለታመመ ሰው ፈውስ ይሆናል ብሎ ቋምጦ የነበረ ቢሆንም፣ በሬው ሲታረድ ጉበቱ የተበላሸ ስለነበር በሬውን አልፈለገም።

ሶስቱም ፍላጎታቸው ስላልተሟላ “በሬውን አንፈልግም፤ ይመለስ” አሉ። ነገር ግን በሬው አንዴ ታርዷልና ወደኋላ መመለስ ስለማይችል ከበሬው ሻጭ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ገቡ፤ ከሶስቱም ፍላጎት ውጪ የነበረው የበሬው ስጋ ግን ሲታይ እዛ አገር ታይቶ የማያውቅ ቆንጆ ስጋ ነበር። ይህንን ቆንጆ ስጋ አካፍለው ሰዎች ስጋውን እንዲበሉ ማድረግ ይችሉ የነበረ ቢሆንም ይህን ማሰብ አልቻሉም። የእነዚህ ሶስት ሰዎች ቤተሰቦች ሲጠየቁ ግን፣ ስለ ቆዳውም፣ በሬው ሆድ ውስጥ ይገኛል ስለተባለው ወርቅም ሆነ ስለጉበቱ ጉዳያቸው አልነበረም። ልክ በሬውን ታርዶ ሲያዩት ፍላታቸው ያረፈው ስጋው ላይ ነበር።”

ከዚህ ምሳሌ የምንረዳው፣ አንዳንድ ጊዜ ህዝቡ የሚፈልገው ነገር እኛ የምንፈልገውን ላይሆን ይችላልና፣ የኛ ቆዳ፣ ወርቅና ጉበት ለህዝቡ ሰላም ካላመጣለት ትርጉም የለውምና ከፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የህዝቡን የልብ ትርታ ማዳመጥ፣ ፍላጎቱን ማወቅና ማክበር፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ መቀራረብ ይገባል በሚል የመጨረሻ መልዕክት ሐሳባቸውን አሳርገዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መጽሔት መጋቢት 2014 ዓ.ም

Recommended For You