ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። በ2013 ዓ.ም ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሪካል እና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። ወጣት አቢጊያ ፍቅረማሪያም። ወጣቷ ከትምህርቷ ጎን ለጎን በሆቴል ቤት ንግድ ሥራ የተሰማሩ ቤተሰቦቿን እያገዘች ማደጓን ትናገራለች። ከዩኒቨርስቲ እንደወጣች በተማረችበት የሙያ ዘርፍ ሥራ ብታገኝም በዚያው የሆቴል ሥራ ላይ መቆየቷን ታመለክታለች። ይሁንና የራሷን የንግድ ድርጅት መክፈት እንዳለባት በማመን አዲስ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የንግድ ሃሳብ በማመንጨት ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያለውን የወይፈን ስጋ ቋንጣ ወደ ማምረት ገባች።
የጀመረችውን የቋንጣ ምርት ውጤታማ ይሆን ዘንድ በተማረችበት ሙያም እየተዘዋወረች እንደምትሠራ አጫውታናለች። ኢትዮጵያ በከብት ሃብት ግንባር ቀደም ሆና ሳለ ሃብቷን በሚገባ ያለመጠቀሟ ጉዳይ ሁልጊዜም የሚያስቆጫት መሆኑን የምትናገረው ወጣት አቢጊያ ፤ በተለይ እሴት ጨምሮ የበለጠ ገቢ ማስገባት ያለመቻሏ ዘወትር ለምን? እና እንዴት? የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭሩባት እንደነበር ታወሳለች። በመሆኑም ምንም እንኳን ከተማረችበት የሙያ ዘርፍ ጋር ከፍተኛ ርቀት ቢኖረውም፤ ከቤተሰቦቿ ያካበተችውን የንግድ ልምድን ምርኩዝ በማድረግ በአቅሟ ራሷንም ሆነ ሃገሯን በዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ቆርጣ መነሳቷን ታመለክታለች። አስቀድማ ግን የጠቆመችው፤ በሃገር ውስጥ ያለውን ተፈላጊነት ለማወቅ ሰፊ ጥናት አካሂዳለች። በጥናቱ መሠረትም በገበያ ላይ ቋንጣ በጣም ተፈላጊ ምርት መሆኑን እንደተገነዘበች ታመለክታለች።
የቋንጣ ምርቱን ኢትዮጵያዊ ጣዕም እና ለዛ እንዲይዝ ከማድረግ ጎን ለጎን ዘመናዊ በመሆነ መንገድ በውስጡ አስፈላጊ ንጥረ ነገር እንዲይዝ እንዲሁም አላስፈላጊ ስቦችን በመለየት ወደ ማዘጋጀት መግባቷን ታብራራለች። ‹‹በአሁኑ ወቅት እያመረትን ያለነው ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያለውንና ለወጥ መሥሪያ የሚያገለግል የተከተፈ ቋንጣ ነው›› ትላለች። ቀዩን ከነጩ ስጋ በመለየት እንደደንበኞቿ ምርጫ አድርቃ እያቀረበች መሆኑን ተናግራለች። ይህም በደምበኞቿ ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱንም አክላለች።
በቀጣይም እንደየሰው ፍላጎት በተለይም ከሕፃናት ጀምሮ ሥጋ በጥሬው መብላት ለሚቸገሩ አካላት ምቹ እና መመገብ በሚቻልበት መንገድ ለማዘጋጀት እቅድ መያዟን ታመለክታለች። ከዚህም ባሻገር አስተማማኝ እና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዓላማ ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አመላክታለች። በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት ተቀባይነት ማግኘት ይቻላል? የሚለውን የገበያ እና የመረጃ ጥናት እያካሄደች መሆኑን ጠቅሳለች።
እንደወጣት አቢጊያ ገለፃ፤ የቋንጣ ሥራ በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ለስድስት ወር ብቻ የሚሠራ ነው። ምክንያቱም ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አማኝ እና ጿሚ በመሆኑ ተፈላጊነቱ የሚያይለው በዓመት ውስጥ ፆም በማይኖርባቸው ስድስት ወራት ብቻ ነው። በመሆኑም ይህንን ጊዜ በመጠቀም ድርጅቷ በስፋት ለማምረት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በተለይም የፋሲካ በዓልን ተከትሎ የቋንጣ ምርታቸው በከፍተኛ መጠን ተፈላጊ በመሆኑ የምርት አቅሟን ከፍ በማድረግ ለተለያዩ ሆቴሎች እና ሱፐር ማርኬቶች በማከፋፈል ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት በቀን ከአስር ኪሎ ሥጋ ያላነሰ ቋንጣ የማዘጋጀት አቅም ላይ የደረሰች ሲሆን፤ ለሰባት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ችላለች። በቀጣይ ግን ምርቷን እና ተደራሽነቷን በማስፋት የሠራተኞቿን ቁጥር ከዚህ በላቀ መልኩ ከፍ ለማድረግ አቅዳለች።
የድርጅቷ ቋንጣ አሠራርም ሆነ የአስተሻሸግ መንገዱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የምትናገረው ወጣት አቢጊያ፤ ሥጋውን የማድረቅ ሂደቱም ንጽሕና እና ጥራት ባለው መንገድ እንዲካሄድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑን ታብራራለች። ‹‹ቋንጣ በባሕሪው የቱንም ያህል ጊዜ ቢቀመጥ የማይበላሽ ቢሆንም በሂደት ጣዕሙ የሚለወጥ በመሆኑ የምናስረክበው ትዕዛዝ እንደተቀበልን ወዲያውኑ ሠርተን ነው።›› በማለትም ታስረዳለች። ይህም የደንበኞቻቻውን ፍላጎት ለማሟላት ከማስቻሉም ባሻገር በብዙዎች ዘንድ ያላቸውን እምነት እና ተቀባይነት እንዲዳብር ምክንያት እንደሆነም ኣመላክታለች። ይህንንም ከደንበኞቻቸው በየጊዜው በምርቶቻቸው ዙሪያ ግብረ መልስ በመጠየቅ የሚረዱበት አሠራር መኖሩንም ጨምራ ጠቁማለች።
ወጣት አቢጊያ እንደምትገልፀው፤ በዘመናዊ መንገድ ቋንጣውን ለማድረቅ የሚከተሉት አሠራር በባሕላዊ መንገድ ይፈጠር የነበረው ጥሩ ያልሆነ ጠረን ወይም ሽታ ለማስወገድ አግዟቸዋል። እንዲሁም ይባክን የነበረውን ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ ቀናት ያላነሰ ጊዜ መታደግ አስችሏቸዋል። በአሁኑ ወቅት ምርታቸውን በስፋት ለማቅረብ ያስችላቸው ዘንድ ከአጋር ድርጅቶች ጋር መግባባት ላይ መደረሱ፤ ይህም አሁን ሆኖ መሬት መውረድ ከቻለ ኢትዮጵያን እንደ ቀንድ ከብት ሃብት መሪነቷ ሁሉ በቋንጣ ምርትም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ያግዛል የሚል እምነት ይዛለች።
ከዚህ ባሻገር የምግብና መድኃኒት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመሆን ምርቱ በየጊዜው ጥራቱ ተጠብቆ መመረቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቦታ እንዲሁም ለማሸግ የሚያስችሉ መሣሪያዎችን በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ታስረዳለች። በተለይ ሰፊ እርድ የሚከናወንበትን ሥፍራ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ታመለክታለች። በተጨማሪ ትልልቅ ሆቴሎች ምርቶቻውን እንዲቀበሉ ለማድረግ በነፃ የማስቀመስ ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግራለች። በዚህ አበረታች ምላሽ እያገኙ መሆናቸው ወደፊት ላለመችው ትልቅ ሕልም መሳካት ተስፋ እንደሰጣት ወጣት አቢጊያ አመልክታለች።
እንደ ወጣት አቢጊያ ገለፃ ፤ በዚህ ሥራ ውስጥ ትልቁ እና ዋነኛው ፈተና የደንበኞችን እምነት ማግኘት ሲሆን በተለይም እንደእርሷ ላለ ዘርፉን ገና ለተቀላቀለ ጀማሪ የኅብረተሰቡን እምነት አግኝቶ መቀጠል ከባድ ነው። ጥቂት የማይባለው ሰው በተጨባጭ የበሬ ሥጋ መሆኑ ላይ ጥርጣሬ ያለው በመሆኑ እነሱን ለማሳመን ብዙ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የገበያ ትስስር ፈጥሮ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠልም የሥራ ፈጣሪን ቁርጠኝነት ይፈልጋል።
በሌላ በኩል በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የበሬ ዋጋ ጋር ተያይዞ የሥጋውም ዋጋ ከፍ ስለሚል ቋንጣውንም ከፍ ባለ ዋጋ ለመሸጥ የሚገደዱ በመሆናቸው ይህም ደግሞ በአንፃራዊ ሁኔታ ደንበኞችን ያሸሻል የሚል ስጋት እንዳላት ወጣት አቢጊያ ትናገራለች። ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የዕርድ ቦታ በማመቻቸት እንዲሁም በራስዋ ድርጅት ውስጥ እርድ በማከናወን የሥጋ ግዢውን ለማቆም እቅድ መያዟን ታመለክታለች። ይህ ደግሞ አላስፈላጊ የገበያ ሰንሰለት ከመቀነስ ባሻገር በየጊዜው እያሻቀበ ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ያስችላል የሚል እምነት አሳድራለች።
እንደማንኛውም ወጣት ሥራ ፈጣሪ ሥራ ስትጀምር በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጠሟት መሆኑን የምትናገረው ይህች ወጣት፤ በተለይም በመንግሥት እና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያለው ቢሮክራሲ እሷንም ሆነ ሌላውን ወጣት ሥራ ፈጣሪ ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑን አልሸሸገችም። በዋናነት ደግሞ ከፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት አታካች በመሆኑ ሥራውን ከፍ ለማድረግም ሆነ ለማስቀጠል ፈተና እንደሆነባት ታመለክታለች። እስከ አሁን ባለው ሂደት ምንም አይነት የብድር አቅርቦት ማግኘት አለመቻሏን፤ አነስተኛ የመሥሪያ ማሽኖችንም በራስዋና በቤተሰቧ ባገኘችው ድጋፍ መግዛት መቻሏን ተናግራለች። ይሁንና እሷ ላቀደችው እቅድ መሳካት አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችን ለመግዛት ከ400 ሺ እስከ 500 ሺ ብር እንደሚያስፈልግ ትገልፃለች።
ወጣት አቢጊያ እንደምትናገረው፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በማፍራት ረገድ ሰፊ ክፍተት አለባቸው። በተለይም ከቀለም ትምህርቱ ጎን ለጎን በክህሎት እና ሥነ-ልቦና የጎለበቱ አድርጎ መቅረፅ ላይ ተጨባጭ ችግር ይስተዋልባቸዋል። በእርግጥ ይህ በሁሉም ተቋማት ላይ የሚታይ ችግር አይደለም፤ ጥቂት የሚባሉ ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ሥርዓቱ በተግባር ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን ከማድረጋቸውም ባሻገር ተማሪዎቹ ተመርቀው ከወጡ በኋላ የሥልጠና እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ራሳቸውን እና ሀገራቸውን እንዲደግፉ የሚያደርጉት ጥረት አለ።
እሷ በተማረችበት ተቋም ይህንን እድል አለማግኘቷን፤ ይሁንና በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የተማሩ ጓደኞቿ የተሻለ ድጋፍ ተደርጎላቸው የሚፈልጉት ዓላማ ላይ መድረሳቸውን ስታይ መንፈሳዊ ቅናትና ቁጭት እንዳደረባት አልሸሸገችም። ‹‹እነዚህ ወጣቶች በሥራ አጋጣሚ ባገኘኋቸው ጊዜ በራስ የመተማመን መንፈስ እና በምን ያህል ፍጥነት ራሳቸውንና ሥራቸውን ማሳደጋቸውን ስመለከት የእኛም ተቋም ምንአለ ይህ እድል በኖረ ብዬ ተመኘሁ፤ እንደእነሱ ድጋፍ ባገኝ ኖሮ ከዚህም በላቀ ድርጅቴን ማስፋት በቻልኩኝ ስልም ቁጭት አድሮብኛል›› ስትል ትናገራለች።
በመሆኑም እንደእርሷ ብዙ የሥራ እቅድ እና ትልቅ አገርን የማሳደግ ሕልም ያላቸውን ወጣቶች ማፍራት ይቻል ዘንድ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ድጋፍ እና የትምህርት ሥርዓት ወጥነት ሊኖረው እንደሚገባ ታስገነዝባለች። በተለይም ማኅበረሰብን መሠረት ያደረጉ ችግር ፈቺ ፕሮጀክት ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት፤ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ወረቀት ላይ ያለው የመፍትሔ ሃሳብ በተጨባጭ መሬት ላይ እንዲወርድ ዋነኛውን ሚና የመጫወት ኃላፊነት እንዳለባቸው ታመለክታለች። ‹‹ዩኒቨርስቲዎቹ ለተማሪዎቿቸው የሚያደርጉት ድጋፍ በተጨባጭ አገሪቷ ላሰበችው የልማት ግብ መሳካት የጎላ ሚና አለው›› በማለትም አክላለች።
በወጣቶች በኩልም ቢሆን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት አልፎ ካሰቡት ሕልም ለመድረስ ጥረት በማድረግ ረገድ ሰፊ ክፍተት ማስተዋሏን ወጣት አቢጊያ ትናገራለች። ለዚህ ደግሞ በዋናነት ከልጅነት ጀምሮ ሁሉንም ነገር በቤተሰብ ጫንቃ ላይ በመመርኮዝ ያደጉ መሆናቸው፤ ራሳቸውን እንዲችሉ ማኅበራዊ የአኗኗር ዘይቤ ተከትለው ባለመቀረፃቸው እንደሆነ ታስረዳለች። በመሆኑም በማደግ ላይ እንዳለች ሀገር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በተለይም የመንግሥት ተቋማት ቢሮክራሲዎችን ዘወትር እያነሱ ከማማረር ይልቅ ሌሎች አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን በማፍለቅ ለራሳቸው ራሳቸው ሊሠሩና ሊተጉ እንደሚገባ፤ የማንንም ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅም ባላቸው ነገር ጀምረው ያንኑ ለማስፋት ጥረት እንዲያደርጉ ነው የመከረችው።
‹‹እርግጥ ከሌላው ጊዜ በተሻለ መንግሥት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን ካለው ሰፊ ወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ድጋፍ አለ ወይም ድጋፉ በቂ ነው ብዬ አላምንም›› በማለት ትናገራለች። በቅርቡ ልማት ባንክ ሥራ ፈጣሪ ለሆኑ ድርጅቶች እንዳመቻቸው ዕድል አይነት ሌሎች የድጋፍ መንገዶችን ማስፋት በተለይም ከመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት የሚጠበቅ መሆኑን፤ ይህንንም ጉዳይ እንደዋና አጀንዳ አድርገው የመንቀሳቀስ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝባለች።
እንደሀገር በተለይም በወጪ ንግድ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ካስፈለገ አዳዲስ እና ጀማሪ ድርጅቶች ዘርፉንም ሆነ ገበያውን እንዲቀላቀሉ ማገዝ ያስፈልጋል ባይ ነች። በዚህ ረገድ አሳሪ አሠራሮችን እና ሕጎችን በማስወገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ወሳኝ እንደሆነ ታስረዳለች። ከዚሁ ጎን ለጎን በአቅም የጎለበቱ ትልልቅ ድርጅቶች ከጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ጋር በጋራ ለመሥራትም ሆነ ለመደገፍ ፍቃደኝነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቃለች።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2015