የዛሬዋ እንግዳችን እየሩሳሌም ነጋሽ አሁን ላይ ‹‹እንቁዋ ታብራ›› የሚል ድርጅት ከፍታ ሴቶችን ለማብቃት እየተጋች ያለች ናት። ቀደም ሲል የብሔራዊ ቡድንና የቡና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋችና አሰልጣኝ የነበረች ሲሆን ሴቶች እግር ኳስ ጨዋታ ላይ መሳተፋቸው በማይበረታታበት ወቅት ነው ብቅ ያለችው። ያኔ በ1985 ዓ.ም እሷ በስድስት ዓመት ዕድሜዋ በሰፈር የጨርቅ ኳስ ስትለማመድ ሴቶች በእግር ኳሱ እንዳይሳተፉ ይደረግ የነበረውን የሕብረተሰብ ተፅዕኖ በ1960 ዎቹ አካባቢ የእግር ኳሱን የተቀላቀሉት የእቱ መላ ምቺና የባቡሩ ቡድን አባላት እንኳን ገና አልሰበሩትም ነበር።
ሴቶች አይችሉም አመለካከቱ ዛሬም እነ ሎዛ አበራና ብዙ ታምራትን የሚሰሩ ሴቶች በተበራከቱበት በወጉ አለመጥራቱን የምታወሳው እየሩሳሌም ይሄንኑ የሴቶች አይችሉም አስተሳሰብ ከእግር ኳሱም ሆነ ከየትኛውም መስክ ላይ ለመስበር ሴቶችን በማብቃት ጠንክራ እየሰራች ትገኛለች።
በዛሬው ጽሑፋችንም ይሄንኑ ሕይወቷን ከሴትነት አኳያ ቃኝተን ልናስቃኛችሁ ወድደናል። ታዲያ እንዳወጋችን በእሷም በደረሰችበት ዘመን ሴት በብዙ ነገር አትበረታታም። በተለይ በእግር ኳስ ጨዋታ መሳተፏ በማህበረሰቡ ዘንድ ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም። ከገባችበት በኋላ ቀደም ያሉትን የሴት እግር ኳስ ቡድን አባላት አግኝታ ሴቶች ከጨዋታው ስለሚገለሉበት ሁኔታ በመጠየቅ ለመረዳት ሞክራ ነበር። እንደነገሯት ስፖርቱ ሴት ልትሳተፍበት የማትችለው የወንድ ነው ተብሎ በመፈረጅ ድምዳሜ ላይ መድረሱ አንዱ ምክንያት ሲሆን ሌላው ደግሞ ኳሱ የወንድ ጨዋታ እንደመሆኑ ሴቷ ብትጫወተው በሴትነቷ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ አለ የሚለው መሆኑን ተረድታለች።
ለአብነትም ጡቷ ላይ እንዲሁም ተፈጥሮ ከቸራት ሕይወትን የማስቀጠል እናትነት ጋር ተያይዞ ወሊድ ላይ ከፍተኛ ችግር ያመጣል የሚለውም ነበረው። በወቅቱ እነዚህ ትክክል ያልሆኑ መረጃዎች በሕብረተሰቡ ውስጥ በሰፊው ተሰራጭተው ነበር። ታድያ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በወቅቱ የነበሩት የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ተገትቶ እንዲቆይ ያስገደደበት ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበርም እየሩሳሌም ወደ ኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች።
‹‹እግር ኳሱ ያንሰራራው በ1980 ዎቹ በእኔና በጓደኞቼ ጊዜ ነው›› ስትልም ተገትቶ የነበረው የሴቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በማድረጉ በኩል እሷና ጓደኞቿ የበኩላቸውን አስተዋጾ ማድረጋቸውን ታወሳለች። እንደምትለው በወቅቱ በተለያዩ የክልል ከተሞች ውስጥ ሴት እግር ኳስ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች ነበሩ። ያም ቢሆን ግን ቁጥራቸው ብዙ አልነበረም። ከራሷ ተሞክሮ ተነስታ የእግር ኳስ አሰልጣኝና ተጫዋቾቹን ሴቶች ቁጥር ማነስ ስታብራራው ‹‹እኔ ኳስ ልጫወት ስነሳ ማህበረሰቡ ፈፅሞ የማይደግፈውና የማይቀበለው ነበር። ቤተሰቤንም ጨምሮ ፍላጎቴን የሚደግፉና የማይቀበሉት ሆኖ ነው ያገኘሁት›› ትላለች።
እንደዚህም ሆኖ ሁለት ወንድምና እህት ያላት ለቤተሰቧ አምስተኛ ልጅ የሆነችው እየሩሳሌም የመጨረሻ ልጅ መሆኗ ጫናው ሳይገድባት በጨዋታው እንድትሳተፍ ሰፊና ምቹ ዕድል እንደፈጠረላትም ታነሳለች። ለስታዲየም ቅርብ በሆነው አዲስ አበባ ቂርቆስ ለገሀር አካባቢ ተወልዳ ማደጓም የራሱ አስተዋጾ እንዳለውም ትጠቅሳለች። አክላም ‹‹ገና በአራትና አምስት ዓመቴ ሴት ልጆች አሻንጉሊት ሲያስገዙ እኔ ኳስ በማስገዛት ለብቻዬ እጫወት ነበር›› የምትለው እየሩሳሌም ሰባት ዓመት ሲሞላት ቤተሰብ በሴት ልጁ ማየት ባለመደው ዓይነት ሁኔታ ከቤት በመውጣት ከሰፈር ወንዶች ልጆች ጋር በመቀላቀል በጨርቅ ኳስ እየተጫወተች ነበር አመለካከቱን መስበር የጀመረችው። እያደርም ውሎዋ ከሰፈር አልፎ በአካባቢው ባለችው ትንሿ ሜዳ እንደተለመደው ከወንዶች ጋር ኳስ በመጫወት የጀመረችውን ጉዞ ወደ ዋናው እግር ኳስ ሜዳ ጠጋ እያለች ታላላቅ ወንዶች ሲጫወቱ ወደ ውጭ የወጣን ኳስ ማቀበልም ጀመረች።
ይሄ በህጻናት የእግር ኳስ ስልጠና ለመታቀፍ አብቅቷታል። በስልጠናው ጨዋታዋን እየጠናከረች መጣች። በተለይ አንዴ ስታዲየም ኳስ ስትጫወትና ወደ ውጭ የወጣችን ኳስ ለማምጣት የሄደችበትን እና በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚለብሰውን ቱታ ለብሰው የሚሮጡ ትልልቅ ሰዎችን በመመልከት ብሄራዊ ተጫዋች የመሆን ብርቱ ፍላጎት ያሳደረባትን አጋጣሚ ፈፅሞ አትዘነጋውም።
‹‹ይህች አጋጣሚ ብዙ ደክሜ ላገኘሁት የእግር ኳስ ስኬት በውስጤ የመሰረት ድንጋይ ያኖርኩባት ነበረች›› ትላለች፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ስፖርት ክለብ ታቅፋ ቡድኑን ለድል ካበቁት ተጠቃሽ የክለቡ አባላት አንዷ የሆነችው እየሩሳሌም። ፍላጎቷን እውን ማድረግን በውስጧ ፀንሳ በ1994 ዓ.ም ለብሔራዊ ቡድን በመመረጥ፤ በተከላካይ መስመር በመጫወት ክለቦቿን ከማኩራቷም በላይ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ለመሆን የሚያበቃትን ብቃት እንድታገኝ አስችሏታል።
እሷ ወደ እግር ኳሱ ለመቀላቀል ከልጅነቷ ጀምሮ የሄደችበትን መንገድ አሁን ላይ ወደ ኋላ መለስ ብላ ስታስበው ማህበረሰቡ ያራምደው ከነበረው አስተሳሰብና አመለካከት ተፅዕኖ ፍፁም ነፃ ነበር ማለት እንደማይቻልም ታብራራለች። ምክንያቱን ስታስረዳም ‹‹ማንኛዋም ሴት ህልሟን ለማሳካት የምትሄድበት መንገድ አለ ብዬ አስባለሁ›› ትላለችም። በተለይ አንዲት ሴት ልጅ ማህበረሰባዊ ተግዳሮቶች ሲገጥሟት ምን ልታደርግ ትችላለች የሚለው ጥያቄ ሲነሳ እሷ ብዙ ጊዜ ራሷን እንደምታስብም ትናገራለች።
‹‹ማህበረሰቡ ኳስ መጫወትን ለወንዶች አሳልፎ ስለሰጠ ያለኝ አማራጭ በምችለው መጠን ሁሉ ወንድ መምሰል ነበር›› የምትለው እየሩሳሌም ማህበረሰቡ ለሴቶች ይሰጠው በነበረው ዕይታ ተገዳም የሴትነቷን ማንነት የወንድ ጾታ ለማስመሰል ከአረማመዷ ጀምሮ ወንድ በመምሰል ጸጉሯን በማሳጠር ሱሪ በመልበስ በአጠቃላይ ወንድ ለመምሰል ያስችሉኛል ያለቻቸውን ሁሉ በማድረግ ታዋቂና ተደናቂ እግር ኳስ ተጫዋች ወደ ሚያደርጋት ህልሟ መንደርደሯን ትናገራለች።
‹‹በ17 ዓመቴ የሴቶች የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አምበል ለመሆን በቃሁ›› የምትለው እየሩሳሌም በዚሁ አካሄዷ የልጅነት ህልሟን ዳር ለማድረስ መቻሏን አጫውታናለች። እሷ ማህበረሰቡ እንዲቀበላት ሴት ሆና ሳለ እንደወንድ በመምሰልና በመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያዋ የሴት አምበል ለመሆን ትብቃ እንጂ በወቅቱ እግር ኳስ የመጫወት ብርቱ ፍላጎትና ችሎታ የነበራቸው ብዙ ሴቶች በሕብረተሰቡ የተዛባ አመለካከት የጋን መብራት ሆነው ዕድሜያቸው ማለፉን ምን አልባት ፍላጎቱና ምኞቱ ያላቸው ሴቶች የመጫወት ዕድሉን ቢያገኙና በማህበረሰቡ ባይገለሉ ኖሮ አስተሳሰቡን በመቀየር የሴቶች እግር ኳስ ተሳትፎን የሚያሳድጉና የአገራቸውን ስም በዓለም ላይ የሚያስጠሩ ይወጡ እንደነበርም ትጠቁማለች። ከዚህ አንፃር ብርቱ መስዋዕትነትን ከፍላና ለፍታ ያገኘች ክብሯ በመሆኑ ለስኬቷ እጅግ ከፍተኛ ግምት እንደምትሰጥም ታነሳለች።
በተለይ ብሄራዊ ቡድንን መቀላቀሏን ስታስብ በእግር ኳሱ ለደረሰችበት ደረጃ የምትሰጠውን ክብር የበለጠ ከፍ የሚያደርግ ስሜት የሚሰማት እንደሆነም እየሩሳሌም አልሸሸገችም። ‹‹አገሬን ወክዬ ቡድኔን መምራት መቻሌ ለትውልዱ በተለይም ሴትነቴን በወንድ ለመቀየር ላጣሁት ማንነት ትልቅ ክፍያ ነው ብዬ ነው የማስበው ››ብላለች። ለአንዲት ሴት ልጅ ሴት ሆኖ እንደወንድ መምሰል ከባድና ከራስ ጋር ተጣልቶ እንደመኖር ያህል ነው።
‹‹ሴት ሆነሽ እንደ ወንድ መሆን፤ እንዴት ዓይነት ከባድ ነገር እንደሆነ እነማን ሊረዱት እንደሚችሉ አላውቅም ›› ትላለች። ሁኔታው በድርጊቱ ከዋኒ ውስጥ እንደ ዘይትና ውሀ ሁሉ እርስ በእርስ የማይታረቁ ነገሮችን አስታርቆ ለመሄድ እንደ መሞከር ከባድ የነበረ መሆኑንም ታነሳለች። እሷ እንደምታብራራው በዚህ ሴትነትን በመሸሽ ወይም መካድ በሚመስል ድባብ ውስጥም ሆኖ በገሀዱ ዓለም መኖርም በብርቱ ይፈትናል። በመሆኑም እሷ በሕብረተሰቡ አስተሳሰብ ተገዳ በዚህ ውስጥ በመኖሯ የሴትነቷን ፀጋ ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮች ነው ለማጣት የተገደደችው።
ይሁንና እየሩሳሌም በዚያ የልጅነት ወቅት ህልሟን ማሳካት ዋና ግቧ ነበርና ይሄን ማድረግ ብዙም የከበዳት እንዳልነበረ ዓመታት ወደ ኋላ ተጉዛ ታስታውሳዋለች።ነገር ግን ከፍ እያለች በመጣችና ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ሦስተኛው አፍሪካ ዋንጫ ባለፈች ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በመወከል፤አንበል ሆና እየመራች ጣፋጩን ድል እንድትቀዳጅ አስችሏታል። ይህ ወቅት 1994 ዓ.ም መሆኑን ታወሳለች።
ይሁንና እየሩሳሌም ጣፋጩን ድል ገና በወጉ ሳታጣጥመው የ19 ዓመት ተኩል ወጣት በነበረችበት ከባድ የእግር ጉዳት ገጠማት። በወቅቱም የኢትዮጵያ ቡና ለሕክምና ወደ ጅዳ ልኮ አሳክሟታል። ይህ ደግሞ ለራሷና ለሙያዋ ትልቅ ክብር አንድትሰጥ አድርጓታል። ‹‹ክለቡ ውጭ ልኮ እኔን ማሳከሙ ለእኔ የነበረውን ፍቅር፤ ችሎታዬን የሚያምንበት እንደሆነና ጨዋታዬ እንዲቋረጥ የማይፈልግ መሆኑን አሳይቶኛል›› ስትል ትገልፀዋለች።
ጅዳ ሄዳ ለመታከም የቻለችው በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና በደጋፊዎቿ ብርቱ ጥረት እንደሆነም ክለቡንና ደጋፊዎቿን አበክራ በማመስገን ደጋግማ ትመሰክራለች። ስትታከም የቆየችው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወንድ ተጨዋቾች ሲጎዱ ሄደው የሚታከሙበት ትልቅ ሆስፒታል ውስጥ እንደነበርም ታስታውሳለች። ከሕክምናው በኋላ ከጉዳቷ አገግማ ወደ አገሯ መመለሷንም ታነሳለች።
‹‹ቢሆንም ከኔ ጋር ጊዜውን ማሳለፍ የሚፈልግ አንድም ሰው አላገኘሁም ›› ስትል ቅሬታዋን የምትገልፀው እየሩሳሌም ሆኖም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በዚህ ወቅትም ከጎኗ እንዳልተለያት ታስረዳለች። ሂልተን ሆቴል ዋና ከመፍቀድ ጀምሮ ብዙ ድጋፎችን ሲያደርግላትና ሲያበረታታት እንደቆየም ታብራራለች። ጎልደን ጅም እንዲሁ ልምምድ የምታደርግበትን ሁኔታ ማመቻቸቱንም ትጠቅሳለች። እሷም በግሏ ተመልሳ እግር ኳስ መጫወት ትናፍቅ እንዲሁም ከዚህም ባሻገር የአገሯን ስም የምታስጠራ በዓለም ታዋቂ የሴት እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት ነበራትና ይሄንኑ ለማሳካት ብዙ ጥረት በማድረግ ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ወደ ክለቧ ተመልሳ የነበረ መሆኑንም ታስታውሳለች።
ብዙ ልምምዶችን መከታተሏንና አፈፃፀሟም ጥሩ እንደነበረም ትጠቅሳለች። ተቀይራ በመግባትም ማሊያዋን ለብሳ በድጋሚ አንድ ጨዋታ ለመጫወትም መብቃቷን ታወሳለች። ሆኖም በጨዋታው ማህል የእግሯ ጉዳት ተቀስቅሶ ሜዳ ላይ ወደቀች። በ 2000 ዓ.ም እየሩሳሌም ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያውቀው ሁኔታ በእግር ኳስ ቋንቋ በይፋ ጫማዋን ሰቀለችና በእግሯ ጉዳት ምክንያት ገና ብዙ ሊያሰራና ስኬት ሊያስጨብጣት በሚችል የአፍላ ዕድሜ ዘመኗ ከምትወደው የሴቶች የእግር ኳስ ጨዋታ ተለየች።
እየሩሳሌም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእግር ኳስ ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ብትለይም ማህበረሰቡ እንደ አገር ሴቶች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መስኮችም በመስበር ለእህቶቿ አጋርነቷን ለማሳየት ‹‹እንቁዋ ታብራ›› በሚል ስያሜ በከፈተችው ድርጅት በሌላ መንገድ በድጋሚ ብቅ አለች።
‹‹ያለ ወንዶች ተሳትፎ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉና የሚያንቋሽሹ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች አይቀረፉም›› የሚል ዕምነት ባላት እየሩሳሌም ድርጅት ወንዶችም ታዳሚ ናቸው። የማህበረሰቡ አስተሳሰብና አመለካከት የሚያደርሰውን ጫና ለማራገፍ አብረዋት ይተጋሉ። ወንዶች ወደፊት የአባትነት፤ የወንድምነትና የባልነት ኃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ በመወጣት ተመጣጣኝ የስርዓተ ጾታ ዕድገት በማምጣት ለአገራቸው ሁለንተናዊ ለውጥ የየበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ከጡት ጀምሮ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ ይደግፏታል።
ሴት ልጅ ብረት መዝጊያ እንድታመጣ ሳይሆን እራሷም ብረት መዝጊያ ሆና እንድታድግ ገና ከልጅነት ዘመን ጀምሮ መሥራት እንደሚገባ የምትመክረው እየሩሳሌም የድርጅቷ ዋና የሥራ ትኩረትም በዚሁ ተግባር ላይ እንደሆነ ታስረዳለች። ሴቶችን ዝቅ በማድረግና ከማህበራሰባዊ ተሳትፎ በማራቅ እየተገለሉ እንዲቀጥሉ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችና አመለካከቶችን በብርቱ እየተዋጋች ትገኛለች። በተለይ ምን ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ፤ ሴት ሲበዛ ጎመን ጠነዛ፤ ሴት የላከው ሞት አይፈራም የሚሉና ሌሎች ሴቶችን የሚያንቋሽሹ፤ዝቅ የሚያደርጉና የሚያገሉ ተረትና ምሳሌዎችን ከጾታ አጋሮቿ ጋር በደቦ በማውገዝ ሴቶች የሚበረታቱባቸውንና ከወንድ አጋሮቻቸው ጋር እኩል መሆናቸውን የሚያሳዩባቸውን በርካታ ሥራዎች በመሥራት በብርቱ እየተጋች ነው። ድርጅቱን የመሰረተችውና በሥራ አስኪያጅነት እያገለገለች ያለችው እየሩሳሌም በርካታ ሴቶች የማህበረሰቡን ጫና ተቋቁመው ለስኬት እንዲበቁ የአእምሮ ውቅር ማስተካከል የሚያስችሉ በርካታ መድረኮችን ስታዘጋጅም ቆይታለች።
እኛም እየሩሳሌም ትጋቷም ሆነ በአእምሮ ውቅር ግንባታ የምታደርገው ዳግም ትግልም በድጋፍ ይጠናከር መልዕክታችን ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2015