አካል ጉዳተኞችን እኩል ተጠቃሚ ያላደረገው የትምህርት ስርዓት

“ልዩ ፍላጎት ሥርዓተ ትምህርት” ከሌሎች ተማሪዎች የተለየ ትኩረትና ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የሚሰጥ ትምህርት ነው። በዚህ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የአእምሮ እድገት ውስንነትና የአእምሮ እድገት መዛባት ያጋጠማቸው፣ አይነ ስውራን፣ መስማት የተሳናቸውና ማንኛውም ዓይነት የአካል ጉዳት ያላቸው እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችና ከእነርሱ በተለየ፣ የመማር ወይም የሚሰጣቸውን ትምህርት የመቀበል ችግር ያለባቸውና የተለየ ተሰጥዖ ያላቸው አሊያም ትምህርት በመቀበል አቅማቸው ከሌላው ተማሪ የፈጠኑ ተማሪዎች ይካተታሉ።

በሀገራችን በተለይም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ልክ እንደ ጉዳት አልባው ተማሪ በትምህርት ገበታ ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ተግዳሮት ይገጥማቸዋል፤ ለተማሪዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ ካለመፈጠሩና አስፈላጊ መሳሪያዎችም ካለመሟላታቸው የተነሳ፤ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ዘንድ እነዚህን ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር ፍላጎትም አናሳ በመሆኑ ሳቢያ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በተገቢ እድሜያቸው ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር እኩል በትምህርት ገበታ ላይ ለመገኘት ይቸገራሉ፤ ይህ ችግር በንጽጽር ከመዲናችን አዲስ አበባ ወጣ ባሉ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ይብሳል። የትምህርት ሚኒስቴር መረጃም እንደሚያመለክተው በሀገራችን አምስት ሚሊየን ህጻናት የልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ ትምህርት ማግኘት የቻሉት 11 ከመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው።

በትምህርት ሚኒስቴር፣ በልዩ ድጋፍና አካቶ ትምህርት፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቡድን መሪ አቶ ዓለማየሁ ወ/ቂርቆስ፣ የልዩ ፍላጎት ሥርዓተ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተለዩ ተማሪዎች ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሊያሰኛቸው የቻለው፣ በመደበኛነት የሚሰጠው ትምህርት ለእነርሱ ፍላጎትና የትምህርት አቀባበል ምቹ ባለመሆኑና የሚሰጠውን ትምህርት በአግባቡ እንዲከታተሉ የአጭር ወይም የረጅም ጊዜ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም፣ መርጃ መሳሪያዎች የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው እንደሆነና ልጆቹ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸው ትምህርት በአግባቡ ሲያገኙ፣ በእድሜያቸው ልክ አስፈላጊውን እውቀት እያገኙ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያደጉ እንዲሄዱ እንደሚያስችላቸው ይገልጻሉ፤ አያይዘውም፣ እነዚህ ልጆች በሚፈልጉት ልክ ድጋፍ ካልተደረገላቸው የምንፈልጋቸው ዓይነት ልጆችን ማፍራት አንችልም ይላሉ፤ አክለውም፣ ይህ የትምህርት ሥርዓቱ ሃላፊነት እንደሆነም አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።

ቀደም ባሉ ጊዜያት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ለብቻ ይሰጥ እንደነበር ያወሱት አቶ አለማየሁ፣ አሁን ግን በአካቶ ትምህርት ሥርዓት ስር እንዳለን በመጥቀስ፣ በዚህ የትምህርት ስርዓት አካል ጉዳተኛ ልጆች በአካባቢያቸው ባሉ ትምህርት ቤቶች፣ ድጋፍ እየተደረገላቸው፣ ከጉዳት አልባ ልጆች ጋር በአንድ ክፍል የሚማሩበት ሥርዓት እንደሆነ ይገልጻሉ። እርሳቸው እንዳሉት፣ በአካቶ ትምህርት ሥርዓት ከትምህርት ቅጥር ጊቢው፣ ከውሃ መጠጫው ከሽንት ቤቱ አንስቶ፣ የማስተማር ዘዴው፣ የትምህርቱ ይዘት፣ የመማር ማስተማሪያ መሳሪያዎችና የፈተና አሰጣጡ ለልጆቹ ተስማሚ እንዲሆን ይደረጋል ወይም ትምህርት ቤቱ ከልጁ ፍላጎት ጋር ራሱን ያስማማል። ነገር ግን፣ ይህ በጽሑፍ እንደሰፈረው በተግባር ብዙም የሚታይ አይደለም።

አካል ጉዳተኞችና ትምህርትን በተመለከተ ሁሉም በኃላፊነት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ሕገ መንግሥቱ ራሱ ትምህርትን በተመለከተ አስገዳጅ ድንጋጌን አላስቀመጠም ያሉት አቶ አለማየሁ፣ ለዚህም ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህጻናት መብት ስምምነት ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ምን ይላሉ? በሚል በ1998 ዓ.ም ያጠናውን ጥናት በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። ሕገ መንግሥቱ ስለ ትምህርት የሚያነሳው በሶስት አንቀጾች (በአንቀጽ36፣ 41 እና 90) ብቻ እንደሆነ አቶ አለማየሁ ያነሳሉ፣ እንደ እርሳቸው ሐሳብ፣ በእነዚህ አንቀጾች ውስጥ “ትምህርት መብት ነው” የሚል ድንጋጌ የለም፤ በተመሳሳይም አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ አምስት ለአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ ይደረግላቸዋል በሚል አገላለጽ፤ ጉዳዩ አስገዳጅ ዓይነት እንዳልሆነ ያስቀምጣል፤ ይህም የትኛውም አካል የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ግዴታዬ ነው ብሎ እንዳይዘው ያደርገዋል። ጎረቤታችን ኬንያ ትምህርትን የተመለከቱ ብቻ በትንሹ 15 አንቀጾች በሕገ መንግሥቷ እንዳካተተች የጠቀሱት አቶ አለማየሁ፣ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሀገርን የሚያሳድግ ትምህርት መሆኑን በሚገባ በመረዳታቸውና ትኩረት በመስጠታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉትም፣ ሀገርን ያለ ትምህርት ማሳደግ ስለማይቻል ትምህርትን በተመለከተ፤ ትምህርት ለሁሉም መብት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተብራርቶ መገለጽ አለበት።

የአካል ጉዳተኛ ልጆች ከቤት ወጥተው ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ለማስቻል በየክልሉ በየአመቱ፣ 15ሺ ዶላር የሚያወጡ መሳሪያዎች የተሟሉላቸው 200 የሚጠጉ የድጋፍ መስጫ ማዕከላት እየተገነቡ እንደሆነ የገለጹት አቶ አለማየሁ፣ ዋነኛው ችግር በማኅበረሰቡም ሆነ በትምህርት ቤቶች ዘንድ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር መኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ። የግንዛቤ ችግሩ ባይኖር አካል ጉዳተኛ ተማሪ ሲመጣ ተቀብሎ ወረዳውን እንዲህ ዓይነት ተማሪ መጥቷል ምን ላድርግ ብሎ መጠየቅ ይችላል፤ ከወረዳውም ሆነ ከክልሉም ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። እነዚህ ልጆች ልክ እንደ ሌላው ልጅ በቂ ነው የሚያስብል ባይሆንም በጀት ተመድቦላቸዋል ያሉት አቶ አለማየሁ የግንዛቤ ችግር፣ ለልዩ ፍላጎት ሲሆን በጀት ማጣት፣ የትምህርት ሥርዓቱ ተለማጭ አለመሆንና የአጋዥ መሳሪያዎች አለመሟላት፣ የልጆቹን ችግርና ተሰጥዖ መለያ ማዕከላት አለመኖርና ሌሎችም በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ክልል ያሉ አካላት ቢደጋገፉና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ቢዘረጋ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይላሉ።

መምህር ክንዴ መኮንን፣ የብሔራዊ ኢትዮጵያ አፀደ ህጻናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ በሀገራችን አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ በርካታ ሕጎችና መመሪያዎች ቢኖሩም፣ አፈጻጸሙ በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ነው። ለምሣሌ ማንኛውም የአካል ጉዳት ያለበት ተማሪ ገና ትምህርት ቤት ሲሄድ፣ ልክ ጉዳት አልባው ተማሪ፤ ወላጅ አምጥተህ፣ ተመዝግበህ፣ መጽሐፍ ውሰድ እንደሚባለው ብሬይል የሚያስፈልገው ተማሪም ብሬይል ተሰጥቶት፣ የምልክት ቋንቋ የሚያስፈልገውም በምልክት ቋንቋ ለመማር ተመቻችቶለት እኩል ትምህርት መጀመር ቢገባውም፣ በተግባር ግን ይህ ሲሆን አይታይም። በጣም ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎች ይህን ለማሳካት ጥረት አያደርጉም። ከዚህም በተጨማሪ፣ የትምህርት ቤት መንገዶችና ቅጥር ግቢዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው ባለመሰራታቸው ለአካል ጉዳተኞች አይመቹም ያሉት መምህር ክንዴ አንዳንድ መንገዶችና የትምህርት ቤት አካባቢዎች፣ እንኳን ለአይነ ስውር፣ አይናማውንም ለአደጋ የሚያጋልጡ እንደሆኑ ይናገራሉ።

በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ አዳዲስ ህንጻዎች በሚገነቡበት ጊዜ ለአካል ጉዳተኞች ተዳፋታዊ መወጣጫ እንዲሰራ ሲጠየቅ፣ ትምህርት ቢሮ ለዚህ በጀት አልመደበለትም፤ በጀት የለም የሚል ምላሽ እንደሚሰጥ የጠቀሱት መምህር ክንዴ፣ ፈቃደኛ ግለሰቦች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ለልዩ ፍላጎት ያለው አመለካከት አነስተኛ መሆኑንና ልጆቹንም ተቀብሎ ለማስተማር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ይናገራሉ። የአካል ጉዳት ያለባቸው ልጆችም አንዱ ትምህርት ቤት እምቢ ሲባሉ፣ ሌላው ጋር ሞክረው ይማራሉ እንጂ፣ ልክ እንደ ሌላው ልጅ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኝ ወይም እነርሱ በፈለጉበት ትምህርት ቤት ገብተው መማር ከባድ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በተለይ ከመጽሐፍ ጋር ተያይዞ መደበኛውን የመማሪያ መጽሐፍ ለአይነ ስውር ተማሪዎች ተብሎ ታስቦ አብሮ እንደማይዘጋጅ ያነሱት መምህር ክንዴ፣ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ብቻ ግዴታ እንደሆነ አውቀው ሲያስጽፉ፣ አብዛኞቹ ግዴታ መሆኑን ካለማወቃቸው የተነሳ የእርዳታ ድርጅቶች እስኪረዱን ጠብቁ የሚሉም እንዳሉ ይጠቅሳሉ። አያይዘውም፣ እርሳቸው የጠቀሷቸውንና ሌሎችም ከልዩ ፍላጎትና ከአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተመለከተ በየጊዜው ምን መደረግ አለበት? በሚለው ላይ የተለያዩ ተቋማት ስብሰባ እንደሚቀመጡ በማስታወስ ነገር ግን፣ የተባለው ሁሉ ተግባር ላይ እንደማይውልና ትንሽ ጅማሮም ሲኖር ብዙ ርቀት እንደማይጓዝ ተናግረዋል።

ተማሪ ብርሃኑ ምናሴ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ እስከ 9ነኛ ክፍል በሻሸመኔ ከተማ እንደተማረ የሚናገረው ተማሪ ብርሃኑ በትምህርት ቤት የነበረው ቆይታ መልካም እንደነበርና አሁንም ከትምህርት አሰጣጡ ጀምሮ በመምህራኖቹ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የሚያደርጉት ድጋፍ መልካም እንደሆነ ተናግሮ ነገር ግን፣ የመማሪያ መጻሕፍት ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች በብሬል ማግኘት ከባድ እንደሆነ ጠቁሟል፤ ከዚህም በተጨማሪ በብሬል የሚይዟቸውን ማስታወሻዎች በእጅ ተነበው የሚዘለቁ ባለመሆናቸው የድምጽ መቅረጫ ቴፕሪከርደሮች ትኩረት ተሰጥቶት እንዲኖርን ቢደረግ ጥሩ ነው ብሏል።

በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ አካል ጉዳተኞችን ምንም የማይችሉ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ይታያል ያለው ተማሪ ብርሀኑ፣ በዚህ አስተሳሰብ ሳቢያ በተለይ ከከተማ ውጪ ያሉ አካል ጉዳተኞች ትምህርት እያገኙ እንዳልሆነ በርካቶችም በወጣትነት እድሜያቸው ልመና ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ በመግለጽ፣ እነዚህን ልጆች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማድረግ ከግለሰብ ሕይወት ጀምሮ ቤተሰብንም ሐገርንም መለወጥ እንደሆነ ተረድቶ፤ አካል ጉዳተኞች ከእክል አልባው ያላነሰ፣ እንዲያውም የተሻለ ትምህርት የመቀበል አቅም እንዳላቸው ተገንዝቦ ማገዝ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

ሌላዋ ያነጋገርናት ወ/ሮ ሐይማኖት ወንድማገኝ፣ የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ስትሆን፣ የሰባት ዓመት የአካል ጉዳተኛ ልጇን ለማስመዝገብ ወደ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት በሄደችበት ጊዜ፣ አካል ጉዳተኛ መሆኗን ስትናገር “አታስመዝግቢያት ትምህርት ሲጀመር ይዘሻት ነይ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣትና ትምህርት ሲጀመር ልጇን ይዛ ስትሄድ ግን፣ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ አንቀበልም የሚል ምላሽ እንደሰጧት ትናገራለች። “እኔ አብሪያት እቆያለሁ፣ ሽንት ቤት በሚያስፈልጋት ጊዜም እኔ አለሁ” ብትልም “አይቻልም”” የሚል ምላሽ ሰጥተው እንደመለሷት የምትናገረው ወ/ሮ ሐይማኖት፣ ማኅበረሰቡም ሆነ ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኛ ያላቸው አመለካከት ሞራልን የሚጎዳ ነው ትላለች፤ ሌላ ትምህርት ቤት ስሄድም “ሞልቷል” ብለው መልሰውኛል ብላለች።

በየመገናኛ ብዙኃኑ አካል ጉዳተኛ ልጆቻችሁን አትደብቁ፣ አውጡ፣ አስተምሩ፣ ህክምና ውሰዱ ይባላል፣ ነገር ግን ህክምና ስንወስድ መንገድ ይዘጋብናል የምትለው ወ/ሮ ሀይማኖት፣ ልጆቻችንን ለማዝናናት እንኳ ይዘናቸው ስንወጣ ሰዉ እንደተለየ ፍጥረት ነው የሚያያቸው በማለት ቅሬታዋን ትገልጻለች፤ በተለይ ልጄን እያዩ ከንፈር የሚመጡት ነገር በጣም ያመኛል ያለችው ወ/ሮ ሐይማኖት፣ በየመገናኛ ብዙኃኑ ስለ አካል ጉዳተኝነት በርካታ አስተማሪ ነገር ቢነገርም፤ የተማረ የሚባለው የማኅበረሰብ ክፍል እንኳ አስተሳሰቡ ገና አልተለወጠም፤ ስለሆነም ሰፊ ስራ መስራት ያስፈልጋል ትላለች።

አቶ ደምሴ ገብሬ ደግሞ፣ በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀስ የ4 ኣመት ልጇን ትምህርት ቤት ማስገባት ያልቻለችን እናት ለማገዝ ህጻኑን ወደ ትምህርት ቤት ይዘው በሄዱበት ጊዜ አሳዛኝ ምላሽ እንደገጠማቸው ያስታውሳሉ፤ አቶ ደምስ እንዳሉት፣ ህጻኑ፣ እኩያ ጓደኛው ትምህርት ቤት ሲሄድ እርሱ ቤት ውስጥ በመቅረቱ አኩርፎ ለሊቱን ሙሉ እንቅልፍ ሳይተኛ በማደሩ፣ እናቱ ልጇ የሆነውን ስትነግራቸው፣ በራሳቸው ፈቃደኝነት ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ቢወስዱትም፣ በቦርድ ነው የሚወሰነው በሚል፣ ሁለት ቀጠሮዎችን ከሰጧቸው በኋላ፣ ልጁ የሚንቀሳቀሰው በዊልቸር በመሆኑ አስተማሪዎቻችን ላይ ጫና እንፈጥራለን፤ ተማሪዎች በሚወጡ በሚገቡበት ጊዜ ማን እያወጣ ያስገባዋል? የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። ልጁን ለሚያወጣና ለሚያስገባ ሰው ተጨማሪ ክፍያ ልክፈል ቢሉም “በፍፁም አንችልም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።

አቶ ደምስ እንዳሉት፣ በቢሾፍቱ ከተማ አንድ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ያለ ሲሆን፣ ይህ ትምህርት ቤት ለአይነስውራንና የመስማት ችግር ያለባቸውን እንጂ፣ ሌላ አካል ጉዳት ያለበትን ልጅ የሚቀበል አይደለም። እውነታውም፣ እንዲህ ዓይነት ልጆች ከጉዳት አልባው ተማሪ ጋር ተቀላቅለው መማር የሚችሉ፤ ነገር ግን የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ያሉት አቶ ደምስ፤ አያይዘውም፣ በየቤቱ ያሉ አካል ጉዳተኛ ልጆች በተለይም ወላጆቻቸው የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን አሟልተው ማስተማር የማይችሏቸውን ልጆች ተቀብሎ የሚያስተምር ትምህርት ቤት በቢሾፍቱ ከተማ መገንባት እንደሚገባውና ለዚህም፣ ከበጎ ፈቃደኛ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የተቻላቸውን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸውልናል።

በዚሁ በቢሾፍቱ ከተማ አድኣ ወረዳ፣ የ“ራዕይ ትውልድ የአካል ጉዳተኞች ማህበር” መስራችና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሀና ፍራንኮ በበኩላቸው፣ በከተማው በርካታ አካል ጉዳተኞች ትምህርት ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ ማኅበሩ አካል ጉዳት ያለባቸውንና ትምህርት ቤቶች አንቀበልም ያሏቸውን ልጆች የትምህርት ድጋፍ በማሟላት ትምህርት እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በርካታ አካል ጉዳተኛ ልጆችን ከተደበቁበት ያወጣና የትምህርት መርጃ መሳሪያ የሚያስፈልጋቸውንም በማገዝ ለቁም ነገር እንዳደረሰ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንዳሉት፣ በርካታ እናቶች አካል ጉዳተኛ ልጆቻቸውን ለማስተማር የትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ እንባቸውን ያፈሳሉ፤ እነዚህ አካል ጉዳተኛ ልጆች ያሏቸው እናቶች ደግሞ አብዛኞቹ ባሎቻቸው ትተዋቸው ሄደው ብቻቸውን ለልጆቻቸው ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው። በርካታ እናቶችም ልጆቻቸውን ያለ ደጋፊ ተሸክመው በመዞር ለከፍተኛ የጤና ችግር ይዳረጋሉ። እነዚህ ልጆች በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ በሆነ ስህተት ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረጉ እንጂ እንደማንኛውም ዜጋ ሀገሪቱ ካላት ሀብት እኩል የመጠቀም፤ እንደ እክል አልባው ልጅ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር መብት ያላቸው ናቸው የሚሉት ወ/ሮ ሀና፣ ነገር ግን ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ብዙዎች እንደ እድሜ እኩዮቻቸው ትምህርት ቤት ውሎ መግባትና መማር እየናፈቃቸው በአልጋ ላይ እንደታሰሩ እድሜያቸው ያልፋል በማለት በቁጭት ይናገራሉ።

አሁንም በርካታ እናቶች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍሉ ያነሱት ወ/ሮ ሀና፣ እነዚህን እናቶች ለማሳረፍ ልጆቹንም ከተጠሙት ትምህርትና ከእኩዮቻቸው ጋር ለማገናኘት መንግሥት፣ አቅሙ ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች በያገባኛል መንፈስ፤ አካል ጉዳተኝነት ነገ እኔም ቤት ላለመግባቱ ዋስትና የለኝም በሚል ስሜት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You