ሽብርተኛው እስከ መቼ በህዝብ ህይወት ?

አሸባሪው ህወሓት ራሱን የትግራይ ህዝብ ዘብ፣ የትግራይ ህዝብ ጠባቂ፤ እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል፤ ይህን ማደናገሪያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደጋግሞ ሲዘምረው ይሰማል። እውነታው ግን፣ አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ህዝብ በእየ ትውልዱ ህይወቱን እየገበረለት እድሜውን ማራዘሚያ ህዝቡንም መደበቂያ ካደረገው ሁለት ሶስት ሥርዓቶች ምስክር ናቸው። ዛሬ ዛሬ ድረስ ደግሞ ዘርፎ በህዝቡ ጉያ እየተሸሸገ ዳግም ዋጋ ሲያስከፍለው እንጂ ጠብ ያለለት ነገር የለም። በመሆኑም ህወሓት የመጀመሪያውን የህዝብ ጠላትነቱን ያስመሰከረበት፣ እድሜውን እያራዘመ ያለው ዋጋ በከፈለለት በትግራይ ህዝብ ነው። ይህንን ሀቅ ራሳቸው የትግራይ ተወላጆችና ህወሓትን በቅርበት የሚያውቁ ታጋዮች ይመሰክራሉ።

ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ህወሓትን ከመሠረቱ ቀደምት ታጋዮች መካከል ይጠቀሳሉ። ከ1968 ዓ.ም እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ በሊቀመንበርነት፣ ከ1971 ዓ.ም እስከ 1976 ዓ.ም ደግሞ የድርጅቱ ወታደራዊ አመራር ሆነው አገልግለዋል። ከ1976 ዓ.ም በኋላ ከድርጅቱ ጋር በተፈጠረ የሀሳብና የዓላማ ልዩነት ድርጅቱንም ሀገራቸውንም ትተው ወጥተዋል፤ ለውጡን ተከትሎ በውጭ ለሚገኙ ፖለቲከኞች የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ ፖለቲኮች መካከል አንዱ ናቸው። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተርም በመሆን ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።

የትግራይ ህዝብና ህወሓት፣ ድርጅቱ ስልጣን ላይ በቆየበት 27 ዓመት ሙሉ ሆድና ጀርባ ሆነው እንደዘለቁ የሚናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፣ ህወሓት ስንል ለሀገር አንድነት፣ ነጻነትና እድገት፣ ህዝብን ከጉስቁልና ሕይወት ለማውጣትና ፍትህ ይሰፍናል በሚል በቅንነት የታገሉ፣ ለትግራይ ህዝብና ለሀገራቸው ህይወታቸውንና አካላቸውን የከፈሉ በርካቶች መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበት፣ በርካቶችን ከጥቂት ስግብግብ ለይቶ ማየት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። አያይዘውም ድርጅቱ የተቋቋመበት ቀዳሚው የትግል ዓላማ፣ የህዝብን ህይወት መለወጥ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ነገር ግን፣ ይህ ብዙዎች ህይወታቸውን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አካላቸውን የገበሩበት ትግልና ድርጅት ኋላ ላይ የጥቂት ባለስልጣናት መጠቀሚያ ሆኗል ይላሉ ዶ/ር አረጋዊ።

እርሳቸው እንዳሉት፣ ቡድኑ ለህዝብ ቆሜያለሁ ቢልም ለህዝብ ላለመቆሙ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታትና ከፌዴራል ስልጣን ተገፍቶ ትግራይ ከመሸገበት ጊዜ አንስቶ ጫካ እስከገባበት ጊዜ ድረስ ያለው ተግባሩ ምስክር ነው። የቡድኑ ከእኩይ ሥራው አለመመለስ የትግራይ ህዝብን ከኑሮ መጎሳቀል በላይ በጦርነትም ገፈት ቀማሽ እንዲሆን አድርጎታል።

እንደ ዶ/ር አረጋዊ ሁሉ፣ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ኢህአዴግን የታገሉት፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ በ1983 ዓ.ም ህወሓት ወደ ስልጣን ሲመጣ የዴሞክራሲና የእኩልነት ጥያቄዎችን እንመልሳለን፣ ፍትሐዊነት  እናሰፍናለን፣ በ10 ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያውያንን በቀን ሶስቴ እናበላለን የሚል ማኑፌስቶ ይዞ እንደነበር በማስታወስ፣ እንኳን ህዝቡን በቀን ሶስቴ ሊያበላ ቀርቶ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አርሶ የሚበላውን አርሶ አደር በጉልበት ከመሬቱ እንዳፈናቀልና፣ በትግራይ ተወላጅ ስም መከላከያን ጨምሮ ሁሉንም ተቋማት ተቆጣጥሮ በርካታ የሀገር ገንዘብ እንደመዘበረ ይናገራሉ። አክለውም ጁንታው የህወሓት ቡድን ከልማት ባንክና ከሌሎች ባንኮች እጅግ በርካታ የሀገር ሀብት በመመዝበር ለራሱ የሚጠቀምባቸውን ህንጻዎች ማሰሪያ ያዋለ፣ አብዛኛውን ደግሞ ወደ ውጭ ባንኮች በዶላር ቀይሮ በመላክ ሀገርን ለኪሳራና ለውድቀት የዳረገ መሆኑን ይገልጻሉ።

ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም /IMF/ ባደረገው ጥናት ቡድኑ ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ ከኢትዮጵያ መውጣቱን ማረጋገጡንም በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ጁንታው የህወሓት ቡድን፣ ህዝብ በብሔር ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ በስትራቴጂ የተደገፈ እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ ዜጎችን ሲያኮላሽና ሲያሳድድ ቆይቷል። ከስልጣን ከተወገደም በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ለመግደልና ሀገርን ለማተራመስ ያደረገው ሙከራ ሳይበቃው የመከላከያ ሰራዊትን በማጥቃት በመጨረሻም የትግራይ ህዝብን አሁን ላለበት መከራ የዳረገ፤ እጅግ አደገኛ አሸባሪ ድርጅት መሆኑን አቶ ታዬ ይናገራሉ።

ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የህወሓት ባለስልጣናት የሚሰሩትን ሴራና ዝርፊያ በሰራባቸው የግል ጋዜጦች በማጋለጥ የሚታወቀው ጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋ ማርያምም የዶ/ር አረጋዊንና የአቶ ታዬን ሃሳብ ያጠናክራል። ጋዜጠኛ አርዓያ ቡድኑ፣ በኢትዮጵያና በትግራይ ተወላጆች ላይ ከበረሃ ትግል አንስቶ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የሰራቸውን ዘግናኝ ግፎችና ዝርፊያዎችን ባጋለጠበት “ከህወሓት ጓዳ” በተሰኘ መጽሐፉ፣ ህወሓት፣ በእርግጥም የተቋቋመለት ቀዳሚ ዓላማ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በትጥቅ ትግል ገርስሶ ለመጣልና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት የነበረ ቢሆንም፣ በብሔር ላይ ተንጠልጥሎ የተደራጀው ኢህአዴግ አንድም ቀን ለህዝብ ፋይዳ ያለው በጎ ስራ ሠርቶ እንደማያውቅ ይናገራል።

ህወሓት፣ ገና ከጅምሩ በግፍ ላይ እየተረማመደ የመጣ ድርጅት ነው የሚለው ጋዜጠኛ አርዓያ፣ ድርጅቱ ገና በልጅነት እድሜው፣ ‹‹በትግራይ ውስጥ ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ሊያደርጉ ይችላሉ›› በሚል ስጋት ብቻ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሕብረት አባልና ፊውዳል ናችሁ›› በሚል፣ ከአርባ ሺህ በላይ ንጹህ የትግራይ አርሶ አደሮችን በየጫካው ጉቶ እያስደገፈ እንደረሸናቸው አስነብቧል።

አርዓያ “ከህወሓት ጓዳ” ላይ እንዳሰፈረው፣ “ህወሓት በ1983 ግንቦት ወር አዲስ አበባን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ የክፋትና የሌብነት ባሕሪው መጋለጥ ቢጀምርም፣ ድርጅቱ ገና ከምስረታው አንስቶ በግፍ ላይ እየተረማመደ የመጣ፣ ሀገር እየመዘበረና እየዘረፈ ክንዱን ያፈረጠመ፣ ጥቂት ግለሰቦችና ቤተሰቦቻቸው ከሀብት ጥግ የደረሱበት የማፊያ ቡድን ነው።”

ጋዜጠኛ አርዓያ እንዳስነበበው፤ የማፊያ ቡድኑ አባላት፣ ህጋዊ ሥርዓትን ባልተከተለ መንገድ በሀገሪቱ ያሉ አትራፊ የንግድ ዘርፎችን በብቸኝነት ሲቆጣጠሩና የንግድ ቤቶቹንም የዘመድ ቤት ሲያደርጉ፣ ከንግድ እንቅስቃሴው ሀገር ታገኝ የነበረውን ግብርና ቀረጥ ቅርጥፍ አድርገው ሲበሉና እንደ ኤፈርት ያሉ ቁልፍ የንግድ ተቋማትን እንደግል ካዝናቸው ሲበዘብዙ፣ ብሎም በህዝብ ሀብት የግል ህንጻዎችን ሲገነቡ ለምን የሚላቸው አካል አልነበረም፤ ለምን የሚል ከተነሳም፣ አብሮ የታገለና የሰራ ጓድ እንኳ ቢሆን፣ የጭካኔ እጃቸውን ያለ ርህራሄ ከማንሳት ወደ ኋላ አይሉም።

በዚህ ሁኔታ ብዙዎች ለህዝብና ለእውነት የቆሙ ታጋዮችን ገድለዋል፤ ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ለስቃይ ዳርገዋል፤ የፍትህ አካላትን በገንዘብ በመደለል በርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ፍርደ ገምድል ውሳኔ አሰጥተዋል። በቃኝን የማያውቁት የዚህ ስግብግብና ገዳይ ቡድን አባላት፣ በቅንጡ ሆቴሎች ውስኪ ሲራጩና የሀገርን ሀብት በማናለብኝነት ሲበትኑ፣ ንጹህ ውሃ ማግኘት ብርቅ ለሆነባቸው የትግራይ እናቶች የጉድጓድ ውሃ በመቅዳት የጎበጠውን ወገብ ቀና ሊያደርጉ አልቻሉም።

የትግራይ ህዝብ ይህን ስግብግብ ጁንታ ከመሃሉ ነቅሎ ማውጣት ያልቻለው አቅም አጥቶ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፣ አክለውም፣ በስግብግብ ቡድኑ የሚመራው ህወሓት ህዝቡን እርስ በእርሱ በመከፋፈል፣ የአንድነት መንፈስ እንዳይኖረው፣ እንደ ጠላት እንዲጠባበቅና እንዳይተማመን አድርገውታል ይላሉ። እንደ እርሳቸው ሃሳብ፣ የትግራይ ህዝብ በተለይም፣ አንድ ለአምስት በሚል መዋቅር አደራጅተው፣ የአንዳንዱን የአንድ ለአምስት መዋቅር አለቆችን የሚይዝ ሌላ አንድ ለአምስት በማዋቀር፣ እገሌ ምን አለ? የሚለውን እየቆጠሩና ለምን ይቺን ተናገርክ? ለምን ይሄን ሰራህ? ብለው ቀንና ማታ እየተቆጣጠሩ ነጻነቱን የገደቡት ህዝብ ነው።

የትግራይ ህዝብ ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደተጎዳ የሚናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፣ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው የልማት እንቅስቃሴ ከትግራይ ክልል የልማት እንቅስቃሴ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው ይላሉ። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ የተደረጉ ጥቂት የልማት እንቅስቃሴዎችም ቢሆኑ፣ ቡድኑ ሀብት እንዲያግበሰብስ ምክንያት ሆኑ እንጂ መሬት ወርደው አልታዩም፤ የህዝቡን ህይወትም አላሻሻሉም። በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ እርሻውን ሊያሳድግም ሆነ በልማት ሊሳተፍ አልቻለም። ህዝቡ ዛሬም ከፈረንጅ ከሚመጣ የልመና እህል አልተላቀቀም። ይህንንም ቢሆን ማግኘት የሚችለው የአንድ ለአምስት መዋቅር አባል በመሆን ታዛዥነትና ታማኝነቱን ሲያሳይ ብቻ ነው። የዚህ መዋቅር አባል ያልሆነ ታማኝ ስላልሆንክ አታገኛትም እየተባለ በቀይ ባህር ወደ ስደት በሊቢያ ምድረ በዳ እያለቀ ያለ ህዝብ ነው።

የትግራይ ህዝብ አሁን ያለበት ሁኔታ ደግሞ ካለፉት ጊዜያት ይልቅ በእጅጉ አሳዛኝ ነው የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ፣ ህዝቡ ከዙሪያው የሚመጣ ጥይት እየቀሰፈው፣ እነርሱ ራሳቸው ደግሞ ከመሃል ሆነው ከመከላከያ ጋር ተባብራችኋል በሚል እየገደሉት እንደሚገኙ ይናገራሉ፤ አያይዘውም፣ ራሳቸው ገድለውት ሲያበቁ የኤርትራን ጃኬት፣ የመከላከያን ኮፍያ ለብሰው ወይ የአማራን ዝናር ይዘው እነርሱ ገደሏቸው እያሉ ህዝብ ማታለሉን ቀጥለውበታል ይላሉ።

አቶ ታዬም በተመሳሳይ፣ ጁንታው አሁንም ህዝቡን በገዛ ክልሉ ላይ ከመንግሥት ጋር ወግናችኋል ያላቸውን እያሰረ፣ እየገደለና አፈናዎች እየፈጸመ መሆኑን፣ ከዚህም በተጨማሪ እራሱ ጁንታው አንዳንዴ በመከላከያ ሰራዊቱ ልብስ አንዳንዴም በኤርትራ መከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም ሲፈጽም የነበረውን ወንጀል በሁለቱ አካላት እያላከከ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ።

ህወሓት ባለፉት ዓመታት፤ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም ሆነ ከስልጣን ከወረደም በኋላ “የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሓት ማለት ነው” “እኛ ከሌለን የትግራይ ህዝብ ሊኖር አይችልም” የሚል ሰበካ ሲያደርግ እንደነበር በመጥቀስ ህዝብና የፖለቲካ ፓርቲ በምንም መለኪያ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፣ ህዝብ ፈጽሞ በፖለቲካ ፓርቲ ሊለካ እንደማይችልም ሊታወቅ ይገባል ይላሉ። በተለይም፣ ጁንታው መከላከያ ሰራዊቱን ካጠቃ በኋላና መንግሥትም የህግ ማስከበር ዘመቻውን አውጆ ቁንጮ ባለስልጣናት ከተገደሉ፣ ግማሾቹ ከተያዙና ገሚሱም ከተበታተነ በኋላ ለአርባ ዓመታት በዘረጋው መዋቅር የተለየ ሰበካ በማድረግ ኅብረተሰቡን የማወናበድና የተለያየ አቅጣጫ ለማስያዝ ብዙ ጥረት እንዳደረገ በመጥቀስ፤ ይህን ቡድን ታግሎ ለመጣል በዋናነት የህዝብ አንድነት ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

ጁንታው ያፈራረሳቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት፣ መንገዶች ለመስራት ኤሌክትሪክ ለመዘርጋት፣ የቴሌኮም ፋሲሊቲዎችን ለማመቻቸት እና ችግር ላይ ያለውን የትግራይ ህዝብ ለመርዳት መንግሥት ከመደበኛ በጀት ውጪ ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ታዬ፣ ይህ ሀብት ከሁሉም ክልሎች በጀት የተቆረጠ፣ ትናንት የተፈጠረው የሲዳማ ክልል ሳይቀር አስተዋጽኦ ያደረገበት ለትግራይ ህዝብና ለትግራይ መልሶ ግንባታ የተበረከተ የኢትዮጵያ ሀብት መሆኑን ማወቅ ይገባል ይላሉ።

አያይዘውም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትግራይ ህዝብ በስሙ ተነገደ እንጂ እንደየትኞቹም የሀገራችን ክልሎች በልማትም ቢሆን በፖለቲካ የተለየ ጥቅም ያላገኘ የሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ችግርን አብሮ የተቸገረ፤ ከሌላው ተለይቶ እንደታየ እንዲያስብና የመጠቃት ስሜት እንዲሰማው የተደረገ ህዝብ መሆኑን በመረዳት አሁንም ከዚህ በፊት በነበረው አካሄድ ከህዝቡ ጋር መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፤ የትግራይ ህዝብም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ሲደግፈውና በችግሩ ጊዜ አብሮ ሲቆም እንደነበር ቆም ብሎ የሚያይበት ጊዜ መሆን አለበት የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ዶ/ር አረጋዊ በበኩላቸው፣ መንግሥት የተኩስ አቁም ጥሪ እናድርግ፣ የኮሙኒኬሽን አውታሮች፣ የትራንስፖርት መስመሮች ይከፈቱ ቢልም እነርሱ ግን ይህንን አጋጣሚ ለራሳቸው ስግብግብ ዓላማ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ በማንሳት፣ በቅርቡ እንኳ የትግራይን ህዝብ ለመደገፍ የተሰማሩ ቅን ዜጎችን ገድለው ሬሳቸውን ለጅብ ሰጥተው፣ ያንን ያዩ ሰዎች ደግሞ ከጅብ አስጥለው ቢቀብሯቸው እንደገና ቆፍረው አውጥተው የጣሉ፤ ሰይጣናዊ ሥራ እየሰሩ ያሉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ይህን ከመሰለው እኩይ ተግባራቸው የተነሳ ህዝቡን የባሰ ችግር ውስጥ፣ ጭንቀትና ፍርሀት ውስጥ እንዲገባ እያደረጉት እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር አረጋዊ፣ ይህ ህዝብ ሥነ ልቡናው ተሰብሯል፤ ድምጹን ሊያሰማ የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው፤ ይህን ህዝብ ከዚህ ሁኔታ ለማላቀቅ የእኛ የህዝብ ፍቅር ያለን ሰዎች፣ ጋዜጠኞች ምሁራንና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት አለብን የሚል ጥሪ ያቀርባሉ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ በአንድነትና በተደራጀ ሁኔታ ከተንቀሳቀሰ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ያላቸውን ተስፋም ይገልጻሉ። ከዚሁ ጋር አያይዘው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡ ሰሞን ወደ መቀሌ ያደረጉትን ጉዞ አንስተው፤ በወቅቱ ህዝቡ በደስታ ብዛት ጥይት እየተኮሰና አበባ እየበተነ እንደተቀበላቸው ያስታወሱት ዶ/ር አረጋዊ፣ በወቅቱ በነበረው የአያያዝ ክፍተት ሽብርተኛው ቡድን ተከበሃል መጡብህ የሚል ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ድሉን ቢቀለብስም፣ በወቅቱ ከነበረው የህዝቡና የወጣቱ ፍላጎት በመነሳት ይሄንን ሁኔታ ማስተካከል፤ በአንድ ተደራጅቶ ተጽዕኖ እንዲፈጥር ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የሽብርተኛ ቡድኑ ስራ ቀቢፀ ተስፋ ነው ያሉት ዶ/ር አረጋዊ ቡድኑ የሚታገለው ለመገንጠል ከሆነ ዓለም ወደ አንድነት እየተሰባሰበ፣ አውሮፓ፣ እስያ፣ ደቡብና ሰሜን አሜሪካ ወደ አንድ በመጡበት፤ የዓለም መተሳሰር እየተጠናከረ ባለበት በዚህ ዘመን መገንጠል የሚባል ኋላ ቀር ትርክትን የትግራይ ህዝብ ፈጽሞ እንደማይቀበለውና፣ ቡድኑ ራሱ የመገንጠልን ሃሳብ የትግራይ ህዝብ እንደማይቀበለው ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ያረጋግጣሉ። የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ እምብርት መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል ያሉት ዶ/ር አረጋዊ የአክሱም ሐውልት፣ የአክሱም ጺዮን ቤተክርስቲያን፣ የአል ነጃሺ መስጊድ ለዚህ ምስክሮች እንደሆኑም አክለው ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም ዶ/ር አረጋዊ ቡድኑ፣ ይህን ተስፋና ዓላማ የሌለው የአጭር ጊዜ ሩጫ ሮጦ መጥፋቱ አይቀሬ ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ይኖራል፤ አንድነቱን አጠናክሮ ከዚህ የአፈና ኑሮ ወጥቶ ነጻነቱን ያውጃል ብለዋል።

እኛም ጽሑፋችንን አቶ ዛዲግ አብርሃ በአንድ ወቅት ለኢዜአ በሰጡት ቃል በተናገሩት ቃል ቋጨን “ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ያለው የትግራይ ህዝብ ከአሸባሪው ህውሃት በፊትም አለ ከህወሓት በኋላም ይቀጥላል!”

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

Recommended For You