
–የክፍያ ሥርዓቱ በመዲናዋ ከዚህ ወር ጀምሮ የሚፈፀም ይሆናል
አዲስ አበባ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ ከሐምሌ ወር ጀምሮ የመብራት አገልግሎት ክፍያ በዲጂታል ሥርዓት የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡ በአዲስ አበባ ከዚህ ወር ጀምሮ የድህረ መብራት ክፍያ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ይሆናል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እስካሁን 30 በመቶ ብቻ የሚሆን ተገልጋይ የድህረ ክፍያ በዲጂታል የክፍያ አማራጭ የሚከፍል ሲሆን በአዲስ አበባ ከዚህ ወር ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የድህረ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በዲጂታል እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡
በቀጣይም በመላ አገሪቱ የሚገኙ አገልግሎት መስጫዎች ከተያዘው ዓመት ሐምሌ አንድ ጀምሮ ድህረ ክፍያ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል አማራጭ እንዲያደርጉ ይደረጋል ብለዋል፡፡ እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ አብዛኞቹ ደንበኞች የድህረ ክፍያ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
እነኚህ ደንበኞች አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ በቆጣሪ አንባቢ አማካኝነት በየወሩ ክፍያቸውን የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ አገልግሎቱን ቀልጣፋ፣ ፈጣን እና ቀላል ለማድረግ የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡
ከአማራጮቹ መካከልም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመሆን ያስጀመርናቸው በሲቢኢ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግ እንዲሁም ዳይሬክት ዴቢት ዋነኞቹ ናቸው ያሉት አቶ መላኩ፤ አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋትም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን ቴሌ ብርን ተግባራዊ አድርገን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ በተመለከተ በሁለት የተከፈሉ ተገልጋዮች አሉት ብለውም፤ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ለመስጠትም ሆነ ለመጠቀም በአንድ ቦታ ታጥሮ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ አገልግሎቱን ለማስፋትም አሁን አጠቃላይ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በማድረግ በሁሉም ማዕከላት የዲጂታል አገልግሎት መሰጠት ተጀምሯል ብለዋል ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በካርድ የማይጠቀሙ ደንበኞች ስማርት ቆጣሪን መጠቀም እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም እስካሁን አምስት ሺህ የሚሆኑ ደንበኞች ላይ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ስማርት ቆጣሪው ብዙ ኃይል ለሚጠቀሙ ደንበኞች ምንም ዓይነት የቆጣሪ አንባቢ ሳይላክ ክፍያውን መክፈል የሚያስችል ነው፡፡ ይህም በዋናነት ተገልጋዩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም