ይህንን የሚያክል ርእስ ይዞ አደባባይ መውጣት ከባድ ነው። ይሁን እንጂ እድሜ ለተመራማሪዎቹ ያንን ያህል የሚያስቸግር አይደለም። እንደምናውቀው በአለማችን ያለ ልክ ከሚቆለጳጰሱ ቃላት (ጽንሰ ሀሳቦች) መካከል አንዱ፣ ምናልባትም ቀዳሚው “ዲሞክራሲ” ነው። በመሆኑም የሁሉንም ልዩ ትኩረት እንዳገኘ፤ በሁሉም እንደ ተጓጓለት፤ ሁሉም እንደ ተመኘው፤ ለሁሉም እኩል እንዳልሆነ . . . እዚህ፣ ዛሬ ድረስ ዘልቆ ይገኛል።
እንድገመው፣ “ዲሞክራሲ”ን ሁሉም እንዳሻው የሚተረጉመው፣ ሁሉም እንዳሻው የሚተገብረው፣ ሁሉም እንዳሻው የሚዘውረው . . . ጽንሰ ሀሳብ ነው። ኢድ አሚንም ዲሞክራት ነበር፤ ሳዳምም ዲሞክራት ነበሩ (ቢያንስ ራሳቸውን ዲሞክራት አድርገው ይቆጥሩ ነበር)፤ አዶልፍ ሂትለርም አስጨብጭቧል። ቆጥረን አንጨርሳቸውም።
“ዲሞክራሲ” ማንም እንደ ፈለገው ያድርገው እንጂ እሱ እንደሆነ ግን ያው ዲሞክራሲ እንጂ ሌላ ሊሆን አልቻለም፤ አይችልምም። በመሆኑም ስለ ዲሞክራሲ ምለው፣ በዲሞክራሲ ስም ቆርበው፣ ዲሞክራሲን ባህላቸው ያደረጉ አገራት (መሪዎች) ተለይተው ይመሰገኑበታል፤ ይሞገሱበታል፤ ይሸለሙበታል፤ ከሁሉም በላይ ለህዝባቸው ከአንጀቱ ጠብ የሚል ተግባር ይፈፅሙለታል።
ከዚሁ አንፃር፣ እንደ ምንጊዜውም፣ ዘንድሮም “ዲሞክራሲ” በአገራት አማካኝነት ያለበት ሁኔታ ተሰፍሯል፤ ተለክቷል፤ ብስል ተጥሬው ታውቆም ተበጥሮም ተንጓሏል። ደረጃና ጥራቱም በመቶኛ ተቀምጧል።
ባለ ጉዳዮቹ እንደሚሉት በአንድ አገር ላይ የተሟላ ዲሞክራሲ (Full democracy) አለ ለማለት የሲቪልም ሆነ መሰረታዊ የፖለቲካ ነፃነቶች መኖርና መከበራቸው ብቻ አይደለም፤ እነዚህና ሌሎች መብቶች በዛ አገር ላይ ባህል ሆነው ሲገኙ እንጂ።
የአንድ አገር ዲሞክራሲ በመሪዎች መለዋወጥ ላይ ከተንጠለጠለ፣ እሱ በደረጃም፤ በጥራትም እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይደለምና ስለ እሱ እዚህ ማውራቱ ትርጉም የለውም። በመሆኑም፣ ይዘለላል።
“መሄድ ቢሉሽ መሄድ ነው ወይ . . .” እንደ ተባለው “ዲሞክራሲ” ስለ ተባለ ብቻ ዲሞክራሲ አለ ማለት አይደለም። የተባለው ዲሞክራሲ በትክክል ስለመኖሩ መለኪያዎች አሉ፤ በመለኪያዎቹ ተለክቶ ሚዛን ካነሳ ብቻ በዛች አገር “ዲሞክራሲ አለ” የሚለው ዝርዝር ስር ያርፋል ማለት ነው።
በቅርቡ በየዓመቱ የዓለም አገራትን የዲሞክራሲ ይዞታ እግር በእግር እየተከታተለ ደረጃና ጥራታቸውን የሚያወጣ ተቋም (World Population Review (Democracy Index) ግኝቱንና ጥናቶችን ጠቅሶ እንዳሰፈረው በአንዳንድ ምሁራን አተያይ በዓለማችን (ከድሮ እስከ ዘንድሮ) ከ2000 በላይ የዲሞክራሲ አይነቶች ተመዝግበው ይገኛሉ።
የአሜሪካው የውክልና ዲሞክራሲ (representative democracy)፤ ምሉእ በኩለሄ የሆነው የካናዳው “ፉል ዲሞክራሲ”፤ የኖርዌዩ ተግባራዊ ዲሞክራሲ (Working Democracy) እና ሌሎችም በማሳያነት ተጠቅሰዋል።
ምናልባት ይህንን ቁጥር ለተመለከተ እራሱ ዲሞክራሲ እንደ ተፈለገና ተጠብቀው ወደ መሬት ሊወርድ ያልቻለው ከብዛቱ፤ እንዲሁም ብዛቱ ከወለደው አለመግባባት ምክንያት ነው ብሎ ማጠቃለያ ላይ ቢደርስ አያስኬደውም ማለት የሚቻልበት መንገድ ያለ አይመስልም።
(ቆይ፣ እኛ አገር ቅድመ ዐቢይ አሕመድ የነበሩትን ሳንጨምር፣ በድህረ ዐቢይ ተፈልፍለው የነበሩትን ከ140 በላይ ፓርቲዎች “በየወገናችሁ” ቢባሉ ከየትኛው የዲሞክራሲ አይነት ስር ይሰለፉ ይሆን? አላስፈላጊ ብዛት አስፈላጊውን መግባባት ያኮላሸዋልና፣ ያ ሆኖ ዛሬ . . .) ወደ ተነሳንበት እንመለስ።
በEconomist Intelligence Unit አማካኝነት ተዘጋጅቶ ለስርጭትና ንባብ የበቃው፣ ከላይ የጠቆምነው ተቋም “Democracy Index: Most Democracy Countries 2023” (10 ሜይ 2023) በሚል ርእስ ሰፊ ሪፖርቱን በቅርቡ ይፋ አድርጓል። በጥናቱም 167 አገራትን እንደ ሸፈነ አስታውቋል። የየአገራቱን ዜጎች ነፃ የሆነ የፖለቲካ ተሳትፎን ፈትሿል። የዜጎች የግለሰብ መብቶችን አይቷል። የፖለቲካ ስርአቶቹ አካታች ናቸው/አይደሉም፤ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ አለ/የለም፤ ያሉት መንግስታት በህዝብ የተመረጡ ናቸው/አይደሉም፤ የዜጎች የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን፤ “መርምሬያለሁ”፤ “በርብሬያለሁ”፤ “አንድም ሳላስቀር ፈትሻለሁ” ነው የሚለው።
እነዚህን ተግባራት ካከናወነ በኋላ “ዋጋቸውን ሰጥቻለሁ” (ዲሞክራሲ ኢንዴክስ) የሚለን ይኸው ጥናት ከአንድ እስከ አስር ያሉትን እንደሚከተለው ያስቀምጣቸዋል፤
ኖርዌ (9.8)፣ ኒው ዚላንድ (9.4)፣ ፊን ላንድ (9.3)፣ ስዊድን (9.3)፣ አይስላንድ (9.2)፣ ዴንማርክ (9.1)፣ አየርላንድ (9.0)፣ ታይዋን (9.0)፣ አውስትራሊያ (8.9)፣ እና (ከኔዘርላንድስ እና ስዊዘርላንድ ጋር በትይዩ የተወቀመጠችው) ካናዳ (8.9)።
ዲሞክራሲን ባህሏ ካደረገችውና ፍትህና ርትዕ እግሩን ተክሎባታል ከተባለላት ኖርዌይ በተቃራኒ ደረጃ (ሁራ) ላይ የምትገኘው አፍጋኒስታን (ዲሞክራሲ ኢንዴክስ 1.08) መሆኗንም ጥናቱ አመልክቷል።
ጥናቱ ይህንን ያስቀመጠው ከደረጃ አኳያ ሲሆን፤ ከዲሞክራሲ ጥራት (Quality of Democracy) አኳያም (የ2020ን ጥናት በመጥቀስ) በሚከተለው መልኩ ያስቀመጣቸው ሲሆን፤ ዴን ማርክ (አጠቃላይ እሴት ኢንዴክስ 0.958) አንደኛ፣ ኖርዋይ (0.956) ሁለተኛ፣ ፊንላንድ (0.946) ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተገኝተዋል።
አንድን ዲሞክራሲ “ጥሩ” ወይም “በጣም ጥሩ” ሊያሰኙት የሚችሉት ምን ምን ጉዳዮች እንደሆኑ የሚፈተሽበት “ጥራት ያለው ዲሞክራሲ” (QD) ሲባል ከአጠቃላይ የፖለቲካ ስርአቱ/መዋቅሩ አኳያ የመንግስታትና ተቋማት ምላሽ ሰጪነት (responsiveness)፣ ተጠያቂነት፣ ውክልና (mandates)፣ የህዝቦች/ዜጎች የተሳትፎ መጠን፣ ፖለቲካው በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት (PT)፣ ወዘተ የሚመለከት ነው፤ የበለጠ ለመረዳት “Quality of Democracy Makes a Difference, but Not for Everyone: How Political Interest, Education, and Conceptions of Democracy Condition the Relationship Between Democratic Quality and Political Trust” (www. frontiersin.org፣ ሜይ 2021) በሚል ርእስ የቀረበን ግሩም ጥናት መመልከት ጠቃሚ ይሆናል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2015