መግቢያ
ሰሞኑን የዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች የመወያያ ርዕስ “የአየር ቅጥ ለውጥ” (“የአየር ንብረት ለውጥ”ም ይባላል) የባለጉዳዮች ኮንፈረንስ (Conference of the Parties/ COP26) ሆኖ እንደሰነበተ ይታወሳል። “ለመሆኑ ይህ ዓለምን ያስጨነቀው ኩነት ምንድን ነው?” ብለን ስንጠይቅ፣ ዋናው ምክንያት “የአየር ቅጥ ለውጥ” ድምበር ዘለል የሆነ፣ የዓለም አቀፍ አንኳር ተግዳሮቶች መንስዔ ሆኖ ስለተገኘ ነው፣ የሚል ምላሽ እናገኛለን።
ሕያውያን (ሕይወት ያላቸው ሁሉ፣የሰው ልጅንም ይጨምራል) ሕልውናቸው ዘላቂነት እንዲኖረው ከአካባቢያቸው ጋር ሚዛኑን የጠበቀ የማይዛነፍ ትስስር እንዲመሠርቱ ያስፈልጋል። በአካባቢው የይዘት ለውጥ ሲከሰት፣ የግንኙነቱ ሥርዓት ይለወጣል/ይዛባል፣ ብሎም ቀውስ ይፈጠራል። ስለሆነም የአካባቢው ይዘት ሲቃወስ፣ በሰው ልጅ ኑሮ/ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮቶችን ያስከትላል። ለሰው ልጅ የሚጠጣው ንፁህ ውሃ፣ የሚተነፍሰው ንፁህ አየር፣ የሚመገበው በቂና ያልተበከለ ምግብ ያስፈልገዋል። የአየር ቅጥ ለውጥ እነኝህን መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዳይሟሉ ለሚያደርጉ ተግዳሮቶች መንስዔ ይሆናል። ዋናው የአየር ቅጥ ለውጥ ምክንያት በህዋ የካርቦን ይዘት / መጠን/ መናር ነው።
ሕይወት ከአካባቢው ጋር ያላት ግንኙነት፣ የረቀቀ እና ሚዛኑን ጠብቆ የሚንቀሳቀስ ነው። ሕይወት ከአካባቢዋ ጋር ያላት ግንኙነት ፈጣን ለውጦችን ለመቋቋም የተሰናዳ አይደለም። ሕይወት አካባቢውን እየቃኘች፣ የአካባቢውን ተጽዕኖ “ከብዝሃ ሕይወት” መሰናዶዎቿ ጋር እያጣጣመች፣ እያስማማች፣ በሂደት፣ “በብዝሃ ሕይወት” እምቅ አቅም፣ አካባቢውን ለመቋቋም የሚያስችል አዲስ ዝግጅት እየተደረገ፣ ሳይቻልም ውደመት እየተከሰተ፣ የተገኘች ፀጋ ናት።
የአካባቢ ለውጦች ዝግምተኛ እስከሆኑ ድረስ፣ ሕይወት ለውጦቹን ለመቋቋም የሚያስችል በብዝሃ ሕይወት አለኝታዋ መሠረታዊ መሰናዶዎች አሉዋት። የአየር ቅጥ የሚያስከትለው ለውጥ ግን፣ በጣም ፈጣን ስለሆነ ሕይወት ልትቋቋመው አትችልም። ለዚህም ነው የአየር ቅጥ ያስከተለው ቀውስ ነገ ዛሬ ሳይባል በአጭር ጊዜ መገታት የሚገባው።
የምድር ከባቢ አየር ነባራዊ ሁኔታ
ምድራችን በህዋ የተሸፈነች (የተከበበች) ስትሆን፣ ሽፋኑ የተለያዩ ጋዞች ጥርቅም ነው። እነሱም ዋና ዋናዎቹ (መጠኖቻቸው ውስን የሆኑ ሌሎች ጋዞች አሉ) የሕያው ግብዓት የሆኑት፣ በይዘት ሰባ ስምንት በመቶ (78%) ናይትሮጅን (Nitrogen)፣ ሃያ አንድ በመቶ (21%) ኦክሲጅን (Oxygen) እና በጣም ውስን (0.03%) “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” (Carbon dioxide-CO2) ናቸው።
በመሬት ዙሪያ ባለው አየር ውስጥ የሚገኘው ካርቦን በሁለት ኬሚካላዊ መዋቅር ይከፈላል፣ “በሜቴን” (methane) ወይም “በካርቦን ዳይኦክሳይድ” ይዘት ይገለጣል፣ ሌሎች መጠነ ውስኖች የሆኑ ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው ጋዞች አሉ። “ሙቀት አማቂ ጋዝ” በመባል የጋዝ ዓይነቶች መሬት ላይ የደረሰው የፀሐይ ሙቀት በቀላሉ ተንፀባርቆ ወደ ህዋ እንዳይመለስ፣ እንደመጋረጃ ሆነው ያገለግላሉ። ይህም “ዝግ ክበብ አየር” (Greenhouse effect) ተብሎ የሚታወቀውን ሁኔታ ያስከስታል (ፀሐይ ላይ መስኮቱ የተዘጋ መኪና ውስጥ ያለው አየር፣ ከውጭ አየር የበለጠ እንደሚሞቅ ዓይነት ማለት ነው)።
ይህ ነው የሕይወት አለኝታ “የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” እና የአባሮቹ “የግሪን ሃውስ ተፅእኖ” (Green House Effect) በመባል የሚታወቀው። በህዋ ውስጥ የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን በአንድ ላይ ሲታዩ እና የድርሻቸው መጠን ሲሰላ (በጠቅላላ ይዘታቸው እንደ አንድ መቶ ተወስዶ) “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” የአንበሳው ድርሻ አለው (85.4%)፣ የ”ሜቴን” መጠን ዝቅ ይላል (8.2%)፣ “የናይተረስ ኦክሳይድ” መጠን ደግሞ “ከሜቴን” መጠንም ዝቅ ይላል (4.4%)። ሌሎች፣ “ሲ ኤፍ ሲ” (CFCs)፣ “ኤፍ ቲ ሲ” (FTCs) ወዘተ. በድምሩ መጠናቸው ሁለት በመቶ ገደማ (2.1%) ብቻ ነው።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ የሚወሱት “ሜቴን” እና “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” ናቸው። “ሜቴን” ከ”ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” ጋር ሲነፃፀር፤ በአየር ውስጥ የሚገኝበት መጠን በጣም ውስን ከመሆኑም በተጨማሪ፣ “ሜቴን” በአጭር ጊዜ ወደ ሌላ ጋዝነት ስለሚቀየር፣ “በዝግ ክበብ አየር” ክስተት ውስጥ ዋና ሚና ያለው “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” ነው። “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” በዋናነት ለኢነርጂ ማመንጫ ነዳጆች ውጤት ሲሆን፣ “ሜቴን” ሳር/ቅጠል/ በል እንስሳት (አመስኳቾች/ አመንዣኪዎች) የቀንድ እንስሳት(የቤትም የዱርም) ሲያገሱ፣ በግሳታቸው ውስጥ የሚገኘው አንዱ ጋዝ ነው፤ እንዲሁም ከረግረግ አካባቢዎችም ተኖ አየርን ይቀላቀላል/ ይበክላል።
የአንድ የጋዝ ዓይነት “ዓለም አቀፍ የሙቀት የማናር አቅም” (Global warming potential/ GWP) የሚለካው ከካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መጠን ጋር ተነፃፅሮ ነው (ቀመሩ ከጊዜ ርዝመትም ጋር ይገኛል፣ ለዚህ ስሌት ስምምነት የተደረሰበት “በአንድ መቶ ዓመት” ከሚለው ላይ ነው)። ከሌሎች ሙቀት አማቂ ጋዞች ጋር ሲነፃፀር የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ አቅም ዝቅተኛው ስለሆነ፣ እንደመለኪያነት ተወስዷል፣ አንድ ተብሎ።
ለምሳሌ አንድ ቶን ሜቴን፣ የሃያ አምስት ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ያህል ሙቀት አምቆ የመያዝ፣ ብሎም የአካባቢውን ሙቀት የማናር አቅም አለው። በጥቅሉ “ሃይድሮ-ፍሎሮ-ካረቦንስ” (Hydrofluorocarbons/HFCs) በመባል የሚታወቁት ለማቀዝቀዣነት፣ እሳት ለማጥፋት እና ጥሩ ማዓዛን ለማሰራጨት ወዘተ. የሚያገለግሉ ኬሚካላዊ ውሁዶቹ የሙቀት ማመቅ አቅማቸው የትየለሌ ነው። ለምሳሌ “ኤች-ኤፍ-ሲ-23” የሚባለው ጋዝ አንድ ቶን፣ የአስራ አራት ሺ ቶን “የከካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” መጠን ያህል ሙቀት የማመቅ፣ ብሎም የአካባቢውን አየር ሙቀት የማናር አቅም አለው።
በአገራችን ከማዳበሪያ አጠቃቀም ብክነት እና ከቆሻሻ እየመነጨ “ለአየር ቅጥ ለውጥ” ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው “ናይተረስ ኦክሳይድ” (Nitrous oxide / N2O) መጠኑ ኢምንት ነው። ሆኖም ይህ የጋዝ ዓይነት አንድ ቶን፣ የሁለት መቶ ዘጠና ስምንት ቶን ከካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ያህል የሙቀት የማመቅ አቅም አለው። መጠኑ በሕዋ ውስጥ ካለው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መጠን ጋር ሲነፃፀር በሃያ እጅ ያንሳል።
በአጠቃላይ ከሌሎች ምድራችንን ከሸፈኑ ጋዞች ጋር ሲነፃፀር፣ በምድራችን ዙሪያ ያለው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መጠኑ በጣም ውስን ቢሆንም፣ ከላይ እንደተወሳው የፀሐይ ጨረር መሬት ላይ ከደረሰ በኋላ በነፀብራቅ ወደ ህዋ ተመልሶ እንዳይሄድ፣ እንዳይባክን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ከመሬት ሽፋን የሚንፀባረቀውን ሙቀት በከፊል ይገታውና የአካባቢውን ሙቀት ይጠብቃል /ያረጋግጣል/። ማለትም ሙቀቱ ታምቆ መሬት ላይ እንዲቆይ ያደርጋል።
“ሙቀት አማቂ ጋዞች” (ዋናው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ነው) ባይኖሩ ኖሮ የመሬት የሙቀት መጠን በአማካኝ በ35 ዲግሪ ሴልሺየስ (0C) ዝቅ ይል ነበር፣ ያም ማለት የመሬት አማካይ ሙቀት -120C (-180C ይሆን ነበር የሚሉ አሉ) ተብሎ ይገመታል። ያ ቢሆን ኖሮ ውቅያኖሶችም በጠቅላላ ወደ በረዶ አለትነት ተቀይረው፣ መሬት ድንጋይ መሰል ጠጣር ሆና፣ ዓለማችን ሕይወት-አልባ ትሆን ነበር (ስለጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ ለማዳበር ስለ ካርቦን ዑደት ተጨማሪ መረጃ ማግኘትን ያሻል) ።
የመሬት የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሽፋን ከበዛ፣ ተንፀባርቆ ወደ ህዋ የሚመለሰው ኃይል ስለሚቀንስ፣ በምድራችን ከፍተኛ (ከነባራዊው ሙቀት ጋር ሲነፃፀር) ሙቀት ይከሰታል፣ በአንፃሩ የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሽፋን ሲቀንስ፣ ተንፀባርቆ ወደ ህዋ የሚመለሰው ኃይል ስለሚጨምር፣ በምድራችን ብርድ (ቅዝቃዜ) ያንሰራራል። ስለሆነም የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሽፋን መጨመርም ሆነ መቀነስ የአካባቢ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው፣ ከባቢያችን አየር ሚዛኑ ሳይዛባ መጠበቅ አለበት።
ከላይ እንደተጠቀሰው በዋናነት በካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ሽፋን መጠን መናር መንስዔ፣ በዓለማችን በተደጋጋሚ ሙቀት እየተከሰተ ነው። ይኸም ሁኔታ ከፀሐይ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የውቅያኖሶች ሰፊ ገፅታንም ያካትታል። ስለሆነም ከባህር የሚተነውን የውሃ መጠን ከፍ ያደርገዋል፣ ያም የተነነ ውሃ ቀዝቅዞ ዝናብ ሆኖ ወደ መሬት ይወርዳል። የተነነው የውሃ መጠን ከፍተኛ ከነበረ፣ የዝናቡም መጠን በተመሳሳይ መንገድ ከፍተኛ ይሆናል። የውቅያኖሶች ሰፊ ገፅታ በቂ ሙቀት ካላገኘ፣ የሚተነው ውሃ መጠን ይቀንሳል። በትነት መቀነስ መንስዔ የዝናብ እጥረት፣ ብሎም ድርቅ ይከሰታል።
ጠቅለል ብሎ ሲታይ በተፈጥሮ አማካይ ከሆነው የሙቀት መጠን በጣም ከፍ ወይም ዝቅ ሲል ነባራዊው ሁኔታ ይዛባል። ይህ ነባር ሁኔታ ወቅት ጠብቆ የሚከሰት ነበር። በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ግን ይህ ሁኔታ በዘመናችን ከነባራዊው ሁኔታ በተዛባ መልክ በድግግሞሽ በመከሰት ላይ ይገኛል። “የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” መጠን ከነባራዊ ይዘት ከፍ ማለቱ የአየር ቅጥ ለውጥ ዋናው መንስዔ ነው።
በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ የተከሰቱ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች
የሕይወት አለኝታዎች የፀሐይ ሙቀት፣ ውሃ እና አየር ናቸው። በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ የአካባቢ ይዘት ሲዛባ፣ የነኝህ ወሳኝ የሕይወት አለኝታዎች ይዘት ይቃወሳል፤ ብሎም የሕልውና ዓቢይ ችግር፣ ተግዳሮት ይሆናል።
በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ የሚከሰቱት ዋና ዋና ተግዳሮቶችም የሚከተሉት ናቸው። (ሀ) የባህር ጠለል ከፍ ማለት እና አካባቢውን በጨው ውሃ ማጥለቅለቅ (በሰላማዊ ውቅያኖስ የሚገኙ የሩቅ ደቡብ ምሥራቅ ደሴቶች እንደምሳሌነት ሊወሰዱ ይችላሉ)። (ለ) የዝናብ መጠን በጣም ከፍ ማለት እና ጎርፍ ማስከተል፣ አልያም ዝናብ ጨርሶ ጠፍቶ ድርቅ መከሰት። (ሐ) ምድራችንን ከአሰጊ ጨረሮች የሚከላከልንን “ኦዞን” ሽፋን (Ozone layer)፣ የምድር ከባቢ (ሸፋን) ጋዝ ለማሳሳት፣ ብሎም አንዳንድ አካባቢዎች ላይም ለመሸንቆር ምክንያት ሆነዋል። ኬሚካላዊ ውሁዶቹ በጥቅሉ “ኤሮሶልስ” /aerosols/ ወይም የሃይድሮ-ፍሎሮ- ካረቦንስ (Hydrofluorocarbons/ HFCs) በመባል ሲታወቁ፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ለማቀዝቀዣነት፣ እሳት ለማጥፋት እና ጥሩ ማዓዛን ለማሰራጨት ወዘተ. የሚያገልግሉ ኬሚካላዊ ውሁዶቹ ናቸው። ይህም የሚያስከትለው ከፀሐይ የሚለቀቁ (የሚመነጩ) ጎጂ ጨረሮች ያለምንም መከላከያ ምድር ላይ ደርሰው ለቆዳ ካንሰር እንደሁም ለማየት መሳን (ለመታወር) ምክንያት ሆነዋል። (መ) የምድር ወገብ አካባቢ የተሰራጩ በሽታዎች የበለጠ እንዲያንሰራሩ ማድረግ (ለምሳሌ የወባ በሽታ) ናቸው።
ጠቅለል ብሎ ሲታይ የአየር ቅጥ ለውጥ የሚያስከትለው የከባቢ አየር ሙቀት መናር ጋር ተዛምዶ፣ የመሬት ዋልታ ክምር በረዶ መሟሟት፣ ጎርፍ በተደጋጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰት፣ የሰደድ እሳትም እንዲሁ፣ በድርቅ መጠቃት እና ወባን መሰል በሽታዎች ማንሰራራት ናቸው። የችግሩን ዓለም አቀፍነት ለማብራራት፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን አመልካች የሆኑ ፎቶግራፎች በጽሑፉ ተካተዋል (ፎቶግራፎቹ የተወሰዱት ከኢንተርኔት (Internet) ነው)። ችግሮቹ ደግሞ ከሰው ልጆች አንፃር ሲተረጎሙ፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ ሰላም ማጣት እና በስደት ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው።
ክስተቱን ከታሪክ አንፃር ስንፈትሸው፣ የኢንዱስትሪ አብዮት ለሰው ልጅ ያበረከተው አቅም አንድ ዓይነት ኃይልን፣ ወደ ሌላ ዓይነት ኃይል መቀየር ማስቻሉ ነው። ለምሳሌ ውሃን በከሰል እስኪፈላ ድረስ አሙቆ፣ ወደ እንፋሎትነት ከቀየረ በኋላ፣ ያን የሙቀት ኃይል ወደ ሞተር ማንቀሳቀሻ “ሜካኒካዊ ኤነርጂ” መቀየር፣ ብሎም በዚያ ኃይል የተለያዩ ሞተሮችን ማንቀሳቀሻነት (ለትራንስፖርት፣ ለድንጋይ መፍለጫ፣ መሬት ማረሻ) ተግባር ማዋል መቻሉ ነው። የሰው ልጅ በሂደት አንድ ዓይነትን ኃይል ወደ ሌላ ዓይነት ኃይል በመመንዘር ህዋን መዳሰስ፣ ቅጽበታዊ ፍጥነትን መጎናጸፍ፣ የትየለሌ ጉልበት ማካበት ችሏል።
ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ፣ የሰው ልጅ ለትራንስፖርትም ሆነ ለፋብሪካ ማንቀሳቀሻ የሚጠቀምበት የኃይል ምንጭ ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊት ምድር ላይ ከነበሩ እፀዋት፣ እንዲሁም ባህር ውስጥ ከነበሩ ረቂቅ ሕያውያን የተገኘ፣ “ካርቦናዊ-ውሁድ” (organic compound) ነው። በከርሰ ምድር ውስጥ የነበረውን የዕፀዋት እና የእንስሳት ቅሬት በነዳጅ መልክ በማቃጠል፣ ለኃይል ማመንጫነት የሰው ልጅ መጠቀሙ፣ በዙሪያው ያለውን የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መጠን ከፍ አድርጎታል። መሠረታዊ የሆነው የካርቦን እንቅስቃሴ፣ ማለት በውሃ በውቅያኖስ እንዲሁም በደለል መኻል ያለው ዝውውር፣ ሚዛኑ የተጠበቀ ነው፣ የችግሩ መንስዔ የዚያ ሚዛን መዛባት ነው።
በከርሰ ምድር የሚገኝ የኤነርጂ ምንጭ (የብረት ከሰል፣ ቤንዚን፣ ጋዝ) በዘመናችን ዋናው የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ ግብዓት ነው። በከርሰ-ምድር ነዳጅ (fuel) ውስጥ ያለው ካርቦን ከመሬታችን ላይ ተሰውሮ፣ በከርሰ-ምድር ተቀብሮ፣ የተከማቸ ስለነበር፤ አየር ውስጥ ካለው ካርቦን ጋር ለብዙ ሚሊዮን ዓመታት ግንኙነት ስለአልነበረው በነባሩ የካርቦን ዑደት ውስጥ አይካተትም ነበር።
በኤነርጂ አጠቃቀም ዙርያ ያለው የአየር ብክለት፣ ከምንጠቀምበት ኢነርጂ መጠን ጋር የተቆራኘ ነው። በኢነርጂ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆኑት አገሮች ባለፀጎች ሆነዋል። ሆኖም የተከተሉት የብልፅግና ጎዳና አሁን ለተከሰተው ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ችግር መንስዔ ሆነ።
ለምሳሌ አንድ አሜሪካዊ የሚበላው ምግብ በአማካኝ የምግብ ግብዓቱ ሁለት ሺ ኪሎ ሜትሮች ከተጓዘ በኋላ ነው ገበታ ላይ የሚቀርበው። በአንፃሩ የአገራችን ገበሬ፣ እንዲሁም ሌሎች የታዳጊ አገሮች ማህበረሰቦች ምግብ በሜትሮች፣ ቢበዛ በጥቂት ኪሎሜትሮች የሚቆጠር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ያም ከአሜሪካዊ ኩነት ጋር ሲነፃፀር ለትራንስፖርት የምንጠቀምበትን የኤነርጂ መጠን ውስን ያደርገዋል፤ እንዲሁም ብክለቱን። በተጨማሪ አንድን ምግብ “በማይክሮ ዌቭ” (Microwave) እንዲበስል የማዘጋጀት መሰናዶ፣ ምግቡን ቀጥታ በምድጃ ላይ ከማብሰል አሥር እጅ የበለጠ የኤነርጂ ፍጆታ ይፈልጋል።
በዝቅተኛ ሙቀት ሁኔታ፣ ለምሳሌ “በሳይቤሪያ” (ሩስያ) አካባቢ፣ መሬቱ አለት መሰል ጠጣር ሆኖ ነው የሚገኝ። የዚያ አካባቢ አፈር በውስጡ ሜቴን ጋዝን አምቆ የያዘ ነው። አካባቢው ከቅዝቃዜ ሲላቀቅ፣ ጭቃ መሰል ይዘትን ይጎናጸፋል። በዚህን ጊዜ አፈር ውስጥ ታምቆ የሚገኝ ሜቴን ጋዝ ይለቀቅና ከባቢውን አየር ይበክላል። ሜቴን በምድራችን ለሙቀት መናር አስተዋፅኦ ካላቸው ጋዞች አንዱ ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው “የሜቴን” ሌላው ምንጭ አመንኳሽ እንስሳት ናቸው። በዓለማችን ላይ ዋናዎቹ የስጋ አበርካቾች፣ የቀንድ ከብቶች ናቸው (ላም/በሬ/በግ/ፍየል)። ከብቶች በተፈጥሮ ከአካላቸው የሚከሉት የጋዝ ዓይነት ሜቴን እና ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ናቸው። ስለሆነም የከብቶች እስትንፋስ ከባቢውን አየር በሜቴን ይበክላል።
እንዲሁም የሰው ልጅ የመሬትን የዛፍ ሽፋን በመክላት (መቁረጥ)፣ እፅዋት በካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መልክ ይምጉት የነበረው ካርቦን ከአየር ከመከላት ገትቶታል። እፅዋትም ሲቃጠሉ የሚለቀቀው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ (ጢሱ) አየር ውስጥ ያለውን የካርቦን መጠን ከፍ ያደርገዋል።
በተጨማሪ፤ ረግረግ የሆኑ ቦታዎችን ማድረቅ፣ መታረስ የሌለባቸውን በሳር እና በቅጠላ ቅጠል የተሸፈኑ ቦታዎችን ለእርሻ ተግባር ማዋልም፣ ሊከላ/ሊወገድ ይችል የነበረን ካርቦን እዚያው ከከባቢ አየሩ ውስጥ እንዲቀር ያደርጋል። ብሎም በአየር ውስጥ ያለውን ካርቦን መጠን ከፍ እንዲል ያደርገዋል።
በባህር ውስጥ መጠነ ብዙ ካርቦን በኬሚካላዊ ውሁድ መልክ ታምቆ ይገኛል። በመሠረቱ በአየር ውስጥ የሚከሰተውን (በነዳጅ ቃጠሎ ምክንያት) የካርቦን መጠን መጨመር ለመከላከል ባህር ከፍተኛ (ካርቦንን ከአየር የመክላት) አቅም አለው። ቀዝቃዛ ውሃ ብዙ ካርቦን አምቆ ሊያስቀር ሲችል፣ ሙቅ ውሃ ግን በተቃራኒው ካርቦንን አምቆ የመያዝ አቅሙ ዝቅተኛ ነው። የውሃው ሙቀት መጨመር በጣም ውስን ቢሆንም የውሃውን ካርቦንን አምቆ የመያዝ አቅሙን በጣም ያኮስሰዋል። የባህር ሙቀት መጨመር ከሁሉም በበለጠ መንገድ ከባቢ አየር ውስጥ ያለውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መጠን ከፍ ያደርገዋል።
ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ለብዙ ዘመናት ያልታየ/ ያልተመዘገበ የሙቀት መጠን በዘመናችን እየተመዘገበ ነው። ይህም የናረ የሙቀት መጠን፣ በሙቀትነቱ ብቻ ለጥቂት አዛውንትና ሕፃናት ሕይወት ማለፍ /መቀሰፍ ምክንያት ሆኗል። የሙቀት መጠን በእጅ አዙር የሚያስከትላቸው ሌሎች አያሌ ችግሮች አሉ።
ለምሳሌ የበረዶ ክምር/ተራራ መሟሟት፣ በበረዶ መልክ “በአርክቲክና” (ሰሜን የምድር ዋልታ) “በአንታርክቲክ” (ደቡብ የምድር ዋልታ) ተከማችቶ የሚገኘው ውሃ ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ተቀይሮ፣ የባህር ወለልን ከፍታ ይጨምረዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኘው ከሺዎች ዓመታት በፊት ወደ በረዶነት (ice) የተቀየረው ጠጣር ውሃ (glacier)፣ በአካባቢው በተከሰተ የሙቀት መናር መንስዔ አሁን እየሟሟ ነው።
የአየር ቅጥ ለውጥ “ኤል ኒኖ” (EL NINO) ተብሎ የሚታወቀው የአየር ባህርያት ለውጥ፣ በመሬት ሙቀት መጨመር መንስዔነት እንደተከሰተ ይታመናል። በብዙ ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር የተንጣለለ የውቅያኖስ ገፅታ ላይ የሚገኝ ውሃ ሙቀት ሲጨምር፣ ከባህር በላይ ያለው የአየሩ ሽፋን ሙቀት አብሮ ይጨምራል። የሙቀት መጨመር፣ አየርንም ሆነ የውቅያኖስን ውሃ እንቅስቃሴ ከነባሩ ሁኔታ ያቃውሳል።
ሙቁ አየር በቀዝቃዛ አየር ወደ ተሸፈነው አካባቢ ሲገሰግስ፣ ከታች ያለውን ውሃ ይጎትተዋል፤ ይስበዋል፤ የውሃው ጉዞ (current) ፍጥነትም እንዲጨምር ያደርገዋል። ያም ሲበረታ የማእበል መንስዔ ይሆናል። የቀውሱ ክስተት ስያሜም እንደየአካባቢው ይለያያል፣ “ቶርኔዶ” (Tornedo)፣ ሃብላይ ነፋስ (አውሎ ነፋስ (Hurricane) እንዲሁም ኩርፊት (Cyclone) እና ኩርፊታዊ ዝናብ (Cyclonic rain) በመባል ይታወቃሉ። ሆኖም ሁሉም ከባህር ውሃ ሙቀት ሁኔታ ጋር የተዛመዱ ናቸው።
የአየር እንቅስቃሴ መቃወስ፣ የዝናብን ሁኔታ ያዛባል (ዝናብ እና ነፋስ የተቆራኙ ስለሆኑ)። ስለሆነም በአንዳንድ ቦታዎች ከፍተኛ ዝናብ፣ በሌሎች ቦታዎች ከፍተኛ ድርቅ ተከሰተ። ያንዱ ድርሻ ያለ አግባብ ለሌላው የተሰጠ ይመስላል። በዚያ ምክንያት የውቅያኖሱ ውሃ ሙቅ በሆነበት አካባቢ መጠነ ግዙፍ ዝናብ፣ ቀዝቃዛ በሆነበት አካባቢ ደግሞ በተቃራኒው አካባቢው ዝናብ አልባ ይሆናል። በተጨማሪ ሙቀት ሲጨምር በደኖች ውስጥ ያለው አፈር ርጥበት አልባ ይሆናል። መሬት ላይ የወደቀው የእፅዋት አካልም በጣም ይደርቃል፤ ስለሆነም ደኑ በቀላሉ ለሰደድ እሳት ይጋለጣል። ከሙቀት ጋር ተዛምዶ የሰው ልጅ ባህርይ እንደሚቀየር ይታመናል፣ ብሎም አካባቢውን ሰላም የመንሳት ሁኔታ ይከሰታል።
በአገር ደረጃ በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ለአደጋ የተጋረጡ አገሮች፣ ምንም ብዙ ቢሆኑም ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡት ኬንያ፣ ሲሪላንካ፣ ሕንድ፣ ሩዋንዳ)፣ ማዳጋስካር፣ ጀርመን፣ ፊሊፒንስ እና ጃፓን ናቸው ተብሎ ይታመናል።
ባለፉት አራት ዓመታት ጀርመን አገር ባልተጠበቀ እና ባልተለመደ ደረጃ ከፍተኛ ሙቀት እየተከሰተ ነው። ይሄም የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተለይ የግብርናውን ክፍል እና የውሃ ፍጆታ ሁኔታ እያቃወሰው ነው። በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ የጀርመን ብዙ አካባቢዎች በጎርፍ እየተጥለቀለቁ ናቸው። በአገረ ጃፓን የሚጥለው በረዶም ሆነ የክረምቱ ወቅት እየቀነሰ ነው። ከፍተኛ ሙቀት፣ መጠነ ብዙ ዝናብ እንዲሁም በተደጋገመ ሁኔታ የሚከሰት ማዕበል አገረ ጃፓንን እያጠቃት ነው። ሁኔታውም የግብናውን ክፍለ ኢኮኖሚ አቃውሶታል።
በሕንድ አገር በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ብዙ ሰዎች ለሕልፈት እየተዳረጉ ነው። ከላቲን አሜሪካ አገሮች አንዷ የሆነችው ሃይቲ በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ለችግር የተጋለጠች ናት። በሴኔጋል በባህር ዳር የሚኖሩ ማህበረሰቦች አሰፋፈራቸው እየተመሰቃቀለ ነው። በዚያ አካባቢ የባህር ጠለል በየዓመቱ ከ3.5 እስከ 4 ሚ.ሜ ከፍ በማለት ላይ ይገኛል። የሴኔጋል አማካዩ ሕዝብ (52%) በባህር ዳር አካባቢ ስለሚኖር፣ የባህር ጠለሉ ከፍ በማለቱ፣ ለከፍተኛ ቀውስ በመጋለጥ ላይ ይገኛሉ።
ኬንያ በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ የማህበረሰቡ የግብርና እና የቱሪስት ዘርፎች ኢኮኖሚ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል። ከብት አርቢዎችም ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ናቸው። በድርቅ መንስዔ ከብት አርቢ ማህበረሰቦች፣ በግብርና ላይ ሕይወታቸውን ወደ መሠረቱ አካባቢዎች እየተሰደዱ፣ በሁለቱ ማህበረሰቦች መሃከል ግጭት በተደጋጋሚ ይከሰታል። በአጠቃላይ ነባራዊ የኑሮ ሁኔታዎቻቸው በመቃወስ ላይ ይገኛል። ይህ ዓይነት ችግር በኢትዮጵያም በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው።
አብዛኞቹ የሩዋንዳ ማህበረሰቦች ኑሮዋቸው ገጠር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ሕልውናቸው ከተፈጥሮ ሀብት ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። ዋናው የኑሮ አለኝታቸውም ግብርና ላይ ነው የተመሠረተ። የአየር ቅጥ ለውጥ የኑሮ አለኝታቸውን አዛብቶታል። በተጨማሪ በምድር ወገብ አካባቢ ሰዎች በበሽታዎች እየተጠቁ ናቸው፤ ዋነኛው ወባ ነው። ይህ በኢትዮጵያም የተከሰተ ነው።
ሲሪላንካ ደሴት እንደመሆኗ፣ ሰፊ የባህር ጠረፍ አካባቢዎች አሏት፣ አካባቢውም በማዕበል እየተጠቃ ነው። በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ፣ የባህር ወለል ከፍ እያለ ስለሚገኝ፣ አካባቢው በውሃ በመጥለቅለቅ ላይ ይገኛል። በተጨማሪ ደኖች እየወደሙ ናቸው፣ የተፈጥሮ አደጋም በተደጋጋሚ እየተከሰተ ይገኛል። በባህር ጠረፍ አካባቢ ብዙ ሰዎች ሰፍረው የሚገኙበት፣ እንደ ባንግላዲሽ ያሉ አገሮች በጎርፍ እና በማዕበል እየተጠቁ ነው። የአካባቢው የባህር ጠለል ከፍ በማለቱም፣ የመጠጥ ውሃ በጨዋማ ውሃ እየተበከለ፣ የመጠጥ ውሃ ችግርም እየተከሰተ ነው።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምሁራን ካናዳ ከየትኛውም አካባቢ በላቀ ሁኔታ በአየር ቅጥ ለውጥ የምትጠቃ መሆኗን ይገልጣሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በካናዳ በብዙ አካባቢዎች ቋያ እሳት እንዲሁም ጎርፍ ከፍተኛ ተግዳሮት እያስከተሉ ይገኛሉ። ችግሩን ለመቋቋም አቅም ያላቸውን ያደጉ አገሮችንም ቢያካትትም በተጎጂነት ደረጃ ግን ታዳጊ አገሮች ናቸው ተጠቂ የሚሆኑት። ለምሳሌ የደቡብ ሩቅ ምሥራቅ ደሴቶች በስጠም (በጨዋማ ውሃ መጥለቅለቅ) ላይ ይገኛሉ። መሬትን ጨርሶ ማጣትን ያህል የሚመጥን ጉዳት የለም።
ፊሊፒንስ በዓመት ቢያንስ ከሃያ ባላነሱ ማዕበሎች (typhoons) ትጠቃለች። ፊሊፒንስ ብዙ ደሴቶችን ያካተተች አገር ስትሆን፣ ከባህር አካባቢ በሚገኝ የምግብ ፍጆታ ከፍተኛ ተጠቃሚ ናት። ሆኖም በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ከባህር ታገኝ የነበረው ምግብ ምርት (ምሳሌ አሳ) በጣም እየተመናመነ መጥቷል። እንዲሁም በተደጋጋሚ በጎርፍ በመጠቃት ላይ ትገኛለች።
የአየር ቅጥ ለውጥ በአብዛኛው ሕዝብ የኑሮ አለኝታ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረገ ነው። እንዲሁም የብዝሃ ሕይወት ባለፀጋ የሆነችው ማዳጋስካር፣ በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ፣ በጎርፍ ወይም በድርቅ ምክንያት በመመናመን ላይ ትገኛለች።
የችግሮች መፍትሄ እና ስምምነቶች
በዓለም ላይ የተከሰተውን የአየር ቅጥ ለውጥ ችግር ለመግታት ብዙ ዓለም አቀፍ ውይይቶች፣ ስምምነቶች እና አገር አቀፍ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ (ዝርዝራቸውን መግለጥ ለጽሑፉ ዓላማ ጠቃሚ ላይሆን ይችላል)። በውይይቶች እና በስምምነቶች የሰው ልጅ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ካልቻለ፣ ህልውናው አጠያያቂ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ተንፀባርቋል።
ችግሩን ለመፍታት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ መሆን ይገባቸዋል። የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም፣ ማለት በአካባቢ አሉታዊ ተፅዕኖ በማያስከትልበት ደረጃ ሃብትን መጠቀም ዋናው አማራጭ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ያምናሉ፤ በውይይቶችም ተመሳሳይ ድምዳሜዎች ላይ ተደረሷል። በዚህ ድምዳሜም “ካርቦን ዳይ
ኦክሳድ” ማመንጨትን መግታት ነው፣ “ካርቦን ዳይ ኦክሳድ” አመንጭ የሆኑ ግብዓቶችን (ቤንዚን፣ የብረት ከሰል፣ ወዘተ. ) መቀነስ፤ ብሎም በሂደት ጨርሶ ማምከን ነው።
የዓለማችንን አየር የሚበክለውን የካርቦን መጠን ለመቀነስ እንደሚያስፈልግ የዓለም መንግሥታት ከሞላ ጎደል ያምናሉ፤ ሆኖም እንዴት በሚለው ላይ አለመግባባቶች ይስተዋለሉ። የአየር ቅጥ ለውጥን በመጠኑም ቢሆን መቋቋም እንዲቻል ሊተገበሩ የሚገባቸው ተግባራት አሉ። ሁሉም ዓላማቸው የአካባቢውን አየር የሚበክሉ “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” እና “ሜቴን” ምንጮቻቸውን ማድረቅ ሲሆን፣ ከመነጩም በኋላ ከአየር የሚከሉበትን መንገድ ሥራ ላይ ማዋል ነው።
ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል እንዲቻል የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ድርጅቶች አሉ። አካባቢያችንን የሚበክለውን የካርቦን ዳይ ኦክሳድ መጠን ለመቀነስ፣ ብዙ ዓለም አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ተቋማቱም የተለያዩ ፕሮግራሞችን ነድፈው ፕሮግራሞቹ በተግባር እንዲተረጎሙ በመገፋፋት ላይ ይገኛሉ። ዋናው መንገድ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም፣ ካርቦን ማመንጨትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ነው። ለዚህም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በተደጋጋሚ እየተካሄዱ አንዳንድ ስምምነቶች ላይ እየተደረሰ ነው (ምንም ስምምነቶቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባይደረጉም)።
የካርቦን ዳይ ኦክሳድ መጠን መጨመር ምክንያት የተከሰተውን የዓለማችን ሙቀት ለመግታት፣ በቅነሳ ሂደት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግብ ተቀምጧል፣ ያም በ2050 ከቅድመ ሁኔታው (ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ከነበረው) ጋር ተነፃፅሮ ከ1.50C ያላለፈ እንዳይሆን ማስቻል ነው።
የአየር ቅጥ ለውጥ ከአካባቢ ቀውስ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስላለው፣ በታዳጊ አገሮች አካባቢ ጥበቃን ማዕከል ያደረጉ እንቅስቃሴዎች በማበረታታት ላይ ይገኛሉ። ያም የደኖችን ውድመት መታደግ ብሎም መልሶ ማቋቋም እና ለተመሳሳይ ችግር ፈች ተግባራት ፖሊሲዎችን መቅረጽ፣ ሕጎችን መደንገግ፣ ደምቦችን ማውጣት፣ ፕሮግራሞችን መቅረጽ ወዘተ. ሲሆኑ፤ እነኝህም ተግባራዊ እንዲሆኑ የዓለም ሕዝቦች ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለፕሮግራም ማስተናገጃ ያደጉ አገሮችም መጠነኛ ድጋፍ ለታዳጊ አገሮች ያደርጋሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የተከሰተውን የአየር ቅጥ ለውጥ ለመቋቋም በ20 ዓመታት 150 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል፤ በኢትይጵያ አቅም ካለድጋፍ ያንን ለመተግበር እንደሚያዳግታት እሙን ነው።
ታዳሽ ኃይል የኢነርጂ ምንጭ (Susatainable Energy Source) ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ስለማያመነጭ (ስለማይተፋ)፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን መጠቀም ዋናው ለችግሩ መፍትሄ የተገኘ አማራጭ ነው። ያደጉ አገሮች ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይችላሉ። ታዳጊ አገሮች ግን በገንዘብ እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት ውስንነት፣ ተመሳሳይ ተግባራትን ማከናወን ይሳናቸዋል። ሆኖም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ያልተሳተፉበት የጥፋት ሂደት፣ ከአጥፊዎቹ በላቀ ሁኔታ ያጠቃቸዋል።
ምንም የተከሰተው ችግር የጋራ ቢሆንም፣ ችግሩን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት የተለያዩ ኃላፊነቶች ያስፈልጋሉ የሚሉ ብዙ ታዳጊ አገሮች አሉ። ዋናው ምክንያት አሁን ላለው ብክለት ዋናው መንስዔ ያደጉ አገሮች አሁን ካሉበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ የተጠቀሙበት የኢነርጂ ማመንጫ ግብዓት ስለሆነ ነው። ያም ከከርሰ ምድር የተገኙ (የብረት ከሰል፣ ቤንዚን እና ጋዝ) ኃይል ሲመነጩ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የሚተፉ ግብዓቶች ስለነበሩ/ ስለሆኑ ነው።
አንዱ የስምምነቱ ዋልታ በካይ ባልሆነ የኢነርጂ ማመንጫ ዘዴ መጠቀም ሲሆን (ለምሳሌ በታዳሽ ኃይል ምንጭ፤ ፀሐይ፣ ነፋስ፣ ውሃ፣ ጂኦተርማል፣ ወዘተ.)፣ ታዳጊ አገሮች በካይ ባልሆኑ ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ገንዘቡ ስለሌላቸው ያንን የጋራ ችግር ለመፍታት ያደጉ አገሮች፣ ለታዳጊ አገሮች የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለባቸው ተብሎ ይታመናል።
የችግሩ ታሪካዊ መንስዔ የሆኑት፣ ማለት በኢኮኖሚ የበለፀጉ፣ የለሙ አገሮች፣ በጋራ በደረሱባቸው ስምምነቶች መሠረት ለታዳጊ አገሮች ቋሚ ድጋፍ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ከላይ እንደተጠቀሰው በመጠኑም ቢሆን ድጋፍ በማድረግ ላይም ይገኛሉ። በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ስምምነት የተደረሰበት፣ ማለት በየዓመቱ አንድ መቶ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በአደጉ አገሮች (በታሪካዊ በካዮች) ለታዳጊ አገሮች ፈሰስ የሚደረግ ገንዘብ እስከ አሁን እውን አልሆነም። ይህም ሁኔታ ባደጉ አገሮች እና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ያለመተማመን ሁኔታ ዋና ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል።
ለምሳሌ ሕንድ፣ አየር በካይ ባልሆኑ ዘመናዊ የኃይል አመንጭ ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም፣ ብሎም በካይ ባልሆነ መንገድ ለመጓዝ እንድትችል፣ ለዚህ ተግባር የገንዘብ ድጎማ ያስፈልጋታል። አለበለዚያ አቅሟ በሚፈቅደው በነባሩ (በካይ ቴክኖሎጂ/ ከሰል በማንደድ) የልማት ሂደቱን ለተወሰነ ጊዜ ለማስተናገድ እንደምትገደድ ደጋግማ ገልጣለች። በተጨማሪ ለታዳጊ አገሮች የሚደረገው የገንዘብ ፈሰስ፣ ከወሬ እንዳላላፈ በብዙ አካባቢ ይታወቃል። ቀደም ሲል ቃል የተገባውም ሆነ ለወደፊት ይተገበራል የተባለው የገንዘብ መጠን አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አይገኝም።
የሕይወት አለኝታቸውን ግብርና ላይ የመሰረቱት ታዳጊ አገሮች የሚያመነጩት በካይ አየር በጣም ውስን ነው (በዓለም ከሚመነጨው ሩብ /26%/ ገደማ ነው)። በተለይ አፍሪካ ለብክለት ዝቅተኛ ተዋናይ ብትሆንም፣ በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ተጎጂነቷ ግን ከፍተኛ መሆኑ ይስተዋላል። ለምሳሌ ማዳጋስካር እና ደቡብ ሱዳን በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ለጎርፍ እንዲሁም ለድርቅ በተደጋጋሚ እየተጋለጡ ናቸው።
በተደጋጋሚ የሚደረጉት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ዋና ዓላማ የከባቢ አየርን የካርቦን ብክለት መቀነስ ሲሆን፣ በብዙ አካባቢዎች ውጤቶች አመርቂ እንዳልሆኑ በየስብሰባዎቹ ይተቻል። ከላይ እንደተወሳው የብከለት ቅነሳው ግብ፣ ከባቢ አየር ሙቀት ቅደመ ኢንዱስትሪ አብዮት ከነበረው የከባቢ አየር ሙቀት በ2050 ከ1.5 0C የላቀ እንዳይሆን ሲሆን፣ እዚያ ለመድረስ በተተለመውም መንገድ ላይ ስምምነት አልተደረሰም። ግብን ለመምታት የበካይ ኢነርጂ አመንጭ ቁሶች አጠቃቀም አሁን ካለው ይዘት በጣም መቀነስ አለበት። በአሁኑ ይዘት ከቀጠለ፣ በ2050 የሚኖረው ሙቀት፣ ከቅድመ ኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ሲነፃፀር ከ2.4 0C ያላነሰ እንደሚሆን ይገመታል።
በመሠረቱ ለዓለማችን አየር ብክለት ዋና ተዋናይ የነበሩት/ የሆኑት በአሁኑ ወቅት ያደጉ አገሮች ተብለው የሚታወቁት አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ናቸው። አሁንም ብክለቱ በነፍስ ወከፍ ሲሰላ ዋና በካዮች እነሱ ናቸው። ብዙ ጊዜ የሚወቀሱት ቻይና እና ሕንድ ግን የሚያስከትሉት ብክለት በነፍስ ወከፍ ሲሰላ ከአሜሪካ በብዙ እጅ ዝቅ ይላል። የኤሌክትሪክ ኃይል “በኪሎ ዋት” የነፍስ ወከፍ አጠቃቀም፣ ከኃይል ማመንጫው ግብዓት አንፃር ታይቶ፣ የብክለት አመላካች ሊሆን ስለሚችል መጥቀሱ ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ የኮረንቲ ኃይል አጠቃቀምን ወስደን፣ ዓመታዊ ይዞታውን በነፍስ ወከፍ “በኪሎ ዋት አወር” ብናሰላ (kwh/ annum/ peson)፣ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ 15 ሺ፣ አሜሪካ 10ሺ፣ ቻይና 4 ሺ፣ ሕንድ 750፣ እና ኢትዮጵያ 73 ነው።
በፀሐይ ኃይል ቀጥተኛ ተጠቃሚው ፋብሪካ “አረንጓዴ ሃመልሚል” (Chlorophyll) “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን” ምጎ በምትኩ ኦክሲጅንን (O2) ይተፋል። “ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” የእፅዋት እድገት ዋና ግብዓት ሲሆን፣ ኦክስጂን ደግሞ የእስትንፋስ አለኝታ ነው። አንዱ “የካረቦን ዳይ ኦክሳይድ” መጨመር ችግር መፍቻ መንገድ ዛፍ መትከል ነው። እፅዋት ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ከአካባቢው አየር ወስደው፣ በፀሐይ ኃይል አጋዥነት ወደራሳቸው አካልነት ቀይረው፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለእንስሳት በጠቅላላ ምግብን ያበረክታሉ፣ እንዲሁም እንስሳት የሚተነፍሱትን አየር ያጠራሉ (ንፁህ ያደርጋሉ)። ያም በዓለማችን ያለው አንዱ እና ዋናው ተዓምር ነው [ዕፅዋት፣ በፀሐይ ኃይል ግብዓትነት፣ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን ከጋዝነት (የአየር አካልነት) ወደ ጠጣር የዕፅዋት አካልነት መቀየር ነው]።
እንጨት ስናነድ የምናገኘው ሙቀት፣ ቀደም ሲል በእፅዋት ከፀሐይ የተዘረፈ ሙቀት ነው። በሂደት ከአየር ቀደም ሲል የተወሰደው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ፣ ከእንጨት (እፅዋት) አካልነት ተወግዶ፣ በጋዝ መልክ ከአየር ጋር ይቀላቀላል (ተፈጥሮ ብክነት አልባ ናት፣ ትገነባለች፣ ታፈርሳለች፣ ፍርስራሹ ሲመነዘር ያው ቀደም ሲል ለግንባታ ግብዓት ወደ ነበረው አካል ነው የሚቀየረው (ለምሳሌ ጡብ ወስደን ሲገነባ የተለያዩ ህንፃዎች፣ ሲፈርስ ጡብ እንደሚሆን ሁሉ)።
በመሠረቱ በታዳጊ አገሮች ደን ማዳበር፣ መንከባከብ፣ ወዘተ. የተቀየሰው፣ ያደጉ አገሮች የሚያመነጩትን በካይ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ የደኖች እፅዋት እንዲምጉት ለማድረግ ነው። ያም የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ብከለትን በመጠኑም ቢሆን ይታደጋል።
ሂደቱ ሰፋ ብሎ ሲታይ፣ አካባቢን ለመታደግ ጥቂት ዓበይት ተግባራት መከናወን አለባቸው ተብሎ ይታመናል። (ሀ) የዓለም ሕዝብ ብዛት እንዳይንር ማድረግ፣ (ለ) የምድርን ገፅ የእፅዋት ሽፋን ማዳበር፣ እንዲሁም ያለውን መንከባከብ፤ (ሐ)የኢነርጂ አጠቃቀምን መቆጠብ (መቀነስ)፣ እንዲሁም በካይ ባልሆኑ በታዳሽ የኃይል ምንጮች (ነፋስ፣ ፀሐይ፣ ውሃ፣ ወዘተ.) መጠቀም፣ ብሎም በሂደት ሙሉ በሙሉ ነባራዊውን ምንጭ (የከርሰ ምድር ዘይት፣ ከሰል፣ ጋዝ) በታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች መተካት ነው።
በችግር መፍትሄ ሂደት የተከሰቱ አወዛጋቢ ጉዳዮች
በስምምነት ለመድረስ አንዱ እና ዋናው እንቅፋት፣ በዓለም ላይ ያንሰራራውን የጋራ ችግር ባለጉዳዮች ከአገሮቻቸው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻቸው አንፃር ብቻ መመልከታቸው ነው። ለምሳሌ በቅርብ “ግላስጎ” (Glasgow) በተደረገው ስብሰባ (COP26) ከፍተኛ የብረት ከሰል አምራች የሆነችው አውስትራሊያ፣ ከፍተኛ ቤንዚን አምራች የሆነችው ሳውዲ አረቢያ፣ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ አምራች የሆነችው አገረ ጃፓን የበካይ ኃይል ማመንጫ ቅነሳ በማድረግ ሂደት የታቀደውን መንገድ ለመቀበል/ለመተግበር ፈቃደኞች አልነበሩም።
ስምምነት ላይ ለመድረስ ዋና ተግዳሮት የሆኑት ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው። ካቀዱት (ካለሙት) እድገት ላይ ያልደረሱ፣ ግን በመገስገስ ላይ የሚገኙ አገሮች፣ በተለይ ቻይና እና ሕንድ፣ በምዕራባውያን የሚላከኩባቸውን አስቸጋሪነት (አዲስ መንገድ በቶሎ አለመቀበል)፣ ከነባር ኩነቶች ጋር እያመሳከሩ፣ ዋነኛ ችግር ፈጣሪዎች እነሱ እንዳልሆኑ ይከራከራሉ፤ ክርክራቸውም እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። እንዲሁም በአማካኝ አንድ አሜሪካዊ የሚጠቀምበት ኢነርጂ፣ አራት ቻይናውያን ከሚጠቀሙበት ይልቃል፣ ከእኛን መሰል አገሮች ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ልዩነቱ የትየለሌ ይሆናል።
የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ማመንጨት በየዓመቱ በነፍስ ወከፍ ሲተለም፣ አሜሪካ 15.52 ቶን፣ ሩስያ 11.44 ቶን፣ ቻይና 7.38 ቶን እና ሕንድ 1.91 ቶን ነው። ያም ሆኖ “የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ” በካይነታቸው በተደጋጋሚ የሚወቀሱበት ቻይና እና ሕንድ ናቸው። ከከሰል ማምረት ጋር ተያይዞ የነፍስ ወከፍ ምርት ሲሰላ፣ አውስትራሊያ 61.1 ቶን፣ ሩስያ 2.95 ቻይና 2.57 ቶን፣ ኢንዶኒዚያ 2.25 ቶን፣ አሜሪካ 1.93 ቶን እና ሕንድ 0.57 ቶን ነው። ያም ሆኖ ሕንድ በብረት ከሰል አጠቃቀም ይዘት በአብካይነት ከሚወቀሱት አገሮች አንዷ ናት።
የአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔና በኢትዮጵያ የተከሰቱ ዓበይት ተግዳሮቶች
የአገራችን ዓበይት ችግሮች ናቸው ተብለው ከሚወሱት ጉዳዮች መካከል፣ አገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሃብት በከፍተኛ የውድመት ሂደት ላይ ያለ መሆኑ ነው። የዚህ ውድመት መከሰቻው የለም አፈር መታጠብ፣ የመሬት የእፅዋት አልባስ መመናመን፣ በአንዳንድ ቦታዎች የምድር አልባስ ጨርሶ መጥፋቱ እና ምንጮች ብሎም ወንዞች መድረቃቸው ናቸው። ችግሮቹ ውስብስብ እና ተመጋጋቢ የሆኑ የርስ በርስ ግንኙነቶችም አሏቸው። እነዚህ እና እነዚህን የመሰሉ ችግሮች ተደራርበው ከፍተኛ የሰው ምግብ እና የከብት መኖ እጥረት (እጦት)፣ የመጠጥ (ውሃ) መጥፋት፣የማገዶ ችግር እና ተመሳሳይ ሌሎች ችግሮች በኢትዮጵያ እንዲከሰቱ አድርገዋል።
የአየር ቅጥ ለውጥ ከዝናብ ጋር ተዛምዶ ለማህበራዊ ቀውስ መንሰዔ እየሆነ ነው። የዝናብ መጠን ቀውስ የሚገለጠው በመጠን ማነስ ወይም መብዛት ብቻ ሳይሆን፣ መቼ እና የት በምን መጠን ከመሰሉ ሁኔታዎችም ጋር ተቆራኝቶ ነው። የዝናቡ መጠን ሲንር የጎርፍ ችግር ይከሰታል፣ ብሎም ማሳዎች በውሃ ተሸፍነው በማሳው ላይ የሰፈረ ሰብል ይቀጭጫል። በውሃ ብዛት መንስዔ የአዝርዕት እድገት፣ ብሎም ምርት ይገታል (ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ጋምቤላ እንደተከሰተው ዓይነት)።
የአገራችን ገበሬዎች የሰብል እህሎች መቼ እና የት እንደሚዘሩ በተለምዶ የዳበረ ባህላዊ እውቀት እና ክህሎት አላቸው። ይህ ነባራዊ እውቀት በአየር ቅጥ ለውጥ መንስዔ ይዛባል። ለምሳሌ ዝናብ ይገኛል ተብሎ ተገምቶ፣ ክረምት ገና ሳይገባ የሚዘሩ ሰብሎች (ለምሳሌ ማሽላ፣ በቆሎ) ዝናብ በተጠበቀው ወቅት ካልዘነበ፣ እንዲሁም መጠኑ ከተቃወሰ፣ በምርት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል።
በነባራዊው ሁኔታ ዝናብ የሚያገኝ ማሳ፣ አፈሩ እርጥበት አዘል ሲሆን፣ የማሳው ሰብል በቂ ውሃ እያገኘ እድገቱ፣ ብሎም ፍሬያማነቱ ይረጋገጣል። በአንፃሩ በዝናብ እጥረት መንስዔ፣ የማሳ አፈር እርጥበት አልባ ይሆናል፣ ብሎም በማሳው ላይ ያለ አዝመራ በውሃ እጥረት መንስዔ ይደርቃል። አፈር እርጥበቱን ሲገፈፍ፣ ድርቅ ተከሰተ ማለት ነው። ያም የአካባቢ ቀውስ ዋና ምክንያት ይሆናል።
የቀውስ መንስዔ የምግብ ፍጆታ ስለሚቀንስ ብሎም ስለሚወደድ ለሰላማዊ ኑሮ እንቅፋት ይሆናል፤ ለምሳሌ ለዝርፊያ መንገድ ይከፍታል። በተፈጥሮ ሃብት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች የሆኑ ከብት አርቢዎች፣ በዝናብ እጦት መንስዔ ከፍተኛ የመኖ እና የውሃ ችግር ይገጥማቸዋል። ያም ሁኔታ ግብርና ላይ ወደ ተሰማሩ ማህበረሰቦች አካባቢዎች ለመሰደድ ያስገድዳቸዋል። ስለሆነም በከብት አርቢዎች እና ግብርና ላይ በተሠማሩ የማህበረሰብ አባላት መሃከል ግጭት በተደጋጋሚ ይከሰታል። በድርቅ መንስዔ የከብት አርቢዎች አለኝታ በተደጋጋሚ ለውድመት እየተዳረገ ይገኛል። ድርቅ የግብርናንም አለኝታ ያኮስሳል።
በዚህ ምክንያት መንግሥትም ከግብርና ውጤቶች የሚያገኘው ጥቅም በጣም ይቀንሳል። ያላመረተ ግብር ለመክፈል ወይም በገበያ ሂደት የመሳተፍ አቅም አይኖረውም። ስለሆነም በበጀት እጥረት መንግሥት መሠረታዊ ተግባራት ለማከናወን ያዳግተዋል።
በአካባቢ ሙቀት መጨመር መንስዔ የወባ በሽታ ወደ ከፍተኛ ወይና ደጋ አካባቢዎች እየተዛመተ ነው። በግብርና ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ እያስከተለ ይገኛል። በአገራችን ድርቅ መከሰት ድግግሞሹ እየጨመረ መጥቷል። የአብዛኛው ማህበረሰብ አባል (80%) የሕይወት አለኝታው ግብርና ነው። ግብርና ለብሄራዊው ኢኮኖሚ የአርባ በመቶ (40%) ድርሻ አለው። የዝናብ እጥረት ወይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የግብርና ምርት ለመቀነስ መንስዔ ነው። የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ማመንጫዎች የሆኑ ግድቦች በቂ ውሃ ካለገኙ፣ የኃይል ማመንጨት አቅማቸው በጣም ዝቅ ይላል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን ለመግታት ያከናወነቻቸው እና /በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት
ለአካባቢ እንክብካቤ ይረዳሉ ተብለው የተቀረጹ ፖሊሲዎች የተደነገጉ ሕጎች/ ደምቦች አሉ፤ ይህም አበረታች ሂደት ነው። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ፣ “የባዮዳይቨርሲቲ- ብዝሃ-ሕይወት” ፖሊሲ፣ የድርቅ መከላከያና ማኔጅመንት ፖሊሲ፣ ኢነርጂ ፖሊሲ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ናቸው። በፌዴራል ደረጃ ብዙ ሕጎች ተደንግገዋል፤ የአካባቢ ጥበቃ፣ የመሬት፣ የደንና የዱር እንስሳት፣ የእህል ዘር፣ የውሃ ሃብት አጠቃቀም፣ የማዕድን፣ ወዘተ. ናቸው። ሆኖም ለመልሶ ማቋቋም የሚቀረጹ ፕሮግራሞች ሁሉ በጊዜና በመጠን ካልተወሰኑ (ለምሳሌ ይህን ያህል መሬት በዚህን ጊዜ ዛፍ ይተከልበታል ካልተባለ) ተግባሮቹ ስኬታማ አይሆኑም።
የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ትኩረት የሰጠው ለግብርና፣ ለደን ልማት፣ ለጤና፣ ለትራንስፖርት፣ ለኃይል ማመንጨት፣ ውሃ እና ከተማ ልማት ነው። ለአየር ንብረት ለውጥ መግቻ ከተወሰዱ እርምጃዎች ዋናዎቹ የኢትዮጵያን የልማት አቅጣጫ ከአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ ስተራቴጂዎች ጋር ማሳለጥ ነው።
በአረንጓዴ የልማት ጎዳና ለመራመድ የሚያስችል ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ የሆኑ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እድገት ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል። እነሱም “ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ” (Climate Resilient Green Economy Strategy-2012)፣ “ለአየር ቅጥ ለውጥ አይበገሬ የግብርና እና የማደነን (ደኖች መመስረት/መንከባከብ) ስትራቴጂ” (Climate Resilient Strategy: Agriculture and Forestry 2016)፣ “የውሃ እና የሥነ ምህዳር ስትራቴጂ” (Climate Resilient Strategy: Water and Ecology 2017) ናቸው። ከዚያም ለነዚህ ስትራቴጂዎች ማጣጣሚያ (Adaptations) እቅድ (Ethiopia’s Climate Resilient Green Economy-National Adaptation Plan-2019) ነድፎ ሥራ ላይ ማዋልን ያካትታል።
ይህም ግብርናን ምርታማ ማድረግ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል፣ ለአካባቢ ጥበቃ በተለይ ለተፋሰስ ከባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠት፣ አፈርን መንከባከብ፣ ውሃ የማቆር ባህልን ማዳበር፣ በጤና አካባቢ መረጃ አሰባሰብን ማጠናከር፣ ብሎም የተቀናጁ ተግባራትን ማስተናገድ፣ ብዝሃ ሕይወትን መንከባከብ፣ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን ማጎልበት፣ ወዘተ. ናቸው።
የከተሞችን አያያዝ አስተዳደር ችግር መቋቋም በሚያስችል መንገድ ለማስተናገድ ዘላቂነት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎትን መመሥረት፣ የኢንዱስተሪ ልማት ችግርን ከመቋቋም አንፃር ፈትሾ ማጎልበት፣ በባህላዊ ችግር መፍቻ ዘዴዎች መጠቀም እንዲሁም ለግብርና እና ለከብት እርባታ ዋስትና ማበጀት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ አስፈላጊ መረጃዎች በአግባብ ወቅታዊ በሆነ መንገድ እንዲስተናገዱ ማድረግ፣ የአየር ቅጥ ለውጥ ተኮር የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማዳበር ብሎም ተግባር ላይ ማዋል፣ በችግሩ አካባቢ ምርምር አካሂዶ ተገቢ እና በቂ መረጃዎችን ማከማቸት፣ ወዘተ. ሊሠሩ የሚገባቸው ተግባራት ናቸው።
ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችን፣ ደምቦችን ማውጣት፤ አስፈጻሚ ተቋማትን መመሥረት፤ ፕሮግራሞችን መንደፍ እና ሥራ ላይ ማዋል ያሻል፤ ያም በከፊል እየተደረገ ነው። ብዙ ጊዜ እንደሚወሳው፣ ቆላማ ቦታዎችን በውሃ ግብዓትነት አልምቶ ብዙ የምግብ እና የኢንዱስትሪ ሰብሎችን ማምረት ይቻላል፤ ከዚያም የተፈጥሮ ሃብትን ብክነት መግታት፣ ብሎም ጨርሶ ማጥፋት ይቻላል።
ለዚህ ፕሮግራም መሳካት መንግሥት በቅድሚያ የመገናኛ እና ሌሎች የልማት አውታሮችን ዘርግቶ መሬቶችን ባለሃብቶች እንዲያለሙ መጋበዝ አለበት። በዚህ ሂደት ከመንግሥት በኩል እንደ መንግሥትነቱ ብዙ ድጋፍ እና ማበረታታት ይጠበቃል። ይህ ሲደረግ ግን ነባር የአካባቢውን ኗሪዎች በጎላ መጠን የልማቱ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ማድረግ ያሻል። በዚህ መልኩ ካልተደረገ ከአሁኑ የላቀ ማህበራዊ/ ሕዝባዊ ችግር ሊከሰት ይችላል።
ገጠሬውን ከመሬት ጋር ካለው ቀጥተኛ ቁራኛነት ለማላቀቅ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ውስጥ ሠርቶ የመተዳደርን ዕድል ከፍቶ እንዲሳተፍባቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያሻል። አሁን የሚካሄደው የኮንስትራክሽን ተግባር አንዱ እና ዋናው የልማት ገጽታው ይህ ሳይሆን አይቀርም።
ለከብት አርቢ ወገኖቻችን ልዩ ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል። በቆላማ ቦታዎች ላይ የሰፈሩ ከብት አርቢ ወገኖች የሚያረቧቸው ከብቶችን ምርታማነት የሚጨምሩ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን ነድፎ ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፤ ያም እየተሞከረ ነው። ከፕሮግራሞችም አንዱ አምራቹ ምርቱን ሽጦ የሚጠቀምበት ዘዴ በቅድሚያ የተዘጋጀ መሆኑን ማረጋገጥ መሆን ይኖርበታል። ይህ አሁንም በከፊል በመተግበር ላይ ይገኛል።
የአየር ቅጥ ለውጡን ለመቋቋም የልማት መዋቅር መገንባት፣ ስለጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ እንዲገኝ ማድረግ፤ በትምህርት፣ በመረጃ አሰጣጥ እና አሰረጫጨት እንዲሁም የኑሮ ዘዴዎች መፈተሸ እና ከአየር ቅጥ መግታት ጋር ማሳለጥ ያስፈልጋል።
መደምደሚያ፤ አገራዊ ምክር አዘል አስተያየት
ዓለም አቀፍ ችግሮች ሊፈቱ እየተሞከሩ ያሉት በዓለም አቀፍ ስምምነቶች አማካኝነት ነው። ዓለም አቀፍ ችግሮች ሁሉ የኢትዮጵያም ችግሮች ናቸው። እንግዲህ ዓለም አቀፍ ችግሮችን ይፈታሉ ተብለው የታሰቡ ስምምነቶችን ወደ ጎን ልተውና ለአገራችን ጉዳይ ትኩረት ልስጥ።
በኢትዮጵያ የአየር ቅጥ ችግሮችን ለመግታት፣ ለመታደግ በቀላሉ ልንተገብራቸው የምንችላቸው ብዙ ተግባራት አሉ። በዘላቂነት ችግርን ለመታደግ ባህላዊ ለውጥ ላይ ያጠነጠነ መፍትሄ ለነገ የማይባል ተግባር ነው። በትምህርት ቤቶች ማዕከልነት በተፈጥሮ እንክብካቤ የባህል ለውጥ ማምጣት ይቻላል። የተፈጥሮ ሃብት መመናመኑ እንዳይቀጥል መደረግ እንዳለበት በማመን በብዙ አካባቢዎች የእፅዋት ተከላ ቢከናወንም፣ የተደረጉት ጥረቶች ተገቢውን (የሚጠበቀውን) ውጤት እንዲሰጡ የባህል ለውጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ያሻል። ችግሩን ለመፍታት ግን መጀመሪያ በተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ዙሪያ ባህላዊ ለውጥን ማምጣት ያስፈልጋል።
መጥፎ ልማድን ለማስጣል እና በምትኩ ጥሩ ልማድን ለመተካት፣ የለውጥ መሠረታዊ ግብዓቶች (አንቀሳቃሾች/ ሞተሮች) ትምህርት ብሎም ዕውቀት/ ክህሎት ናቸው። ጉዞውም ረጅም ነው- አርቆ ማየት ያሻል። የባህልን ለውጥ ለማምጣት ከሚያገለግሉ መድረኮች ዋነኛው ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ፣ ከትምህርት ጋር አቀናጅቶ ጥሩ ጥሩ ልማዶችን/ ባህሎችን መመሥረት ብሎም ማዳበር ይቻላል። በብዙ አገሮች የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ባህል የሚዳብረው በክለቦች፣ (አብዛኛው ከትምህርት ቤቶች ጋር የተቆራኙ መሆን ይገባቸዋል) አማካኝነት ነው። ስለሆነም፣ በየትምህርት ቤቱ አንዳንድ የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ክለቦች፣ በብቸኝነትም ሆነ ከሳይንስ ክለቦች ጋር ተቀናጅተው በጣምራ እንዲመሰረቱ ጥረት ማድረግ ያሻል። የተመሰረቱም ካሉ እንዲጎለብቱ ማድረጉ ይበጃል።
የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ዋና ዓላማው ያደረገ አንድ ምዕራፍ፣ በአገሪቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ማካተት ያሻል። ወጣት ተማሪዎች ስለ ተፈጥሮ ሃብት መጠነኛ ግንዛቤ አንግበው በወደፊት ሕይወታቸው ለተፈጥሮ ሃብት ጥንቃቄ እንዲያደርጉና እንዲንከባከቡ፣ መጠነኛ ዕውቀትን እና ክህሎትን ለማስጨበጥ ካሁኑ የበለጠ ጥረት መደረግ አለበት። በዚህ ስልት/ ዘዴ/ እቅድ (strategy) አሁን በሚያሰጋ ደረጃ እየመነመነ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ውድመት በከፊልም ቢሆን ለመግታት፣ ብሎም የአየር ቅጥ ለውጥን ለመታደግ ይቻላል።
የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ባህል ማዳበር ዋና ዓላማው የሆነ ፕሮግራም የሚከተሉትን ዝርዝር ዓላማዎች ያካተተ ቢሆን ይመረጣል። ይህም የተፈጥሮ ሃብትን ባግባቡ አለመጠቀም ስለሚያስከትለው ችግር ግንዛቤ በጥሞና ማስጨበጥ፣ በየትምህርት ቤቶች የሳይንስና የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ክበቦችን ማቋቋም/ማጎልበት እንዲሁም በአጠቃላይ ስለተፈጥሮ ሃብት ያለውን ግንዛቤ ማጠናከርን ያካትታል።
ይህን ዓላማ ለማስፈፀም፤ (ሀ) አገር በቀል ዛፎች መትከል፤ ቀደም ሲል የሚገኙትንም መንከባከብ። ለትምህርት ቤቶች ቅርበት ያላቸው የማይታረሱ ቦታዎችን ለዚህ ተግባራት ማዋል፤ ስያሜዎቻቸውም “የእፅዋት አደባባዮች” ሊባሉ ይችላሉ። (ለ) “የእፅዋት አደባባይ” የሚገኙ ዛፎችን እድገት/መጠን መጨመር ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ተማሪዎች እንዲከታተሉ ማድረግ (ቁመት፣ ውፍረት፣ የቅርንጫፍ ቅጠል ብዛት፣ ቅርፅ፣ ሌሎች ሕዋሳትን መመዝገብ፣ ወዘተ.)። በሚመሠረቱ የእፀዋት አደባባዮች አካባቢ ምን ምን ዓይነት እንስሳት እንደሚኖሩ መመዝገብ። ይህም የመረጃ አሰባሰብን ክህሎት ያዳብራል። (ሐ) ክበቦች በተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ገላጭ የሆነች የየራሳቸውን ትንሽ ወቅታዊ መጽሔት በየጊዜው ማዘጋጀት (ከአራት ገፅ ያልበለጠች)፣ የመጽሔቶች ስያሜም ሲመረጥ ባህላዊ ይዘትን (አካባቢን) ያገናዘበ መሆን ይገባዋል።
በላቦራቶሪ እንዲሁም በእንስሳትና እፅዋት መዘክር እገዛ ይህ ነው የሚባል ዕውቀትን/ ክህሎትን ለማግኘት በማይቻልባቸው ትምህርት ቤቶቻችን የእነዚህ ዓይነት የተፈጥሮ ሃብትን ማስገንዘቢያ ማዕከሎች መኖራቸው ፈርጀ-ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ እገም ታለሁ።
በዚህ ሂደት ውስጥ ክለቦች የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን ሁሉ መዳሰስ አለባቸው፤ ይህም ሲደረግ አካባቢውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። የየክልሉ መንግሥት ብልጫ ላሳዩ ለተወሰኑ ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ ሽልማት መስጠት ይገባዋል። ለዚህ ተግባር ማስፈጸሚያ የሚሆን መንግሥት መጠነኛ በጀት መመደብ ይኖርበታል። የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ለዚህ ተግባር ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ። በዚህ መንገድ የአየር ቅጥ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር መቀነስ ብሎም መቋቋም ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።
ሽብሩ ተድላ /ፕሮፌሰር ኤሚሪተስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/
ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም