“በቀበሮ ጉድጓድ…”

ሕወሓት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በተደረገ ሕግ የማስከበር ዘመቻ መቐለን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ ከተሞችን በሦስት ሳምንት ውስጥ መቆጣጠር መቻሉ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መቐሌ መያዟን ተከትሎ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ጦርነቱ መጠናቀቁን ጠቅሰው ቀጣይ የመንግሥታቸው ተግባር በሕግ የሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋልና ትግራይን መልሶ መገንባት መሆኑን አስታውቀዋል። መከላከያ ሠራዊት በትግራይ በነበረው ቆይታ ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮችን በቁጥጥር ስር አውሎና ደምስሶ ከስምንት ወራት በኋላ የተናጥል ተኩስ አቁም በማወጅ ሙሉ ለሙሉ ክልሉን ለቅቆ መውጣቱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ሕወሓት በከፈተው ጦርነት የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። የሱዳን ጦር አጋጣሚውን በመጠቀም የኢትዮጵያን መሬት ወርሯል። ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የሚተነትነው ጂኦ ፖለቲክስ የተባለው ተቋም ያጋለጠው መረጃ እንደሚያመለክተው የሕወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት ባለስልጣናት እ.ኤ.አ ኅዳር አንድ ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ሊዳከም በሚችልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገው ባለ ሰባት ገጽ ሰነድ እስከ ማዘጋጀት ደርሰዋል።

ምዕራባውያኑ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተጠቅመው የአዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን መሆን ለማደናቀፍና ለእነሱ ታዛዥ የሆነ እንደፈለጉ እጁን የሚጠመዝዙት መንግሥት ለመመሥረት ሕወሓትን በተለያየ መንገድ በማገዝ፣ ለወንጀሎቹ ሽፋን በመስጠት የተለያዩ አካላትን ያሳተፈና የተናበበ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህ ጽሑፍ በዚህ ረገድ ያለውን የምዕራባውያኑን ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴ፣ የኢትዮጵያን ተጋድሎ እና የወዳጅ አገራትን ድጋፍ ይቃኛል።

የተቀናጀ ዘመቻ

ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችና ብዙኃን መገናኛዎች የኢትዮጵያን ስም በማጠልሸት ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ለማበርታትና ማዕቀቦችን ለማስከተል በተደጋጋሚ የተቀናጁ ዘመቻዎችን አድርገዋል። ሲ. ኤን. ኤን፣ ሮይተርስ፣ ኒውዮርክ ታይምስ፣ አሶሼትድ ፕረስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ቢቢሲ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሙያዊ መርኅን ባልተከተሉ ሐሰተኛ ዘገባዎች የኢትዮጵያን እውነት አዛብተው ለዓለም ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ አሁንም ቀጥለውበታል።

ሲ. ኤን. ኤን. ብቻ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አያሌ ሐሰተኛ ዘገባዎችን አሰራጭቷል። ለአብነትም ጳጉሜ 4/2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ወታደሮች ተገድለው ተከዜ ወንዝ ውስጥ ስለመጣላቸው “የአስከሬን ምርመራ ባለሙያዎች ማረጋገጫ ሰጥተውበታል” በሚል ያለ ተጨባጭ ማስረጃ ያቀረበው ዘገባ ተጠቃሽ ነው። ጣቢያው “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ጎረቤት አገር ኤርትራ አጓጉዟል” ሲልም መሠረተ ቢስ ክስ በማቅረብ የአየር መንገዱን ስም ለማጠልሸት ሞክሯል። በአንጻሩ በማይካድራ፣ በአፋር ክልል ጋሊኮማ፣ በአማራ ክልል ዳባት እና ጭና በተባሉ አካባቢዎች አሸባሪው በርካታ ንጹሐንን በጅምላ መፍጀቱን እንዲሁም በደብረ ታቦርና ተቆጣጥሯቸው በነበሩት አካባቢዎችም ባደረሰው ጥቃት በርካታ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት መዘረፍና መውደማቸውን ለመዘገብ አልደፈረም።

እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ በሰብአዊነት ስም የፖለቲካ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እና በተ.መ.ድ ስር ያሉ ድርጅቶች ለአሸባሪው ቡድን የወገኑ የተጋነኑ እና የፈጠራ ሪፖርቶችን በማውጣት የምዕራባውያኑን ፍላጎት ለማስፈጸም በከፍተኛ ደረጃ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል።

የተ.መ.ድ አድሏዊነት ፀሐይ ከሞቀ ከራርሟል። እስራኤል እየገነባች ባለችው የአይሁድ ሠፈራ መንደሮች የፍልስጤምን ጩኸት የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለቱ፤ በኢራን የኑክሌር መርኅ ግብር ላይ አሜሪካንን ኮቴ እየተከተለ ድጋፍ በመቸሩ እና ዛሬም ላይ እየወደሙ ስላሉት ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያና ሶማሊያ ግድ የማይሰጠው ድርጅት መሆኑና ምንም አለመፈየዱን በመጥቀስ የሚተቹት በርካቶች ናቸው። ምዕራባውያን ሶሪያን ለማውደም ጣልቃ በመግባት ዐማፅያኑን በመደገፍ የእርስ በእርስ ግጭቱን ለዓመታት ሲነዱት ተ.መ.ድ ዝምታን መርጧል።

ድርጅቱ ከውልደቱ እስከ ጉልምስናው በምዕራባውያኑ ቁጥጥር ስር ያለ አሻንጉሊት መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ሩዋንዳ ውስጥ የተከሰተውን የዘር ማጥፋት እልቂት ቀድሞ መከላከል ያልቻለው ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ባላቸው አሜሪካን እና ፈረንሳይ ውሳኔ ነው። አሜሪካ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ፣ ፈረንሳይ ደግሞ አጋሮቿን ላለማጣት በሚል ከየጥቅሞቻቸው በመነሣት ስሌት ውስጥ በመግባታቸው የአንድ ሚሊዮን ገደማ ሩዋንዳውያንን እልቂት ማስቆም ሳይቻል ቀርቷል።

ኢትዮጵያ ከ53 የድርጅቱ መሥራች ሀገሮች አንዷ ነች። ለዓለም አቀፍ ሰላምና የጋራ እንቅስቃሴ ማደግ የበኩሏን አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች። ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ሚናዋን በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ሶማሊያ፣ አብዬና ዳርፉርም በሚገባ ተወጥታለች። ይኸው ተሳትፎ አሁንም ቀጥሏል። በ1959 ዓ.ም፣ ከ1981 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን ተመርጣ ለሦስት ጊዜ አገልግላለች። ድርጅቱ ለዚህ ውለታዋ የማይመጥን ምላሽ ሲሰጣት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ኢትዮጵያ በጣሊያን ዳግም ወረራ በተፈጸመባት ወቅትም ፍርደ ገምድልነቱን በተግባር አሳይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቅርቡ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪውን ቡድን “ጠንካራ ተዋጊ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያሸንፈው አይችልም” ሲሉ በማሞካሸት ከድርጅታቸው መርኅ ጋር የሚጣረስ አስተያየት እስከመስጠት መድረሳቸው ይታወሳል። ጉተሬዝ ይህን መሰል አስተያየት ሰጥተው ሲያበቁ፣ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ. ኦ. ኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን አቻንግን እና የሥነ ሕዝብ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ዴኒያ ጌይልን “የድርጅቱን እሴቶች የማያንጸባርቅ” አስተያየት ሰጥታችኋል በሚል

 ኒውዮርክ ወደ ሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተጠርተው አስተዳደራዊ ዕረፍት እንዲወስዱ አድርገዋል። ኃላፊዎቹ ከኢትዮጵያ የተጠሩት ተ.መ.ድ ከሽብርተኛው ቡድን ሕወሓት ጋር ባለው ግንኙነት ተቋማዊ አድሏዊነትን መከተሉን በግልፅ በመናገራቸው፤ አሸባሪውን ቡድን ‹‹ጨካኝ›› ብለው በመግለጻቸው እና የተ.መ.ድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች አዲስ አበባ የሚገኙ ከፍተኛ የተ.መ.ድ ኃላፊዎችን በማግለል በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ካሉ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ ብለው በመናገራቸው ነው።

አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ አንድሪው ኮርይብኮ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የፈጸማቸው ሦስት ቅሌቶች” በሚል ባቀረቡት ጽሑፍ ፣ ተ.መ.ድ እና አሜሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት ሙሰኛ ሠራተኞች አማካይነት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለማሳደር እያከናወኑት ያለውን ድብቅ ሴራ አጋልጠዋል። ለአብነትም የሰብአዊ እርዳታ ጭነው ትግራይ ክልል የገቡ የዓለም ምግብ ድርጅት 428 ተሽከርካሪዎች ሳይመለሱ ስለመቅረታቸው ተ.መ.ድም ሆነ አሜሪካ ምንም ዓይነት መረጃና ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን አንሥተዋል። ተሽከርካሪዎቹን ሕወሓት ወደ ጦር ሜዳ አስገብቶ እየተጠቀማቸው መሆኑን ለመናገር እንዳልደፈሩም ጠቅሰዋል።

በተገላቢጦሹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰብአዊ አቅርቦት እንዳይደርስ መተላለፊያ መንገዶችን ዘግቷል የሚል መሠረተ ቢስ ክስ ላይ መጠመዱን ይገልጻሉ። ይህም የመንግሥታቱ ድርጅት እና አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ባለፈ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳት እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማጠልሸት ብሎም እውቅና ላለመስጠት የሚያደርጉት ሴራ ነው ይላሉ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ የተሰማሩ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰባት ሙሰኛ ሠራተኞች ከተሰጣቸው የሥራ ሃላፊነት ውጪ ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ ሲሰጡ በመገኘታቸው ከሀገር እንዲወጡ ማድረጉን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞቹ የፈጸሙትን ያልተገባ ሥራ ማጣራት እና ቅጣት ማስተላለፍ እንዲሁም በሌሎች ታማኝ ሠራተኞች መተካት ሲገባው ዓይኑን በጨው አጥቦ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማሳደር ታትሮ እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ ተችተዋል።

ትዕዛዝ እና ዛቻ

አሜሪካ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ከራሱ ግዛት እንዲወጣ ትዕዛዝ እስከመስጠት ደርሳለች። በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ መንግሥታት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩት አሌክስ ሮንዶስ እና ማርክ ሜዲሽ ፖለቲኮ በተባለ መጽሔት ላይ በጋራ ባወጡት ጽሐፍ “ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ካልተፋጠነ ኢትዮጵያ የዩጎዝላቪያ ዕጣ ሊገጥማት ይችላል ውጤቱም የከፋ ይሆናል” ሲሉ ዝተዋል።

የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ከሚሰጡት ብድር የተወሰነውን እንዲይዙ ሊያደርጉ እንደሚችሉ እና ኢትዮጵያን ምርታቸውን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ ከሚልኩ የአፍሪካ አገራት ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት በመዛት የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማንበርከክ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ተጨማሪም በየፊናቸውም ለኢትዮጵያ ለመስጠት ያቀዱትን በመቶ ሚሊየኖች ዶላር የሚቆጠር ድጋፍ በማቀብ እርምጃዎችን ወስደዋል።

በካሊፎርኒያ እስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰሩ አለማየሁ ገብረማርያም በቅርቡ ከዘመን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ የባይደን አስተዳደር ሁሉንም ዓይነቶች የኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ማዕቀቦች በመጠቀም አስፈራርቷል። አሜሪካ የአውሮፓ የገንዘብ ተቋማት ተመሳሳይ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ተናባ እየሠራች ነው። አሜሪካ በምታደርገው ማዕቀብ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ ማኅበረሰባዊ እና የፖለቲካ ሂደት በማተራመስ አከርካሪዋን ለመስበር እና ጉልበቷ ስር ለማንበርከክ ሁሉንም ነገር ትጠቀማለች። አሜሪካ ከአውሮፖ ኅብረት ጋር በመሆን በጉልበቷ እንደ ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አዳዲስ ብድሮችን እንዲከለክሉ፣ የብድር መክፈያ ጊዜ እንዳያራዝሙ ወዘተ እና ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ስምምነቶችን እንዳያድሱ ለመከልከል ተባብራ እየሠራች ነው ብለው እንደሚያስቡ ገልጸው ነበር። የሆነውና እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ምዕራባውያኑ የምናዛችሁን ካልፈጸማችሁ እንዲህ ያለ ቅጣት ይከተላችኋል በሚል ማስፈራሪያ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛቸውን ለማስፈጸም አሮጌ አቁማዳቸውን ይዘው ኢትዮጵያ በር ላይ ቆመዋል።

መቀመጫቸውን ካናዳ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ፊትዝ ጄራልድ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ይተቻሉ። “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሕጋዊው የኢትዮጵያ መንግሥትና በጦርነቱ ከተጎዱት ከትግራይ፣ ከአማራ እንዲሁም ከአፋር ክልሎች ጋር ነው መቆም ያለበት። በሕወሓት በተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ላይ በማተኮር መሣሪያውን እንዲያስቀምጥ ጥሪ ማቅረብ አለባቸው” ሲሉም ይመክራሉ።

የወዳጅ አገራት አጋርነት

ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላት ግንኙነት በመሻከሩ አሸባሪው ቡድን የሰነዘረባትን ጥቃት ለመቀልበስ ከሌሎች ወዳጅ አገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት አጠናክራለች። ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ ከኢራን፣ ከቱርክ እና ከቻይና፤ የገንዘብ ብድር ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስና ሳዑዲ አረቢያ እንዲሁም ፖለቲካዊ ድጋፍ ደግሞ ከሩሲያና ቻይና በማግኘት ከምዕራባውያን ውጪ የምትፈልገውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰች ነው” በሚል ስጋት ሲገባቸው እየተስተዋለ ነው። ሩሲያና ቻይና በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ በአሜሪካና አጋፋሪዎቿ የሚቀርቡ የውሳኔ ሐሳቦችን ውድቅ ማድረጋቸው የስጋታቸው እምብርት ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ከዐሥር ጊዜ በላይ ስብሰባዎችን አድርጓል። አየርላንድ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስላለው የሰብአዊ እርዳታ የኢትዮጵያን መንግሥት በመጫን በአንድ ድምፅ መናገር አለበት ስትል የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ እና ኢስቶኒያን ድጋፍ ይዛ በተደጋጋሚ ብትወተውትም ሩሲያ እና ቻይና “በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው” የሚል አቋም በማራመዳቸው ምክንያት ያለውጤት ተበትኗል።

በእነዚህ መድረኮች ቻይና “በሰብአዊ እርዳታ ስም የውጪ ጣልቃ ገብነት መኖር የለበትም። የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን ይፈታ” የሚል አቋም ይዛለች። ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረሩ እና ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብሱ መሆናቸውን በመግለጽም የምዕራባውያኑን እርምጃ ተቃውማለች።

ሩሲያ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰብአዊ ሁኔታ ከፖለቲካ ጉዳይ መነጠል ያስፈልጋል። በትግራይ በሚደረገው ሰብአዊ እርዳታ መድልዎ መኖርም የለበትም ብላለች። የውጭ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነት በጠበቀ መልኩ ብቻ መሰጠት አለበት ስትልም አሳስባለች። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አገሪቱን በአንድነት ወደ ሰላም የመውሰድ አቅም አለው ብላ በጽኑ እንደምታምን በመግለጽ እንደ ቻይና ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን አውግዛለች። የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያቆም በመጠየቅ ሩሲያ ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት አሳይተዋል።

ሕንድ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ ቀውስ ለማሻሻል እያደረገ ባለው ጥረት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና ሊሰጣትና አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል። በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገው ጥረት በእራሷ በኢትዮጵያ የሚመራና በሕገ መንግሥቷ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን አለበት በማለት ሕንድ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛቷ መከበር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።

ሌላዋ የኢትዮጵያ ወዳጅ ቱርክም አጋርነቷን በአደባባይ ገልጻለች። ፕሬዝደንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት “ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች፤ ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች” ሲሉ ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውን አረጋግጠዋል።

በኋላም ፕሬዝደንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በቱርክ የስራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ያቀረቡላቸውን ግብዣ ተቀብለው ወደ ቱርክ ያቀኑት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ በወታደራዊና በውኃ ዘርፎች የሚደረጉ ትብብሮችን ያካተተ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ አሸባሪውን ቡድን ለማስወገድ እየወሰደች ያለችው እርምጃ የአንድ አገር ውስጣዊ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ከምዕራባውያኑ በተቃራኒ አቅጣጫ በመቆም ድጋፋቸውን ችረዋታል። በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ባደረጓቸው ንግግሮች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን መቆማቸውን የገለጹበት መንገድ ይህን የሚያረጋግጥ ነው።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን

ምዕራባውያን አገራት ኢትዮጵያን አላወቋትም፤ ፈጽሞ አልተረዷትም። ደበበ ሰይፉ “የብርሃን ፍቅር” በሚል ርዕስ ባሳተመው የግጥም ስብስቡ “በቀበሮ ጉድጓድ” የተሰኘ አንድ ግጥም አካቷል። ግጥሙ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሄዱበት መንገድ ከኢትዮጵያ በኩል ያልጠበቁትን ምላሽ ይዞ እንደሚመጣ ፈጽሞ አለማሰባቸውን ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ነው።

በቀበሮ ጉድጓድ ቀበሮ መስሏቸው

በቀበሮ ጉድጓድ ቀበሮ መስሏቸው

ውሾቹ አጓሩ በዛ ጩኸታቸው

አየሩን በከለው

ምድሩን አገረኘው፣

ትፋት ድንፋታቸው!

አይ የውሾች ነገር

ማን በነገራቸው

ማን ባስተማራቸው

አንበሳ እንደሆነ የሚጠብቃቸው !

አንበሳ እንደሆነ የሚጠብቃቸው !

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለ2014 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያን የሚፈትኗት ኢትዮጵያን የማያውቋት ናቸው። ኢትዮጵያ ለሺሕ ዓመታት በነጻነት ኖረች ሲባል ትርጉሙን አይረዱትም ማለት ነው። ጠላት አጥታ አይደለም ሺሕ ዘመን በነጻነት የኖረችው። ፈተና ረስቷት አይደለም የነጻነት ቀንዲሏ ሳይጠፋ እስከ ዛሬ ያለው። ከከፍታዋ ያልወረደችው ኃያላን ራርተውላት አይደለም ። ሁሉንም እንደ አመጣጣቸው አሸንፋ ብቻ ነው። ታሪካችንን ሳያውቁ የሚገጥሙንን ታሪካችንን ዐውቀን እንጠብቃቸዋለን። ለወዳጃችን ወተት፣ ለጠላታችን ዕሬት መስጠት እንችልበታለን። ከቶም ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከማሸነፍ እንጂ ከመሸነፍ ጋራ ተጠርቶ አያውቅም። ከነጻነት እንጂ ከባርነት ጋራ ዝምድና የለውም። ኢትዮጵያ ተፈትና ታውቃለች። ተሸንፋ ግን አታውቅም። ቀጥና ታውቃለች፤ ተበጥሳ ግን አታውቅም። የዘመመች መስላ ታውቃለች፤ ወድቃ ግን አታውቅም” በማለት ለምዕራባውያኑ ቆፍጠን ያለ አቋማቸውን አሳውቀዋቸዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምዕራባውያኑ በአንዲት ሉዐላዊት አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን እያደረጉ ያሉትን ጥረት ተቃውመዋል። በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኒውዮርክ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት፣ በ ሲ. ኤን. ኤን. እና በኒውዮርክ ታይምስ ቢሮዎች በመገኘት ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። የመንግሥታቱ ድርጅትና ሌሎችም አካላት በጽንፈኛው የሕወሓት ደጋፊዎች የሚሰራጨውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ተመርኩዘው በኢትዮጵያ ላይ ለመፍጠር እየሞከሩ ያለውን ያልተገባና ኢ- ፍትሃዊ ጫና እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ አሜሪካዊያን የዜጎች ምክር ቤትም በሲ.ኤን.ኤን የሚስተናገዱ ዘገባዎች ሙያዊ መርኅን ያከበሩና ትክክለኛ እንዲሆኑ ጣቢያውን ጠይቋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግሥትና ዜጎቿ ምዕራባውያኑና በጥቅም የሚደለሉ የተ.መ.ድ. ሠራተኞች በውስጥ ጉዳያቸው ላይ እያደረጉ ያሉትን ጣልቃ ገብነት በማስረጃ በማጋለጥ በተደራጀ መንገድ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብረው ከሚንቀሳቀሱ አጋር አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስሮችን ለማደርጀትም በትኩረት መሥራት አለባቸው።

 የትናየት ፈሩ

ዘመን መፅሄት ኅዳር 2014 ዓ.ም

Recommended For You