ያለን ምርጫ፣ መክተት ብቻ!

አሸባሪው ሕወሓት መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ ያለፉት 30 ዓመታት የጋራ መስተጋብራችንን የሚበጥስና አብሮነትን የሚንድ በርካታ ተግባራትን ፈፅሟል። መለያየትን ሥርዓታዊና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት በማስያዝ፣ የተጨቆኑ ማንነቶችን እውቅና ለመስጠት በሚል ሽፋን ኢትዮጵያዊነት እንዲፈርስ ቀላል የማይባል ዘመቻ አከናውኗል። ለአገር ክብርና ለሕዝቦች አንድነት የተጋደሉ ብዙዎችን ገድሏል፣ተሰደው አገር አልባ ሆነዋል።

በተባበረ ሕዝባዊ ትግል ከፈላጭ ቆራጭነቱ ሲሸኝ ግን የሠራው ሴራ መክኖ፣ ያወረደው መዓት ተገቶ የሀገር አንድነትን ማስቀጠል ወደሚያስችል አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ተችሏል። በአገራችን አዲስ የለውጥ ጅምርና የመደመር ቀንዲል መለኮሱ ደግሞ አዲስ ተስፋ አጭሯል። ይሁን እንጂ ከማእከል ተገፍቶ የወጣው ይህ አሸባሪ ኃይል ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን የለውጥ ሂደት ከመፈታተን አልቦዘነም። በተለይም ከስምንት ወራት ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይን ሲያስተዳድር በነበረው ይህ ጠንቀኛ ቡድን በለኳሽነት ጦርነት መቀስቀሱ የለውጡን ሂደት ፈተና አክብዶታል።

ይህ አደገኛ ኃይል ራሱን ወደ ጁንታነት ቀይሮ ሥርዓተ መንግሥቱን ለማፍረስ በመሞከሩ፣ ራሱንና የወጣበትን ማኅበረሰብ ለከፋ ችግር አጋልጧል። አካባቢው እንዳይረጋጋ፣ ቀውሱ እንዳይቆም፣ ሕዝቡም መከራ በዛብኝ ብሎ በመንግሥቱ ላይ ይበልጥ እንዲማረር እየሠራ ነው። ከዚያም አልፎ በውሸት ፕሮፖጋንዳ ዓለምን በማሳሳት የውጭ ኃይሎች በአገር ላይ ጫና እንዲያደርሱ አድርጓል። አሸባሪው ሀገር በማፍረስ፣ዜጎችን በመግደል፣ በማፈናቀል፣ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመፈጸም፣ ጥላቻ በመስበክ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል። ከሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በግልጽ እየሠራም ነው። በአጎራባች ክልሎች ወረራዎችን ፈጽሟል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን አንድ መገንዘብ ያለብን ቁምነገር ማንም ይሁን ማን ሕግን ጥሶ፣ በእብሪት ሥርዓትን ገርስሶ እንዲኖር መፍቀድ ዘላቂ ጉዳትን በራሳችንና በቀጣይ ትውልድ ላይመጋበዝ መሆኑን ነው። አንድነታችንም ሆነ ሰላማችን ሊጠበቅ የሚችለው ሕግና ሥርዓት ሲከበር፣ አሸባሪና ከሃዲ ኃይሎች ሲቀጡ፣ ለየትኛውም ጫና ሳንበረከክ የጉዟችንን እንቅፋት ለመጥረግ ስንረባረብ ነው!!

በመሆኑም ወቅቱ አገርን ለመበታተን ቆርጦ ከተነሣ አሸባሪ ቡድን ጋር እየተፋለምን የምንገኝበት ነው። ደኅንነታችንን ማስጠበቅ የምንችለው፣ ሀገር እንዲኖረን ማድረግ የምንችለው ይህን ኃይል በአንድነት ቆመን በመመከት ብቻ ነው። ጠላት ከመሣሪያው በላይ በምላሱ ሳያሸብረን፣ አንድነታችን ሳይፈተን፣ ከሠራዊታችን ጎን መቆም አማራጭ የሌለው ነው። በተለይ በጠላት የፕሮፓጋንዳ ታክቲክ ሳንፈታ፣ በጊዜያዊ ችግሮች ልባችን ሳይከፈል ወቅቱን የሚመጥን ስነ-ልቦና መያዝ ይኖርብናል። ወቅቱ የህልውና ጦርነት እየተካሄደበት ያለበት ወቅት በመሆኑ በህልውና ዘመቻው መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ራስን አዘጋጅቶ እና ተደራጅቶ ጠላት በመጣበት አግባብ ምላሽ መስጠት አማራጭ የሌለው ነው።

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You