ኢትዮጵያ ሀገርና ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ ለህልውናዋ፣ ለብልጽግናዋ፣ ለክብሯ የሚደክሙ በርካታ የተከበሩ ብርቅዬ ዜጎች አሏት። እነዚህ የተወደዱ ልጆቿ ከልጅነት እስከ ዕውቀታቸው ባላቸው ዕውቀት፣ሙያ፣ ሀብት እና ጉልብት ዋጋ ሲከፍሉላት የኖሩ በብዙ የሀገሪቱ መልካም እርምጃዎች ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩ ናቸው። የፖለቲካ የሃይማኖት፣ የባህል ወገንተኝነት ሳይታይባቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ብቻ ብለው ለሁሉም የሠሩ ብርቱዎች አሉ። ጥቂት ቢሆኑም ትሩፋታቸው ግን ብዙ ነው። ከእነዚህ ምርጥ ኢትዮጵያውያን የሀገር ባለውለታዎች መካከል አንዱ ክቡር ዶክተር ኃይሌ ገብሬ ሉቤ ናቸው። የእኚህ ወድ የኢትዮጵያ ልጅ ታሪክና የህይወት ተሞክሮ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሊከተሉት የሚገባ ፈለግ ነውና ልናስቃኛችሁ ወደድን፤ እነሆ።
ውልደትና ዕድገት
ህጻን አብዲ ዱጎ ሉቤ በቀድሞ አጠራር በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በጌዲዮ አውራጃ በይርጋ ጨፌ ወረዳ በአሁኑ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ሚያዝያ 23 ቀን 1940 ዓ.ም. ተወለደ። አቅሙ ጠንከር ሲል ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመቱ ጥጆችን እየጠበቀ አደገ። የጉጂ ቤተሰብ በዚያን ወቅት የሚበዛው አርብቶ አደር ስለሆነ ወተት በብዛት ይገኛል፤ ህጻን አብዲም ወተት መጠጣትን በእጅጉ የሚወድ ሆኖ አደገ። በዚህም ምክንያት በሚወደው እንዲደሰት ከአያቱና ከወላጆቹ የተሰጡት ሶስት የወትት ላሞች ነበሩት።
የሚሻውን ሁሉ እያገኘ በምቾት ያድግ የነበረው ይህ ሕጻን ገና በሕፃንነት ዕድሜው ለስደት የሚዳርግ የታሪክ ክስተትን ተጋፈጠ። ስምንት ዓመት ሊሆነው አካባቢ በመሬት ስሪት(በመሬት አከፋፈል ስርዓት) ምክንያት የአባቱ መሬት ለሌላ ሰው ስለተሰጠ አባቱና ሌሎች ተቃውሞ በማሰማታቸው በተነሳ ግጭት በአባታቸው እጅ የሰው ህይወት አለፈ፤ ጫካ ገቡ። ይህም በመሆኑ ቤተሰባቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ ቤት ንብረታቸውን ትተው አካባቢውን ለቀው ወጡ፤ ወደ ተለያዩ ቦታዎችም ተሰደዱ። ንብረታቸው በሙሉ ተዘረፈ፤ ተቃጠለ።
በጊዜው የህጻን አብዲ ዱጎ እናት ልጃቸውን ይዘው ወደ ይርጋለም አካባቢ ተሰደዱ። ከዚያ በኋላ ህጻን አብዲ አባቱን ለማየት ዕድል ሳያገኝ እናቱ ዘንድ አደገ። ትንሽ ቆይቶም አባቱን ለመያዝ ዘመቻ ሲከናወን የአባቱ ህይወት አለፈ። እናትም ልጃቸው ማንነቱ እንዳይታወቅ ስሙንና የአባቱን ስም በክርስትና ስም ቀይረው (ኃይለማርያም ገብረየሱስ) ኃይሌ ገብሬ ብለው ትምህርት ቤት አስገቡት። ቤራ መሰረተ ትምህርት ት/ ቤት ከሚኖርበት አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ የሚገኝ ሥፍራ ቢሆንም ከትምህርቱ ይልቅ ለሚሰጠው ወተት ሲል በጠዋት ተነስቶ መሄድ ቀጠለ። ወተት ለመጠጣት ብሎ የጀመረው ትምህርት በጊዜ ሂደት እየወደደው ስለሄደ እስከ ስድስተኛ ክፍል አንደኛ የሚወጣ ተማሪ ሆነ። ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ይርጋለም ከተማ እየተማረ፣ እያረሰ እና እየነገደ ቤተሰቡን በጉልበትም ሆነ በገንዘብ እያገዘ የደረጃ ተማሪ በመሆን አስራ አንደኛ ክፍልን አጠናቀቀ።
ወጣቱ ኃይሌ ገብሬ ሉቤ በየጊዜው በተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚደርስበትን የዱላ ጥቃትን ለመከላከል ወታደር መሆን መፍትሔ ይሆናል በማለት ያስብ ስለነበረ አስረኛ ክፍል እያለ የሐረር ጦር አካዳሚ ውስጥ ለመግባት እንቅስቃሴ ሲጀምር የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ዩኒቨርሲቲ ነው መግባት ያለብህ በማለት ከለከሉት። አስራ አንደኛ ክፍል አዲስ አበባ በዕደማርያም ትምህርት ቤት ለመግባት ጥረት ሲያደርግ አሁንም ርዕሰ መምህሩ ዩኒቨርሲቲ መግባት አለብህ በማለት አልፈቀዱለትም። አስራ አንደኛ ክፍል ሲጨርስ ርዕሰ መምህሩ በሌሉበት በክረምት የባህር ኃይል አባላት መጥተው ሲመለምሉ ፈተናውን አልፎ ጠበቃቸው። በዚያን ጊዜ አሁን አልከለክልህም መሄድ ትችላለህ በማለት ፈቀዱለት።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባል ሆኖ ወታደራዊውን ትምህርት ከጨረሰ በኋላ አንድ ዓመት ያህል በሥራ ላይ ስልጠና ወስዶ የማሪን ኮማንዶ ትምህርት እማራለሁ ብሎ ሲያስብ ‹‹ውጤትህ ጥሩ ስለሆነ ኢንጅነር ነው መማር ያለብህ›› በመባሉ ሥራውን በመተው ወደ ቤተሰቡ በመመለስ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ተምሮ አጠናቀቀ።
በ1966 ዓ.ም. ጥሩ ውጤት አምጥቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢገባም ጥር ወር ላይ ግርግር በመነሳቱ ትምህርት ለመቀጠል አስቸጋሪ ሲሆንበት ካሳንቺስ የሥራ ማስታወቂያ አይቶ ተፈትኖ አለፈ። ለአንድ ዓመት የሚሰጠውን የህብረት ሥራና ግብይት ስልጠና ወስዶ ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ሲዳማ አውራጃ ሀገረሰላም ወረዳ በህብረት ስራ አደራጅነት ከ1967 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 1968 ዓ.ም. ከሠራ በኋላ ‹‹የበግ ለምድ የለበሱ አብዮተኞች›› በሚል ሰበብ በደርግ ስርዓት ይርጋለምና አዋሳ ለእስር ተዳረገ። ምክንያቱ በመኢሶን አባልነቱ የህዝባዊ መንግሥት ይመስረት ጥያቄን አቀንቅኗል በሚል ነው። ከ18 ዓመት እስከ ሞት የሚያስቀጣ አንቀጽ ተጠቅሶበት ክስ ተመሠረተበት። 36 ጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠ ችሎት ከቀረበ በኋላ ከእስር በነጻ እንዲለቀቅ ፋይሉ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲዳሞ ለቀጠሮ ይሄዳል። ፋይሉ ዳኛ ቀኝ አዝማች በለጠ ዘንድ ሲቀርብ እንደ መጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ተከሳሽ ወላጅ እንዲያመጣ በመጠየቅ ቀጠሮ ይያዛል። እናቱ በቀጠሮው ቀን ሲመጡ ተከሳሽ ልጃቸው በነጻ የተለቀቀ ቢሆንም ከእስር ቤት ቢለቀቅ እቤቱ ሳይደርስ ስለሚገሉት እስኪረጋጋ በወላጅ ፈቃድ በዳኛ ውሳኔ ለሶስት ወር እንዲታሰር ዳኛው ፈቃድ ጠየቁ። እናትም በመፍቀዳቸው የሶስት ወር እስር ተበየነበት። ወጣት ኃይሌ እስር ላይ እያለ መኢሶን ፈረጠጠ ተባለ፤ ከፍተኛ መገዳደል ሆነ። አብረውት ከነበሩ ሕዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም ጥረት ካደረጉ 13 ጓደኛማቾች ውስጥ በህይወት የተረፈው እሱ ብቻ ነው። ሌሎቹ ተረሽነዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ በ1970 ዓ.ም. መጨረሻ በነጻ ተለቀቀ።
ከፍተኛ ትምህርት
ከእስር ከተፈታ በኋላ ሲሠራበት ወደ ነበረው መሥሪያ ቤት ተመልሶ ገባ። መስከረም 1971 ዓ.ም. በዳግም ምዝገባ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ሲሄድ በኢሕአፓ፣ በመኢሶንና በሌላም ድርጅት ውስጥ ገብተው በተለያዩ ቦታዎች ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ወጣቶች ሁሉ ተሰባስበው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲፋጠጡ ይመለከታል። እዚህ ውስጥ ከምገባ ሲዳማ ሄጄ የቀድሞ ሥራዬን እየሠራሁ የውጭ ትምህርት ዕድል ብጠብቅ ይሻላል በማለት ወደ ሲዳማ ይሄዳል። በትምህርት ሚኒስቴር የተመዘገበው የውጭ ትምህርት ዕድል ቼኮዝላቫኪያ ህክምና እንዲያጠና ሲደርሰው፤ በሚሠራበት በግብርና ሚኒስቴር በኩል ደግሞ በህብረት ሥራ ትምህርት ራሽያ እንዲሄድ ዕድሉ ደረሰው። የራሺያውን ዕድል መርጦ ሁሉን ነገር ጨርሶ ለመሄድ አውሮፕላን ውስጥ ለመግባት በሩ ላይ ሲደርስ ከሀገር ውስጥ መውጣት አትችልም፤ ፓስፓርትህን አስረክብ ተባለ። የተጫነው ሻንጣ ራሽያ ሲሄድ እሱ አዲስ አበባ ካሳንቺስ የሚያውቃቸው ሰዎች ቤት ሄዶ አደረ።
ጠዋት የሚያደርገው ግራ ገብቶት በእግሩ እየሄደ ሳለ አንድ ሰው ጠርቶት ትከሻውን ያዘው። ትናንት ከአውሮፕላን ላይ አውርደውኛል፤ ዛሬ ደግሞ ሊጨርሱኝ ነው ብሎ ዞር ብሎ ሲያይ አስረኛ ክፍል አብሮት የተማረ የትምህርት ቤት ጓደኛው ልዑል ሰገድ ሆኖ አገኘው፤ ችግሩንም ነገረው። ልዑል ሰገድ በወቅቱ ካድሬ ስለነበረ ኢሚግሬሽን አንድ ኮሎኔል ፊት ወጣቱን ኃይሌን አቅርቦ ‹‹ታላቅ ወንድሜ ነው፤ እኔ ለአብዮቱ ስታገል አልተማርኩም፤ እሱ እንዳይማር ለምን ከአውሮፕላን ላይ አወረዳችሁት?›› ብሎ ይጠይቃል። ኮሎኔሉም ከጠረጴዛቸው ስር መሳቢያቸውን ስበው የኃይሌን ፓስፖርት አውጥተው ‹‹ከግብርና ሚኒስቴር ተጠቁሞ ነው እንጂ ከደህንነት የተሰጠ አቅጣጫ የለም›› ብለው ፓስፓርቱን ለኃይሌ አስረከቡት። በሳምንቱ ወደ ራሽያ ሄደ፤ ከሻንጣው ጋርም ተገናኘ።
ራሽያ አምስት ዓመት ተምሮ በማስተርስ ዲግሪ ተመረቀ። ሌሎቹ ተማሪዎች በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ እየሄዱ ቤተሰባቸውን ሲጠይቁ እሱ ግን ሀገር ቤት ብሄድ እዛው አስቀርተውኝ ትምህርቱ ይቋረጥብኛል በሚል ፍራቻ እናቱን፣ ባለቤቱን እንዲሁም ልጆቹን ሳያይ ቆየ። ከምረቃ በኋላ 20 ቀን ብቻ ቆይቶ ብዙ ሰዎች ወደ ሀገር ቤት እንዳትሄድ ብለው ቢመክርቱም ‹‹ሀገሬ ገብቼ ከአውሮፕላን ስወርድ በጥይት ግንባሬን ቢመቱኝ የምወድቀው ሀገሬ ላይ ስለሆነ ገብቼ የሚሆነው ይሁን›› በማለት ወደ ኢትዮጵያ መጣ።
ህብረት ሥራ
አቶ ኃይሌ ገብሬ ሉቤ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ግን የፈራው ሳይሆንበት፣ የሚወደውን የሚሠራበት ዕድል አገኘ። ‹‹አንቱ›› ያስባለውን ሥራ ወደመከወን ገባ። እኛም ‹‹አንቱ››› እያልን ወርቃማውን ታሪክ እናውሳ!
ከራሺያ ትምህርታቸውን ጨርሰው ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ አርዳይታ የካቲት 25 የኅብረት ሥራ ኢንስቲትዩት ለስምንት ዓመት አስተማሩ። ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘ በኋላ በ1984 ዓ.ም. በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ ሆነው እየሠሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሚመራ ቡድን ውስጥ የቡድን መሪ በመሆን የህብረት ሥራ አዋጅ ቁጥር 85/86 እንዲሁም 147/1991 አረቀቁ። በ1994 ዓ.ም. ቡድኑ ወደ ኮሚሽን ሲለወጥ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሆኑ።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲሠሩ የህብረት ሥራ ማህበራት፣ የገንዘብ ቁጠባ ማህበራት፣ የቤት ሥራ ማህበራት ወዘተ… አባላት ከማህበራዊ ተጠቃሚነት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አዋጁ እንዲፈቅድና በተግባርም በገንዘብ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ተግተው ሠርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ህብረት ሥራ እንደ አንድ የዕውቀት ዘርፍ ማደግ ስላለበት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአቅም ግንባታ ጋር በመነጋገር በዩኒቨርሲቲ ስር በትግራይ፣ በአምቦ እና በሀረማያ ላይ እንዲሰጥ አድርገዋል። አሁን እስከ ፒ. ኤች. ዲ ድረስ እየተሰጠ ይገኛል።
የህብረት ሥራ ትኩረት አግኝቶ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ቢሆንም ኮሚሽኑ ሲቋቋም የነበረበት
ተግዳሮት ከዚህ በፊት ሶሻሊዝምን ከመጥላት የተነሳ ህብረት ሥራ ማለት “ሶሻሊዝም” ነው ብሎ መጥላት ነበር። በማህበር የተደራጁ አካላት የገንዘብ ተጠቃሚ መሆን ሲጀምሩ ህብረት ሥራን እየወደዱት መምጣት ጀመሩ፤ አባላቱም እየበዙ መጡ። አቶ ኃይሌም የተገኘውን እመርታ ሲያነሡ ‹‹ይህ የተገኘው በቀላል አይደለም አመለካካት መለወጥ፣ ስርዓት መዘርጋት፣አቅም መገንባት፣ ካፒታል ማሰባሰብ እንዲሁም ይህንን ወደ አንድ ተቋም በማምጣት የኢኮኖሚ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ ማድረግን ይጠይቅ ነበር›› ይላሉ።
አቶ ኃይሌ ገብሬ በዚህ ረገድ የተገኘው እርምጃ ብዙ አንድምታ እንደነበረውም ያስታውሳሉ፤ ኮንድሚኒየም የተጀመረው በህብረት ሥራ ነው። ገርጂ እንዲሁም ዘነበወርቅ እና አካባቢው ላይ ባለ ሁለት ብሎክ ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ ህንጻ በመሥራት አሳይቷል። ከዚህ በተጨማሪ የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበርትን በማጠናከር ተግባር እንዲሁም የገንዘብና ብድር ተቋም ማህበራትን የማቋቋምና የማጠናከር ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህ ተግባራቸው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዘንድ ሙሉ የማኔጅመንት አባላቶቻቸው ተጠርተው ቀርበው ከተነጋገሩ በኋላ ‹‹ገጠሩም፣ ከተማውም ስለሚከብድህ ከተማውን እኔ ላግዝህ›› ስለተባሉና ሙሉ ትኩረታቸውን ገጠሩ ላይ እንዲያሳርፉ ሀሳብ ስለቀረበላቸው እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ ገጠሩ ላይ በማተኮር በኮሚሽነርነት ከሠሩ በኋላ ጡረታ ወጡ።
ከአቶ ኃይሌ ጋር ራሺያ የህብረት ሥራ የተማሩና በተለያዩ ቦታዎች አብረው የሥራ ባልደረባ የነበሩት አቶ ዘሪሁን ዓለማየሁ ምስክርነት ሲሰጡ ‹‹ ኃይሌ ሹም ሆኖ የሹም ትከሻ አሳይቶ የማያውቅ ቅን፣ ትሁትና ተጫዋች ሰው ነው። በብዙ አቅጣጫ ማየት የሚችል አስተሳሰብ ያለው፤ ሌት ተቀን ስለልማት የሚያስብ ሰው ነው። ሁልጊዜ የማስታውሰው አባባል አለው ‹ድህነት መቅኔያችን ውስጥ ገብቶል፤ ያለህብረት ሥራ እሱን ማውጣት አንችልምና ተግተን እንሥራ› ይለን ነበር። ተግቶ ይሠራልም፤ ያሠራልም። ለዚህ ነው ኃይሌ “የዘመናዊው የህብረት ሥራ አባት” የሚለውን መጠሪያ ያገኘው›› በማለት ያስታውሳሉ።
ከጡረታ በኋላ
ጡረታ ሲወጡ አራት ነገር አከናውናለሁ የሚል ግብ ይዘው ነበር። አንደኛው ሬሳቸው የሚወጣበት የግል ቤት ስለሌላቸው ቤት መሥራት። ሁለተኛው የተወለዱበት አካባቢ በመሄድ የህብረት ሥራ ማደራጀት እንዲሁም ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት። ሶስተኛ በጊዜው የነበረውን የኢህአዴግ እና የኦነግን ፍጥጫ ለማርገብ እንዲሁም ዕርቅ ለማምጣት ድንጋይም ተሸክመውም ቢሆን ጥረት ማድረግ። አራተኛ ዚግዛግ የሆነውን ህይወታቸውን ለሰው ልጅ ይጠቅም ከሆነ አንዳንድ ነገር ጫር ጫር አድርጎ ማስቀመጥ ነበር።
ጡረታ ከወጡ በኋላ ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ገጠር በመሄድ በሻኪሶ ወረዳ መጋዶ በሚባል መንደር የሬሳዬ መውጫ የሚሉትን መኖሪያ ቤት ሠሩ። በ28 ሰዎች እንዲሁም በሰላሳ ሺህ ካፒታል የተመሰረተ ሞርሞራ አካባቢ የተፈጥሮ ቡና ልማት ማህበር (ሞርዶፍ ኮፍ) በሚል መጠሪያ “ከቡና ዛፍ እስከ ቡና ስኒ ድረስ መስራት” የሚል ዓላማ ይዞ ከቡና ዛፍ ተከላ ጀምሮ እስከ ቡና ተጠቃሚው(ጠጭው) ድረስ ያለውን ሥራ በመሥራት የሚንቀሳቀስ ማህበር መስርተዋል። አሁን 110 ቋሚ አባላት እንዲሁም ግማሽ ቢሊዮን ካፒታል ያለው የህብረት ሥራ ማህበር ለመሆን ችሏል። ከምስረታው አንስቶ እስከ አሁን የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን እያገለጉ ይገኛሉ።
በተወለዱበት አካባቢ የህብረት ሥራ ማህበር ከመመስረት በተጨማሪ “ግርጃ ሩራል ዲቨሎፕመንት ኦርጋናይዜይሽን” የሚል የልማት ማህበር በማቋቋም በቦርድ ሰብሳቢነት ይመራሉ። ማህበሩ ትምህርት ቤት ይጠግናል፣ አዲስ ትምህርት ቤት ይሠራል፣ ንፁህ ውሃ አቅርቦት ላይ እንዲሁም እናትና አባት የሌላቸውን ልጆች የሚረዳ ማህበር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎችም ማህበራዊ ሥራዎች ይሠራል።
አቶ ኃይሌ ገብሬ ሉቤ በግላቸው የሚከተሉት አሳታፊ የአመራር ስልትን እንደሆነ ይናገራሉ። ሀሳብ ከገበሬዎችም ሆነ አብረው ከሚሠሯቸው እንዲመጣ ይፈልጋሉ፤ በመጨረሻ እሳቸው ከወሰኑ በኋላ ወደ ተግባር ይገባሉ፤ ችግር ካለው በጊዜ ሂደት ይስተካከላል የሚል መርህ አላቸው። በሥራ ላይ ስላጋጠማቸው ተግዳሮት ሲናገሩ በህይወቴ ከተጀመረ ሥራ ላይ ገብቼ አላውቅም። የህብረት ሥራ ለመሥራት ሀገረ ሰላም ስሄድ ጀማሪው ነኝ፣ አርዳይታ ኢንስቲትዩት ሲቋቋም ከጀማሪዎቹ ነኝ፣ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ሳቋቋም ከባዶ ነው። 100 ብር ከኪሴ አውጥቼ መዝገብ ገዝቻለሁ፤ 200 ብር አውጥቼ ማህተም በመግዛት ህብረት ሥራ ኮሚሽን አቋቋምኩኝ ብል ማንም ኢትዮጵያዊ ላያምነኝ ይችላል። በሥራዬ አጋጣሚ ትልቅ የተማርኩት ነገር ተግዳሮትን መሸከም ነው። በቦርድ ሰብሳቢነት በመሠረትኩት ማህበር ውስጥ ቡና የሚሰጣበት እንጨትን ሚስማር መግዣ አጥቼ ሐረግ ቆርጬ ነበር የማስረውና ቡናው እንዲደርቅ አደርግ የነበረው በማለት ያስረዳሉ።
ጡረታ ሲወጡ እሠራዋለሁ ካሉት ውስጥ ዚግዛግ የሆነውን ያሳለፉትን ህይወታቸውን መጻፍ የሚለው አንዱ ነበር። አሁን የተለያዩ ጽሑፎች እየጻፉ ነው፤ በተጠናከረ መልኩ ጽፈው ለማጠናቀቅ በመትጋት ላይ ይገኛሉ።
ሽምግልና
ጡረታ ከወጡ በኋላ አከናውነዋለሁ ብለው ስለነበረው የሽምግልና ተግባር ሲናገሩ ‹‹ሽምግልናው የተጀመረው በአቶ መለስ ጊዜ ጥቅምት 13 ቀን 2001 ዓ.ም. አካባቢ ነው። ወደ 175 የሀገር ሽማግሌዎች ከመላው ኦሮሚያ ከኬኒያ፣ ከአሜሪካ፣ ከሌላም ተሰባስበን ኢምፔሪያል ሆቴል ኢህአዴግን ከኦነግ ጋር ለማቀራረብ ችግሩን እንዴት እንፍታው በማለት ከተማከርን በኋላ አቶ መለስ ጋር ቀረብን። አቶ መለስ ‹የሀገር ሽማግሌዎች የምትሉትን እቀበላለሁ፤ ኦነግ ሕገ መንግስቱን ተቀብያለሁ ካለ ለመነጋገርም ሆነ ከአሸባሪነት ለመሰረዝ ዝግጁ ነኝ› አለ። ከእኛ አንድ ቡድን በቄስ ኢተፋ ጎበና ሰብሳቢነት የሚመራ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ እና አቶ አበራ ቶላ ያሉበት አንድ ቡድን ሱዳን በመሄድ አቶ ዳውድን አነጋግረው ሕገ መንግስቱን እንደሚቀበሉ ተነግሯቸው መጡ። ምላሹን ለአቶ መለስ ሲነገረው ‹ይህ ቃል በደብዳቤ ሆኖ በጽሑፍ ይቅረብልኝ። ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ ይወስን እንዳልል መሰብሰቡ ይከብዳል፤ በሥራ አስፈጻሚ ብል ለውሳኔ ያንሳል፤ በማዕከላዊ ኮሚቴያቸው ብቻ ወስነው ደብዳቤ ይስጡኝ። ይህ ከሆነ በኋላ ኦነግ ከአሸባሪነት እንዲነሳ ፓርላማ ለውሳኔ አቀርባለሁ። እስረኞችም እንዲፈቱ አደርጋለሁ። በእናንተ በሽማግሌዎች ፊት ቃል የምገባው ከዛሬ ጀምሮ ኦነግ ካልተኮሰ በስተቀር አንተኩስም፤ እንዳይተኩስ እናንተም ከልክሉልኝ› ብሎን ነበር›› በማለት የተኩስ ማቆም ሥራ ተጀምሮ እንደነበረ ይገልጻሉ።
በመቀጠልም ሶስቱ የቡድኑ አባላት ሱዳን ሄደው ሁኔታውን ለአቶ ዳውድ ያስረዱ ቢሆንም በጽሑፍ ማድረጉ ላይ ዘገየ። ክቡር አምባሳደር ብርሃኑ ታመሙ፣ ሞቱ፤ አቶ መለስም ሞቱ ሳይሳካ ቀረ። ጥረቱ ግን አልቆመም በአቶ ኃይለማሪያም ጊዜም ተሞክሮ ነበር። እንደ አቶ መለስ ጊዜ ግን ሊሆን አልቻለም። ከለውጡ በኋላም ከኦነግ ጋር መቀራረብ ለማምጣት ሰፊ የሽምግልና ሥራ እንደተሠራ በመግለጽ ጥረቱ የቆየ እንጂ በጥቂት ቀን መጥቶ የተፈጸመ ድርጊት እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ሽምግልና በጣም ከባድ ነገር ነው የሚሉት አቶ ኃይሌ ገብሬ ሉቤ ሽማግሌ የሚሆን ሰው ከየትኛውም ወገን መወገን የለበትም፣ ስለሽምግልናው ሳይወራ በቅድሚያ ሀሳባቸውን መቀበልና ሁለቱን ወገን በቅድሚያ ማለሳለስ ከዚያም ማቀራረብ ይገባል። የሽምግልና ሂደት ገና እንደተጀመረ የተወጣጠረው ነገር ሳይለሳለስ ወደ ሚዲያ መሄድ ችግር ይፈጠራል በማለት ይመክራሉ።
በሽምግልና ተግባር ላይ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን አብረዋቸው የተሳተፉት ሼክ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ስለ አቶ ኃይሌ ሲናገሩ በሽምግልና ከተገናኘንበት ጊዜ ጀምሮ ለሀገር ሰላም፣ ደህንነትና ዕድገት የሚያስቡ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። ንቃትና ቅንነት ያላቸው እንዲሁም ችሎታ ያላቸው አሸማጋይ መሆናቸው መመስከር እችላለሁ። ወደ ወለጋ ሰላም ለማምጣት ባደረግነው ጉዞ እሳቸው ሰብሳቢ ሆነው ያደረጉት ተጋድሎ በቀላሉ የሚታይ አይደለም በማለትያስረዳሉ። በሽምግልናው ሂደት አባል በመሆን የተሳተፉት ወ/ሮ መኪያ ማሚዮ ደግሞ ሀገር ወዳድና የእውነተኛ አባት ስሜት ያላቸው ተስፋ የማይቆርጡ አሸማጋይ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ በማለት ይገልጻሉ።
ቤተሰብ
ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ትዳር መስርተው በመኖር የስድስት ሴት ልጆች አባት ሆነዋል። ሶስቱ ልጆች የራሳቸው ሥራ የሚሰሩ ሲሆን ሶስቱ ደግሞ ሞርዶ ኮፍ በሚል በአስር ልጅ፣ የልጅ ልጅ እና አያት ስም በተቋቋመው ድርጅት ውስጥ የሥራ ድርሻ ኖሯቸው እየሠሩ ይገኛሉ። ባለቤታቸው ወይዘሮ ድንብላል እንዳለ ብዙ ችግሮችን ከእሳቸው ጋር እንዳሳለፉና አሁን ላሉበት ደረጃ መድረስ ከፍተኛውን ድርሻ እንዳበረከቱ ከምስጋና ጋር ያወሳሉ።
ሽልማትና ዕውቅና
ለሰው ልጆች ደግ መሥራት፤ ለሰው ልጅ መልካም ሥራ መሥራት የሚል የሕይወት መመሪያ ያላቸው እንግዳችን ከልጅነት እስከ እርጅና ድረስ የሠሩበት ቦታ ላይ ሁሉ ሽልማት፣ ዕውቅና እና ምስጋና ሲሰጣቸው መቆየቱን ይናገራሉ። በሥራ ፈጣሪነት ሽልማት ከማግኘታቸው በተጨማሪ ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የክቡር ዶክተር ዲግሪ ተቀብለዋል።
ምክር
ወጣትነት ንፁህ ልብ ያለበት ጊዜ ስለሆነ አራት ነገሮችን ወጣቶች ማገናዘብ እንደሚኖርባቸው ያስረዳሉ። አንደኛው ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል፤ ያለዕውቀት የሚሠራ ሥራ ሄዶ ሄዶ የሚጎዳው ራስን ነው። ሁለተኛ ወጣቶች ለማንኛውም ነገር ውሳኔ ሲሰጡ ምክንያታዊ መሆን ይገባቸዋል። ሁለትና ሶስት አማራጭ በማምጣት ደጉ አማራጭ የቱ ነው ብሎ በምክንያታዊነት በመተንተን መምረጥ ያስፈልጋቸዋል። ሶስተኛው ከሽማግሌዎች ተሞክሮና ምክር መውሰድ፣ ሽማግሌዎቹ ያሳለፉትን ስህተት አለመድገም እንዲሁም መልካም ልምዳቸውን መጠቀም ይገባል። አራተኛ ወጣቱ በቅንነት፣ በታማኝነት እና ሀገርን በመውደድ መሥራት ይጠበቅበታል በማለት ይመክራሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች። ትልቅ ብቻ ሳትሆን ብዝሃነት ያላት የባለ ብዙ ሕዝብ ሀገር ነች። ሀገሪቷ ውስጥ ሁለት ስቃዩ የሚጠዘጥዝ ንፍፊት ያለበት ሁኔታ አለ። አንደኛው ሃይማኖት ነው፤ በሃይማኖት ዙሪያ መቻቻል ብቻ ሳይሆን መቀራረብና አብሮ መሆን ይገባል። የሃይማኖት አባቶች የእውነት ተቀራርበው ሀገራቸውን አንድ የማድረግ ሥራ መሥራት አለባቸው። ይህ ሲሆን ትልልቅ ችግሮችን በቀላሉ አሸንፎ መውጣት ይቻላል። ሁለተኛው ንፍፊት የፖለቲካ አመለካከት ላይ ያለ ነው። ፖለቲካ ከጊዜ ጋር ይቀያየራል፤ ስለዚህ ለሰው ልጆች እኩልነት፣ ልዕልና እንዲሁም ብልጽግና በማሰብ የእኔ ብቻ ካልሆነ ብሎ ከማለት ለሀገር ይበጃል በሚል በመመካከር ወደ ተሻለ መንገድ ማሸጋገር ይገባል። ፖለቲከኞቹ ይሄን መተግበር ካልቻሉ ደም በደም መሆን ነው የሚያስከትለው፤ በተለይ የወጣቱ ደም መጫወቻ ነው የሚሆነው። ለሀገሪቱ የሚጠቅመው የወጣቱን ላብና ጉልበት በመጠቀም ልማትና ዕድገት ማምጣት ነው በማለት ለሃይማኖት አባቶችና ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ምክር ይሰጣሉ።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ደግሞ አንዴ ወደ ላይ ስንሄድ ስንዋጋ፣ አንዴ ወደ ታች ስንሄድ ስንዋጋ ሀገራችንን ዛሬ ባለችበት ሁኔታ ገንብተናል። ያለፈው ጊዜ እውነቱ ወጥቶ ይቅር ተባብሎ መተው፤ እንዲሁም እንዳይደገም በማድረግ አንድነትን መጠበቅ ይገባል። ለይቅርታ ቦታ ሳይሰጥ፣ የባለፈውን ቁስል እየጎረጎሩ መገዳደል ሀገርን ይጎዳል። ህብረት ከፈጠርን የዛሬ አስር ዓመት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላቅ አስር ሀገሮች አንዷ ትሆናለች። የዛሬ ሃያ ዓመት ትስስራችን ጎልብቶ ህብረታችን ከጠነከረ ከዓለም ትልቅ ሀገራት ውስጥ እንገባለን። ለዚህም እግዚአብሔር ይረዳናል በማለት ኢትዮጵያውያን ህብረታቸውን እንዲያጠናክሩ ይመክራሉ።
ዝግጅት ክፍላችን ክቡር ዶክተር ኃይሌ ገብሬ ለኢትዮጵያ ካላቸው መልካም ህልም አንጻር በሥራ ዘመናቸውም ይሁን በጡረታ ዘመናቸው ለሠሩት መልካም ሥራ ሁሉ ዝግጅት ክፍላችን እያመሰገነ፤ ኢትዮጵያ እንድትደርስበት የሚፈልጉትን ከፍታ ማየት እንዲችሉም መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
ስሜነህ ደስታ