ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን ተገዳዳሪ፣ ተሻሚ፣ ተቀናቃኝ አያጣውም። ሁሌ መደላደል የለም፤ ጎንታይና ተጎንታይ ይኖራል። ለተጎንታይም ሆነ ለጎንታይ ደግሞ ተከታይ ተጽዕኖ መፍጠሪያ ኃይል አላቸው። ሁሉም በየደጁ ኃያል ነው። ወይም በሶሻሊስቶች አባባል ሁሉም በየመደቡ ኃይል ያደራጃል። እነዚህ የመገዳደር አካሄዶች የሚፈቱባቸው መንገዶችም ልዩ ልዩ ሆነው ታይተዋል። አንዳንዱ በኃይል ተገዳዳሪውን ከነወገኑ አጥፍቶ ወይም ረግጦ ለጊዜያት የመግዛት አካሄድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰላማዊ በሚባለው መንገድ ልዩ ልዩ ማቻቻያ ጥበቦችን ተጠቅሞ ማለዘብ ነው። ከግጭት፣ ከፍጭት፣ ከጥፋት፣ ከምሬት አውጥቶ ተቻችሎ ለመዝለቅ ደግሞ እንደየመንግሥቱ ባሕርይ ችግር መፍቻ ጥበቦች ነበሩ።
መንግሥታት ንጉሣዊ/ዘውዳዊ/ ሥርዓት መልክ ይዘው ሊገኙ ይችላሉ። መንግሥታት ሪፐብሊክ ሆነው ሊሠሩ ይችላሉ። በፕሬዚዳንቶች፣ በጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚመሩ መንግሥታት አሉ። እንዲሁ በአንድ ፓርቲ የሚመሩ እና መድብለ ፓርቲ ሥርዓት የሚከተሉም መንግሥታት ይኖራሉ። እነዚህን መሰል ቅርጽ ይዘው በሚሄዱት የትኞቹም መንግሥታት ግን ገዢውን የሚገዳደር ኃይል ይጠፋል ማለት አይቻልም።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ረጅሙን ጊዜ የወሰደው የዘውዳዊ ሥርዓት ነበር። ዘውዳዊ ሥርዓት መሆኑ ግን ተገዳዳሪ እንዳይበቅልበት ሊከለክል አይችልም። ስለዚህ የራሱ ሥልጣን ማጋሪያ መንገድ ይኖረዋል። ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡን የባህልና ቱሪዝም ስተራቴጂ ኢክስፐርትና በታሪክና ቋንቋ ምሁር የሆኑት ዶክተር ታደለ ፈንታው ‹‹የዘውድ ሥርዓት ሥልጣን መቆናጠጫ ዋነኛ መስፈርቱ ደም ነው። ከንጉሣዊው ዘር የመወለድ ነገር ዙፋን የመቆናጠጥ ቁልፍ መንገድ ነው።›› ይላሉ። በእርግጥም የኢትዮጵያ የዘውዳዊ ሥርዓት መወሰኛ ዋናው ሰነድ ክብረ ነገሥት ሆኖ ቆይቷል። ክብረ ነገሥት በዙፋን የሚቀመጠው ሰው ከእስራኤሉ ንጉሥ ከሰሎሞን እና ከንግሥተ ሳባ የሚወለደው የቀዳማዊ ምኒልክ ዘር የዙፋኑ ወራሽ መሆኑን ይወስናል።
ክብረ ነገሥት በምዕራፍ 87 ላይ ንግሥት ማክዳ ስላደረገችው ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ ‹‹መኳንንቶቹንም ‹በኢትዮጵያ መንግሥት ዙፋን ላይ የዳዊት ዘር ከሆነው ከንጉሥ ሰሎሞን ወንድ ልጅ ካልሆነ በቀር ለዘላለሙ ሴቶችን እንዳታነግሡ ማሉ› አለቻቸው። ሁሉም የቤተ መንግሥቱ ታላላቆችና መኳንንቱ አማካሪዎችና ሹማምንቱ ሁሉ ማሉ። መንግሥቱንም አደሱ።…›› በዚህም መሠረት በትረ ሥልጣን የሚገባቸው ሰዎች ማንነት የንጉሥ ዳዊት የዘር ግንድ ብቻ ነው።
ክብረ ነገሥት እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ድረስ ለኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ያህል ያገለግል ነበር። መጽሐፉ ተፈላጊና ለሚነግሡ ሰዎች የሥልጣን ዋስትና መስጫ መሆኑን ለመረዳት ዐፄ ዮሐንስ ተዘርፎ ጠፍቶ የሄደ ክብረ ነገሥት ከእንግሊዝ ለማስመለስ ያደረጉትን ጥረት ማስተዋል ይቻላል።
ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ (1864 ዓ.ም – 1881 ዓ.ም) ለንግሥት ቪክቶሪያ በነሐሴ 8 ቀን 1864 ዓ.ም በላኩት ደብዳቤ የእንግሊዝ ጦር ዐፄ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ በምርኮ ከመቅደላ ከተወሰዱት ንብረቶች መካከል ክብረ ነገሥት እንዲመለስላቸው ሲጠይቁ ‹‹… ደግሞ ክብረ ነገሥት አለ፤ አብሮ ሂዷል። የአገሬ ሹማምንቱን የአብያተ ክርስቲያናትን ስሪት የሚናገር ነው፤ ባገሬ ተፋልሶ ሁኖብኛል፤ አሁንም ሁለቱን ክብረ ነገሥቱንና ኩራተ ርእሱን ቢሰዱልኝ እወዳለሁ፤ ካለበት ሁሉ አስፈልገው። …›› በማለት ደብዳቤ መጻፋቸው፤ የክብረ ነገሥትን አስፈላጊነትና ምን ያህል ጠቀሜታ እንደነበረው የሚያሳይ ነው። /ሕገ መንግሥት በኢትዮጵያ፣ቃለዓብ ታደሰ ሥጋቱ፣2009 ዓ.ም/
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ዘመናዊ የሚባል ሕገ መንግሥት ተዘጋጀ በተባለበት ጊዜ ይኸው የክብረ ነገሥት የሥልጣን ማቆናጠጫ ሐሳብ የወጣው አዲስ ሕገ መንግሥት መነሻ ነበር። በ1923 ዓ.ም የወጣው ሕገ መንግሥት ምዕራፍ አንድ ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ተወላጅነትና ስለ ዘውዱ አወራረስ ሲናገር በመጀመሪያው አንቀጽ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዙፋንና ዘውድ ከኢየሩሳሌም ንጉሥ ከሰሎሞንና ንግሥተ ሣባ ከተባለችው ከኢትዮጵያ ንግሥት ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ተያይዞ ለመጣው ለንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘር ሊተላለፍ በሕግ ተወስኗል።›› ይላል።
በ1948 ዓ.ም ተሻሽሎም ሲዘጋጅ በአንቀጽ ሁለት እና አራት ያሉት ይዘቶች የሚከተለውን የሚሉ ነበሩ።‹‹ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት ከኢትዮጵያ ንግሥት ከንግሥተ ሳባና ከኢየሩሳሌም ንጉሥ ከሰሎሞን ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ ነገድ ሳያቋርጥ ተያይዞ ከመጣው ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘር ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትውልድ ሳይወጣ ምንጊዜም ይኖራል።››
‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ከነጋሢ ዘር በመሆኑና ቅብዐ መንግሥት በመቀባቱ ክብሩ የማይቀነስ፣ ማዕረጉ የማይገሰስ፣ ሥልጣኑ የማይደፈር ሆኖ በቆየውም ልማድ በአዲሱም ሕግ በሚገባው ክብር ሁሉ ይከበራል። ክብሩንም ለመንካት በድፍረት የሚነሣ ማንም ሰው በሕግ እንዲቀጣ ተወስኗል።››
ይህ የሚያመለክተው ለረጅም ዘመናት የሥልጣን ምንጭ የሆነው ደም/ከነገሥታት ዘር መወለድ ነው። ይህ ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ በነገሥታት ዘመን የነበሩ የገዢዎቹ ተገዳዳሪዎች ተቀናቃኝነታቸውን አንዲያለዝቡና የሥልጣን ተካፋይነት እንዲሰማቸው የሚደረግብት መንገድ የተቃውሞ መሪ የሆነው ሽፍታ፣ መስፍን፣ መኰንን… በጋብቻ ከትውልዱ እንዲቀላቀል በማድረግ ነበር።
ሄራን ሠረቀብርሃን የተባሉ ጸሐፊ በዓለም አቀፉ የአፍሪካ የታሪክ ጥናት መጽሔት ላይ Marriage and politics in the Nineteenth Century Ethiopia በሚል ርዕስ በጻፉት ጥናት የፖለቲካ ጋብቻ ሁነኛ ተቃዋሚዎችን ሥልጣን ማጋሪያ ሆኖ ሲያገልግል የቆየ ነው። ከጥንት የነበረውን ትተን በቅርብ ስለነበረው እናውሳ። ዐጼ ምኒልክ ልጅ ኢያሱን አልጋ ወራሽ አድርገው ሲናዘዙ ሥልጣኑን ለማደላደል ግን ከትግሬ ሰዎች፣ ከትግሬ መሳፍንት ጋር ያላቸውን ፍትጊያ መፍታት ስለሚያስፈልግ ኢያሱ የትግራዩን የራስ መንገሻ ዮሐንስን የሰባት ዓመት ሕፃን ልጅ ሮማነወርቅን እንዲያገባ ተደርጎ ነበር። የፖለቲካ ጋብቻ ሁኔታ እቴጌ ጣይቱን የዚህ አካሄድ ቀንደኛ ፈጻሚ ሆነው ተስለው እናገኛቸዋለን።
ፕሮፌሰር ባሕሩ በመጽሐፋቸው ‹‹ሮማነወርቅ ለጣይቱም ዝምድና ስለነበራት ጋብቻው የንግሥቲቱንም ፍላጎት ለማርካት ተብሎ ሳይሆን አይቀርም። ›› /ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 126/ ብለዋል። ‹‹የፖለቲካ ጋብቻ ለኢትዮጵያ እንግዳ ነገር ባይሆንም እንደ ጣይቱ ግን ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰው ሰው የለም ተብሎ ይታመናል። እንዲህ ካመቻቸቻቸው ጋብቻዎች ምናልባት ዋነኛው የወንድሟ የራስ ወሌ ብጡል ልጅ የሆነው የራስ ጉግሳ ወሌና የዘውዲቱ ምኒልክ ጋብቻ ነው። ››/ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ገጽ 127/ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ከትግሬና ከሌሎችም አካባቢዎች የፖለቲካ ልሂቃን ጋር የነበራቸውን ተገዳዳሪነት ለማለዘብ ይህንኑ መንገድ ተከትለዋል። ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በውጤቱ ብዙም ባይጠቀሙም፣ እስከ ክህደትም ድረስ የደረሰ ተገዳዳሪነት ቢያጋጥማቸውም ልዕልት ዘነበወርቅን ለትግራዩ ራስ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ድረው ነበር።
ዶክተር ታደለ ፈንታውም በጋብቻ የሚሰጠውን ሥልጣን በተመለከተ ሲያብራሩ የፖለቲካ ጋብቻ የባላንጣዎችን ጫና ለማቅለል፣ የራስን ሥልጣን የበለጠ ሰላማዊና የተደላደለ ለማድረግ ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ጠቅሟል ይላሉ። ጋብቻው በነገሥታቱ ሳይወሰን መሳፍንቱና መኳንንቱ ተፎካካሪና ተገዳዳሪዎቻቸውን በዚሁ መንገድ ለማለዘብ ያውሉት ነበር። መሠረቱ ተገዳድለው በደም የሚፈላለጉ ሰዎች ደም ለማድረቅ እንደ መፍትሔ ይጠቀሙበት ከነበረውም ባህል ጋር የተሳሰረ ይመስላል።
የፖለቲካ ሥልጣኑ ግን በደም ውርስ መሆኑ ጋብቻን ብቸኛ መፍትሔ ማድረግ ለዘውድ ሥርዓቱ እንደ ጥበብ ነበር። ከዚህ ያፈነገጠውን ግን አፈንጋጭ፣ ዘረ ቢስ፣ ወረኛ፣ ሕግ አፍራሽ ወዘተ ብሎ ማውገዙ የተለመደ ነው። አገው ሥርወ መንግሥት በሰሎሞናውያን ይነቀፍ የነበረው ይህን በክብረ ነገሥት የተቀመጠውን የሰሎሞናዊ ደም በዙፋን ከማስቀመጥ ያፈነገጠ አዲስ ሥርወ መንግሥት ሆኖ በመገኘቱ ነበር።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የጂኦፖለቲክስ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ በበኩላቸው በዳግማዊ ምኒልክና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የሚኒስቴር ቦታዎችን በዘር ሳይሆን በተጫለ መጠን ብቃት ላላቸው ሰዎች የመስጠት ልምምድ እንደነበርም መረሳት የለበትም ይላሉ። ዓላማው ግን መንግሥትን የማዘመንና የማደላደል እንጂ የማጋራት ሐሳብ መሆኑ ላይ ጥያቄ ሊነሣ እንደሚችል ያሳስባሉ።
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት መውደቅ በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ባህል ወደ ጎን የገፋ ነው። የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ለመውጣት እንደ መደራጃ ሆኖ መታየት የጀመረው ርዕዮተ ዓለም ነው። ንጉሡን ሥልጣን ያስለቀቀው ወታደሩ ኃይል ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ያቋቋመ ሲሆን፣ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም ለዜጎች ቃል ገብቶ ነበር። ይሁን እንጂ የነገሩ ሁኔታ ያላማራቸው የማኅብረሰብ ክፍሎች በተለይም የተማረው ክፍል የሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ጥያቄ በማንሣት ለጊዜው ለተደራጀው መንግሥታዊ ኃይል ጎንታይ ሆነው ወጥተዋል። እነዚህ ወገኖች በሂደት ለሥልጣን የሚያሰልፍ የፓርቲ አደረጃጀት መፍጠር ቀጥለዋል። በምሕጻረ ቃል ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኢጭአት፣ ወዝሊግ፣ ማሌሪድ የተባሉ የግራ ክንፍ ፖለቲካን የሚከተሉ ኃይሎች ወጥተዋል። የደርግ ሰዎችም ይሄንን የአደረጃጀት ሰልፍ የሚገዳደር ሌላ የፖለቲካ ኃይል ለማደራጀት ተነሥተው አብዮታዊ ሰደድ የተባለ የመለዮ ለባሹ ጓዶች መታገያ ሆኖ ተመሥርቶ ነበር። በእርግጥ የተቋቋሙት ሁሉ ድርጅቶች /ከኢሕአፓ በስተቀር/ ራሳቸውን ፓርቲ ሳይሉ ንቅናቄ፣ ሊግ፣ ትግል፣ድርጅት፣ ሰደድ እያሉ ነበር።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በመጽሐፋቸው እንዳብራሩት ሕዝቡ ሳይነቃ መሪ ፓርቲ ማቋቋም አይቻልም የሚል እምነት የነበራቸው ብዙ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ግን በርዕዮተ ዓለም የግራ ክንፍ ፖለቲከኞች መሆናቸው ከመገዳዳር፣ ከመገፋፋት አላዳናቸውም። ስለዚህ የነበረው ጥያቄ የሥልጣን ቅርምት መሆኑን ያመላክታል። ደርግ ለጊዜው ነገሮችን በመቻቻል የያዛቸው ቢመስልም ኢሕአፓ ወዲያውኑ የደርግ መንግሥት መራር ተቃዋሚ ሆኖ ወጣ። ወዝሊግ እና መኢሶን ግን የደርግ አባሪ፣ ተባባሪ ሆነው ተሰልፈው ነበር። በ1968 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ሕዝብን ለማጥቃትና ለማደረጃት ለሚደረገው ጥረት የፕሮግራሙ አስፈጻሚ አካል ሆኖ ጊዜያዊ ሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ሥራ ሲጀምር በተቋቋመው ኮሚሲዮን ውስጥ መኢሶን ሰብሳቢ እስከ መሆን ደርሶ ሌሎችንም በስፋት ያሳተፈ እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር። ነገሩ ሲጀመር አብዮቱ ዲሞክራሲያዊ መልክ የያዘ መስሎ እንዲታይና ሥልጣንን ሁሉም የሚጋራበት ሥርዓት የሚመጣ አስመስሎ ነበር።
ከኢሕአፓ በስተቀር ሌሎቹ የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ አንድ ግንባር ቀደም ፓርቲ ሊመሠረት የሚችለው ሰፊውን ሕዝብና ተራማጅ ኃይሎችን በማንቃትና በማደረጃት ነው በሚል በ1969 የሚስማሙት ቡድኖች በጋራ ኢማሌድኅን በየካቲት 1969 አቋቋሙ። ይህ ኅብረት ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ልምድ ያደረጉበት የመጀመሪያ ምዕራፍ ይመስላል። ይሁን እንጂ ይዞታው ከመጠራጠር ያልጸዳና፣ ከአደገኛ የሥልጣን ጥማት ያልራቀ ትብብር በመሆኑ ውጤት እንዳላመጣ ፕሮፌሰር ባሕሩ እንዲህ ይገልጹታል ‹‹ኢማሌድኅ እንደታሰበው የግንባር ቀደሙ ፓርቲ አዋላጅ መሆኑ ቀርቶ አባል ቡድኖቹ ለድርጅታዊ የበላይነት የሚፋለሙበት መድረክ ሆኖ አረፈው። በተለይ መኢሶን ያነሳ የነበረው የበላይነትና የመኵራራት ስሜት የሌሎቹን የተባበረ ጥላቻ አተረፈ››/ዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ገጽ 259/ ።
እነዚህ ሁኔታዎች ሄደው ሄደው ዜጎች ሰላም የሚያገኙበት፣ ሀገር የምትረጋጋበት የሥልጣን ተሳትፎ ሥርዓት ማበጀት አልቻለም። በአንድ በኩል የኢሕአፓ ትግል እየከረረ መምጣትና የሽብር ድርጊቶች መስፋፋት፣ በሌሎቹ ድርጅቶችም መካከል የነበረው መጠራጠር አድጎ እስከ መጠፋፋት መደረሱ በመጨረሻ ደርግ ብቸኛው የሥልጣን ባለቤት ሆኖ ለዓመታት እንዲቆይ አድርጎታል። ስለዚህ ሥልጣንን አጋርቶ ሀገራዊ መንግሥትን የማጽናት አካሄድ ከሽፏል።
ደርግ ሥልጣኑን የሚገዳደሩ ብቻ ሳይሆን በኃይል ከሥልጣን ለማስወገድ የተነሡ በርካታ ኃይሎች ከበቡት። በመጨረሻም ኢህአዴግ ድል ቀንቶት አዲስ አበባ ሲገባ አብረውት ታግለው የመጡና ሰላማዊ ፖለቲካን እንመርጣለን ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተሰባስበው ነበር።
ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ይሄንን ወቅት የተወሰነ ሥልጣን የማጋራት ጅምር የታየበት ነበር ይላሉ። ኢሕአዴግ በሚመራው በዚህ የሽግግር እንቅስቃሴ የታጠቁና ያልታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦችን ያቀፈ 87 ተሳታፊዎች የተሳተፉበት ምክር ቤት ተቋቁሞ ነበር። ከዚህም 32 ያህሉ ኢሕአዴግ ድርጅቶች የያዙት ሲሆኑ ከሌሎቹም ተሳታፊዎች በአመዛኙ ለኢሕአዴግ የማይጎረብጡ አካላት የያዙት ቦታ ነበር። ይህም እንደ ደርግ ሁሉ ለሽግግር ጊዜ እንዲያጅቡ ተፈልጎ የተጋበዙ ወይስ ኢሕአዴግ የምር በጊዜያዊው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ልዩ ሐሳብ ያላቸውን ወገኖች ለማካተት ቁርጠኝነት ስለነበረው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር።
ይህ ምክር ቤት ያልተመረጠውን ኢሕአዴግ የሚመራውን አስፈጻሚ ለመደገፍ ተቋቋመ። በዚህ ባልተመረጠና በጊዜያዊው መንግሥት ፕሬዚዳንት መለስና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ታምራት ላይኔ የተመረጡ የካቢኔ አባላትን ሥራ ይደግፍ ነበር። በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በተቋቋመው የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ድርጅቶች በተወከሉበት ምክር ቤት ከነበረው የተለያዩ ወገኖች የሥልጣን ተሳትፎ በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአስፈጻሚው አካል ውስጥ ተካቶ ሥራዎችን እንዲመራ መሰየሙም የተለየ ሥልጣን የማጋራት ጅምር ነበር። ከኦነግ ዶክተር ዲማ ነገዎ በማስታወቂያ ሚኒስትርነት፣ አቶ ኢብሳ ጉተማ በትምህርት ሚኒስትርነት፣ አቶ አህመድ ሁሴን በንግድ ሚኒስቴርነት፣ አቶ ዘገየ አስፋው በግብርና ሚኒስትርነት እንዲሠሩ ተመደበው ነበር። በኋላም ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በትምህርት ሚኒስቴርንት፣ ሌሎችም ኢሕአፓ ከነበሩና ለኢሕአዴግ መራር ጥላቻ ካልነበራቸው ሰዎች ለአስፈጻሚነት የታጩ ነበሩ።
የተቋቋመ የሽግግር መንግሥት በጦርነቱ የተመሰቃቀሉ ነገሮችን የማስተካከልና ሕዝብን የማረጋጋት ሥራዎችን፣ የሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሂደቶችን ሲመራ ቆይቷል። በዚህ የሥልጣን ማጋራት ተስፋ ተጥሎበት የነበረው አካሄድ ግን ዓመት እንኳን ሳይሞላው ኦነግ እንዲሰደድ በማድረግ ከሸፈ። ኦነግ እና ከሽግግር መንግሥት ምሥረታው ስምንት ወራት በኋላ የተቋቋመው መአሕድ በሂደት በክልሎች ሊቋቋሙ ለታሰቡት ምክር ቤቶች ተሳትፎ ለማድረግ ለሚደረገው ምርጫ በሚንቀሳቀሱብት ጊዜ የገጠማቸው ወከባና ጥቃት ከሂደቱ ራሳቸውን እንዲያገሉ አስገድዶ ነበር። ስለዚህም ኢሕአዴግ ሥልጣን ለማጋራት አሳይቷል የተባለው አዝማሚያ ከጅምሩ ችግር አጋጥሞታል።
በኋላም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ከጸደቀ በኋላ በተካሄዱ ምርጫዎች በፌዴራሉ ባለው የተወካዮች ምክር ቤት በሕግ አውጪነት በሕግ አስፈጻሚነት የሚገኙ የሥልጣን ቦታዎችን በማጋራት ረገድ የነበረው መንግሥት ጅምር እንጂ በጊዜው የሚያድግ ለውጦች አልታዩም። በተቻለ መጠን በተካሄዱ ተከታታይ ምርጫዎች በተወካዮች ምክር ቤት የሚሳተፉ በሕዝብ የተመረጡ በጣት የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች መሳተፍ ችለዋል። ሕግ አውጪው አንዱ የመንግሥት ሥልጣን ማጋሪያ በመሆኑ በዚህ ረገድ ከቀድሞው ሥርዓት በተሻለ ገጽታው ቢለወጥም ሥርዓቱ ለማስመሰል በሚደረግ የዲሞክራሲ ሂደት የተሞላ መሆኑን ራሱን አጋለጠ እንጂ ተስፋ አልሰጠም።
ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ በኢትዮጵያ ሥልጣን የማጋራት ልምምዶች ጠፍተው ሳይሆን ለጊዜው ያለው የሥልጣን አጋሪው ዓላማ ምንድነው የሚለው ነው። የተጀመረው የማይቀጥለው፣ የበቀለው የማያድገው በዚያ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።
ኢሕአዴግም ከሕግ አውጪው በመለስ በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ከኢሕአዴግና አጋሮቹ ከሚላቸው በራሱ ካድሬዎች ከሚዘወሩ ድርጅቶች በቀር ሌሎች ዝር የማይሉበት መዋቅር ነበር። በሕግ አውጪው አካልም ቢሆን መደረግ ያለበት ነገር እየመነመነ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ የምክር ቤት ወንበርን በመቆጣጠር ሥልጣኑን መያዙን ታይቷል።
ይህ ሁኔታ ግን ለሚመራው የመንግሥት አካልም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሆኖ አልተገኘም። ኢሕአዴግ ከራሱ መዋቅር፣ ከሕዝቡ፣ ከተቃዋሚዎች የፖለቲካ ትግል ለውጥ እንዲያመጣ ሲገደድ በ2010 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራ አዲስ አካሄድ ለመከተል ቃል ገብቶ ሥልጣን ቀጠለ። ኢሕአዴግ በዚህ የለውጥ ሂደት የግንባሩ ቁልፍ ሚና የነበረው ሕወሓት ተጽእኖውን እንዲያጣ በማድረግ ድርጅታዊ ውሕደት ለመፍጠርና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መርኅ አድርጎ ሲነሣ ሕወሓት ከድርጅቱ አኩርፎ ለመውጣትና ዋነኛው የዐቢይ አህመድ መግሥት ተገዳዳሪ ሆኖ ተገኘ። በፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ይዘው የነበሩ የሕወሓት ሰዎችና የምክር ቤት አባላትም በዐመጽ ኃላፊነታቸውን ለቀው መቀሌ ገብተዋል።
በዐቢይ አሕምድ የሚመራው መንግሥት ሌሎች ተቃዋሚዎችን ሥልጣን የማጋራት ፍላጎት እንዳለው ማሳየት የጀመረው ከ2013 ምርጫ በፊት ነበር። በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ በዳይሬክተርነትና በቦርድ አባልነት በማሳተፍ ልምምዱን ጀምሯል። ለዚህም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ፣ ለሶሕዴፓ ሊቀመንበር ለፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ለአብኑ ጣሂር ሞሐመድ፣ ለኦፌኮ ሊቀመንበር ለፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተሰጠቷቸው የነበረውን ኃላፊነት በምሳሌነት ማንሣት ይቻላል።
ይሁን እንጂ ሕወሓት ከዚያም አልፎ ሥርዓት አልበኝነትንና ሕገ ወጥነትን ግጭትን በማስፋፋት በመቀጠሉ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ወደ ጦርነት ገባ። መንግሥት በ2013 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ አድርጎም መንግሥት በማቋቋም ሥልጣንን አጋርቶ መንግሥት የማደላደል ፍላጎት እንዳለው ፍንጭ ሰጠ። ይህም ተስፋ ሲደረግ የነበረ አካሄድ ስለሆነ ሕዝቡ በተስፋ ወደ ምርጫው ተሳተፈ። የምርጫው ውጤት ውሕዱ ፓርቲ ብልጽግና የተሸነፈበት ሲሆን በተቻለ መጠን በምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚዎችም የምርጫውን ውጤት በአዎንታ የተቀበሉበት የተሻለ ምዕራፍ ሆኖ ተገኘ። በምክር ቤት አሸንፈው የገቡ ተቃዋሚዎች በሕግ አውጪው ለመሳተፍ መቻላቸው አዲስ ምዕራፍ ባይሆንም ከምርጫ በኋላ ግን አዲሱ መንግሥት የፖለቲካ ተፎካካሪዎቹን በአስፈጻሚነት በየደረጃው ለማሳተፍ የሰጠውን ተስፋ እውን ማድረግ ችሏል።
በዚህም በፌዴራል መንግሥት የአስፈጻሚ የመንግሥት መዋቅር ኦነግ፣ ኢዜማ እና አብንን ለማሳታፍ ያደረገውን ጥረት ተስፋ ሰጪ ሆኖ ተመዝግቧል። ይንንም በየክልሉ ምክር ቤቶች ከገቡ ተቃዋሚዎች በተጨማሪ በክልል መንግሥታትም አስፈጻሚ ሆነው ተቃዋሚዎች እንዲገቡ በሁሉም ምርጫ በተደረገባቸው ክልሎች ጥረት መደረጉ ነገሩን አዲስ ምዕራፍ የሚያሰኘው ነበር። በኦሮሚያ ክልል ኦነግ፣ በአማራ ክልል አዴሃንና አብን፣ በአዲስ አበባ አስተዳዳር ኢዜማና አብን፣ በሶማሌ ክልል ኦብነግ፣ በደቡብ ክልል ኢዜማ፣ ሶሕዴፓ፣ ነእፓ በቤኒሻንጉልም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሥልጣን ለማጋራት ተችሏል።
ከዚህ አንጻር አስተያየት እንዲሰጡ የጋበዝናቸው ዶክተር የሺጥላ ነገሩን በአዎንታ አይተውት ዘላቂነት ላለው አካሄድና አዲስ ምዕራፍነቱን ለማጽናት የፖለቲካ ምኅዳሩን የምር ማስፋቱ የተሻለ ይሆናል ብለው ይመክራሉ።
እኛም በመንግሥትና በተፎካካሪዎች መካከል ያለው መቀራረብ በብሔራዊ እርቀ ሰላም የበለጠ እንደሚያብብ ተስፋ እያደረግን የተጀመረው ይቀጥል እንላለን።
ማለደ ዋስይሁን
ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም