የምሁሩ ሚና ምን ቢሆን ይሻላል?

ችግራችን ሥረ ብዙ ነው። ዓይነተ ብዙ ነው። ክቡድ ነው። ሸክሙ ከዚህ አንስተን እዚህ እናደርሰዋለን የማንለውን ዝክንትል የያዘ ነው። ያለብን በአንድ አዳር ልናስተካክለው፣ ልንበጣጥሰው፣ ልናፈራርሰው የማንችለው የተውተበተበ የችግር ድር ነው። ችግርን ከሥር ከሥሩ አልፈታንምና በችግር ላይ ችግር ተደርቦ ዛሬ የተሸከምነውን እዳ አሸከመን።

የትምህርት ሥርዓት ሲንሸዋረር ዝም ስላልን አሁን የተማረውና ወረቀት የገዛው በአንድ ገበታ መቀመጥ ጀመሩ። የተማረ የሚባለው አልፎ አልፎ ብቻ ድምፁን ለማሰማት ሲሞክር ወረቀት የገዛው ደግሞ ከሚዲያ ባለሙያዊነት እስከ ሕግና ፖሊሲ አውጪነት ተቆልሎ የምናይበት አጋጣሚ ሰፍቷል። (ወረቀት የገዛችሁ ባለሙያዎችና ባለሥልጣኖች ስሕተታችሁን በውስጥ እመኑልኝ፣ ቀለል ያለ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ያለበለዚያ በአደባባይ ትዋረዳላችሁ የሚለው የመንግሥት ጥሪ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን አይደል?)

መከላከያው የአንድ መንደር ካድሬዎች መፈንጫ ሲሆን፣ ምንም ባለማድረጋችን አርበኛ እና ባንዳ በአንድ ዩኒፎርም ሥር ሆነው ለማየት ተገደድን። ድፍን አንድ ዓመት ያስቆጠረውና በዘመናት መኻል አንዴ ብቅ የሚለው ታላቁ ክህደት በመከላከያ ላይ መፈጸሙ አሁን ድረስ ላልተጠናቀቀው ጦርነት ትልቁ ሰበብ ነው። ይሄም እንደ ላይኛው ነው፤ የአርበኞች ቤት መሆን ሲገባው የባንዶች ቤት ጭምር ሆኖ እንዲሠራ ሲደረግ ዘረኞች ቤቱን ለመበከል የሄዱበትን ርቀት አውቀን ያሰማነው ድምፅ አናሳ መሆኑ ነበር። (አሁንም እንኳ ስለመንቃታችን ማንም እርግጠኛ መሆን የሚችል አይመስልም። በዚህ ጦርነት እንኳ የውጭ ሀገር ምስሎች ተቀናብረው በጠላቶች ሲለቀቁ ‹አዎ ልክ ነው› ብለን አምነን የምንሸበረውን ያህል የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚሰጡትን ትዕዛዝ፣ የሚያስመዘግቡትን ድልና የሚሰጡትን መረጃ ላለመቀበል ሲያቅለሸልሸን እንታያለን)።

በተመደብንበት ቦታ ሠርተን ከማሠራት ይልቅ የውሸት ሪፖርት ሲጻፍ እያየን፣ እንድንጽፍ ስንገደድም አንዳች ነገር ትንፍሽ ባለማለታችን ዛሬ ያልተመረተ ተመረተ ሲባል፣ የተገደለ አልተገደለም ሲባል፣ የታሠረ አልታሠረም ሲባል ብቻ ሳይሆን የተሳደበ ክብር ተሰጥቶት ፓርላማ ሲገባ አየን። ከዚህም ከፍቷል፤ የመንግሥትና ዜጋ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆኑ የባልና ሚስት፣ የወላጅና ልጅ፣ የልጅና የወላጅ ጉዳዮቻችን ሳይቀሩ በሐሰተኛ ሪፖርቶች እንዲስተካከሉልን የምንፈልግ እየበዛን ነው። ልጅ ያልዋለበትን ሪፖርት ሲያደርግ ወላጆችም እርስ በእርስ ያልዋሉበትን ሪፖርት ያደርጋሉ።

ሕክምና፣ ምሕንድስና፣ የሕግ ትምህርት ሁሉ እንደ ካድሬነት በዘመቻ (በኮታ) ሲሰጡ ትንፍሽ ባለማለታችን ወይም የረባ ለውጥ ለማምጣት ባለመሥራታችን ዛሬ ለነፍሰ ጡር የሬሳ ማድረቂያ መርፌ የሚወጋ ሐኪም፣ ጋሪ ሲሄድበት የሚያረገርግ ድልድይ የሚሠራ መሐንዲስ፣ ፍትሕን ሳይሆን ፓርቲን የሚያስቀድም ዐቃቢ ሕግን የምናይበት ሁነት ተፈጠረ። ዛሬ እላይ ያሉ መሪዎቻችን ምንም ያህል ቅን ቢመኙ፣ ምንም ያህል ሀገር ለማበልጸግ ሕዝብ ለማሻገር ቢነሱ ረጅም ዘመናትን ደንብሸን ያደነበሽናቸው የበታች አመራሮች ያለጉቦ እንዳያገለግሉ፣ ያለመታያ ፍትሕን እንዳይደርሱባት፣ ያለ ጉርሻ የተሻለ አገልግሎትን እንዳይሰጡ አድርገን ሠርተናቸዋል። ሐኪም ቤት ሄደን ብንሰለፍ፣ ፍርድ ቤት ሄደን ብንገተር፣ መብታችን የሆነውን የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት ስድስት ወራት ብንንቃቃ፣ ትናንት አዲስ ብለን ያገኘነው ቤት ዛሬ ውስጡ ፍሳሽ በፍሳሽ ቢሆን የእኛው ውጤት!

መጠበቅን ስንለማመድ ተው እንጅ የሚለን መካሪ አጥተን የማይመጣውን ስንጠብቅ፣ ለማናወቀው ሰፊ ጊዜያችንን ስንሰዋ ጠባቂነት እያሳሳቀ ወስዶን ጫት ቤት እና አረቂ ቤት ከመረን። አሁን መውጣት ተሳነን፣ ሀገር ተወሮ ከመቆጨትና ከመነሳት ይልቅ ቁጭ ብሎ ጫት ያበሰበሰው ጥርስን እያንገለጠጡ ወሬ መሰለቅ ድርሻችን ሲሆን አየን። ሲርበን መንግሥት እንዲደርስልን እንመኛለን እንጅ ወጣ ብለን የወንዝ ዳርቻ ላይ ድንች ወይ ጎመን ስለመዝራት አናስብም። የትምህርት ውጤታችን ቢያሽቆለቁል ጾታችንን፣ ጎሳችንን አለዚያም ሃይማኖታችንን መታያ አድርገን መንግሥት ‹‹አስተያየት›› እንዲያደርግልን እንጠይቃለን፣ እንጠብቃለን። ጥንቃቄ አድርጉ ስንባል አሻፈረኝ ብለን ባመጣነው በሽታ ስንጎሳቆል መንግሥት ካልደረሰልን ብለን እንጠይቃለን፤ እንጠብቃለን።

ይህ ሁሉ ሲደራረብ የመጣ ችግራችን ነው። አንድ ቀን ብቻ የተሠራ አይደለም። ለዘመናት የተሻገረ ነው። ተነስተን ለውጥ ከማምጣት ይልቅ የሆነ አካል መጥቶ ለውጡን እንዲሰጠን እንጠብቃለን፤ ሀሞታችን ፈስሷል። ዐሥር አምራቾች ያመረቱትን አንድ ሺህ ሆነን እንደልለዋን። በድለላ ስም እናጭበረብራለን፤ ባዬ በሰማ ጥቅም እንጠይቃለን። ያገኘነውን ዲናር ይዘን አረቂ ቤት እንወተፋለን፤ ደግሞ ነገ በስልክ ስለምንደልለው እናስባለን እንጅ ተነስተን ስለማምረት አናስብም።

የማናውቀውን ነገር ተምረነዋል ብለን እናወራለን። ጠንካራ ጠያቂ ሲገጥመን ‹ያው ወረቀቱን ልያዘው ብዬ› እንላለን። ተምረን ሥራ አጣን ብለን ለማማረር የሚቀድመን የለም። በዓመት ውስጥ ሦስት ቀን ክፍል ውስጥ ገብተን ሠላሳ ቀን ለጓኞቻችን ‹‹አቴንዳንስ›› አስፈርመን፣ ዐሥራ ዘጠኝ የተገለበጠ ወረቀት ላይ ስማችንን አስጽፈን፣ ከስልካችን ላይ መልስ ገልብጠን ‹‹ተፈትነን› ‹የተማርን› እኛ ሥራ ጠፋ፣ መንግሥት ሥራ አልሰጠንም እንነሳ እና መንገድ እንዝጋ፣ ፌስ ቡክ ላይ ጫጫታ እናስነሳ ብለን እንዶልታለን። አዎ ችግራችን ብዙ ነው።

የዕለት ከዕለት ሕይወታችንን በቅጡ ለመምራት እንቸገራለን። የማናውቃው ቢበዛም ቅሉ ‹‹አውቀዋለሁ›› ብለን ለመናገር የድፍረት ችግር የለብንም። ያለንበትን ሕይወት ማሸነፍ አቅቶን ብንንገዳገድም ቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመተቸት የሞራል ችግር የለብንም። ትዳራችንን በቅጡ ለማቆም የተቸገርን፣ በብድር ሰቆቃ ውስጥ ተዘፍቀን ሱሳችንን ለማስታገስ የምንታትር ሆነን የከንቲባዋን ‹‹የአፈጻጸም ብቃት›› አበሻቅጦ ለመጣል እምብዛም አናቅማማም። በብድር ላይ ብድር ከምረን፣ ፊታችንን በብዙ ኮፍያና መነጽር ደብቀን ከሰፈር እየወጣን፣ አምሽተን እየገባን ራሳችንን የምንሸውድ እዳው ካልተከፈለው የአረቄ ብርጭቆ ፊት ለፊት ቁጭ ብለን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በፌስ ቡክ ልንመራ እንታትራለን።

ስለዚህ ሁሉ መፍትሔ እንሻለን። እንደምንገምተው የመፍትሔ ምንጩ ደግሞ ‹‹ምሁሩ›› ነው። ይህ ምሁር የሚባለው በትልቁ ምስል ሀገርን ከድህነት፣ ሕዝብን ከችጋር ከርሃብና ከሰቀቀን አላቅቆ በምድር ላይ ላሉ ፍጠርታት ሁሉ ጤናን፣ ሰላምን እና ረፍትን ማጎናጸፍ ትልቁ አደራው ነው ይባላል። በትንሹ ምስል ደግሞ አለባበሱ፣ አነጋገሩ፣ አኗኗርና የህይወት ዘይቤው ማራኪነት እና አርአያነት ያለው ለሚያየው፣ ለሚያዳምጠው እና ለሚያነበው መረጋጋትን የሚሰጥ ለተቸገሩም መፍትሔ የሚያመላክት እንዲሆን ይጠበቃል።

ምሁሩ ባደጉት ሀገራት ምን ሚና ነበረው?

 ምሁሩ ለበለጸጉት ማኅበረሰቦች ምን አድርጎላቸው ነበር? ምሁሩ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ አስተሳሰቦች ላይ ምን እጅ ነበረው? ምሁሩ በሚያድግ ሀገር ውስጥ ምን ቦታ አለው? ምሁሩ ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ በነገሠበት ሥፍራ ምን ያድርግ? ምሁሩ ርሃብ፣ ግጭት፣ ተንኮል በነገሠበት ማኅበረሰብ ውስጥስ ምን ሚና ይኑረው?

አስቀድሞ ምሁርነትን ከገለልተኝነት፣ ከወገንተኝነት እና ከአሳቢነት አንጻር እንየው። ለመሆኑ ምሁር መቆም ያለበት ከሥርዓት ጋር ወይስ ከእውነት ጋር? አስቅድሞ ይሄንን መመለስ አንገብጋቢ ይሆናል። ነገር ግን ‹‹ምሁር›› ከሚለው ቃል ጋር ብዙዎቻችን ቤተኛ የሆንን ይምሰለን እንጅ በትርጉም ደረጃ ቃሉ የጠለቀ በመሆኑ የምናውቀው እየመሰለን የማናውቀው መሆናችንን የምንገነዘበው ቆይተን ነው።

ምሁር የሆነውን እና ያልሆነውን ለመለየት የምንቸገረውም ለዚህ ይመስለኛል። ለምሁሩ የሚገባውን ሁሉ ምሁር ለመሰለው ስንሰጥ የምንታይበትም ሰበብ ከዚህ ብዙ የሚርቅ አይደለም። የምሁር ትርጓሜ ምን ያህል አሻሚ እንደሆነ እንደሚከተለው እንይ። ከፍ ሲል እንዳልኩት አንደኛው መገለጫ ‹‹ገለልተኝነት›› ነው ብለን እንነሳ። ነገር ግን ገለልተኝነት ደግሞ በራሱ አሻሚ ነው።

የቃሉ አሻሚነት የሚመነጨው ሰው ከመሆን ላይ ነው። እያንዳንዱ ሰው በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ጥቅም፣ ፍላጎት፣ ምኞት፣ ያለው በመሆኑ እነዚህን ሁሉ ለማሟላት ደግሞ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ይኖሩታል። በእነዚህ ተግባቦቶች (መስተጋብሮች) የሚኖር ሰው ደግሞ በሙያህ ገለልተኛ ሁን ቢባል ምን ያህል ያስኬዳል ነው?

እነዚህ እውነታዎች እንዳሉ ሆነው ዋልዶ ኤመርሰን ደግሞ ምሁር ለምሁርነቱ መቆም አለበት ይላል። ይህን ለማለት ያነሳሳውን ምክንያት ሲገልጽ ኤመርሰን ምሁርነት ማለት የኅብረተሰቡ የማስተዋያ ዓይን፣ ማገናዘቢያ ጭንቅላት ማውጠንጠኛ አዕምሮ በመሆኑ ነው። ምሁሩ የበራለትን ሁሉ እያበራ ማኅበራዊ ጠንቆችን ከማኅበረሰቡ ይመነጥራል። ስለዚህ ምሁር ሲባል የራሱን የኢኮኖሚ ጎን፣ የፖለቲካ ጎን፣ የሃይማኖት ጎን ወዘተ… እያሰበ ኪሱን ለመሙላት ሳይሆን የሚሠራው በጭንቅ እና በማኅበረሰብ መሃል በንጽሕና ቆሞ ማኅበራዊ ጣጣዎችን የሚፋለም ነው።

የራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን እይታ በእርግጥ ለብቻው የሚቆም አይደለም፤ ይልቁንም ጥበብን ለጥበብ (Art for art sake) ከሚለው የቆየ ፍልስፍና ጋር የሚጃመል እንጅ።

ይሄም ይባል እንጅ ኅብረተሰብ ደግሞ ለምሁር የተመቸ ሜዳ ሆኖ የተገኘበት የዓለም ታሪክ ብዙም የለም። የእውቀትን አባቶች በሄምሎይክ መርዝ የገደለ፣ ፊዚዝቶችን በስቅላት የቀጣ፣ ፈላስፎችን በእሳት ያቃጠለ፣ አሳቢዎችን በመጥረቢያ ያስፈለጠ መሆኑ የዚህ ዓለም አንድ ብቻ ሳይሆን ሁነኛ ታሪክ ሆኖ የተመዘገበ ሀቅ ነው።

ምሁሩ ፊት ለፊት ካለው ጨለማ ባሻገር ያለውን ብርሃን ስለሚያይ ጨለማ ላይ ብቻ በሚያተኩረው ማኅበረሰብ ጥርጣሬ ውስጥ ይወድቃል። ይፈራል። ይነቀፋል። ‹‹መናፍቅ›› ተብሎ ይታማል። ይወገራልም። ይህም የሚሆነው ኅብረተሰቡ ጨካኝ ስለሆነ ሳይሆን ይልቁንም የትኛውም ማኅበረሰብ ጨለማ አፍቃሪ እና ለብርሃን ፍቅር እምብዛም ያልታደለ መንጋ ስለሚበዛበት ነው።

ስለዚህም ነው ምሁርነት ከገለልተኝነት እና ከወገንተኝነት ተጻራሪ አቋሞች መሃል ገብቶ የሚፈተተው። በአንድ በኩል ወገንተኛ ይሁን የሚባለው ምሁር በሌላ በኩል ገለልተኛ ይሁን ይባላል። ለሙያው በመታመን ኅብረተሰብ ይጠቅማል ብሎ ሐሳብ የሚያመነጭ ሰው ያ፤ ሐሳብ ተግባራዊ እንዳይሆን ከሚያግዱት አሠራሮችና እውነቶች ገለልተኛ ሊሆን የሚችለውን ያህል ያንን ሃሳብ ወደ መሬት አውርዶ ማኅበራዊ ጠንቆችን ሊያስወግድልኝ ይችላል ብሎ ከሚያስበው አሠራር ወይም ተቋም ጋር ወገንተኛ ቢሆን የሚለው አዎንታዊ መከራከሪያ የመሆኑን ያህል ‹ለሆዱ› የወገነ ወይም የተገለለ እንደሆነ ልክ በመንደርደሪያችን እንዳልነው ዘመናትን የሚሻገር የትውልድ ፈተና ሲመጣ መጋፈጥ ያልቻለ ሐሳዊ ‹ምሁር› ተብሎ የሚመዘገብ ይሆናል።

ስለዚህ ሐሳብ ገለልተኛም ወገንተኛ አይደለም፣ እንዲያው ብቻ ሐሳብ ነው በሚል ነጥብ መስማማት የቻልን እንደሆነ ይሄንን ጽሑፍ እንቀጥል። ነገር ግን እንዲህም ማለት ይገባናል። ምሁሩ ሐሳብ የሚያመነጭ ከሆነ ከአንድ ኅብረተሰብ ክፍል ጋር መወገን የለበትም፤ መወገን ያለበት ይልቁንም ከእውነት ጋር ነው። ይሄ ምን ማለት ነው? አንድ ሥፍራ የተወለደ ኢትዮጵያዊ የአካባቢውን ወይም በዘመኑ አጠራር የጎሳውን ችግር አጠና እንበል፣ ከዚያ ለመፍታት ተነሳ። ይህን ችግር ለመፍታት ሲል ግን ከዚህ ጎሳ ጋር ወግኖ የቆመ እንደሆነ ምሁር አይሆንም፤ ከእውነት ጋር አልቆመምና። እውነትስ እዚህ ሥፍራ የቷ ናት? ያ፣ ጎሳ ብቻውን የሚቆም ሊሆን አይችልም፤ በአንድ ሰው ብቻም ሊሰጠው የሚችለው መፍትሔ አይኖርም። ቢያንስ ‹ጎሳ› መሆኑ እንዲታወቅለት ሌሎች ጎሳዎች መኖር እና መቀጠል አለባቸው። ስለዚህ ይህ ‹‹ምሁር›› የሚያመጣው የመፍትሔ ሐሳብ አካታች እንጅ ወገንተኝነት ያለበት ከሆነ የከሸፈ ይሆናል።

ደግሞ ሌላ ምሳሌ ማንሳት እንችላለን፤ በገዥው ፓርቲ እና በተቃዋሚዎቹ መካከል የጦፈ ክርክር የተነሳ እንዲሆን በሕዝብ እንዲወደድ ብሎ ገዥውን የተቃወመ እንደሆነ ወይም ኪሴ እንዲደልብ ብሎ ገዥውን የደገፈ እንደሆነ ምሁርነቱ እምብዛም ነው፤ አድሏዊ ይሆናል። ከዚህ ‹‹ምሁር›› የሚጠበቀው በሁለት ተሟጋቾች መሃል መቆም ያለባትን ‹እውነት› በአመክንዮ ተንትኖ ማሳየት እና ይህችን እውነት ሁሉም እንዲያውቋት ማድረግ ነው።

ይሄንን ማድረግ የቻለ እንደሆነ እውነት ሁሌም ከፊት እንድትቆም ማድረግ ይችላል። ተከራካሪዎች ጊዜያዊያን ናቸው። ዛሬ የተከራከሩቱ ብቻ ሳይሆን በአፈሙዝ የተፈላለጉቱ ነገን አይኖሩም፤ ሁለቱም ያልፋሉ። ሀገር፣ ሕዝብና እውነት ግን ይቀጥላሉ። ያችን እውነት የሚያስተዋውቃት፣ የሚጠብቃትና የሚያስጠብቃት ደግሞ ምሁሩ ነው።

ስለዚህ ምሁራን ከእውነት ጋር እንዲቆሙ ሁሌም ይጠየቃሉ። ከእውነት ጋር መቆም የቻሉት ምሁራን አናሳ መሆናቸው ሀገራችን ላለፉት ዘመናት የመጣችበትን አቀበትና ቁልቁለት አልፋ አሁን ያለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ የወደቀች እንድትሆን በር ከፍቷል። በዚህ ችግር አስተዋጽኦ ካላቸው ወገኖች ምሁሩ ስሙ ይነሳል። ምክንያቱም ከእውነት ጋር አልቆመም ነበርና፤ ቆሞማ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለንበት ዘርፈ ብዙ ችግር ቢያንሰ ዘርፈ ጥቂት በሆነ ነበር።

አሁንም ምሁሩ ብዙ ድርሻ ያለበት ይመስላል። ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ቃላትን የሚያሰማምር ከሆነ ሐሳዊ ምሁር መሆኑን ይወቀው። ትናንት ከገዥው ፓርቲ ጋር እንደቆመው ሁሉ ዛሬም ከገዥው ፓርቲ ጎን ልለጠፍ ያለም እንደሆነ ሐሳዊ ምሁር ነው። ትናንት ገንዘብ ለማካማበት ዝምታን በመምረጡ ሀገር እንዲህ ያለ ችግር ውስጥ መዘፈቋን ሳይረዳ ዛሬም ባለህበት ሂድን የሚያዜም ካለ ከምሁርነት ይልቅ ለድንቁርና የቀረበ መሆኑን ይወቀው። በዚህና በዚያ ብሎ ሀገርን ማስቀደም ድርሻው መሆኑን ያልተረዳ እንደሆነ አሁንም ‹‹ምሁርነት›› ከችግር ያልተላቀቀ ነው!

ደሳለኝ ሥዩም

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You