አዲስ አበባ፡- የፍትህ ሥርዓቱን ነፃነት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት በማስፈን፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ትናንት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ከሚገኙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት እንዳስታወቁት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ለፍትህ ሥርዓቱ መጎልበት በትጋት ይሰራል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የፍትህ ዘርፉን ዓላማዎች እና እቅዶች በማሳካት የህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን በማጉላት ለአዳጊ ፍላጎቱ ቀጣይና ሁለንተናዊ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ በላቀ ሁኔታ ህዝብን በማገልገል እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት በለውጥ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የፍትህ አስተዳደሩን የማገዝ ኃላፊነት የተጣለባቸው ጠበቆች በሙያ ዘርፋቸው አገልግሎት ሲሰጡ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። በመሆኑም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን የመፀየፍና ሁል ጊዜ ከተግባርና ከልምድ በመማር መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፣ የዜጎች ሰላም፣ ድህነትና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት አገር ለመፍጠር የህግ ባለሙያው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ገለፃ አገሪቱ የጀመረችውን ዘርፈ ብዙ ለውጦችን በማስቀጠል ጠበቆች ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በወቅቱም የጥናት ቡድኑ አባላት የጠበቆች አስተዳደር አዋጅን ለማሻሻል የተደረገውን ጥናት፣ በፍትህ ስርዓቱ የጠበቆች ሚና፣ እንዲሁም የጥብቅና ሙያና ሥነ ምግባር በሚሉ ርዕሶች ጽሁፋቸውን ለመድረኩ ተሳታፊዎች አቅርበዋል።
በመጨረሻም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና በክቡር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ አማካኝነት በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠትና ለረቂቅ አዋጁ መሻሻል ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን በመውሰድ እንዲሁም በቀጣይ ሌሎች ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር