አዲስ አበባ፡- መንግሥት የሠራተኛውን ሕገ- መንግሥታዊ መብት እንዲያስከብር እና የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም ተፈጥሮ ምርትና ምርታማነት አድጎ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ጠየቀ።
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ የዓለም የሠራተኞች ቀን ‹‹ሠላም ለሀገር አንድነት ለሠራተኛው መደራጀትና ለሁለንተናዊ አንድነት መሰረት ነው›› በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ130ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ44ኛ ጊዜ በተከበረበት ወቅት እንደተናገሩት ሰራተኞች በማህበር ተደራጅተው መብትና ጥቅሞቻቸውን ሊያስከብሩ ይገባል።
እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲረጋገጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሠራተኞችን ከሥራ እስከማባረር የሚደርስ ተጽዕኖ እየደረሰባቸው ነው ብለው አንዳንድ ተቋማት ለህብረት ድርድር ፈቃደኛ አለመሆን፣ የሰራተኛውን የደመወዝ፣ የደህንነትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን አለማክበር በአንዳንድ አሰሪ ድርጅቶች በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን አስታውቀዋል።
በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ላይም ሆነ በኢፌዴሪ ህገመንግሥት በአንቀጽ 42 ላይ በግልጽ ከመስፈሩ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸውና የፈረመችው የዓለም ሥራ ድርጅት ድንጋጌ የሀገሪቱ የህግ አካል ሆኖ ጸድቋል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ሠራተኛው በኢትዮጵያ የልማት እድገት እና የለውጥ ጎዳና ጉልህ ሚና ያለውመሆኑን በማስታወስ እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦም ሊመሰገን እንደሚገባ ገልጸዋል። በመሪ ቃሉ ውስጥ ስለሰራተኛው መደራጀት የተላለፈው መዕክት ጆሮ ሊሰጠው እንደሚገባ የጠቆሙት ሚኒስትሯ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ በሥራ ዓለም ውስጥ ማህበራዊ ምክክር ባህል እንዲሆንና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
ካነጋገርናቸው የበዓሉ ታዳሚዎች መካከል በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአቃቂ ቤዚክ ሜታል ኢንዱስትሪስ ሰራተኛ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ መስከረም ነጋሽ በሰጡት አስተያየት ሰራተኛው በማህበር ተደራጅቶ ቢንቀሳቀስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈን ከፍተኛ ፋይዳ ይታመናል። ይሁን እንጂ በተቋማቸው መደራጀት ያልተፈቀደበትና ሰራተኛውን አፍኖ ሲያሰራ እንደነበር አስረድተዋል። ለውጥ ከመጣ ከአንድ ዓመት ወዲህ ግን ያለው ሠራተኛውን የሚያነቃቃ እንቅስቃሴ መኖሩን አመልክተዋል።
በኤሊኮ አዋ ቆዳ ፋብሪካ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ የሸዋጌጥ በቀለ በበኩላቸው የወሊድ ፈቃድ አራት ወራት መሆኑ እየታወቀ ተቋማቸው ሶስት ወር ብቻ እንደሚፈቅድና በመንግሥት የተሰጣቸው መብት እየተጣሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። መንግሥት እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል።
ሀሳባቸውን በመጋራት አስተያየታቸውን የሰጡት የጨርቃጨርቅ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ መስፍን አድነው በአንዳንድ ድርጅቶች የሕፃናት ማቆያ ባለመኖሩ ሴት ሰራተኞች እየተቸገሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ወጥ የሆነ የደመወዝ ክፍያ አለመኖር፣ ጥቅማጥቅሞች አለመከበር ዜጎች ስደትን እንዲመርጡ እያደረገ መሆኑንም አስተያየት ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በለምለም መንግሥቱ