የሳይበር ምኅዳሩን ያለ ስጋትና ያለ ጥቃት!

የሳይበር ምኅዳር ሁሉን አቀፍ መሆን ለዓለማችን ብሎም ሀገራችን አያሌ መልካም እድሎችን ይዞ የመምጣቱን ያህል በተቃራኒው ደግሞ ለሀገራት ሉዓላዊነትና ለሕዝቦች ደኅንነት የስጋት ምንጭ እየሆነ እንደመጣ ይነገራል። ዓለም በሳይበር ምኅዳር ምክንያት አንድ እየሆነችበት ባለችበት በዚህ ጊዜ ቴክኖሎጂው የሚሰጠውን መልካም እድል ተጠቅሞ የስጋት ምንጮችን ለመቀነስ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤን መያዝ እንደሚያሻ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎች አጥብቀው ያሳስባሉ።

ባለፈው ጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ተኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ “የሳይበር ደኅንነት የጋራ ኃላፊነት ነው! እንወቅ! እንጠንቀቅ!” በሚል መሪ ቃል የተከበረው የሳይበር ደኅንነት ዋነኛ ዓላማም ግንዛቤን ማስረጽ ነበር። ለመሆኑ “የሳይበር ምኅዳር” ምን ማለት ነው? የሳይበር ጥቃት ሲባልስ? ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ የሚባሉት የተለዩ አካላትስ እነማን ናቸው? ግለሰቦችስ የሳይበር ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል ወይ? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሣት ዘመን መጽሔት በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይበር ደኅንነት ንቃተ ኅሊናና ባሕል ግንባታ ማዕከል ኃላፊ አቶ ቢኒያም ማስረሻን፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ቡድን መሪ እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የሲስኮ ኔትዎርኪንግ አካዳሚ በመምህርነትና በሥራ አስኪያጅነት እያገለገሉ የሚገኙትን አቶ ዘሪሁን በፍቃዱንና በሳይበር ደኅንነት ላይ የሚሠራው የThe Secured Tech company መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ኢንጂነር ፋሪስ ሙሀመድን አነጋግራለች።

የሳይበር ምኅዳር ምንነት

ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱም ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት የሳይበር ምኅዳር የሰው ልጅ የእርስ በእርስ ግንኙነቱ ማደግ፣ የመሠረተ ልማት መስፋፋትና የመረጃ ፍላጎት የፈጠረው ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ብዙዎች እንደሚያስቡት ትላልቅ ተቋማትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ማንኛውም ከስልክ ጀምሮ ወደ ኢንተርኔት ሥርዓት የሚገባውን እያንዳንዱን ግለሰብ ጭምር የሚመለከት ነው። ማንኛውም በኮምፒውተር ወይም በኢንተርኔት የሚያልፍ እንቅስቃሴ በሳይበር ምኅዳር ውስጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ኮምፒውተሮችን፣ ስልኮችንና ሌሎች መሰል መሣሪያዎችን የሚያገናኘው ምናባዊ ድር (web) ደግሞ ሳይበር (Cyber) ይሰኛል።

የሳይበር ደኅንነት መጠበቂያ መሠረቶች

እንደ አቶ ቢኒያም ገለጻ የመረጃ ምስጢራዊነት፣ ምሉዕነትና ተደራሽነት ሦስቱ የሳይበር ደኅንነት መጠበቂያ መሠረታዊ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ የመረጃ ምስጢራዊነት (Confidentiality) የምንለው አንድን መረጃ ሊያየው ከሚገባው ሰው ውጪ እንዳያየው መጠበቅ ወይም ከሌላ ፈቃድ ከሌለው አካል ወይም በርባሪ መሰወርን የሚገልጽ ነው። ይህም ምስጢራዊውን መረጃ ሌላ ያልተፈቀደለት አካል እንዳያገኘውና ለሌላ ዓላማም እንዳይጠቀምበት ያደርገዋል። የመረጃ ምሉዕነት (Integrity) ስንል ደግሞ መረጃዎች ፈቃድ በሌላቸው አካላት እጅ ሳይገቡ፣ ይዘታቸው ሳይጨምር ሳይቀንስ፣ ትክክለኛነታቸውን እንደጠበቁ እንዲገኙ ማድረግ ሲሆን፣ በሦስተኛነት የተቀመጠው የመረጃ ተደራሽነት (Availability) አንድ መረጃ ወይም ዳታ በተፈለገበት ፍጥነትና ሰዓት ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ በመፍጠር ይገለጻል።

የሳይበር ጥቃት ምንነት

አቶ ዘሪሁን “የሳይበር ጥቃትን” ከዘራፊ ሽፍታ ጋር በማነጻጸር በምሳሌ ያስረዳሉ፡- እርሳቸው እንዳሉት፣ በድሮ ጊዜ አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ ሲንቀሳቀስ ዘራፊ ሽፍቶች ያስቸግሩት፤ የያዘውንም ይዘርፉት እንደነበረ ሁሉ፤ በኢንተርኔት አማካኝነት ካለንበት ቦታ ተነሥተን እንደ ጎግል፣ ዩቲዩብና ጂሜይል ያሉ በርካታ ሰርቨሮችን ለማግኘት በምንሞክርበት ወይም የሳይበር ምኅዳር ውስጥ በምንገባበት ጊዜ በመሐል በመረጃ ጠላፊዎች መረጃ ሊሰረቅብን ይችላል። ከመረጃ ስርቆትም ባለፈ ጠላፊዎቹ የእኛን መልእክት ይዘት በመቀየር፣ እኛን መስለው የመረጃ ልውውጡን ለተለያየ ዓላማ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ይህ ዓይነቱን ስርቆት የሳይበር ጥቃት ብለን እንጠራዋለን።

የሳይበር ጥቃት ሲባል የሳይበር ወንጀለኞች የግለሰብን ወይም የድርጅትን ኮምፒውተር ወይም ሲስተም ሰብረው በመግባት የድርጅቱን፣ የባለድርሻ አካላትን አሊያም የሠራተኛውን የግል መረጃ ለተለያዩ ጥቅሞች የሚያውሉበት ሁኔታ ነው ያሉን ደግሞ ኢንጂነር ፋሪስ ናቸው። ኢንጂነሩ የሳይበር ጥቃት ብዙ ዓይነት መልክ እንዳለውም ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ ትላልቅ ተቋማትን ዒላማ አድርጎ ገንዘብ ለመስረቅ ወይም የፖለቲካ አጀንዳን ለማስፈጸምና የፖለቲካ ኪሳራን ለማድረስ ዓላማ ከሚደረገው የሳይበር ጥቃት በተጨማሪ፣ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ የፌስ ቡክ አድራሻው የይለፍ ቃል ተሰርቆ ከእርሱ እውቅና ውጪ በፌስቡክ ገጹ ላይ ፎቶ አሊያም ሌላ እርሱን የማይመለከት መልእክት ቢለጠፍበት ይህንን የሳይበር ጥቃት እንለዋለን።

ሌላው ከሳይበር ጥቃት ጋር ተያያዥነት ያለው “የሳይበር ትንኮሳ” ሲሆን፣ ይህም አብዛኛውን ጊዜ አብረው የቆዩ ባልና ሚስት ወይም ፍቅረኛሞች ሲጣሉ በተለይም በሴቷ ስም የፌስ ቡክ አካውንት በመክፈት በሰላሙ ጊዜ እጃቸው የገቡ ፎቶዎችን በመጠቀም የሚደረግ ስም የማጥፋትና የማበላሸት ተግባር ወይም እንደ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራምና ቴሌግራም የመሳሰሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም አሉታዊና ሐሰተኛ ይዘት ያላቸውን መልእክቶች መላክና መለጠፍ፣ የግልና ሚስጥራዊ መረጃዎችን ሆን ብሎ የሰዎችን ሥነ ልቡና ለመጉዳት ማሰራጨት ነው።

ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ አካላትና አጋላጭ ሁኔታዎች

አቶ ቢኒያም እንዳሉት፣ ሌሎች ባለሙያዎችም እንደሚጋሩት ማንኛውም ወደ ሳይበር ምኅዳሩ የገባ ግለሰብም ሆነ ተቋም ወይም ከስልክ ጀምሮ ኮምፒውተርና ውስብስብ የሆኑ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም ሁሉ በየትኛውም ጊዜ ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ነው። አንዳንድ ሰው ከግንዛቤ ማነስ እኔ ምንም የምደብቀው ነገር የለም፤ የማዘዋውረው ገንዘብ የለኝም ምን አስጨነቀኝ በሚል የተሳሳተ አረዳድ ይዘናጋል፤ ነገር ግን፣ ግለሰቦችም ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ ከመሆናቸውም ባሻገር በእነርሱ የይለፍ ቃል፣ የስልክና የኮምፒውተር አጠቃቀም ግዴለሽነት የተነሣ የሳይበር አጥቂዎች የእነዚህን ሰዎች መሣሪያና አድራሻ፣ ሌሎች ሰዎችንና ኮምፒውተሮችን ለማጥቃት መግቢያ አድርገው ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ለወንጀለኞች መሣሪያ ከመሆንም ባሻገር የሕግ ተጠያቂነትንም ያስከትላል።

መንግሥታት፣ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች፣ የተደራጁ ወንጀለኞችና ከተቋም የተሰናበቱና በሥራ ላይ ያሉ የውስጥ ሠራተኞች ዋነኞቹ የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ አብዛኛው የሳይበር ጥቃት ገንዘብን ዒላማ ባደረጉ የተደራጁ የሳይበር ጥቃት አድራሾች የሚደርስ ነው። እነዚህ ቡድኖች ለዓላማቸው መሳካት ገንዘብ ላይ የሚሠሩ ተቋማትንና የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ግለሰቦችን ዒላማ ያደርጋሉ። የአንድ ተቋም የቀደሙም ይሁን የውስጥ ሠራተኞች ለበቀል ዓላማ የተቋሙን መረጃ አሳልፎ በመስጠት ለሳይበር ጥቃት ሊያጋልጡ ይችላሉ። ሌላውና በዓለም ሀገራት በብዛት የሚፈፀመው የሳይበር ጥቃት የፖለቲካ ዓላማ ያለው ነው። ይህ በአብዛኛው በጦርነት ወቅት የሚፈፀምና እንደ ቴሌ፣ መብራት ኃይል፣ የትራንስፖርት አውታር ያሉ ቁልፍ የሀገራት መሠረተ ልማቶች ላይ የሚያነጣጥር የሳይበር ጥቃት ነው።

ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ የአንድን ሀገር የፈጠራ ሥራ ለመሰለልና ለመስረቅ፣ የኮምፒውተር ሥርዓትን ለማውደም፣ የፖለቲካ አቋምንና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ለማራመድና የአንድ ተቋም የኮምፒውተር ኔትወርክ እንዳይሠራ በማድረግ እገሌን አጠቃን ለማለት ወይም ዝና ማትረፍን ዓላማ በማድረግ የሳይበር ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችልም አቶ ቢንያም ይገልጻሉ።

አቶ ዘሪሁን በበኩላቸው፣ ተንቀሳቃሽ ስልካችን ወይም ኮምፒውተራችን በእጃችን ላይ እያለ እኛ በማናውቀው ሁኔታ ሌሎች በሚጠቀሙበት ጊዜ ሳይበር ጥቃት ደረሰ ማለት ነው ይላሉ። በርካታ ለሳይበር ጥቃት አጋላጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም በቀላሉ ሊያጋልጡን የሚችሉ ናቸው ያሏቸውንም በዝርዝር ያስረዳሉ። ቀዳሚውና ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው ያሉት ለሳይበር ጥቃት አጋላጭ ሁኔታ ስለ ሳይበር ምኅዳር በቂ ግንዛቤን አለመያዝ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከስልካችንና ኮምፒውተሮቻችን ጀምሮ በኢንተርኔት አማካኝነት ለምንጠቀማቸውን እንደ ኢሜይል፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም የመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛዎች ጠንካራ የይለፍ ቃል አለመጠቀምና እነዚህን መገናኛዎች በስልኮቻችን አሊያም በኮምፒውተሮቻችን ከፍተን ከተጠቀምን በኋላ በተገቢ ሁኔታ ዘግተን አለመውጣት፣ ለሳይበር አጥቂዎች ቀላልና ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ያስረዳሉ።

ኢንጂነር ፋሪስ ደግሞ፣ የሚከተሉትን በመተግበር ራስን ብሎም ሌሎችን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንደሚቻል ያስረዳሉ። ልክ እንደ አቶ ዘሪሁን ሁሉ ሳይበርን በተመለከተ ተገቢ ግንዛቤን መያዝ ቀዳሚው ተግባር እንደሆነ የተናገሩት ኢንጂነሩ ጠንካራ የይለፍ ቃሎችን በመጠቀም እንዲሁም የይለፍ ቃልን በየጊዜው በመቀያየር፣ ደኅንነታቸው ያልተጠበቁ ድረ ገፆችን ከመጎብኘት በመቆጠብ፣ አድራሻቸው በግልጽ ከማይታወቁ አካውንቶች የሚላኩ ሊንኮችና አባሪዎችን (Attachments) ባለመክፈትና የምንጠቀማቸውን ሶፍትዌሮች በየጊዜው በማደስ (update) የምንጠቀማቸውን የመገናኛ መሣሪያዎች ከስርቆት በመጠበቅ ራስን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንደሚቻል ያስገነዝባሉ።

የሳይበር ጥቃት ጉዳት እስከምን ይደርሳል?

በአሜሪካ በዓመት 60 ከመቶ የሚሆኑ ትንንሽ ድርጅቶች በሳይበር ወንጀል ምክንያት ከሥራ ውጪ እንደሚሆኑ የጠቀሱት ኢንጂነር ፋሪስ አንድ ድርጅት ላይ የሳይበር ጥቃት ደረሰ ቢባል ደንበኞች በድርጅቱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲወርድ ከማድረግ ጀምሮ ከፍተኛ የፋይናንስ ኪሳራን እንደሚያስከትል ይናገራሉ።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፣ ሀገርን የሚያንቀሳቅሱ ከፍተኛ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት የሚያስከትለው ሀገራዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ በሀገራችን ቁልፍ የሚባሉ ባንክ፣ ቴሌና የኃይል ማመንጫ ዓይነት መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ቢደርስ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ያስከትላሉ፤ ቀውሱ የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳም ጭምር ይሆናል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢራን ኒውክሊየር ማበልጸጊያ የኮምፒውተር መረጃ ላይ እስራኤል ያደረሰችውን የሳይበር ጥቃት በማሳያነት የጠቀሱት አቶ ቢኒያም፣ የኮምፒውተር መረጃዎችን አጥፊ ሶፍትዌር በፍላሽ ላይ በማዘጋጀት ብቻ፣ ፍላሹ ኮምፒውተር ላይ በሚሰካበት ጊዜ የኮምፒውተሮችን መረጃ እንዲያጠፋ በማድረግ ኢራን ለ10 ዓመታት ስትሠራበት የነበረውን የኒውክሊየር ማበልፀጊያ ሥርዓት እንዳጠፋና 10 ዓመታትን ወደኋላ እንደመለሳት ይናገራሉ። አያይዘውም ጥቃቱ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሥነ ልቡና ኪሳራን እንዳስከተለ ያክላሉ። በቅርቡም በአሜሪካ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለታቸው ላይ የደረሰውን የሳይበር ጥቃት ያነሡት አቶ ቢኒያም፣ የኮምፒውተሮች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም በማድረግ በተፈጸመው በዚህ የሳይበር ጥቃት፣ በአሜሪካ በሁሉም ከተሞች የነዳጅ አቅርቦትን እንዲቆም እንዳደረገውና ለሁለት ቀናት ያህል የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እንደረበሸው ያወሳሉ።

በሀገራችንም በርካታ የመሠረተ ልማት ተቋማቶቻችን ላይ የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶች ዓላማቸውን አሳክተው ቢሆንና ባይከሽፉ ኖሮ ከፍተኛ ሀገራዊ ቀውሶችን ሊያስከትሉብን እንደነበርም አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።

አቶ ዘሪሁንም፣ የሳይበር ጥቃት በቀላሉ አንድ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ ወደ ሚፈለገው ሰው ሊልከው የነበረው ገንዘብ በመሐል ተጠልፎ ወደ ሌላ ሰው የባንክ አካውንት እንዲገባ ቢደረግበትና ቢሰረቅ፤ ላኪው እንደላከ ነው የሚያውቀው፣ ተቀባዩ ጋር ግን የደረሰ ነገር የለም፤ እንዲህ ዓይነት የሳይበር ጥቃት ሊያስከትል ከሚችለው

 ግለሰባዊና ማኅበራዊ ቀውስ ጀምሮ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ ተቋማት ቢጠቁ የአንድ ሀገርን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚከት ቀውስን ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለዋል። አያይዘውም አሁን አሁን በሀገራት መካከል ያለው ጦርነት እንደ ድሮው በመሣሪያና በጦር ሳይሆን በአብዛኛው በሳይበር አማካኝነት በመሆኑ በሀገር ደረጃ ራሳችንን ከሳይበር ጦርነት (Ciber War) ለመጠበቅ ወይም ለመመከት ዝግጁ መሆን እንደሚገባን ያሳስባሉ።

የሳይበር ደኅንነትን እንዴት መጠበቅ እንችላለን?

የሳይበር ደኅንነትን መጠበቅ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ድርጅት ብቻ ኃላፊነት እንዳልሆነ ኢንጂነር ፋሪስ አስምረው ይናገራሉ። አያይዘውም፣ ምግብ በየዕለቱ እንደምንበላው ሁሉ ወይም ዛሬ ስለበላን ለነገ አያስፈልገንም እንደማንለው ሁሉ የሳይበር ምኅዳር መልኩ በየዕለቱ የሚቀያየር እንደመሆኑ ደኅንነቱን የመጠበቁም ተግባር አንዴ ተሠርቶ የሚያልቅ ሳይሆን በየዕለቱ የሚከወን ሂደት መሆኑን ማወቅ ያሻል ይላሉ።

እንደ ኢንጂነር ፋሪስ ገለጻ፣ ከስልክ ጀምሮ የተለያዩ የኢንተርኔት እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ግለሰብም ሆነ ተቋም ራሱን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከል ጥልቅ የሆነ መከላከያ ያስፈልገዋል። ይህ ማለት፣ አንድ ሰው የቤቱን ደኅንነት ለመጠበቅ የግቢ አጥር፣ የግቢውን በር፣ የመኖሪያ ቤቱን በር ይዘጋል። ከዚያ መስኮቱን ይዘጋል፤ የተለየ እቃ ያለበት ክፍልም ካለ በደንብ አድርጎ ይዘጋል። ልክ እንዲሁ ተገቢና ሊገመቱ የማይችሉ የይለፍ ቃላትን በመጠቀም መረጃዎቻችንን በሚገባ በመደበቅ፣ ለስርቆትና ለጠለፋ እንዳይመቹ በማድረግ የሳይበር ጥቃትን መከላከልና ማክሸፍ ይቻላል።

ሁሉም ሰው ራሱን ከየትኛውም ወንጀል ለመከላከል ጥረት እንደሚያደርገው ወይም ራሳችንን ከበሽታ ለመጠበቅ የምናደርጋቸው መከላከያዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ሁሉም አካል ራሱን ከሳይበር ጥቃት መከላከል አለበት ያሉን ደግሞ አቶ ቢኒያም ናቸው። ከ40 ከመቶ እስከ 60 ከመቶ ያህሉ የሳይበር ጥቃት በኢሜይል አማካኝነት የሚደርስ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ቢኒያም በቀላሉ የኢሜይል የይለፍ ቃልን ጠንካራ በማድረግና ኢሜይላችንን ከተጠቀምን በኋላ በመዝጋት ወይም ክፍት ባለመተው ራሳችንን ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ እንደምንችል ያስረዳሉ። እንደ እርሳቸው ሀሳብ፣ ሁሉም ሰው ግንዛቤው ኖሮት ራሱን ካልጠበቀ፣ ተቋማትም በከፍተኛ ንቃት ኃላፊነት ወስደው ራሳቸውን ካልጠበቁ የሳይበር ጥቃትን በአንድ ተቋም ብቻ መከላከል በፍጹም የሚቻል አይደለም። ለዚህ ደግሞ ተቋማት የየራሳቸው የሳይበር ጥቃትን መከላከል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሊታጠቁ፣ ለሠራተኞቻቸውም ምን ዓይነት የሳይበር ጥቃት ሊደርስና እንዴት ያለ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ወቅቱን የጠበቀ ስልጠና ሊሰጡ ይገባል። በዚህ መልኩ ተቋማትም ግለሰቦችም የየራሳቸውን ኃላፊነት ሲወጡ የሳይበር ደኅንነት የጋራ ኃላፊነት ይሆናል።

የሳይበር ወንጀለኞች አንድ ቀዳዳ ብቻ ነው የሚያስፈልጋቸው ያሉት ኢንጂነር ፋሪስ፣ እኛ ግን ራሳችንን ከሳይበር ወንጀለኞች ለመጠበቅ መቶ ያህሉን ቀዳዳ መሸፈን እንደሚጠበቅብን ያሳስባሉ። ሁሉም የኢንተርኔትና የማኅበራዊ መገናኛዎችን የሚጠቀም ሰው ለአንዱ አካውንት የተጠቀመውን የይለፍ ቃል ለሌላው ባለመጠቀም፤ ለምሳሌ ለፌስ ቡክ የተጠቀመውን የይለፍ ቃል ለኢሜይል አካውንቱና ለሌሎችም ባለመጠቀም በትንሹ ራሱን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንደሚችል ያስረዳሉ።

አቶ ዘሪሁንም ልክ እንደ ሌሎቹ ባለሙያዎች ሁሉ ትናንሽ መዘናጋቶች ትላልቅ ችግሮችን ይዘው ሊመጡ ይችላሉና ምንጊዜም ንቁ ልንሆን እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ራሳችንን ከሳይበር ጥቃት ስንጠብቅ ከራሳችን አልፈን ሌሎችን ብሎም የተቋማችንን መረጃና ገጽ ከሳይበር ጥቃት እየጠበቅን እንደሆነም ልናውቅ ይገባልም ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ምን እያከናወነ ነው?

ኤጀንሲው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን የማስተባበርና ንቃተ ኅሊናንም የማጎልበት ኃላፊነት አለበት ያሉት አቶ ቢኒያም፣ ከዚህ አንጻር ሰፊ ሥራ እየሠራ እንዳለም ይናገራሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ ኤጀንሲው ከሳይበር ጥቃት አኳያ ተቋማት ያሉበትን ቁመና እንዲያውቁት፣ እንዴትስ መከላከል አለባቸው የሚለውንም እንዲረዱት ሥልጠና የመስጠት፣ ቴክኖሎጂን የማካተት፣ የአሠራር ሥርዓት ፖሊሲዎችን የማማከርና ጥቃት ከደረሰም በኋላ በ933 የጥሪ ማዕከል በሚደርሰው ሪፖርት መሠረት ጥቃት በተሰነዘረበት ሥፍራ በመገኘት ችግሩን በፍጥነት ችግሩን የመፍታት ወይም ጥቃቱን የመመከት ሥራ ይሠራል። ይህንን የሚሠሩ ሠራተኞችም ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ 24 ሰዓት ዝግጁ ሆነው ይጠባበቃሉ። ይህ ለሁሉም አካል የሚሰጥ አገልግሎት ቢሆንም በይበልጥ ጥቃት ቢደርስባቸው ሀገር ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ቁልፍ የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ዓይኑን ሳይነቅል ይሠራል።

ኤጀንሲው 2008 ላይ 214 ያህል በትላልቅ ተቋማት ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን ማክሸፍ ችሏል፣ በ2009፣ 479 ጥቃቶችን መከላከል ችሏል፣ ይህም የጥቃቱ መጠን በአንድ ዓመት ውስጥ ከእጥፍ በላይ እንደጨመረ ያሳያል፤ በ2010 ዓ.ም 576 ጥቃቶችን ማክሸፍ ችሏል፤ ይህ ማለት ወደ 35 ከመቶ ያህል ጭማሪ አለው። በ2011 ዓ.ም 791 ጥቃቶች ከሽፈዋል፣ በ2012 ዓ.ም 1087 ጥቃቶችን ማክሸፍ ችሏል። ባሳለፍነው 2013 ዓ.ም ደግሞ 2800 እንደ ሀገር ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን ማክሸፍ ችሏል። ይህ መረጃ የሳይበር ጥቃት በምን ያህል ፍጥነት እየጨመረ እንደመጣ ያሳየናል ያሉት አቶ ቢኒያም ጥቃቱ እየበዛ የመምጣቱን ያህል የተቋማችን ጥቃትን የመመከት ዝግጁነትና አቅምም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በአጠቃላይ ሲታይ ለሀገር እድገትና ብልጽግና የሳይበሩ ምኅዳር መስፋፋት ወሳኝ ሆኖ ሳለ በብዙ ፈተናዎች የተከበበ መሆኑ የታወቀ ነው። በመሆኑም ጥቅሙን በተረዳንበት ልክ ከሚመጡበት ማሰናከያዎች የመጠበቅ ተግባሩም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መረዳት አስፈላጊ ይሆናል።

 ዮርዳኖስ ፍቅሩ

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You