የማዕድን ዘርፍ ለአገር ምጣኔ ሀብት እድገት በተለይ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለዜጎች የገቢ ምንጭነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።አገራችንም በአስር ዓመቱ መሪ እቅድ የማዕድን ዘርፉ ለምጣኔ ሀብት ያለውን አበርክቶ ታሳቢ በማድረግ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች።ይህን ተከትሎም በዘርፉ በርካታ የማዕድን ጥናትና ልየታ ሥራዎች ተከናውነዋል። በወርቅ ማዕድን ልማት በኩል ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ እየገቡም ይገኛሉ።እነዚህ ኩባንያዎች ወርቅ ማምረት ሲጀምሩ አሁን በባህላዊ መንገድ ከሚገኘው የላቀ እንደሚያስገኙ ከማዕድን ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሚመረተው ወርቅ አብዛኛው በባህላዊ መንገድ የሚገኝ ነው። በዚህ መንገድ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሲቀርብ ቆይቷል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለብሔራዊ ባንክ የሚገባው መጠን መቀሰኑ እየተገለጸ ይገኛል።ምከንያቱ ደግሞ በሕገወጥ የወርቅ ግብይት ሳቢያ መሆኑ ታውቋል፡፡
መጋቢት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ለብሔራዊ ባንክ መግባት ያለበትን ያህል ወርቅ በዚህ አመት ገቢ እንዳልተደረገ ገልጸዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ከአሶሳ 20 ኩንታል ወርቅ ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቦ አንደነበር፣ ዘንድሮ ግን ሦስት ኩንታል ብቻ መቅረቡን አስታውቀዋል።ብሔራዊ ባንክም ወደ ክምችት ክፍሉ የሚገባው የወርቅ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ከወራት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
የማዕድን ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸምን ዋቢ ያደረገ የኢዜአ ዘገባ እንዳመለከተው፣ በዘጠኝ ወሩ በአጠቃላይ ከማዕድናት ኤከስፖርት 172 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል።ከተገኘው ገቢ 150 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ከወርቅ የተገኘ ነው።ይህ አፈጻጸም ከ2014 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን በ61 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ በ66 በመቶ ቅናሽ ታይቶበታል።
ከዚህ መረጃ መረዳት የሚቻለው በሕገወጥ የወርቅ ግብይት የተነሳ አገሪቱ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን እየተደረገች መሆኑን ነው።መንግሥት ችግሩን በሚገባ ተገንዝቦ ለመፍታት እየሠራ ነው።ወርቅ አምራች ክልሎች እንደ ክልል እየሠሩ ይገኛሉ። በሌላም በኩል የማዕድን ሚኒስቴር፣ የወርቅ አምራች ክልሎች፣ የተለያዩ እርከን አስተዳደሮችና ወርቅ ገዥው ብሔራዊ ባንክ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ሕገ ወጥ ግብይቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
የአገሪቱ የጸጥታና ደህንነት ግብረ ኃይልም በሕገወጦች ላይ እርምጃዎች እየወሰደ ነው።በሕገወጥ ድርጊት ፈጻሚዎቹ ላይ በክልልም በፌዴራል መንግሥት ደረጃም እርምጃዎች ተወሰዷል። በቅርቡ የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በሰጠው መግለጫ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው የሆኑትን ኢትዮጵያውያን ከእነ ማስረጃዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፤ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መመላከቱ ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ ባንክም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የወርቅ ዋጋ ከፍ ያለ ጭማሪ በማድረግ ወርቅ ከአምራቾች ሲረከብ ቆይቷል።ባንኩ ባለፈው ዓመት ሰኔ 16 ቀን 2014ዓ.ም ከወርቅ የዓለም ዋጋ የ35 በመቶ (35%) ተጨማሪ ክፍያ እንደሚያደርግ አስታውቆ የወርቅ ግብይቱን ሲያከናውን እንደነበር ይታወሳል።ባንኩ ማሻሻያው ወቅታዊውን ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑንም በወቅቱ ተጠቅሷል።ጭማሪውም ወደ ብሔራዊ ባንኩ የሚገባው የወርቅ መጠን ከፍ እንዲል ማስቻሉን ያስታወቀበት ሁኔታም እንደነበር ይታወሳል።
ባንኩ ሰሞኑንም ወርቅ ከአምራቾች በሚገዛበት ዋጋ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።ማሻሻያውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቀው፤ ቦርዱ ሚያዝያ 25 ቀን 2015ዓ.ም በጉዳዩ አስፈላጊነት ላይ ውይይት በማካሄድ ውሳኔ ማሳለፉን ነግሮናል።በውሳኔው መሠረትም ከሚያዝያ 28 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ ለአቅራቢዎች ይከፈል የነበረውን የ35 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ በማስቀረት በየዕለቱ በሚወጣው የዓለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ላይ ጭማሪውን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኘው ነው የገለፀው፡፡
ባንኩ በወሰደው የማሻሻያ እርምጃም ከ50 እስከ 150 ግራም ወርቅ ለሚያቀርቡ የ35 በመቶ፣ ከ150 ነጥብ 01 እስከ 1000 ግራም 52 በመቶ፣ ከ1000 ነጥብ 01 እስከ 5000 ግራም 55 በመቶ፣ ከ5000 ነጥብ 01 ግራም በላይ ለሚያቀርቡ ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ ለወርቅ አቅራቢዎች ክፍያ ለመፈጸም ባንኩ በውሳኔው አስታውቋል።
ይህ የባንኩ እርምጃ ለወርቅ ግብይቱ ባለው ፋይዳና ሕገወጥ ግብይቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መደረግ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎችም ቀጣዩን ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ። ሙያዊ ምክረ ሃሳቡን የሰጡን የማዕድን ዘርፉን በምርምር፣ የድጋፍ ጥያቄ ሲቀርብለትም በሀሳብና በተለያዩ መንገዶች በማገዝ ከአማራ ክልል ማዕድን ቢሮ ጋር እየሠራ ያለው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሥነምድር ሳይንስ (ጂኦሎጂ) ትምህርት ክፍል ዲን የሆኑት ዶክተር ምንያህል ተፈሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የማዕድን ዘርፉን ከፈተኑት አንዱ ሕገ ወጥ ግብይት ነው።
ዶክተር ምንያህል ይህን ድርጊት መንግሥት መሥመር ማስያዝ ካልቻለ እንደ አገር ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አይቻልም። የማዕድን ዘርፉ አገር ሳትሆን ግለሰቦችና ደላላዎች የሚበለጽጉበት ሆኖ የሚቀጥልበት ሁኔታ ይፈጠራል በማለትም ስጋታቸውን ያመለክታሉ።
ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርብበትን ዋጋ ማሻሻል አንዱ ጥሩ የመፍትሄ እርምጃ መሆኑን ዶክተር ምንያህል ጠቅሰው፣ የወርቅ ግብይቱ የሚከናወንበትን የረዘመ ሰንሰለት ማሳጠርም ሌላው መፍትሄ መሆን እንደሚኖርበት ይጠቁማሉ።ልማቱ በሚካሄድበት ስፍራ ላይ ግብይት የሚከናወንበት መንገድ የተሳለጠ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
«ግብይቱ ካልተመቻቸ አልሚው ለመሸጥ ረጅም መንገድ ሲጓዝ ለሕገወጥ ደላሎች የሚጋለጥበት ሁኔታ ይፈጠራል» የሚሉት ዶክተር ምንያህል ይህን ለማስቀረት አልሚውና ግዥውን የሚፈፅመው ሕጋዊ አካል በቅርበት የሚገበያዩበትን ሁኔታ በማመቻቸት ችግሩን መቀነስ ሌላው መፍትሄ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የማዕድን ልማቱ በሚገኝበት ቦታ ከክልል ርእስ መስተዳድሮች ጀምሮ እስከታችኛው የመዋቅር እርከን ድረስ የማዕድን አወጣጡንና ግብይቱን የሚከታተልና የሚቆጣጠር የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የተጠናከረ ተግባር ማከናወን ከመንግሥት ይጠበቃል።እያንዳንዱ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ከተቻለ ሕገወጥ ሰንሰለቱ እየላላ ይሄዳል።በዚህ መንገድ ያልተቋረጠ ሥራ ከተሠራ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባይወገድም መቀነስ ይቻላል፤ ሕጋዊ አሠራር የግድ መኖር አለበት፡፡
ዶክተር ምንያህል፣ እሴት ያልተጨመረበት ማዕድን ለገበያ ማቅረብ ለሕገወጥነት መስፋፋት ሌላው መንገድ እንደሆነም ይጠቅሳሉ።እስካሁን ባለው ተሞክሮ በስፋት ለገበያ እየቀረበ ያለው ጥሬ ማዕድን መሆኑንም በመግለጽ፣ ማዕድኑ በዚህ መልኩ ለገበያ ሲውልም ሊያወጣ የሚችለው ዋጋም የሚሰጠውን ከፍተኛ ግምት ያህል አይደለም ሲሉም ያብራራሉ።በተለይ እሴት የተጨመረበት ማዕድን ለገበያ አለማቅረብ የተሻለ ገበያ እንዳይገኝ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የጥራት መጓደልም ሌላው ችግር ነው።የማዕድን ልማቱ በሳይንሳዊ መንገድና በቴክኖሎጂ የታገዘ አለመሆኑም ለጥራት መጓደል ምክንያት እንዲሆን አድርጓል።የጥራት መጓደል ለዋጋ መውረድም መንስኤ ስለሚሆን ይህም ሊታሰብበት ይገባል።ቴክኖሎጂ የጥራት ብክነትንም ለማስቀረት እንደሚረዳ በመጥቀስ፣ ልማቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።በማህበር ተደራጅተው በዘርፉ ላይ የሚሠሩት አልሚዎች ክህሎቱ እንዲኖራቸው ማድረግም ይገባል ሲሉ ይገልጻሉ።መሀል ላይ ሆኖ በመደለል የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያሳድደውንም ማስወጣት የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር ሌላው መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ማድረግ ከተቻለ ከዘርፉ የተሻለና የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
«ማዕድን አልሚዎች በቀጥታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቁን በሕጋዊ መንገድ ቢያስረክቡ ደስተኛ ይሆናሉ» የሚሉት የትምህርት ክፍሉ ዲን፣ ባንኩ የሚሰጣቸው ዋጋም የተሻለ ነው ብዬ እገምታለሁ ይላሉ።እሳቸው በሕገወጥ ግብይቱ ደላላው እንጂ አልሚው ተጠቃሚ አይሆንም የሚል እምነት ነው ያላቸው።ለወርቅ አልሚው የተሻለ የሚሆነው በቀጥታ ከባንኩ ጋር ግብይት ማካሄዱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ተግዳሮት በመፍታት ረገድ ከማን ምን ይጠበቃል በሚል ለቀርበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፤ ግብይቱን ከሕገወጥነት ለመከላከል ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።ማዕድን ሚኒስቴር፣ ልማቱ በሚካሄድበት ሥፍራ የተቋቋሙት ቢሮዎች ቀጥታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩበትን አሠራር መፍጠር ይኖርባቸዋል።የተናበበ ሥራ ከተሠራ ተግዳሮቶችን በጋራ መቋቋም ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አናሶራ፣ ቦሬ፣ ኦርዳጂላ ወረዳዎች ውስጥ በቅርቡ በወርቅ ማውጣት ሥራ የተሰማራውና የገናሌ ወንዝ ተፋሰስን ተከትሎ በስፍራው ለማከናወን ላቀደው የወርቅ ልማት ሥራም የወርቅ ማጠቢያ ማሽን የተከለው የጀኔራል ቢዝነስ ግሩፕ አካል የሆነው የታይም ባለቤት አቶ መኩሪያ ባሳዬ ግን ብሔራዊ ባንክ የወሰደው የዋጋ ማሻሻያ እርምጃ ሕገወጥ የወርቅ ግብይቱን በዘላቂነት ለመቆጣጠር መፍትሄ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።ማሻሻያው መደረጉን ተከትሎ የጥቁር ገበያውን ከፍ ማለቱን ነው የጠቆሙት።
‹‹በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር የገበያ ጉዳይ ብቻ አይደለም›› የሚሉት አቶ መኩሪያ፣ ክትትልና ቁጥጥሩን በማጥበቅ ሕጋዊ መሥመር ማስያዙ ላይ መሠራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።ድርጅታቸው የአካባቢው አስተዳደር ለሥራቸው ምቹ ሁኔታ ባለመፍጠሩ የተነሳ በበጀት ዓመቱ በማልማት ላይ እንዳልነበር ጠቅሰው፣ ጉዳዩን ማዕድን ሚኒስቴር እንዲያውቀው በደብዳቤ ማሳወቃቸውንም ይገልጻሉ።
ከጀመሩት የወርቅ ልማት ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ከፀጥታ አካል የደረሳቸው የስልክ ጥሪ ተስፋ እንደሰጣቸው የሚናገሩት አቶ መኩሪያ፣ የፀጥታው አካል በአካባቢው ላይ አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ሥራ ከሠራ ድርጅታቸው 24 ሰዓት በመሥራት አገር ከዘርፉ የምትጠብቀውን ውጤት ለማሳካት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
አቶ መኩሪያ ደጋግመው ያስገነዘቡት ሕገወጥነትን ለመከላከል የቁጥጥር ሥርዓቱ እንዲጠብቅ ማድረግ ላይ ነው።መንግሥት በሕገወጥ የማዕድን ግብይት ላይ የተሰማሩትን ለይቶ በማውጣት ለሕግ ማቅረብ እንዲሁም የክትትል ሥርዓቱን ማጠናከር ይኖርበታል ሲሉ ያስገነዝባሉ።ወርቅ ወደ ጎረቤት አገራት ሶማሌ፣ ኬንያና ወደ ተለያዩ አገራት በሕገወጥ መንገድ መሸጡን ቀጥሏል ሲሉም ይጠቁማሉ።ዛሬ በታንታለም ማዕድን የማትታወቀው ኬንያ ታንታለም ለዓለም ገበያ እያቀረበች መሆኑን ጠቅሰውም፣ የታንታለሙ ምንጭ ኢትዮጵያ እንደሆነች በመግለጽ በቁጭት ተናግረዋል፡፡
‹‹ወርቅ ከመሬት የሚገኝ ሀብት ነው።ልማቱ እንዲከናወን ለአምራቹ ፈቃድ የሚሰጠው መንግሥት ነው።ፈቃድ የሰጠው አካል አምራቹ ያመረተውን ወርቅ ለሕገወጦች እንዳያቀርብ መከታተልና መቆጣጠር ይጠበቅበታል።ቁጥጥር በመላላቱ አገር እንዳትጠቀም ሆኗል›› ሲሉ አቶ መኩሪያ አመልክተው፣ ጉዳዩን የአገርን ጥቅም ከማሳጣት ጋር ያያይዙታል።
ሕገወጥ ግብይቱን የመከላከሉ ሥራ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም አቶ መኩሪያ ያስገነዝባሉ።እንደ አገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ማጋጠሙ ዜጎች በኢኮኖሚ እንዲጎዱ፣ ህሙማን መድኃኒትና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዳያገኙ እያደረገ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህ ተግዳሮት መንግሥትን ብቻ ሊያሳስበው አይገባም፤ በልማቱ ላይ የተሰማራው አካልም ኃላፊነት አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ዶክተር ምንያህል ሕገወጥ ድርጊቱን ተቀናጅቶ መከላከል ይገባል ሲሉ የሰጡትን ሀሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ በመስጠትም ሕገወጥ ድርጊቱን የመከላከሉ ሥራ የጋራ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።‹‹ትብብሩ ሲኖር ችግሩም ይወገዳል›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2015