• የኢትዮጵያ የሙስሊም ጉዳዮች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የጥናት ሪፖርቱን አቀረበ
አዲስ አበባ፡- ‹‹ጠንካራ የሙስሊም ኡማ / ማህበረሰብ/ ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረት ነው ብለን በጽኑ እናምናለን። በመሆኑም ስብሰባው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንድ ሁነው ሥለ ሰላም፣ሥለ ፍቅር፣ሥለ አንድ የሚሰብኩበት ሊሆን ይገባዋል። ›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የሙስሊም ዑለማዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንዳስታወቁት መንግስትና የሙስሊሙ ወኪሎች በጋራ የሚሰሩት የሙስሊሙን ጥያቄ ለማስከበር፣ ለማክበር የዜግነትና መንግስታዊ ኃላፊነት ሥላለባቸው ብቻ ሳይሆን የሙስሊሙ አንድነት መረጋገጥ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ እንዲሁም እድገት ለማረጋገጥ በጽኑ በመረዳትና በማመን ነው።
የሰላም ሚንስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው እንዳስገነዘቡት፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በመካከላቸው የሚስተዋለውን የመከፋፈል፣የጥላቻና የልዩነት ችግር ለመቅረፍ ከዚህ የተሻለ ጊዜ የሚጠብቅ ካለ የዋህነት ነው። ሥለዚህ ይህ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጊዜ ወስዶ በጥንቃቄና በዝርዝር ያቀረባቸውን አንኳር ነጥቦች በአጽንኦት ተረድቶ የመፍትሔው አካል መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
ዘጠኝ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በጥናት የደረሰባቸውን አራት አንኳር ነጥቦች ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ከ300 በላይ ኡላሞች፣ ወጣቶች፣ጠቅላይ ሚንስትሩና የሰላም ሚንስትሯ በተገኙበት ይፋ አድርገዋል።
‹‹ሁላችሁም ሙስሊሞች አንድ ናችሁ። አለመስማማቱ፣አለመግባባቱ፣ንትርኩና ግጭቱ የሚፈጠረው አመለካከታችን ላይ ባለው የተዛነፈ ነገር የተነሳ ነው። ሥለዚህ የተዛነፈውን ማንነታችንን አስወግደን አንድነትን በመፍጠር የተጀመረውን ለውጥ አቅማችን በፈቀደ ልክ ልናግዝና ልንደግፍ ይገባል›› ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሐጅ ሙፍቲ ኡመር ኢድሪስ ናቸው።
በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖዎችንና ውስንነቶችን ተቋቁሞ ከደረሰባቸው የመፍትሄ ሐሳቦች መካከል የሚከተሉት ነጥቦች ተጠቃሾች ናቸው ሲል የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው አብራርቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሕጋዊ ሰውነት ከማንኛውም ተራ ማህበር ያልተለየ በመሆኑ በተቋሙ ነጻነት፣ማንነትና አደረጃጀት አቅም እንዲሁም በሌሎች ነጻ ኢስላማዊ ማህበራት መቋቋም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነው። በመሆኑም በአዲስ መልክ ሊደራጅ የሚችልበትን ብቻ ሳይሆን በሥሩም እህት ድርጅቶችን የማቋቋም ሥልጣን እንዲኖረው በሚያስችል መልኩ የሚያደራጅበት ጥናት ተዘጋጅቷል። ለሚመለከተው መንግስታዊ አካልም ተልኳል ብሏል ኮሚቴው።
እንደ ኮሚቴው ገለፃ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብና መዋቅር ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታና ወደፊትም ሊደረስበት የሚችለውን ግብ ሊያሳልጥ በሚችል መልክ መከለስ እንዳለበት በመታመኑ በዚህ አቅጣጫም በርካታ ገጽታ ያለው ረቂቅ የመተዳደሪያ ደንብና መዋቅር ተዘጋጅቷል።
የእስልምና ሐይማኖት ጥልቅና የሐሳብ ብዝኃነትን የሚያሥተናግድ ቢሆንም በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሸሪዓው በሚፈቅደው አግባብ ለመፍታት ያስቸገረበት ገጽታ መኖሩን ያስታወሰው ኮሚቴው ሁኔታው ሁሉንም ያሳዘነ ነው ሲል ተናግሯል። በዚህ ሰበብም ወንድም ከወንድም፣ እህት ከእህት፣ኡስታዝ ከኡስታዝ፣ሸህ ከሸህ ተጠላልፎ በጠላትነት የመተያየት አዝማሚያ ተስተውሏልም ነው ያለው ኮሚቴው።
ይህን አደጋ ለመታደግ መሪ ድርጅት እንዲቋቋም ተቋሙ የተወሰኑ ቡድኖች ብቸኛ ንብረት መስሎ እንዳይታይ፤ ያለፉ ቀውሶችንም ለማረም እንዲቻል የወደፊት ሁሉን አቀፍ መጅሊስ ሊመራበት የሚገባው ባለ 8 ዓላማ የሥነስርዓት ደንብና የመግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉንም ኮሚቴው አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2011
በመሐመድ ሁሴን