የብዙዎችን የእለት ተእለት ሕይወት እየፈተነ የሚገኘው የኑሮ ውድነትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ መቀጠሉ፣ የሕዝብን ኑሮ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው። ወላጆችንም ለ ምሬት አየዳረገ ይገኛል::
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተካሄደው ጦርነት እና ጦርነቱን ተከትሎ በአበዳሪዎች እና ድጋፍ ሰጪ አካላት የተጣሉ ማእቀቦች በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ናቸው። ራስ ወዳድ ነጋዴዎችና ደላሎችም ለችግሩ መባባስ ተጠያቂዎች ናቸው::
የዋጋ ግሽበቱ የእድገት መጠኑ ይለያይ እንጂ ከምግብ እስከ ቁሳቁስ፣ ከአልባሳት እስከ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ሁሉም ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የሚስታዋል ነው፤ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እየፈተነ ይገኛል:: ችግሩ አሁን ላይ ዝቅተኛ ገቢ ካለው የማኅበረሰብ ክፍል አልፎ መካከለኛ ገቢ እስካለው የማኅበረሰብ ክፍል እየፈተነ ነው::
ችግሩን ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም፤ ሁኔታዎች በተጠበቀው መልኩ ሊቀየሩ አልቻሉም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ደግሞ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ዙሪያ እየተደመጠ ያለው የትምህርት ቤቶች ወርሃዊ የክፍያ ጭማሪ ለኑሮ ውድነቱ ሌላ ጫና ይዞ መምጣቱ የማይቀር ነው::
ቀደም ባለው ጊዜ ሆነ አሁን ላይ የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ጭማሪ ወላጆችን እያማረራቸው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲሰማ የቆየ ነው። ገቢያቸውን ታሳቢ ያላደረገው የትምህርት ቤቶቹ የክፍያ ጭማሪ ሆነ የመመዝገቢያ ክፍያ እና መሰል ምክንያታዊ ያልሆኑ ክፍያዎች እየተለመዱ ከመጡም ቆይተዋል::
በዘርፉ ያሉ የክፍያ መመሪያዎች ትምህርት ቤቶች ለመመዝገቢያ ከወርሀዊ ክፍያ ከ25 በመቶ በላይ እንዳያስከፍሉ የሚል አሰራር ቢኖርም ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም፤ አሁን ላይ ትምህርት ቤቶቹ ለምዝገባ ብቻ ከ65 እስከ 70 ከመቶ እያስከፈሉ ያሉበት ሁኔታ በብዛት ይስተዋላል::
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች አሰራር ላይ ቁጥጥሩ የላለ እንደሆነ ተደጋግሞ ቢነሳም፤ እስካሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ብዙም የተለወጠ ነገር አለ ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም:: በችግሩ በየአዲስ ዓመቱ አጀንዳ መሆኑ እየተለመደ መጥቷል።
ትምህርት ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንደመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በዘርፉ የሚያካሂዱት ኢንቨስትመንት ትርፍ ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ትልቅ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለበት በአግባቡ ሊረዱት ይገባል:: በተጋነነ የትምህርት ወጪ ምክንያት ትምህርቱን መከታተል ያልቻለ ዜጋ መፍጠር ጉዳቱ እንደ አገር የሁሉም ነው::
በርግጥ ትምህርት ቤቶቹ ለዋጋ መጨመር እንደ ሰበብ የሚያቀርቡት የመምህራን ደመወዝ ጭማሪ፣ የትምህርት ቤቶቹን ከባቢ ማሻሻል፣ ግብአቶችን ማሟላት የሚሉ እና መሰል ምክንያቶች ናቸው:: በኮቪድ በደረሰባቸው ከፍተኛ ኪሳራ እና በ2015 ዓ.ም ጭማሪ እንዳያደርጉ መከልከላቸው ገበያው ላይ ለመቆየት የግድ ጭማሪ ለማድረግ እንሚያስገድዳቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ ይደመጣል።
የተሻለ የትምህርት አካባቢን ለመፍጠር እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ትርፍ አግኝተው ለመዝለቅ የክፍያ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል:: ትምህርት ቤቶች ዝግ በሚሆኑበት ሐምሌ እና ነሐሴ ለመምህራን የሚከፈለው ክፍያ እና የትምህርት ግብአቶችን ለማቅረብ አሁን ያለው የገበያ ዋጋ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑም ብዙ አያነጋግርም።
ጥያቄ የሚሆነው ግን ትምህርት ቤቶቹ እንደሚሉት ለመምህራን የደሞዝ ጭማሪ ያደርጋሉ? የትምህርት ቤቶቹን ከባቢ ለመማር ማስተማሩ ውጤታማነት በሚሉት ደረጃ የተመቻቸ ነው? በትምህርት ግብአቶች ማሟላት ዙሪያ ያለው እውነታ እንደሚናገሩት ነው ወይ የሚለው ነው።
አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የሚሰበስቡትን ገንዘብ ያክል ቃላቸውን እንደማያከብሩ በወላጆች በተደጋጋሚ ቅሬታ ይነሳባቸዋል:: የወረቀት ግዥ፣ አጋዥ የትምህርት መሳሪያዎች እና መሰል ግብዓቶችን ለማሟላት ተማሪዎቻቸውን ተጨማሪ ገንዘብ ሲጠይቁ ይስተዋላል።
ለመምህራን ክፍያ ተብሎ እንደ ምክንያት የሚቀርበው ጉዳይ ሚዛን የሚደፈ አይደለም:: ምክንያቱም የግድ ጭማሪ ማድረግ ቢያስፈልግ እንኳ በአማካይ ቀድሞ ከነበረው 20 ከመቶ በታች ወራዊ የክፍያ ጭማሪ በማድረግ ጤናማ የአሰራር ሂደት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል። ትምህርት ቤቶቹ ግን አሁን ላይ እያደረጉ ያለው ከ70 እስከ 100 ከመቶ ጭማሪ ማድረግ ነው::
ችግሩ በአንድም ይሁን በሌላ የትውልድ ግንባታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጥብቅ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጉዳዩ በትምህርት ቤቶቹና በወላጆች ዙሪያ የተገደበ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ብዙም የሚያስኬድ አይደለም ”
መንግስት ትምህርት ቤቶቹን ስርአት ከማስያዝ ባለፈ ከግል ትምህርት ቤቶችን ለቅቀው የሚሄዱ ተማሪዎች ወደ መንግሥት ትምህርት ቤቶች ሲሄዱ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖር ሊሰራ ይገባል:: በቁጥር እና ጥረት የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ማስፋት ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል::
ጉዳዩ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን በበኩሉ፣ የክፍያ ጭማሪ ከመደረጉ በፊት ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆች ጋር ውይይት እንዲያደርጉና የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከማድረግ ጀምሮ ፤ የትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪም ትርጉም ያለው እንዲሆን በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
ትምህርት ቤቶቹ የሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ፤ ጭማሪውም የወላጆችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ እንዲሆን በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ መስራት ይጠበቅበታል።
በከተማ አስተዳደሩ 1 ሺህ 558 የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪን አስመልክቶ 1 ሺህ 257 ትምህርት ቤቶች ለባለሥልጣኑ ፕሮፖዛል ማስገባታቸውን፤ ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 31 ትምህርት ቤቶች በጋራ በተደረሰበት የክፍያ መጠን ላይ መስማማታቸውን አስታውቋል።
ስምምነቱ የተደረሰበት መንገድ የአብዛኛው ወላጅ ፍላጎት መሆኑን ማረጋገጥ፤ ካልሆነም የእርምት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። መንግሥት ካስቀመጠው ሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ውጭ በሚያስተምሩት እና መጽሐፍት እና ሌሎች ግብአቶችን በግድ በሚያስገዙት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ተገቢውን እርምጃም መውሰድ ይጠበቅበታል።
በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ከመሆኑ አንጻር፤ መንግስት ሆነ በዘርፉ የተሰማሩ በለሀብቶችና መላው ህዝብ በትምህርት ዙሪያ ለሚከሰቱ ችግሮች ፈትነው የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል፤ በተለይ የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ያልተገቡ አካሄዶች እንደ አገር ሊያስከትሉ የሚችለውን ቀውስ ታሳቢ በማድረግ ለችግሮች በቂ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው እላለሁ።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015