አመል ያወጣል ከመሐል

የልጅነት የጨዋታ ጊዜዬን ሳስታውስ ከማይረሱኝ አጋጣሚዎች አንዱ የጩሎ ረብሻ ነው። ከጩሎ በዕድሜ በወራት ብንበላለጥ ነው። እኩያ ነን። ያለአቅሙ ራሱን እንደ አለቃ የሚቆጥር አምባገነን ሕፃን ነበር።

ጩሎ ከቤቱ ወጥቶ ከመንድሩ ልጆችጋ ለመጫወት ከፍተኛ ጉጉት አለው። እናቱ እቴማንቺ ወጥቶ፣ ተጣልቶ ይመጣል ብለው ስለሚሰጉ ከቤት ባይወጣባቸው ይመርጣሉ። የጩሎ ጩኸት ግን የእትዬ እቴምአንቺን አንጀት ስለሚረብሸው ‹‹በል ሄደህ›› ተጫወት ይሉታል። ገና ከአፋቸው ‹‹ሂድ›› የሚለውን ቃል ሳይጨርሱ የቤታቸውን የቆርቆሮ በር በርግዶ ይወጣል። የከፈተውን በር ሳይዘጋ እየጮኸ ከእኛ መሐል ይገባል።

ጩሎ እንደመጣ ሁሉንም የናፈቀ ሆኖ ይቀርባል። እየተጠመጠመ ይስመናል። ትንሽ ቆይቶ ግን ጩሎ የጭቃ ጅራፉን፦ ክፉ አመሉን ያወጣል። ከጓደኞቹ መካከል ያማረ መጫወቻ የያዘውን አይቶ ‹‹ስጠኝ!›› ብሎ ይጮኻል፤ ለመስጠት ያልፈቀደ ሕፃን ካለ በሕፃኑ ጩሎ ጩኸትና ጉልበት መጫወቻውን ይጥላል።፡ የፈረደበት ሕፃን ያለቅሳል። ጩሎ ከጓደኞቹ የሚቀማው መጫወቻ ሁሉ የራሱ እንደሆነ ያህል ያስባል። የወሰደውን መጫወቻ እንዴት እንደሚጫወትበት እንኳን አያውቅም፤ የተነጠቀው ሕፃን መነጠቁን ለምዶ ተረጋግቶ ይጫወታል። ጩሎ ግን የሌሎችን መጫወቻ እስኪወላልቅ ይጫወትበታል። ወዲያውኑ ይሰለቸዋል። ከዚያ የሌላ ሕፃን መጫወቻ ያያል እንደለመደው ነጥቆ ይጫወታል።

ሌላ የደመቀ ጨዋታ የጀመርን ሕፃናት ካለን ጩሎ እራሱን የጨዋታው አንበል ካልሆነ ደስታ አይሰጠውም። መሃል ይገባል። የውድድር ጨዋታ ከሆነ ያፍራል። የታፈረባቸው ጓደኞቹ ከእርሱ ሸሽተን ሌላ ጨዋታ ስንጀመር ተከትሎ ይመጣል። ጓደኞቻችን የጩሎ አምባገነንነት ሲበዛባቸው በቡድን ሆነው ይደበድቡታል። መትተውት መጮኽ ሲጀምር ወደየቤታቸው ይበተናሉ።

የጩሎ ጩኸት ሀገሩን ያዳርሳል። በተለይ ከቆሰለ ከደማ መንደሩ ሁሉ በጩኸቱ ይታወካል። የፈረደባቸው እናቱ እትዬ እቴማንቺ አርጩማያቸውን ይዘው ይወጣሉ። መሐል ገብቶ ሲያጫውት የነበረ ልጃቸው ብቻውን ሜዳ ላይ ሲጮኽ ያገኙታል። ጩሎ የመቱትን ሁሉ በስም እየጠራ ለእናቱ ይከሳል። እቴማንቺ በየቤቱ እየመጡ አርጩሜያቸውን አሹለው ለየሕፃኑ ወላጅ ሁሉ አቤቱታ ያቀርባሉ። አንዳንዶቹ ወላጆች የጩሎን ክፉ አመል ስለሚያውቁ ከእቴማንቺ ጋር እሰጥ አገባ ይገባሉ። እትዬ እቴማንቺ በየቀኑ በየሳምንቱ የልጅ አቤቱታ ማሰማት ሰለቻቸው። ስለዚህም ጩሎ በጮኸ ቁጥር አርጩሜያቸውን እርሱው ላይ ይጨርሱ ጀምር። በየቀኑ ከመንደሩ ሕፃን ሁሉጋ አምበል ሆኖ ሲጫወት የነበረው ጩሎ በወር እንኳን ከቤት መውጣት ተከልክሎ ከቤቱ በራፍ ላይ ቆሞ የደመቀ የእኛን ጨዋታ ለማየት ይገደድ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ታዲያ አያቴ ጩሎን ከመጫወት ተከልክሎ ከቤታቸው የቆርቆሮ በር አጠገብ ቆሞ በርቀት ስሞቻችን ሲጣራ ሲያዩ ‹‹አዬ አመል ያወጣል ከመሐል አሉ›› ብለው ይተርቱበታል።

ዛሬ አድጌ፣ ጎልምሼ የአያቴን አባባል የሰማሁበት ጊዜ ወደኋላ ረጅም ቢሆንም አባባሉን ትርጉም ፍጹም የተረዳሁበት ጊዜ ወደ ኋላ አጭር ነው። ‹‹ዕድሜ ለሕወሓት›› በጣም ነው የገባኝ። በ1960- እስከ 1970ዎቹ ዳር ዳሩን ሲል የነበረው የሕወሓት አንጋች ፖለቲካ ‹‹ዕድሜ ለደርግ›› መዝረክርክ እያለ ኦነግና ኢሕአዴንን አጃቢ አድርጎ መሐሉን ሲቆጣጠር ‹‹በሆታ ግባ በእልልታ›› ያሉት ባልንጀሬዎቹ ኦነግና ኢህዴን ለአመሉ ብፅዕና ለተግባሩ ቅድስና ጥርጣሬ አልነበራቸውም። በፖለቲካው ጨዋታ አብረውት ሊጫወቱ ተሰይመው ነበር።

ሕወሓት በ1983 ዓ.ም ግንቦት ወር አራት ኪሎ ሲደርስ ንጉሥም ጳጳስም ሆኖ ብፁዕ መባሉን ቀጠለ፤ የምርም የመሃሉን ጨዋታ ተጫዋችም መሪም ሆኖ የአዲስ ዘመን ብሥራት ነጋሪ ሆነ። ኢሕዴን ኦሕዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴን እየሆነ በሕወሓት ሲሸነሸን እንደተወለደ እንዳደገ አራት ኪሎ የደረሰውን ሕወሓትን ግን የሸነሸነው አልነበረም። እርሱ በልክና በወሰናቸው አጃቢዎቹን ሲያሰማራ እርሱ መሃል ሆኖ አንጋሽና ቀዳሽም ነበር። ቦታ ቦታ ይዘው ዳር ዳሩን እንዲጫወቱ የተደረጉት የግንባሩ ድርጅቶች የግንባራቸውን ማእከል የሕወሓትን ፊሽካ ሳይሰሙ ምንም እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አልነበሩም።

ሕወሓት የበለጠ መሃሉን የሚያስይዘው ሌላ ተጨማሪ አጃቢ ከባቢ ለማሰለፍ አሁንም አላረፈም። እርሱ የመሃሉ መሐል ሆኖ ‹‹አጋር›› የተባሉ የበዪ ተመልካች ኢትዮጵያውያንን እርሱን የከበበው ንብርብር ቅርፊት አደረጋቸው። የብጽእና ውሃ ልክ አድርጎ ራሱን በማሳሰብ ሌሎቹንም ‹‹ያመነ ይድናል›› ብለው እንዲሰለፉ አደረጋቸው።

ኦነግ በተቻለ መጠን መሃሉን መጋራት ይፈልግ ነበር። የሕወሓት ትከሻ ሰፊ ስለነበር ኦነግ ተጋፍቶ መሃል መግባት አልሆነለትም። በተሰጠው መስመር ተወስኖ በሕወሓት ሜዳ መጫወቱን ቀጠለ። ያቺንም በሕወሓት የተወሰነችለትን መጫወቻ እንደ ልቡ ሊጫወትባት እንዳልቻለ የተረዳው ኦነግ የሕወሓትን አመል መጠርጠር ያዘ፤ ‹‹ብፁዕ›› ሲለው የነበረው ሕወሓት የቀበሮ ባህታዊ ሆነበት። አልያዝ፣ አልጨበጥ አለው። የኦነግ ምኞትና ትልም እንደጉም እየበነነ የሕወሓትን መሃልነት የተቀበለው ኦህዴድ ወደዳር አሽንቀጥሮ ሲያወጣው ከመሃል ብቻ ሳይሆን ከጨዋታ ውጪ ለመሆን ተገደደ። በዚህ ጊዜ ግን በዳይ ሆኖ የተሳለው ኦነግ ነበር። ‹‹ተከዳሁ፣ ሕግ ተጣሰ፣ ታመጸብኝ›› ያለው ሕወሓት ኢሕአዴግ ነበር። ነገሩ ‹‹አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው›› ሆኖ በትዝብት ታለፈ።

የመሃል ዳኛውም፣ የመስመር ዳኛውም ሕወሓት በሆነበት ጨዋታ ኦነግ መሐል የሚገባበትን አዲስ የጨዋታ ሜዳ በኃይል ለመፍጠር የሚቆፍረው መሬት ፍለጋ በየጫካው ተሰገሰገ።

ሕወሓት በከፍተኛ የማስመሰል ጨዋታ እንዲህ መሃል መሃሉን ራሱን አደላድሎ ቢያስቀምጥም በአዲስ ዐውድ ውስጥ አዲስ አመል መያዝ ግን አልሆነለትም። በምርጫም ይሁን በቅርጫ መሃሉን የመያዝ ፍላጎት አላቸው የሚላቸውን ሁሉ በየተራ እየዘረረ ዓመታትን ተሻገረ። ሕወሓትን ከመሃል የሚያስወጣ የመሰለውን የሃይማኖት ወገን፣ የንግድ ድርጅት፣ የፖለቲካ ኃይል፣ ታዋቂ ሰው ሁሉ ተራግጦ ሰበረ። ተደላደለ። ነገር ግን ክፉ አመል አለበትና የሰበረውን ያደቃል፤ በሞተው ላይ ይተኩሳል። የወደቀውን ይረግጣል፤ ስደተኛውን ያድናል።

ሕወሓት ግን መደላደልን አያውቅም ‹‹ድመት መነኩሳ አመሏን አትረሳ›› እየሆነበት አሙቀው አድምቀው እያጨበጨቡ መሃል የሚያስጨፍሩትን አጃቢዎቹን መራገጥ ቀጠለ። ፈረስ የሚጋልብበትን የምቾት ኮርቻውን ኢሕአዴግን መዘንጠል ቀጠለ፤ ፈጥና የምትጋለብ ፈረሱን ሀገሪቱን በሰከንድ በደቂቃ በእሾሕ አለንጋው መዠለጥ ቀጠለ። ወይ አመል!

በአለንጋው አቆሰላት፤ ጌጧን ሁሉ አረገፈው፤ መንገዷን ሁሉ አስጠፋት፤ አስበረገጋት፤ ከዕለት ዕለት አከሳት፤ አቅም አነሳት።

ስለዚህም ዳር ዳር ሆነው የሚያጫውቱት የኢሕአዴግ ክንፎችና አጋሮች ትከሻቸው ደማ ቆሰለ ሕወሓትን ሊሸከሙት አልቻሉም። ተባብረው ከመሃል ጨዋታ ማስወጣት ፈለጉ፣ አለሙ፣ አቀዱ፣ ተራመዱ፣ ደረሱ፤ ችለውም ዳር አወጡት።

ሕወሓት ግን ‹‹የፈሲታ ተቆጢታ›› ሆነ። ‹‹በጥላቻ፣ በዘረኝነት የተፈጸመብኝ መገፋት ነው›› አለ። ጩኸቱን አቀለጠው። ጓደኛዬ ጩሎ ከመሃል ጨዋታው ሲወጣ እናቱን እትዬ እቴማንቺን ይጠራ እንደነበር ሕወሓትም መሃል መልሰው ሊያስገቡት ይችላሉ ያላቸውን የፌዴራሊስት ኃይሎች ማሰባሰብ ቢሞክርም የእነርሱ አርጩሜ አባልና አጋሮቹን ተሰብስበው እንዲያጫውቱት ሊያደርግ አልቻለም።

ስለዚህም ሕወሓት በአባልና አጋሮቹ ላይ ድንጋይ መወርወር መፈንከትና ማቁሰል ጀመረ። ዜጎች አፈናቃይ፣ የግጭት ምንጭ፣ የሁከት ጠማቂ፣ የቀጠናው አሸባሪ ለመሆን ወሰነ። ጩሎው ሕወሓት ራሱ ባጠፋው ሌሎችን መክሰስ ቀጠለ። ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል ተተረተበት።

ጩሎው ሕወሓት ድንጋይ ውርወራና ጩኸቱ ሲበዛ የሀገሩ ዜጎች ሁሉ ተባብረው ዘመቱበት። መቁሰልና መድማት ጀመረ። ክንዳቸውን መቋቋም አልቻለም። ሮጦ እየጮኸ ከዋሻው ገባ። ጩኸቱን ቀጠለ። ሲ.ኤን.ኤን፣ ሮይተርስ፣ ቢቢሲ…. የዚህ ጩኸት አስተጋቢዎች ናቸው።

የልጃቸውን አመል ያላወቁት እትዬ እቴማንቺ ልጃቸውን ከመቅጣት ከማረም ይልቅ የመንደሩን ሕፃናት ሁሉ እንደሚከሱት የሕወሓት የክፋት ሐሳብ ወላጆች ምዕራባውያን ሕወሓት ለምን ተነካ ብለው ክስና አቤቱታቸውን አቅልጠውታል። የማዕቀብ አርጩሜ ይዘው የኢትዮጵያ ሰዎችን ያስፈራራሉ። ይህ ግን ሕወሓትን ወደ መሃል ሊመልስ አልቻለም፤ አይችልምም።

ሕወሓትን ከመሃል ያስወጣው፤ ዳርም የጣለው፣ የኢትዮጵያውያን ጭፍን ጥላቻ አይደለም። ዘረኝነትም አይደለም። አድልዎም አይደለም። የጨቋኝነት ፍላጎትም አይደለም። ይሄ ሁሉ አመል የሕወሓት እና የጀሌዎቹ እንጂ የሌሎች ኢትዮጵያውያን አይደልም። ከመሃል ያስወጣውም ይሄው የዘረኝነት፣ የጨቋኝነት፣ የአድልዎ፣ የሌብነትና የጥላቻ አመል ነው። ክፉ አመል ነው። ክፉ አመል እንኳን ከማሃል ከዳርም ለመቆም አያበቃም። አመል ያወጣል ከመሐል።

 ቶኩማ ሮባ

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You