ኢትዮጵያ የምዕራባውያን የሽንፈት መድረክ

ቀደምት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለመቀራመት ቋምጠው ከሚመጡ የየዘመኑ ጉልበተኞች ጋር በዱር በገደሉ ተዋደቀው ነጻነታቸውን አስከብረው ኖረዋል። ነጻ አገርና ኩሩ ሕዝብ ሆነን የምንኖረው ቀደምቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው በከፈሉት የሕይወት ዋጋ ነው። የኢትዮጵያውያን ጀግንነት፣ ነጻነት ወዳድነት፣ አትንኩኝ ባይነት እና አርበኝነት እንዲህ ባለ ውድ ዋጋ የተገዛ ነው።

ዛሬም የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች “ከአገር ሞት በላይ ሞት የለምና” ብለው ልማደኞቹ ጉልበተኞች የሚጋልቡትን ባንዳ እየተፋለሙ፣ የለመዱትን ድል እያጣጣሙ ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊነት ወደፊትም ተጨማሪ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ማንም ሊደፍረው የማይችል ማንነት ሆኖ ይቀጥላል።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት በምዕራባውያኑ የደረሰባትን ክህደት፣ ጫና እና ማዋከብ እንዴት ተቋቁሟ እዚህ እንደደረሰች በማሳየት ዛሬም እየተደረገባት ያለውን የተቀናጀ ዘመቻ አሸንፋ ነጻነቷን አስጠብቃ ለመቀጠል በሚያስችላት ሀዲድ ላይ እየተጓዘች መሆኗን ማሳየት ነው። ለዚህም የታሪክ ተመራማሪ ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪና መምህር የሆኑ ሦስት ምሁራንን ጋብዘናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር እና የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው የምዕራባውያን ጫና አሁን የተጀመረ አለመሆኑን ሲገልጹ “አነሰ ቢባል ከ1860ዎቹ እና 70ዎቹ የሚጀምር ነው። በወቅቱ የግብጽ መንግሥት የአባይን ተፋሰስ አካባቢ በቁጥጥሬ ስር አደርጋለሁ ብሎ ሲነሳ ግብጽ ከባድ ችግር ውስጥ ነበረች። ከፈረንሳይና እንግሊዝ መንግሥታት ለስዊዝ ካናል ግንባታ የተበደረችው ዕዳ ነበረባት። የግብጽ የተስፋፊነት ባህሪ በተለይም የቱርክ መንግሥት ይገዛቸው የነበሩትን እንደነ ምጽዋና ዘይላን የመሳሰሉና ሌሎችንም አካባቢዎች በመያዝ በአጠቃላይ የአባይ ተፋሰስ አካል የሆነውን የኢትዮጵያ አካባቢ ለመቆጣጠር ስትመጣ አፄ ዮሐንስ አውሮፓውያን ወረራውን እንዲያስቆሙ በመጠየቅ ብዙ ጥረት አድርገው ነበር። ›› ይላሉ።

ንጉሡ ለመስኮብ/ራሺያ/ና ለነምሳ/ኦስትሪያ/ መንግሥት ስለገጠማቸው የግብጽ ተገዳዳሪነት ደብዳቤዎችን ጽፈው እንደነበር የሚጠቅሱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው የግብጹ መሪ ኬዲቭ እስማዔል ፓሻ ግብጽን ከአውሮፓ አገር እንደ አንዷ በማየት አባዜ ውስጥ ሆኖ ‹እኛም ኢትዮጵያን ልናሰለጥን፣ ልንገዛ ይገባናል› የሚል አቋም ይዞ ኢትዮጵያን ለመውረር መምጣቱን ከራሺያ በስተቀር ምዕራባውያኑ በተለይም በወቅቱ ኃያላን የነበሩት ፈረንሳይና እንግሊዝ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውንም ይተርካሉ።

ከአድዋ ድል ቀድሞም ተመሳሳይ ነገር ነበረ የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው ጣሊያን የቅኝ ግዛት ዓላማዋን ለማሳካት ከውጫሌ ውል ጋር አያይዛ አስቀድማ ኤርትራን ይዛ ነበር። ነገር ግን በውሉ የተፈቀደላቸውን ቦታ ሳይሆን አልፈው መጥተው መስፋፋት ሲጀምሩ አፄ ምኒልክ ብዙ ጥረቶችን አድርገዋል። እንደ አፄ ዮሐንስ ሁሉ አፄ ምኒልክም ለወቅቱ የአውሮፓ ኃያል አገሮች ጣሊያን ወረራውን እንድታቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፈው ነበር። ነገር ግን ፈረንሳይም እንግሊዝም ዝምታን ነው የመረጡት። ዝምታ ማለት በተዘዋዋሪ የጣሊያንን ቅኝ ገዢነት አምናችሁ በመቀበል መገዛት አለባችሁ የሚል ይሁንታ መሆኑን ይገልጻሉ።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ክህደት የፈጸሙበት የታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ የዓለም መንግሥታት ማህበር አባል በነበረችበት ወቅት በ1928 ዓ.ም ነው። እንደ አንድ አባል አገር በማንኛውም አባል በሆነ አገርም ሆነ በሌላ መጠቃት የለባትም በሚለው ስምምነት መሠረት የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ወረራ ለማስቆም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን እንግሊዝና ፈረንሳይ ኢትዮጵያ የጣሊያን

 ቅኝ ተገዢ እንድትሆን ተስማሙ። በአጋጣሚው ሙሶሎኒን ከሂትለር ጉያ ለመንጠቅ ኢትዮጵያን የጦስ ዶሮ አድርገው ሰጡ። የኢትዮጵያን የነጻነት ጉዳይ ችላ ብለው በአደባባይ ክህደት ፈጽመውባት በእጅ አዙር ህልውናዋንና ነጻነቷን ተጋፍተዋታል። ውሎ አድሮ ግን እነሱም ላይ ያ ግፍ ደርሶ ሂትለር ወሯቸዋል፤ ጣሊያንም ፈረንሳይን ወግታለች።

ኢትዮጵያውያን በአትንኩኝ ባይነት እና በአይደፈሬነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግሩን ለመፍታት በተንቀሳቀሱበት ልክ በእምቢተኝነት የመጣውን ደግሞ በጀግንነት በመቅጣት ኢትዮጵያ የእብሪተኞች መሸነፊያ መድረክ መሆኗን የሚያሳይ ታሪክ እንዳላቸው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው በሦስት አቅጣጫ መጥቶ በሁለቱ አቅጣጫ ጉራዓ እና ጉንዲት ላይ ድል የተነሳውን በአፋሮችም እስከ ታጁራ የተሳደደውን በወርነር ሙዚንገር የሚመራው የግብጽ ሠራዊት የሽንፈት ታሪክ፤በአድዋ የደረሰው የጣሊያኖች አሳፋሪ የሽንፈት ታሪክ፣ በኋላም በአምስቱ ዓመት የወረራ ጊዜ የነበረው የአርበኝነት ተጋድሎ ኢትዮጵያውያን በነጻነታቸው ላይ ተደራድረው እንደማያውቁ ጉልህ ማስረጃዎች መሆናቸውንም ያብራራሉ።

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሱራፌል ጌታሁንም በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ደባ ሲፈጸም የአሁኑ አጋጣሚ የመጀመሪያ አይደለም ይላሉ። ከዚህ በፊት በአፄ ዮሐንስ ዘመን ምዕራባውያኑ በሄዌት ስምምነት/The Hewett Treaty/ የተደረገውን ስምምነት ክደው ጣሊያን ኢትዮጵያን እንድትይዝ የጋበዙበት ሁኔታ አለ። ግብጾች በጉንደትና ጉራዓ ላይ ከተሸነፉ በኋላ ከእንግሊዞች ጋር ያደረጉት ስምምነት ነበረ። በስምምነቱ መሠረት ሱዳን ላይ ተከቦ የነበረው የግብጽ ጦር በኢትዮጵያ አቋርጦ በቀይ ባህር በኩል ወደ አገሩ እንዲገባ፣ ግብጽም ምጽዋን ጨምሮ ሰራዊቷ ከሰፈረባቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች ለቃ እንድትወጣ ይፈቅዳል። ኢትዮጵያ በስምምነቱ መሠረት ቃሏን አክብራ የግብጽ ወታደሮች በግዛቷ አልፈው ወደ አገራቸው ከገቡ በኋላ ግን እንግሊዝ ምጽዋን ጨምሮ የኢትዮጵያን ባህር ዳርቻዎች ለጣሊያን አሳልፋ በመስጠት ኢትዮጵያ ላይ ክህደት መፈጸሟን ይጠቅሳሉ።

በ1903 ዓ.ም አፄ ምኒልክ መታመማቸውን ተከትሎ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለመከፋፈል ማሴራቸውን በመጥቀስም ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ደክማለች ብለው በሚያስቡበት ወቅት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ክህደት የሚፈጽሙባት አፍሪካ ላይ የነበራቸውን ምኞት በአጭሩ እንዲቀጭ ስላደረገች መሆኑን ይገልጻሉ።

አያይዘውም በኋላም ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ 1923 የመንግሥታቱ ማኅበር አባል ከሆነች በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዋዜማ ጣሊያን ወረራ ስትፈጽምባት ምዕራባውያኑ ዲፕሎማሲያዊ ደባ ፈጽመውባታል። የመንግሥታቱ ማኅበር የተመሰረተው አንድ አባል አገር በሌላ አገር በሚወረርበት ጊዜ በጋራ ያንን አገር የመከላከል ትልቅ ተልዕኮ ይዞ ነው። ነገር ግን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጄኔቭ ተገኝተው ኢትዮጵያ ላይ የተካሄደውን ወረራና ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያ ውስጥ እየፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋና የመርዝ ጋዝ ፍጅት ለማኅበሩ አባል አገራት ሲገልፁ በወቅቱ ኃያላን አገራት የነበሩት ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ዝምታን በመምረጥ የኢትዮጵያን በደል አይተው እንዳላዩ አልፈዋል። በ1970 ዎቹም የዚያድ ባሬ ጦር ሰባት መቶ ኪሎ ሜትሮች ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በገባበት ወቅት በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ወረራውን ለመቀልበስ ከአሜሪካኖች ጋር የመሣሪያ ግዢ ስምምነት ተፈራርሞ ክፍያውንም ፈጽሞ ነበር። አሜሪካኖች መሣሪያዎቹን ባለማስረከብ ኢትዮጵያ እጅ እንዳይገቡ በማድረግ ክህደት መፈጸማቸውን ያወሳሉ።

ተመራማሪው ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ ለመጫን እና ለማዋከብ የሚተጉት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ የተመዘገበው ድል የእነሱን የረጅም ዘመናት አፍሪካን በቅኝ ግዛት የማቆየት ሕልም ሰብሮ በማስቀረቱ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ድሉ ለፓን አፍሪካኒዝም መነቃቃት፣ ከ1940ዎቹ አንስቶ እስከ 1960ዎቹ ለነበረው የአፍሪካ አገራት ነጻነትን መቀዳጀት ስንቅ መሆኑንና ነጻነታቸውን ካገኙት አገራት መካከል 13 ያህሉ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ትእምርት አድርገው የወሰዱበት መንገድ የራሱ የሆነ አንድምታ እንዳለውም ይተንትናሉ።

ስለዚህም ይሄንን የአሸናፊነት መንፈስ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እስከማቋቋም የተራመደ የመሪነትና ለነጻነት የማስተባበር ሥነልቡና የመስበር ወይም ታዛዥ መንግሥት አዲስ አበባ ላይ የማስቀመጥ ፍላጎታቸውን ባገኙት ሁኔታ ውስጥ ሁሉ እውን ለማድረግ እንደሚፈልጉም ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ የምትገኝ ትልቅ ሕዝብና ታሪክ ያላት የአፍሪካ ኮሪደር መሆኗ መረሳት የለበትም የሚሉት መምህሩ ዛሬ ላይ እያየን እንዳለነውም ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን የመቃወም የ‹‹በቃ›› እንቅስቃሴ በኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ተንጸባርቋል። የአገራቱ ዜጎች የፈረንሳይ ወታደሮች ምድራቸውን ለቀው እንዲወጡ ከፍተኛ ተቃውሞ በማድረግ ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ ቀና አለች ማለት አፍሪካ ቀና አለች ማለት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን መምታት ማለት አፍሪካን መምታት ነው። ኢትዮጵያ ላይ ይህን ሁሉ ጫና እያደረጉ ያሉት ኢትዮጵያን ካፈረስን ዕድሜ ልካችንን በአፍሪካ ያለንን ጥቅም እናስጠብቃለን የሚል እምነት ስላላቸው ነው ብለው ያምናሉ።

ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችው እንዲህ ያሉትን ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችና ተጽዕኖዎች ተቋቁማ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል የሚሉት ተመራመሪው ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሴሩት ዛሬን በትናንት መነጽር እየተመለከቱ መሆኑን የአየርላንድ መንግሥትን እንቅስቃሴ አብነት በማድረግ ያስረዳሉ። አየርላንዶች ሕወሓት የኢትዮጵያን መንግሥት በሚወጋበት ዘመን በአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅታቸው በኩል ትግራይ አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ይንቀሳቀሱ ነበር። ይህ ድርጅት በእርዳታ ስም ይንቀሳቀስ እንጂ በዋነኝነት ለአማጺያኑ

 ስንቅና የጦር መሣሪያ ሲያቀርብ የነበረ ነው። ድርጅቱ የዩኬ ቢሆንም አየርላንድ ነው የሚገኘው። በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የተከሰተውን ረሃብ ሽፋን በማድርግ ከ ሲ.አይ.ኤ ጋር በመሆን በሁመራ በኩል ከሱዳን ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ሲያስተላልፍ ነበር። አየርላንዶች የሕወሓት መራሹ መንግሥት አዲስ አበባ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከድርጅቱ ጋር የመሠረቱትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክረዋል። አሁን ደግሞ ዲፕሎማቶቻቸው የኢትዮጵያ ደኅንነቶች የማያቁትን ያልተፈቀደ መሣሪያዎችን ይዘው ተገኝተዋል። እነዚህ ዲፕሎማቶች በሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው የምናያቸው ትናንት ለሕወሓት የዋሉለትን ውለታ ዛሬም መድገም ስለሚፈልጉ ነው። ይህን የሚያደርጉት በዋነኝነት የጥቅም ተጋሪ ስለሆኑ ነው ይላሉ።

የአየርላንድ መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤትና የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ዛሬም የመሪነት ሚናን እየተጫወተ የሚገኝበትን ምክንያት ሲያስረግጡም “ሕወሓታውያን የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ቅንጣት ታክል አያሳስባቸውም። ምዕራባውያኑ የሚፈልጉት ደግሞ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ እንዲዚህ ያለ ልክስክስ መንግሥት ነው። አየርላንዶች ሕወሓት ትናንትም በእኛ እርዳታ ነው ሥልጣን ላይ የወጣው ብለው ስለሚያምኑ አሁንም የመጡት ያንኑ የዛሬ 30 ዓመት የነበረውን የፖለቲካ አካሄዳቸውን ይዘው ነው። ዛሬ ዓለም ተለውጦ ብዙ ነገሮች በተቀያየሩበት ሁኔታ ላይ እነሱ ትናንት ላይ ተሰንቅረው አሁንም ሕወሓትን ለማዳን ጥረት እያደረጉ ነው። ለዚህ ነው አየርላንድ እዚህም እዚያም እያለች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጉዳይ ጣልቃ እየገባች መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ እየተንቀሳቀሰች ያለችው” ሲሉ ይሞግታሉ።

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪው ኢትዮጵያ የምዕራባውያኑን ጫና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ የሄደችበት ርቀት አበረታች ውጤት አምጥቷል ይላሉ። ለዚህም ቻይና፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቱርክና ሌሎችም የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት በጸጥታው ምክር ቤት እና በሌሎች መንገዶች ለኢትዮጵያ ያሳዩት ድጋፍ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በኩል በየጊዜው ማብራሪያዎችን መስጠቱና ደባዎችን ማጋለጡ፣ በተለይም ርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ከተላኩት ከተ.መ.ድ 1 ሺህ 200 መኪኖች ከ 900 በላዩ እዚያው እንደቀሩ የቀረበው ሪፖርትና ከዚያም ተያይዞ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችን የሚመሩ ኃላፊዎች አንዳንድ መግለጫዎችን ማውጣታቸውን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

አሁናዊ ሁኔታዎችን ሲገልጹም የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ ጠንካራ ዲያስፖራ እንዳላት በማየት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ እንቅስቃሴ ለማቆም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶቻቸው አካሔዶችን እያጤኑ ነው። ይህ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው። ኢትዮጵያውያን ችግር ሲመጣ በአገራችን ላይ እንደማንደራደር እና ለማንም እንደማንበረከክ ያሳየንበት ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው። ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ አፍሪካውያንን ከጎናችን ማሰለፍ መቻላችንም ተጠቃሽ ስኬታችን ነው። ምንም እንኳን የፖለቲካ ነጻነት ቢኖራቸውም ብዙ የአፍሪካ አገራት አሁንም ያሉት በምዕራባውያኑ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛ ስር ነው።

እነዚህ አገራት ጭምር ‹‹በቃ›› በማለት ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈዋል። በተለይም ደግሞ ወጣት ትውልድ የሚባሉት ፓን አፍሪካኒስቶች ንቅናቄውን እያቀነቀኑት በመላው አፍሪካ እንቅስቃሴው እየተቀጣጠለ ነው። ኢትዮጵያውያን “በቃ” በሚል እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ትልቅ ስንቅና አዲስ ማነቃቂያ ሆኗቸዋል። ይህ እንቅስቃሴ አሁን ያለውን ግለት ይዞ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ያለውን አንድነት ማስጠበቅ ቀጣዩ የመንግሥት ሥራ መሆን አለበት ይላሉ።

ተመራማሪው የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሲጠቁሙም “በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ሳምንታዊ መግለጫ ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን እየሰጠ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕወሓት እየፈጸመ ያለውን አገር የማፍረስ ተግባርና ግፍ በየቀኑ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ እየተደረገ ነው።

የመንግሥት ሰዎች እንደ ሲ.ኤን.ኤ እና ፎክስ ኒውስ ያሉ ትላልቅ የዜና ተቋማት ላይ ቀርበው የኢትዮጵያን እውነት እያስረዱ ነው። እነዚህ ብዙ ወሬዎችን የሚያሰራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዓለም ዙሪያ በርካታ ተከታዮች አሏቸው። በጭፍን የሚነዱ ግለሰቦች የመኖራቸውን ያህል ብዙ ሚዛናዊ የሆኑ ሰዎች ስላሉ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ላይ ለምን ይህን ሁሉ ጫና እያሳደሩ እንዳሉ ለማስረዳት ያግዛል። እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። አሁንም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዓይኑን እንዲገልጥ ለማድረግ ብዙ የዲፕሎማሲ ስራ ይጠብቀናል” በማለት ያሳስባሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ምዕራባውያን በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች በተለይም ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ከሞላ ጎደል የአሁንን የሚመስል ጫናዎችን በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ተንቀሳቅሰዋል። በጣሊያን ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል የነበረች አገር ናት። የሞሶሎኒ መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የጋራ ደህንነትን ለማስጠበቅ የተቋቋመው የዓለም መንግሥታት ማህበር ወረራውን በዝምታ ተመልክቷል።

በተለይም ፈረንሳይ ወረራውን በተግባር ደግፋለች። አሜሪካም በገለልተኝነት ስም ድምጿን ብታጠፋም ወረራው እየገፋ ሲሄድ ከሞሶሎኒ አስተዳደር ጋር ግንኙነት የፈጠረችበት ሁኔታ አለ። ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜም በወቅቱ አሜሪካን ይመራ የነበረው የካርተር አስተዳደር ኢትዮጵያ የከፈለችበትን መሣሪያ የማገድ እርምጃ ወስዷል። በተጨማሪም በተከታታይ ኢትዮጵያን የመሩ አስተዳዳሪዎችን በደል በመቃወም ሕዝቡ ለመብት ፣ እኩልነት እና ሕጋዊነት በሚታገልበት ጊዜ ምዕራባውያኑ የአስተዳዳሪዎቹ ተባባሪዎች ነበሩ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን የጎበኙት ፕሬዚዳንት ኦባማ እንኳን አንድ ገዢ ፓርቲ ጠቅላላ ስልጣኑንን በፓርላማ፣ በአስፈጻሚውና በሌሎችም ጠቅልሎ በያዘበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ የሆነ በሕዝብ የተመረጠ መልካም ሥራዎችን እየሠራ ያለ መንግሥት ነው ብለው እስከማሞካሸት የደረሱበትሁኔታ እናያለን በማለት ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን ያዞሩባቸውን ሁኔታና ጊዜዎች ያስታውሳሉ።

በዚህ ወቅትም በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሁኔታ የአሜሪካን አስተዳደርና የአውሮፓ ኅብረት በተናጠልና በቅንጅት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንም ጭምር ተጠቅመው ሳይቀር የሚያደርጓቸውን ጫናዎች እየተመለከትን ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ምዕራባውያኑ ይህን የሚያደርጉባቸው የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች እንዳሏቸው ሲገልጹ “አንደኛ ቀደም ሲል ከነበረው አስተዳደር ቁንጮዎች ጋር በግልም ሆነ በቡድን የነበራቸው የጥቅም ትስስርና የአዛዥና ታዛዥ ግንኙነት እየተቋረጠ ነው በሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

ሁለተኛ በእነሱ ይሁንታና ውሳኔ ላይ ያልተመሠረተ አገራዊና ቀጠናዊ እንቅስቃሴዎች ጥቅማቸውን እና ሚናቸውን አደጋ ላይ የጣለ ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያና ኤርትራ የጠላትነትን ስሜት ለማስወገድና ለመተባበር ያደረጉት ሙከራ የእነሱ ይሁንታና ውሳኔ ስለሌለበት አስጊ ሆኖ ያዩት ይመስላል። ኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲቀራረቡና የጦርነት ሁኔታን እንዲያስወግዱ አይፈልጉም ማለቴ አይደለም። ነገር ግን ሁለቱ አገሮች በራሳቸው ተነሳሽነት ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት። የእነሱ ይሁንታ ስለሌለበት ጥቅማቸውን የማያስጠብቅና አስቸጋሪ አድርገው አዩት። ” ይላሉ።

አያይዘውም ከ2010 ዓ.ም ወዲህ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አስተዳደር በቀጠናው የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች አሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠራቸው፤ ኬኒያና ሶማሊያ የነበራቸውን መቃቃር ለማስወገድ ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና እና በሌሎችም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ በማሰብ ስጋት ላይ የወደቁ ይመስለኛል ሲሉ ምክንያቶች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ያስቀምጣሉ።

በፕሮፌሰሩ እይታ በኢትዮጵያ የአገራዊ ስሜት ማቆጥቆጥም በምዕራባውያኑ ዓይን እንደ አደጋ የታየ ክስተት ነው። “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚለው ነገር ከ2010 ዓ.ም በፊት ከነበረው ሁኔታ በተቃራኒ እያደገ መጥቷል። ምዕራባውያን አገራዊ ስሜትን የሚያራምዱ መሪዎችን እንደ ስጋት ይቆጥራሉ። ለምሳሌ በ1950ዎቹ በኢራን በሕዝብ የተመረጠ ሞሳዴግ የሚባል በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው አስተዳደር የኢራንን ጥቅም በማስከበር የምዕራባውያኑን ጥቅም መስመር ለማስያዝ ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች መሠረት አድርገው ከሥልጣን በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደውት የሚፈልጉትን አካል በማስቀመጥ ጥቅሞቻቸውን ማስቀጠል ችለዋል።

በአፍሪካም በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን። በኮንጎ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረውን ፓትሪስ ሉሙምባን፣ በጋና ክዋሜ ንክሩማህ፣ በቶጎ ኦሊፒዮን በኩዴታ ቅጥረኞቻቸው በሆኑ ወታደራዊና ሲቪል ኃይሎች በማስወገድ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛቸውን በጣም በረቀቀ መንገድ ማስቀጠል ችለዋል። በላቲን አሜሪካም ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ጥቅሞቻቸውን አስከብረው ቆይተዋል። እነሱም ራሳቸው ደጋግመው እንደሚሉት እንደ ዋና መርሕ የሚከተሉት ነገር ቢኖር ወዳጅነት ወይም ጠላትነት ሳይሆን በቋሚነት ጥቅማቸውን ለማስከበር መንቀሳቀስን ነው። ” ሲሉ የኢትዮጵያውያን አንድነት እየተጠናከረ መምጣቱ ምዕራባውያኑ ላይ ተጨማሪ ስጋት መፍጠሩን ያስረዳሉ።

አሁንም የምዕራባውያን ተጽዕኖ ያለባቸው አስተዳደሮች ያሏቸው አገሮች በርካቶች ናቸው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ አማራጭ በማጣት ወይም ለሥልጣንና ጥቅም ሲባል ለምዕራባውያኑ ያድራሉ። የምዕራባውያንን የእጅ አዙር አገዛዝን መታገል በሂደት በእነዚህ አገራት ውስጥ እየሰረጸ ይሄዳል። ምክንያቱም ሕዝቦች ምዕራባውያን ከጨቋኝ መንግሥታቶቻቸው ጋር ሆነው የሚያደርሱባቸውን ነገሮች ይረዳሉ። ለዚህ ነው እንደ ማሊ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ ካሉ እና በሌሎችም የአፍሪካ አገራት የሚገኙ ዜጎች በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጦርነት በአፍሪካ ላይ የተደረገ ነው በሚል በቃ የተሰኘውን እንቅስቃሴ እየተቀላቀሉ ያሉት። በዚህም በአፍሪካ ምድር የምዕራባውያን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ጨለማ እንደሚሆን ይተነብያሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የቀድሞ ሸሪኮቻቸው በጦር ግንባር ውድቀት እየገጠማቸው በመሆኑ እና ወታደራዊ ቁመናቸው እየተዳከመ በመሄዱ ተስፋቸው አጠራጣሪ እየሆነባቸው መጥቷል የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርጉት ጫና ጋር ተያይዞ ‹‹በቃ›› የሚለው እንቅስቃሴ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ አገሮችና አፍሪካ ውስጥ እየተቀጣጠለ መጥቷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች እንቅስቃሴ በፍጹም ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። ይሄም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።

ለምሳሌ በቅርቡ በተለያዩ የአሜሪካን ክፍለ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በዋሽንግተን ዲሲ ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በዚህ ጊዜ አሜሪካውያን ምን እየሆነ ነው፤ ምን ቢደረግ ነው እንደዚህ አይነት ምሬት የመጣው የሚል ጥያቄዎችን ሊያነሱ ይችላሉ። እኛ ታክስ ከፋዮች በምናደርገው አስተዋጽኦ ምን እየተደረገ ነው የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኮንግረስ ውስጥ ያሉ ሰዎችን አግኝተው እያነጋገሩ ነው። ይሄ ደግሞ የመንግሥት አስተዳደር አካባቢ ይደርሳል ይላሉ።

ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ እየተጠናከረች ደጋፊዎችን እያበዛች መርሐዊ የሆነ አቋሟን አስጠብቃ ከቀጠለች ሁኔታው የመቀልበስ ዕድል አለው። ነገር ግን እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የጀመሩት ጫና የማሳደር ነገር ይቀጥላል፤ በአንድ ጊዜ ይቆማል ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያ ወዳጅ እያበዛች እውነቷን ደግሞ የምዕራባውያኑን አገራት ዜጎች ጨምሮ ለዓለም ኅብረተሰብ እያስረዳች በሄደች ቁጥር ቀስ በቀስ ጫናዎቻቸው ይቀንሳሉ። ለምሳሌ በቅርቡ ፈረንሳይ የዓለም ቅርስ የሆኑትን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን እድሳት እንደምትቀጥል ገልጻለች። በተጨማሪም በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እርዳታዎችን መስጠት ጀምራለች። ሌሎቹም እንደሚከተሉና ኢትዮጵያ ምዕራባዊያኑን ማሸነፏ አይቀሬ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በ1997 ዓ.ም በአገራችን የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተነሳው ውዝግብ ምክንያት በመለስ ዜናዊ ሲመራ የነበረውን አስተዳደር የማውገዝና ማዕቀብ የመጣል እንዲሁም እርዳታዎችን የማስተጓጎል ሁኔታዎች ነበሩ። የመለስ ዜናዊ መንግሥት ለራሱ ፍላጎት ሲል በአቋሙ ጸንቶ በመቀጠሉ ‹ምን እናድርግልህ› ብለው እስከመጠየቅ ደረጃ ለመድረስ ጊዜ አልፈጁም ነበር ሲሉም አስረጅ በመጥቀስ የኋላ ኋላ ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያን ደጅ ይጠናሉ ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ። የፈለገውን ነገር ቢያደርጉ አሁን ባለንበት ሁኔታ መናገር የምንችለው የኢትዮጵያን እጅ ጠምዝዘው አቋሟን የማስቀየር ወይም የቀድሞ ሸሪኮቻቸውን ወደፊት የማምጣቱ ነገር ተስፋ ያለው ነገር መስሎ አይታይም በማለት የምዕራባውያኑ ጫና እየቀነሰ ይሄዳል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

በቀጣይ ኢትዮጵያ ምን አይነት እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባት ሲጠቁሙም አንደኛ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተነሳውን ግጭትና የዓባይን ጉዳይ በተመለከተ ያለውን ሁኔታ በመረጃዎች አስደግፎ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለማቋረጥ ማስረዳት አለበት። ነገሩን የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት አያቁትም ወይም ያጡታል ማለት አይደለም። ነገር ግን የተለያዩ የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች ብዙ ግልጽ የሆነ ነገር የላቸውም። እየሰሙ ያሉት ዜጎቻቸው አስተዳደሮቻቸውና ወትዋች (አግባቢ) ቡድኖች የሚነግሯቸውን ብቻ ነው። ስለዚህ እዚህ ላይ በርትቶ መሥራት ያስፈልጋል። እንደ እድል ሆኖ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በምዕራቡ አገራት አሉን። እሱን በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ።

በሁለተኛነት መወሰድ ስለሚገባው እርመረጃ ሲያብራሩም በኮንግረስና ሚዲያ አስተዳደር ውስጥ ያሉ የተዛባ መረጃና አስተሳሰብ የያዙ ሰዎችን መቅረብ ያስፈልጋል። ማናቸውም ዋና ወይም መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን/ ሜይን ስትሪሚንግ ሚዲያዎች/ የሚሠሩት ከየመንግሥቶቻቸው ጋር ተቀራርበው ነው። የነገሮችን መነሻና የተከታተሉትን ሂደቶች አያቁም ማለት አይደለም። ዋና ዓላማቸው ዋሽተውና አወናብደው አስተዳደራቸው የሚፈልገውን ነገር ማድረግ ነው።

ነገር ግን ጉዳዩን በልኩ ያላወቁት በርካቶች ስላሉ በአስተዳደርና በማኅበረሰብ ደረጃ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ስለዚህ እዚህ ላይ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል። የአገራችን ሚዲያዎችም ለጊዜው አንዳንድ አስቸኳይና ወቅታዊ ያልሆኑ ፕሮግራሞቻቸውን ወደ ኋላ አድርገው በእነዚህ ነገሮች ላይ እጅግ በጣም ጠንክረው በመሥራት የአፍሪካ ማኅበረሰቦችን እና አስተዳደሮችን በሚቻለው ሁሉ ማዳረስ ያስፈልጋል። ዋናው ትግል መሆን ያለበት እውነታውን የማሳየትና የማውጣት ነው ሲሉ ይመክራሉ።

የትናየት ፈሩ

ዘመን መፅሄት ታህሳስ 2014 ዓ.ም

Recommended For You