ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ ኃይል ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን ለማድረግ በመንግስትም ሆነ በተለያዩ ተቋማት ጥረት በመደረግ ላይ ነው:: ሆኖም በተለይም አዳዲስ የምርምር ሥራ ይዘው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ወጣቶችን በመደገፍም ሆነ ራዕያቸውን እንዲሳካ ከማገዝ አኳያ እየተሰራ ያለው ሥራ ያን ያህል አመርቂ እንዳልሆነ ይታመናል:: ይህም ወጣቱን ከማደራጀትና በገንዘብ ከመደገፍ ባለፈ፣ አመለካከቱ ላይ እምብዛም ትኩረት ያለመደረጉ ውጤት ስለመሆኑም ይነገራል:: ይህም ትልልቅ ሃሳብ የያዙትን ወጣቶች ሳይቀር ሥራአጥ ያደረገ መሆኑን ነው የዘርፉ ተንታኞች የሚያስረዱት:: ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘም በወጣቶች የአስተሳሰብ ቀረፃ ላይ በማተኮር ሥልጠና እየሰጠ ካለና የእኔ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲብ የተባለ ድርጅት መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ከሆነው ወጣት ዮናስ ዱጉማ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
የወጣቶች አመለካከት ቀረጻ እሳቤና ጅማሮ
ከተጀመረ ሰባት ዓመት የሆነው የእኔ ኢትዮጵያ፤ ይህንን ሥራ የጀመረው እነ ወጣት ዮናስ የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያሉ ነበር:: ወጣት ዮናስ እንደሚናገረው፤ ይሄ ሃሳብ የመጣው ዩኒቨርስቲ ውስጥ በነበሩ ወጣቶች ሲሆን፤ ዋና ትኩረታቸውም ወጣቶች ነበሩ:: መነሻውም የሰዎችን አስተሳብ በመቀየር ህይወታቸውን አብሮ መቀየር ይቻላል የሚል ሲሆን፤ ለዚህም የተለያዩ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት የሰዎችን ህይወት አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመለወጥ ነው:: እስካሁንም ስልጠናውን በራሳቸው ወጪ ወጣቶች እየሰጡ ይገኛል::
ወጣት ዮናስ ስለ እሳቤውና ጅማሬው ሲያስረዳ፤ ወደዚህ ሥራ የገባንበት አጋጣሚ እኛ ተማሪ ሳለን በበርካታ ወጣቶች ላይ ብዙ አልባሌ ነገሮች ተመልክተን በእኛ አቅም ምን መቅረፍ እንችላለን ብለን በማሰብ ነው:: በተለይ እኛ የነበርንበት ሐዋሳ አካባቢ በርካታ ወጣቶች በሱስና በተለያዩ ችግር ውስጥ ሆነው እንመለከት ነበረ:: እናም ብዙ ጊዜ ወጣቶች ወደአላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገቡት ትክክለኛ ግንዛቤ ስላልጨበጡና መንገዱን የሚያሳያቸው በማጣታቸው እንደሆነ በማሰብ የአመለካከት ቀረጻ ላይ አተኮርን::
ስልጠናውን ከመስጠታችን በፊት ግን ራሳችን መሰልጠን አለብን ብለን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሚሰጡ ስልጠናዎችና ትምህርቶች ላይ በመሳተፍ በቂ ግንዛቤና ተሞክሮ ለመጨበጥ ጥረት አድርገናል:: በመቀጠልም ”የእኔ ኢትዮጵያ” የሚል የበጎ አድራት ድርጅት ከፍተን ችግር ውስጥ ያሉ በርካታ ወጣቶችን በመጋበዝ የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ ስልጠናዎችን መስጠት ቀጠልን:: ትኩረታችንም በተለያዩ ሱሶችና ጭንቀት ውስጥ ያሉት ላይ ነው:: ፕሮጀክት ቀርፀን ስንቀሳቀስ የቆየነው ወጣቱ የሚሰማው፤ ችግሩን የሚረዳለት ሰው ይፈልጋል በሚል በቅርበት ሆነን ለመደጋገፍ በሚያመች ሁኔታ ነው::
በዋናነት ትኩረት አድርገን የምንሰራውም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከመንግስት ተቋማት ጋር ሲሆን፤ በወረዳዎች እና በክፍለከተማ ደረጃ ለተደራጁ ወጣቶች ስልጠናውን እንሰጣለን:: በዩኒቨርሲቲዎችም ጥያቄ ሲቀርብልን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ወጣቶችን እናሰለጥናለን:: እስካሁን ባለው ሂደት ከመንግስት ተቋማት ጋር ብቻ ባለን የግንኙነት በዓመት ከሁለት ሺ እስከ ሶስት ሺ የሚሆኑ ወጣቶችን በነፃ እናሰለጥናለን::
የሥልጠናው ውጤታማነት
ሀሳብ ወደ ተግባር ሲለወጥ በውጤት ሊታጀብ ይገባል:: በዚህ ረገድ እነ ወጣት ዮናስም አበረታች ውጤት ያዩ ሲሆን፤ ይሄን አስመልክቶም ወጣት ዮናስ እንዲህ ሲል ነው የገለጸው:: በዚህ ስልጠናም በወጣቱ ላይ ተጨባጭ የአመለካከት ለውጥ ማየት የተቻለ ሲሆን፤ ተለውጠው በጥሩ የህይወት ጎዳና ላይ ያሉ ወጣቶችም የሚነግሩን ይሄንኑ ነው:: ይህን ድርጅት የመሰረቱት አብዛኞቹ ወጣቶችም በተለያዩ ሱሶችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ ናቸው:: ከእነዚህም መካከል አንደኛው ከነበረበት ሱስ ወጥቶ የመርከብ ካፒቴን ሆኗል፤ ሌላኛው ደግሞ ፓይለት ሆኖ አገሩን እያገለገለ ነው::
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የምናገኛቸው ተማሪዎችም ያመጡትን ለውጥ በፅሁፍ ይገልፁልናል:: ተቋማቱም እስካሁን ባለው ሂደት በወጣቶቻቸው ላይ የመጣውን ለውጥ በይፋ ከመንገር ባለፈ የተለያዩ ምስክሮችን ሰጥተውናል:: ስለዚህ እነዚህ ድምር አስተያየቶችና ግብረ መልሶች እየሰራን ያለነው ሥራ ውጤታማ መሆኑን አመላካቾች ናቸው::
አሁናዊ ችግርና መፍትሄዎቹ
እንደ ወጣት ዮናስ ገለጻ፤ ትልቁ አሁናዊው ችግር የወጣቱ ቁጥርና የስራ እድል ያለመመጣጠን ነው:: አሁንም በርካታ ወጣቶች ስራአጥ ናቸው:: ከሁሉ በላይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለፍተው ከተማሩ በኋላ ሲወጡ ስራ ስለማያገኙ ወደ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለሚገቡ በሱስ ውስጥ የሚዘፈቁበት አጋጣሚ ብዙ ነው:: ለዚህ ደግሞ አንደኛው ምክንያት ተማሪዎቹ ጋር ያለ የጠባቂነት አስተሳሰብ ነው:: በመሆኑም በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ከተቀጣሪነት አስተሳሰብ ወጥተው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ አስተሳሰባቸውን አስቀድሞ መቅረፅ ይገባል:: ለዚህም የሚያነቃቁ ስልጠናዎችን ማግኘት አለባቸው::
በመንግስት በኩል ወጣቶችን አንድ ላይ አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ ጥረት ቢኖርም፤ ብዙ ጊዜ ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም:: ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከማደራጀት ባለፈ አስቀድሞ የግንዛቤ ለውጥ የሚያመጣ ስልጠና የማያገኙ በመሆኑ ነው:: በተጓዳኝ አብሮ ለመስራት የሚያስችል የተግባቦት ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ሥልጠና መስጠት ግድ ይላል:: የእኛም ሥልጠና ይህንን ክፍተት የለየ ሲሆን በዚህም አዎንታዊ ውጤት እያየንበት ነው:: ዩኒቨርሲቲዎችም ይሄን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው::
በተለይ የአመለካከት ቀረፃ ላይ የሚሰሩ ስራዎች አነቃቂ ስለሆኑ ከመደበኛ ትምህርቱ በተሻለ ወጣቱን የመሳብ ኃይል አላቸው:: እስከዛሬ ባለኝ ልምድ መታዘብ የቻልኩትም ተማሪዎች ከዋና ትምህርታቸው በላይ ወደተግባር የሚያንደረድራቸውን የአመለካከት ሥልጠና የማግኘት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው:: ከዚህ አንፃር አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና የሚሰጡ ቢሆንም ቀጣይነት ግን አይታይባቸውም:: በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስመሰግነው ስራ እየሰራ ነው:: ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ተከታታይነት ያለው ስልጠና ሊሰጡ ይገባል:: ምክንያቱም ወጣቶች ከተመረቁም በኋላ ከጠባቂነት አስተሳሰብ የማይወጡት አስቀድሞ የሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ አነስተኛ በመሆኑ ነው::
ከማደራጀት እና አመለካከትን ከማነጽ አንጻር
ተመራቂ ወጣቶች የሚያከናውኗቸውን የምርምር ስራዎች መደገፍ ተገቢ ነው:: በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል አደረጃጀቶችን በመፍጠር ለመደገፍ ጥረት ይደረጋል:: ትልቁ ችግር እንዲህ አይነቱን ነገር ዘላቂ ያለመሆኑ ላይ ነው:: ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲ እንደወጡ አደራጅቶ ገንዘብ የመስጠት ሙከራ እናያለን:: ግን አብዛኞቹ ሲከሽፉ ነው የሚታዩት:: ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደምናስታውሰው በጣም ከፍተኛ የሚባል ገንዘብ ለተደራጁ ወጣቶች ሲሰጥ ነበር:: መጀመሪያ ግን ብሩን ከመስጠት በፊት ወጣቶቹን ማሰልጠንና ግንዛቤያቸውን ማሳደግ ይገባ ነበር:: እኛ ባለን አጋጣሚ ሁሉ የመንግስት አካላት አስቀድሞ የአመላከከት ቀረፃ ላይ እንዲሰሩ እንወተውታለን::
ምክንያቱም ወጣቶቹን ከማደራጀትና ገንዝብ ከመስጠት በፊት የአመለካከት ቀረፃው ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: ከዚህ አንፃር በቅርቡ ልማት ባንክ የጀመረው ነገር የሚያበረታታ ነው:: ሆኖም ካለው ሰፊ ሥራአጥ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር አጥጋቢ አይደለም:: በመሆኑም ሥራ የለም ከማለት ቢሰራ መቀየር ይቻላል ወደሚል አስተሳሰብ ወጣቱን ማምጣት ይገባናል:: ለዚህ ደግሞ የወጣቶቹ አመለካከት ላይ መስራት ያስፈልጋል:: ወጣቶች የሚኖሩበት ምክንያትና ህልም ሊኖራቸው ይገባል:: እኛም ከወጣት አደረጃጀቶች እየሰራን ያለነው ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው::
እንደእኛ በማደግ ላይ ላለ አገር ደግሞ መደራጀቱ ክፋት የለውም:: ተደራጅቶ መስራቱ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሐኒቱ›› እንደሚባለው ጠቀሜታው የጎላ ነው:: ይሁንና ከማደራጀታችን በፊት ግን ወጣቶቹን ወደአንድ አመለካከትና መግባባት ማምጣት ያስፈልጋል:: ይህ ማለት ሁሉም አንድ አይነት እይታ ሊኖረው ይገባል ማለት ሳይሆን የሚሰሩበት አንድ ዓላማ እንዲኖራቸው ማድረግ መቻል ነው:: ምክንያቱም ወጣቱ ‹‹ሼር ማለት ሸር ነው፤ ሰውን ማመን ቀብሮ ነው›› እየተባለ ነው ያደገው:: ብዙ ጊዜ እንደሚታየው የተደራጁ ወጣቶች ብሩን እንደተቀበሉ ምንም ሳይሰሩ ገንዘቡን አባክነው የሚቀሩት አመለካከት ላይ ባለመስራታችን ነው:: በመጀመሪያ ይህ አመለካከት መሰበር አለበት:: ደግሞም በዓለም ላይ እንደሚታየውም ትልልቅ የሚባሉ ለውጦች የመጡት በግለሰብ ሳይሆን በቡድን በመሰራታቸው ነው:: ከእያንዳንዱ ትልልቅ ስኬቶች ጀርባ የቡድን ሥራ አለ::
ስለዚህ አብሮ መስራቱ መልካም ነው:: አደረጃጀቶቹ ግን መሰረታዊ የሚባል ችግር አለባቸው:: የሚያደራጁት ሰዎች ራሳቸው የሚያደራጁበት ምክንያት ግልፅ ሊሆን ይገባል:: ዋነኛ አላማቸው ወጣቱን መጥቀም ከሆነ ወጣቱ የሚፈልገውን አስቀድመው ማወቅ አለባቸው:: ወጣቱ ራዕዩን እንዲያሳካ መደገፍ እንጂ ፍላጎቱም ሆነ ራዕዩ ባልሆነ ነገር እንዲዳክር ማስገድድ አይገባም:: መዳረሻውን ለማያውቅ ወጣት ገንዘብ ሰጥተን ውጤት እንዲያመጣ መጠበቅ ከፈረሱ ጋሪው እንደሚባለው አይነት ነው የሚሆነው:: ዝም ብለን ብር የሰጠነው ወጣት ተመልሶ የአገርና የህዝብ ጠንቅ ነው የሚሆነው:: እንዳውም ያጠፋውን ብር ላለመመለስ ሲል ነውጠኛ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ::
መልዕክት
ወጣቱን ማብቃትና እይታውን ማስተካከል ያስፈልጋል:: መብራቱን ከቆጣሪ አጥፍተን ቴሌቪዥኑ እንዲሰራ እንደማንጠብቀው ሁሉ፤ የሰው ልጅ አስተሳሰቡ አጥፍቶ የቱንም ያህል ገንዘብ ብንሰጠው ውጤታማ ሊሆን አይችልም:: እይታው ሲበራና ሲስተካከል ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በርካታ አማራጮች ማየት ይችላል:: ይሄን መልካም አማራጭ ትተን ግን እፀፆችን እናንሳ ካልን የኢትዮጵያ አዳጊ የኢኮኖሚ ሁኔታ መዘንጋት ነው::
ላለመስራት ከታሰበ በርካታ እንቅፋቶች አሉ፤ ግን እንቅፋቶችን ከመደርደር ይልቅ መፍትሔዎችን መፈለጉ ነው የሚያዋጣው:: ከዚህ ጎን ለጎን ግን ወጣቶቹ በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚያነሱትን ችግሮች ለመፍታት ከመንግስትም ሆነ ከተቋማቱ ቁርጠኝነት መስራት ያስፈልጋል:: አሁን ያለውን በቢሮክራሲ የታጠረ አሰራር ለማስቀረት የሚያስችል ስርዓት መፍጠር ይገባል:: የፋይናንስ ተቋማቱም ሆነ መንግስት በወጣቱ ላይ እምነት ሊያሳድር ይገባዋል:: ከሁሉ በላይ ግን ወጣቱ ችግር አጋጠመኝ ብሎ እጁን አጣጥፎ ሊቀመጥ አይገባም:: ከትንሽ ነገር ጀምሮ መነሳትን መለማመድ አለበት::
ለምሳሌ እኔ፣ ይህንን ድርጅት ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ባቋቁምም ከዩኒቨርሲቲ ስወጣ ቋሚ የገቢ ምንጭ የሚያስገኝ ሥራ በተማርኩበት ዘርፍ ፈልጎ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው የሆነብኝ:: ሰው እደሚለው ማመልከቻ ባስገባም የሚጠራኝ ግን ላገኝ አልቻልኩም:: መጨረሻ ላይ ሲሰለቸኝ አንድ ተቋም ላይ በድፍረት ባለቤቱን አግኝቼ ዓለማዬን፤ በሙያዬ ከእነሱ ድርጅት ጋር ለመስራት ያለኝን ፍላጎት እና ራዕይ ሳስረዳው በድፍረቴ እና ያለኝም ተስፋ ስላስደነቀው ቀጠረኝ:: ጥቂት ከሰራሁ በኋላ የማስተርስ ዲግሪዬን ይዤ የራሴን ድርጅት ከፍቼ እየሰራሁ ነው:: አሁን ላይ በራሴ መንገድ ውጤታማ ነኝ ብዬ አምናለሁ::
ይህ ግን ሁሉም ጋር ይሰራል ማለት አይደለም:: ግን ደግሞ ትክክለኛ ራዕይ ያለው ሰው የቱንም ያህል ዋጋ ከከፈለ ከሚፈልገው መድረሱ አይቀርም:: አሁንም ቢሆን መናገር የምፈልገው ነገር በዚህች አገር ላይ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ መሰራት ያለበት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለው ወጣቱ ላይ ነው:: ለዚህ ደግሞ በዋናነት የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ላይ ነው ትኩረት ሊደረግ የሚገባው::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2015