የሰላምን ምንነት በአጭርና ቀላል መንገድ መግለጽ ከባድ ነው። ሰላም ሲኖር በቀላሉ የሚወሰድ፣ ሲደፈርስ ብቻ ዋጋው ምን ያህል ከባድና አስፈላጊ የሆነ በትውልዶች መፈራረቅ የዳበረ እሴት መሆኑን መረዳት ይቻላል። ሰላም ከጥንት ፈላስፎች እስከቅርብ ጊዜ ሊቃውንት የተጠበቡበት ለሰው ልጆች በጣም አስፈላጊ የሆነ እሴት ነው።
ስለ ሰላም ዋጋ የጦርነት አውዳሚነት በመጥቀስ በርካቶች ሰብከዋል፤ ጽፈዋል። ከእነዚህ መካከል ዕውቁ ግሪካዊ ጸሐፊና የታሪክ ሰው ሔሮዶቱስ የጦርነትን አስከፊነት እና ሰላም የውሃና የአየር ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጾታል።
“ In peace, sons bury their fathers. In war, fathers bury their sons! ” (በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤ በጦርነት ጊዜ አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ) ሲል። ይህ ግሪካዊ የታሪክ አዋቂ አባባል የጦርነት እጅግ አስከፊ ገጽን ብቻ ሳይሆን የሰላምን ጥቅም አድማሳዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።
በእውነቱ ከሆነ የሰላምን አቻ የለሽነት፤ የጦርነትን ጎታችነት፣ አውዳሚነት፣ ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚያውቀው አለ ብሎ መናገር ይከብዳል። በተጨባጭ የጦርነትን አስከፊነት አይተነዋል። የጦርነት መራርነትን ቀምሰን፣ የሰላምን ዋጋ የተረዳን፣ ብዙም የተማርን ህዝቦች ነን።
ብዙም ሳንርቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት የቆየንበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ከማድረሱም በላይ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጉዳት እንደ ዋዛ የሚረሳ አይደለም። በርግጥ እንደ አገር ዋጋ ያስከፈለንን ጦርነት በመደራደር በሰላማዊ መንገድ መቋጨቱ ትልቅ ድል ነው።
የዓለም ታሪክ የሚያስረዳንም ጦርነት ለሰላም በተዘረጉ እጆች እንጂ በመሣሪያ እጦት እንደማይቆም ነው። እንዲሁም በሰላማዊ ድርድር እንጂ በአሸናፊና በተሸናፊ መንፈስ የተቋጩ ጦርነቶች ዘላቂ ሰላም አያሰፍኑም። በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሆነው ይሄው ነው። ከብዙ ጥረት በኋላ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ንግግር እውን ሊሆን ችሏል።
ይህ በኢትዮጵያ የተጀመረው ሰላምን የማጽናት ተግባር እንደ ሰሜኑ ሁሉ በምዕራቡም እውን እንዲሆን እየተሰራነው። በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተገኘው የሰላም መንገድ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያም ማየት የብዙዎች መሻት ነው። በርግጥ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሰው ሸኔ በፌደራል ሆነ ኦሮሚያ ክልል በኩል ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲደረግለት እንደነበር ይታወቃል።
ላለፉት አምስት ዓመታት በአካባቢው በነበሩ ግጭቶች የብዙ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፣ ደም ፈሷል። አካል ጎድሏል። ንብረት ወድሟል። በርካታ ንጹሀን ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መስራት፣ ሀብት ማፍራትና በሰላም ወጥቶ መግባትን የመሳሰሉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችም ተገድበዋል።
የፌደራል መንግስቱም የቡድኑን ጥፋት ለማስቆም ጥረት ከማድረግ ባሻገር ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ከመናገር ቦዝኖ አያውቅም። በመጨረሻው በምዕራብ ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በሰላም ለመፍታት የያዘው አቋም ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ጠረጴዛ መጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የሰላም ፍላጎት እና በአፈ ሙዝ የሚደረግ ትግል ወደ ጠረጴዛ የማምጣት ፍላጎት መልስ ሊያገኝ እንደሆነ ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ እንዲህ ሲሉ፤ “ የሰሜኑንም ብቻ አይደለም የምዕራቡን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ልኡክ ተሰናድቶ እንቅስቃሴ ተጀምሯል “ ሲሉ ማብሰራቸው ይታወሳል።
የእርሳቸውን ቃል ተከትሎ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በታንዛኒያ የሰላም ውይይቱ ተጀምሯል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዳስታወቀው፣ የሰላም ውይይቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በአብዛኛው አወንታዊ በሆነ መልክ የተካሄደ ሲሆን አንዳንድ ጉዳዮችም በይደር ተላልፏል።
ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ ተግባብተዋል። ይህም በተለይ መንግስት ችግሮችን በውይይት የመፍታት በጎ ጅምር በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ያለውን ፅኑ አቋም ዳግም ያረጋገጠ ነው።
ድርድሩን የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ አብዝተው የሚሹት ነው። የጠረጴዛ ዙሪያ የሰላም ውይይት ጅማሮው የሰላምን ዋጋ ለሚረዳ፣ እርስ በእርስ መገዳደል ለሰለቸው፣ የዜጎች ሰቀቀን ለሚሰማው ሁሉ ልብን በደስታ የሚሞላ፣ ‘ጮቤ’ የሚያስረግጥ ነው።
የሰላም ውይይት ጅማሬው ንፁሃን ዜጎች እየከፈሉት ያለውን ያልተገባ ዋጋ ስቃይ ፣ ጥፋት በፍጥነት ለማስቆም አቅሙ ግዙፍ ነው። ከጅማሮው መረዳት እንደሚቻለውም የሰላም ጉዞው የኢትዮጵያን አሸናፊነት ባረጋገጠ መልኩ እንደሚጠናቀቅ ተስፋ ይሰጣል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለበት አለመረጋጋት እፎይ እንዲል የተጀመረው የሰላም ውይይት የሁሉም ወገን ውጤታማ ድርድር ማድረግን ይጠበቃል። በዚህም መንግሥት ከሁሉም በላይ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ ካለበት ኃላፊነት አንጻር ችግሮችን በሆደ ሰፊነት በድርድር ለመፍታት የጀመረው ጥረት ሊደነቅ፤ ጅማሮም ትርጉም ያለው ውጤት እያመጣ ባለው አካሄዱ በበለጠ ቁርጠኝነት ሊቀጥልበት ይገባል።
የሰላም ውይይት በውጤት እንዲጠናቀቅ ከመንግስት በተጓዳኝ ቡድኑ የቀረበለትን መልካም አጋጣሚ ሳያባክን የሕዝቡን ጥቅም መሰረት ባደረገ መልኩ ለውይይቱ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጾኦ ሊደርግ ይገባል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የሰላም ውይይቱ እንዲሳካ የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል።
በአንድ ክልል ሰላም አለመስፈን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁሉንም ክልሎች ሰላም የሚያናጋ፤ የጦርነቶችም ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ራሱ ኅብረተሰቡ በመሆኑ፤ ከትናንት የጦርነት ታሪኮቻችን በመማር የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎችን በቃችሁ ሊል፤ ለሰላም ዘብ መቆምና ጦርነትን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማውገዝ ይጠበቅበታል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2015