የተዘነጋው የፑሽኪን ሐውልት

የአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሩሲያውያን ረቂቅ ሥነ-ጽሑፍ ከሳችና የዘመናዊ ሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ ፈልሳፊ ታላቁ የጥበብ ሰው አሌክሳንደር ሰርጌቪች ፑሽኪን የተወለደው እ.ኤ.አ. ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 1799 ዓ.ም ነው። ትውልዱ ከዘመኑ ባላባቶች እና ምሁራን ቤተሰብ ነበር። በ12 ዓመቱም በፔተርስቡርግ ከተማ አጠገብ በዛርስኮይ ሴሎ ውስጥ በሚገኘው በተከበረው የመሳፍንት ልጆች ትምህርት ቤት ገብቷል። በ15 ዓመቱ ግጥሞችን መጻፍ የጀመረው ፑሽኪን በ18 ዓመቱ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቋል። በሩሲያ ቋንቋና ግጥሞች ላይ አስተውሎት እንዲያዳብር እና የሩሲያን ባሕላዊ ልማዶች ፣ እምነቶች፣ አፈታሪኮች፣ አገርኛ ተረቶች እና ዜማዎች በመረዳት ጥበባዊ ምናቡ እንዲሰፋ ያስቻሉት ገጠር በገባርነት ይኖሩ የነበሩት የሦስት ልጆች እናት ወይዘሮ አሪና ሮዲኦኖቭ እና ሞግዚቱ ነበሩ።

አሌክሳንደር ፑሽኪን ለወይዘሮ አሪና እ.ኤ.አ. በ1856 በጻፈው ‹‹ሞግዚቴ›› ግጥሙ አክብሮቱን ገልጦላቸዋል። ዛሬ ወይዘሮ አሪና ሮዲኦኖቭና ፑሽኪን ለሩሲያ አገርኛ ጥበብ ዕድገት ለዋሉት ውለታ ‹‹የሩሲያ ምግዚት›› የሚል ታሪካዊ ስያሜ ተሰጥቷቸው ሐውልቶች ቆመውላቸዋል ፤ እና አደባባዮች ተሰይመውላቸዋል።

በትምህርት ቤት ዘመኑ ለታላላቅ ሰዎች፣ አገረ ገዢዎች፣ የንጉሡ አገልጋዮች እና ደራሲዎች ይዘጋጅ በነበረው የልጆች ክህሎት ማቅረቢያ የትርኢት መርሐግብር ላይ ይሳተፍ ነበር። የሰብአዊ ነጻነት ጥልቅ ሃሳብ የዘለቀበትን እና በምናብ ንዝረት የመጠቀ እሳቤ የሚገለጥበትን የፈጠራ ጽሑፍ ሀተታውን እንዲሁም የመድረክ ዕይታውን እና የትረካውን ወግ ልቆ መገኘት የትምህርት ቤት ጓደኞቹና መምህራኖቹ ይመሰክሩለታል።

በልጅነቱ በቤታቸው በነበረው የአባቱ ግዙፍ ቤተመጽሐፍት በፈረንሳይ ቋንቋዎች የተጻፉ መጽሐፎች የሞሉበት ስለነበርና በመሳፍንቱም ዘንድ የተለመደው መነጋገሪያ ቋንቋም ፈረንሳይኛ ስለነበር ፑሽኪን በፈረንሳይኛ ቋንቋ ንባብ ፣ ንግግር እና ጽሑፍ ብቃቱ የተነገረለት ነበር።

የዚያን ዘመኑ ፑሽኪን የልጅ አዋቂነቱንና የወደፊት ታላቅነቱን በግለታሪክ ድራማ የኪነጥበብ ወግ በሩሲያ የሥነ-ጥበብ ራዕይ (ፊልም) ተዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤአ. እሮብ የካቲት 10 ቀን 1937 ዓ.ም በፒተርስቡርግ ለሕዝብ ቀርቧል። ‹‹የገጣሚው ወጣትነት›› በሚል ርዕስ የተሰናዳውና 85 ደቂቃዎች የሚረዝመው ጥቁርና ነጭ ተንቀሳቃሽ ሥዕል በአብራም ናሮድቸስኪ (1906-2000 እ.ኤ.አ.) አዘጋጅነት በሌን ፊልም ኢንዱስትሪ የተመረተ ነው። ስራው በፑሽኪን 100ኛ የሙት ዓመት ላይ መቅረቡ መነሻ ሆኖ እስከዛሬም የፑሽኪን የጥበብ ሥራዎች ታሪካዊ ወግ በተንቀሳቃሽ ምስሎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

በሩሲያ ሥነ-ጽሑፍ ረጃጅምና አጫጭር ተውኔታዊ ግጥሞች ፣ ሙዚቃዎች ፣ ኦፔራ እና ባሌት ውዝዋዜዎች በምርምር የተሳተፉ ከሁሉም አህጉራት የተወጣጡ ባለሙያዎች በፑሽኪን ሥነ- ግጥሞች ልሳኖቻቸውን አሟስተዋል። እንደምሳሌ ፑሽኪን እ.ኤ.አ. 1829 ጽፎት በ1830 ለሕትመት የበቃው ከአስር መስመሮች የማይበልጠው ‹‹አፈቅርዎት ነበር›› የተሰኘ ግጥሙ የፑሽኪን ሐውልቶች በቆሙባቸው አገራት፤ በተለይ የኪነ- ጥበባት ደቀመዛሙርት፤ በተመስጦ መድረክ የሥነ-ግጥም ድምጻቸውን የሚያፍታቱበት የወጣት ትውልድ የክላሲካል ሥራዎች ከበሬታ ማስተዋያ ሥጦታ ሆኖ ይኖራል። ለዚህ ግጥም የ19ኛው ክፍለ ዘመን የሩሲያ ክላሲካል ሙዚቃ ደራሲ እና አዘጋጅ ሞክሼው አሌክሳንደር ሴርጌቪች ዳርጎሚዥስኪ (1813-1869 እ.ኤ.አ.) እ.ኤ.አ. በ1830ዎቹ መጀመሪያ ሙዚቃዊ ድርሰት ፈጥሮለት ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ አዘጋጅቶለታል።

በፑሽኪን ረዣዥም ግጥሞች ላይ በመመስረት ታላላቅ የሙዚቃና ኦፔራ ደራሲዎች እና አዘጋጆች በቴያትር አስገራሚ ትርዒቶች ያቀርቡ ነበር። እስከዛሬም በዓለም ኦፔራዎች የሚያስተጋቡት ‹‹የቭጌኒ አኔጊን›› በታላቁ የሙዚቃ ክላሲክ ደራሲ ኢሊየች ቻይኮቭስኪ (1840-1890 እ.ኤአ.) ሥራዎች እንደ አብነት ሆኖ እ.ኤ.አ. ከ1878 ጀምሮ በኦፔራዎች የሚጠቀስ ነው። እ.ኤ.አ. በ1830 ፑሽኪን የጻፈው ታሪካዊ ተውኔት ‹‹ቦሪስ ጎዱኖቭ›› በክላሲካል ሙዚቃ ደራሲው ሞደስት ሙሰርግስኪ (1839-1881 እ.ኤ.አ.) ለኦፔራ እና ለባሌት ተጽፎ እ.ኤ.አ. በ1874 ለሕዝብ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በዘመናት ሽግግር በየጊዜው ለትውልድ እየቀረበ ያለ ነው።

የ‹‹ቦሪስ ጎዱኖቭ›› ተውኔት፤ ኦፔራ እና ባሌት እ.ኤ.አ. በ1954 በሥነ-ራዕይ ጥበብ ሥራ መሪዋ ቬራ መሪዎ ስትሮየቫ ()1903-1991 እ.ኤ.አ.) ባለ 110 ደቂቃ ርዝመት ያለው ተንቀሳቃሽ ሥዕል ለመጀመሪያ ጊዜ ተሠርቶ ከቀረበ በኋላም ይኸው የፑሽኪን ታሪካዊ ድራማ ጽሑፍ ‹‹በሪስ ጎዳኖቭ›› እ.ኤ.አ. በ1986 በሥነ-ራዕይ ሥራ መሪነት፣ በጽሐፊነት እና በመሪ ተዋናይነት ሴርጌ ባንዳርቹክ (እ.ኤ.አ. 1920-1994) ባለ 141 ደቂቃ ርዝመት ሥነ -ራዕይ አዘጋጅተው አቅርበውታል። ዛሬም በአሌክሳንደር ፑሽኪን ትረካዎች ላይ መሠረተ ተውኔት እየተጻፈባቸው በሥዕለ ድምፅ (ቴሌቪዥን) የሚቀርቡ ሥራዎች እንደቀጠሉ ናቸው።

ፑሽኪን ትምህርቱን ባጠናቀቀበት ዘመን በፔተርስቡርግ ከተማ እንደ ወጉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እየሠራ አገሩን አገልግሏል። በርካታ ግጥሞችን ፣ ታሪካዊ ተውኔቶችን እና መጻሕፍትን ሲጽፍም ቆይቷል። በሕትመት ቅድመ ምርመራ የታገዱ ጹሑፎቹም ነበሩ። እስብታቸውም የንጉሡን ሥርዐት የሚቃወሙ ናቸው በማለት እየተነቀፉ ሲሆን በዚያም ሳቢያ ከፅኑ ቅጣት ይድን የነበረው በሚወዱት ባለሥልጣናት ድጋፍ ነበር።

ፑሺኪን በንጉሡ ትእዛዝ በግዞት ይላክባቸው በነበሩት ሥፍራዎች ሁሉ ለሥነ-ጽሑፍ የፈጠራ ሥራውዎ እጅግ ተፈጥሯዊ የስልሳሌ ግብአት እየሰጠው ያልፍ ነበር። ከሥራውም በራሱ ፈቃድ ለመልቀቅ በወሰነበት ወቅት በሩሲያ በሚገኘው በሴት አያቱ ርስት ፕስኮቭ እንዲኖር ተወስኖበት ቆይቷል።

ፑሽኪን አዋቂ እና ታዋቂ ሆኖ በግጥሙ እና በሥነጽሑፍ ዘመኑን ሲያስደምም ፤ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት በማግኘቱ የትዳር አጋሩን ናታሊያ ፑሽኪንን አግብቶ በፒተርስቡርግ ቤተ መንግሥት ግቢ ልጆችም ወልደው ይኖሩ ነበር። ናታሊ (1812-1863 እ.ኤ.አ.) በውበቷ ወደር የሌላት ቆንጆ ተብላ በመልካምም ባሕርይዋ ፑሽኪንም በዕውቀቱ እና በታላቅ ተግባሩ ይደነቁ በነበረበት ወቅት ፤ እጅግ በጣም የሚቀኑባቸውም ክፉዎች ግለሰቦችም ነበሩ። ነገር አዋሳጆችም ናታሪያ ቆንጂት የተባለላትን በወቅቱ ለሩሲያ መንግሥት ያገለግል የነበረው የፈረንሳይ የጦር መኮንን ደ አንቴስ (እ.ኤ.አ. 1812-1895) እቁባቱ እንደሆነች ከሹክሹክታ ባለፈ በምንም እና በማንም ያልተረጋገጠ አሉባልታ የያዘ ደብዳቤ ካልታወቀ ተንኮለኛ ሰው ካልተጠቀሰ አድራሻ ለፑሽኪን ይደርሰዋል።

በዚያ አሳዛኝ የቤተመንግሥት ውስጠ ዙሪያ ሤራ አሌክሳንደር ፑሽኪን ስለክብሩ መነካት የሽጉጥ ፍልሚያ እንደሚጠይቅ በዘመኑ ሥርዐት ተጠባቂ ነበር። ከጦር መኮንኑ ደ አንቴስም ጋር ሲፋለሙ እ.ኤ.አ. እሑድ ጥር 29 ቀን 1837 በጽኑ ቆስሎ እጅግ በርካታ ወዳጆቹ አክባሪዎቹ በከፍተኛ ሐዘን ተሰባስበው እንደቆዘሙ ብዕር ሲያፍተለትሉ የኖሩት የአሌክሳንደር ጣቶች በክር ታሠሩ። በሥጋም ማረፉ በአገሩ ተስተጋባ።

አሌክሳንደር ፑሽኪን በፍልሚያ ከወደቀባት ሥፍራ ዛሬ ከሚታየው የማስታወሻ ሐውልት ጀምሮ ዛሬም በዓለም ዙሪያ አደባባዮች እና ሐውልቶች የቅርስ ወግ እና የኪነ ጥበብ ታሪክ ምልክት ሆነው ይኖራሉ። የቆንጂቱና አስደማሚዋ ሚስቱ ናታሊያ እና የፑሽኪን አብሮነት ወግ መታሰቢያ ሐውልቶች በቆሙባቸው አደባባዮች ላይ ሁሉ ትውልድን በስልሳሌ ትኩረቱን ሲማርኩት ይኖራሉ።

የታላቁ ገጣሚ አሌክሳንድ ፑሽኪን ታሪኩና የጥበብ ሥራዎቹ ለትውልድ ታሳቢ ሆነው እንዲኖሩ ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጣቸው የተለያዩ ሐውልቶች ዛሬም ድረስ በዓለም የተለያዩ ከተሞች እየተተከሉ ይመረቃሉ። አብዛኛዎቹም ሐውልቶች ከሩሲያ መንግሥት ወይም ከሩሲያ ደራሲያን ማኅበር በሥጦታ የተበረከቱ እና የሚሰጡ ናቸው።

ሕዳር 10 ቀን 1995 ዓ.ም የአሌክሳደር ፑሽኪን ከደረት በላይ የተቀረጸው ሐውልቱ በአዲስ አበባ ሣር ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቆሞ ጎዳናውም በስሙ ተሰይሞለት ነበር። በወቅቱ የኢፌዲሪ የወጣቶች ስፖርትና የባሕል ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ አቶ ዓሊ አብዶ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ተገኝተው ነበር።

በሥነ ሥርዓቱ የክብር እንግዳ በወቅቱ የሞስኮ ከተማ ምክርቤት ተጠሪ ቪ..አይ. ሚሊሽኮቭ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለክፍለ ዘመናት ጸንቶ የቆየው የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ወዳጅነት በአሁኑ ጊዜም በሞስኮ እና በአዲስ አበባ መካከል በሚደረጉ የትብብር ሥራዎች ቀጣይ በምጣኔ ሀብት ፣ በንግድ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሥነፍጥረት ምርምር፣ በትምህርት፣ በባሕልና ቱሪዝም በጋራ ለመሥራት እንደሚያስችሉ ጠቅሰው ነበር።

የፑሽኪን ሐውልት በመዲናችን አዲስ አበባ ተመርቆ ሲቆም በዓለም ላይ በተለያዩ ጊዜያት ተመርቀው ከቆሙት 294 ከሚደርሱ መታሰቢያ ሐውልቶች ለአፍሪቃ የመጀመሪያው እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ ከተማችን የሚከናወነው የመንገዶችና እና የመሠረተ ልማት ግንባታ የፑሽኪን አደባባይ በሚገኝበት ሳርቤት አካባቢም በመቀጠሉ ምክንያት የፑሽኪን ሐውልት ከአደባባዩ ተነስቶ ቅርሶች በአደራ በሚቀመጡበት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲቆይ ለብሔራዊ ቤተመዘክር ተሰጥቶ ለዕይታ ቆሞ ቆይቷል። በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም የፑሽኪን አደባባይ እና ጎዳና የግንባታው ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ አደባባዩን የሚመጥን ባለ 11 ሜትር ሙሉ ቁመና ያለው የፑሽኪን አዲስ ሐውልት ታንፆ ከሞስኮ ለአዲስ አበባ በሥጦታ ሊበረከት መዘጋጀቱን ፤ የማጓጓዣው ዝግጅት ጉዳይ ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሆነና በቅርብ እንደሚመጣ ተገልጾ እንደነበር ይታወቃል።

በዚያ አጋጣሚም የወቅቱ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ በአዲስ አበባ እና በአፍሪካ ሕብረት ለሥራ ጉብኝት መጥተው ስለነበር ጉዳዩም በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋዊ መግለጫ ተሰጥቶበት እንደነበር በዓለም የመገናኛ ብዙኃን ተሰራጭቷል። የፑሽኪንም አደባባይ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ሲውል በታሪካዊው ቅርስ ፈንታ በማይገባ እና ወጉም ባልሆነ መልኩ ቦታው በንግድ ተወሯል።

የአሌክሳንደር ፑሽኪንን ሐውልት ከሞስኮ የመረከቡ አካሄድ የመዘግየቱ ሰበብ ግልጽ ባለመሆኑ በዚያው የሹክሹክታ ወግ የመደመጡ ሁኔታ በወቅቱ በአስመራና በአዲስ አበባ ባለሥልጣናት መካከል በእጅጉ ሻክሮ በነበረው የዠርዐ-ነገር ግንኙነት ብሎም የፑሽኪን ሙሉ ቁመናው የሚታይበት ሐውልት በአስመራ ከተማ መመረቁ በአዲስ አበባ ባለሥልጣናት ዘንድ ኩርፊያ አንግሦ ጉዳዩን በቸልታ የማረሳሳት ወግ ሸፈነው።

በየዓመቱ በሚከበረው የፑሽኪን ልደት መታሰቢያ በአዲስ አበባ በሩሲያ ሳይንስና ባሕል ማዕከል በፑሽኪን አዳራሽ የውይይት መድረክ ላይ የፑሽኪን ባለሙሉ ቁመና አዲስ ሐውልት ከሞስኮ በሥጦታ የሚበረከት ነው በተባለው መሠረት ተጓጉዞ በአደባባዩ ላይ እንዲቆም ባነሳሁት ሃሳብ ላይ የወቅቱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ‹‹… በእኛ በኢትዮጵያዊያን በራሳችን ሠዓሊዎችና ቀራጺዎች ሐውልቱን ለማሠራት የውድድር ጥሪ ዕቅድ ይዘጋጃል …›› የሚል ከዕውነታው የራቀ መግለጫ ተሰጠ። ዛሬም ዓመታት አልፈው የመግለጫቸውን ምሥል እና ድምፅ ሳስተውል በዐይነ ኅሊናዬ ንግርት የቀረበው ወግ የትዝብት ፈገግታ ያጭርብኛል። ምክንያቱም በወቅቱ የፑሽኪንን ሙሉ ቁመና በመዳብ ወይም በነሐስ ወ.ዘ.ተ ገንብቶ ለማቆም፤ የውድድር ጥሪ ለማድረግ ማንኛውም የመንግሥትም ይሁን የግል ድርጅት ዕቅድ አልነበረውም።

ይሁን እንጂ ትክክለኛው የሞስኮ እና የአዲስ አበባ ዕቅድ የአሌክሳንደር ፑሽኪን የሐውልት ርክክብ ጉዳይ ተራማጅ ሃሳብ ይጠብቁ ለነበሩት በወቅቱ ውይይቱን ለፈቀዱልን የሳይንስና የባሕል ማዕከሉ ሥራ መሪ ቭያችስላቭ አሌክሳንደር ኮኒክ የነበረውን እስብት ያለምንም መሸፋፈን ቅሬታ በሸፈነው ፈገግታ ማስረዳት ነበረብኝ። በወቅቱ የኔ እስብታ ትንታኔ ሌሎች አገራት ያደረጉት እንደነበርና እያደረጉም እንደሚታየው ሥጦታውን በጸጋ ተቀብሎ በአደባባዩ ላይ ለታሪክ ማቆም ፤ በዚያም የጥበብ ሥራ ተነሳሽነትን በማበልፀግ ቅርስና ባሕልን በማጥናት የምርምርንም ተሞክሮ ለመጪው ትውልድ ትሩፋት ለማድረግ ነበር።

የፑሽኪን ሐውልቶች እና አደባባዮች የሚታዩባቸውን ሌሎች አገራት እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህል በቻይና ዩዬ አንግሉ ፣ በሜክሲኮ በጀርዲን ቱሽኪን መናፈሻ ፣ በቤላሩስ፣ በብራስልስ፣ ቤልጂየም፣ ዋሺንግተን ዲሲ፣ በጃክሰን ኒውጀርሲ እንዲሁም ሞንሮይ ኒዮርክ ፣ በግሪክ እና በቡልጋርያ ይገኛሉ። በተለየ ሁኔታ ደግሞ ስድሳ የሚሆኑ የፑሽኪን ሐውልቶች በዩክሬይን የተለያዩ ከተሞች እና አደባባዮች ላይ ይገኛሉ። 140 በአይነታቸው የተለያዩ ጥበባዊ አቋም እና ይዘት ያሏቸው የፑሽኪን ሐውልቶች በሩሲያ የተለያዩ ከተሞች አደባባዮች ላይ ቆመው ትውልድን በጥበብ ታሪክ ወግ እያስደመሙ ይገኛሉ።

ለዚህ ጽሑፌ ማጠቃለያ ለመድረስ የሚቀረኝ እስብታ፤ በሥነ ጥበብ ውጤቶች አስተውሎ ማለፉ ነው። ይኸውም ፑሽኪን ‹‹የራስ ምሥል›› ብሎ ከሠራቸው እና በግጥሞቹ የፈጠራ ተመስጦ ውስጥ ሲመላለስ በንድፍ ሥዕል ካኖራቸው አሻራዎቹ በየድርሰቶቹ እና ግጥሞቹ ውስጥ ተሰንደው መገኘታቸውን እና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም የሥነጥበብ ዘርፍ በአድናቆት ከሚነገርላቸው ከሃያ በላይ ሠዓልያን ፑሽኪን በእርሳስ ንድፍ ፣ በቀለም ቅብ ፣ በውሃ ቀለም ቅብ ወዘተ የሠራቸው ምሥሎች አራት ሺህ የሚደርሱ ስብስቦች እና እጅግ በተከበሩ መዘክሮች እንዲሁም የትርኢት ሥፍራዎች ተቀምጠው የሚታዩ የጥበብ ወጎች መሆናቸውን በማስታወስ ነው።

 በሥነ-ራእይ ሥራ መሪ ብርሃኑ ሽብሩ

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You