አዲስ አበባ፦ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ መሻሻል እያሳየ የመጣና ዓለም የመሰከረለት ቢሆንም፤ ዕድገቱ እያንዳንዱን ዜጋ ተደራሽ ያላደረገና በቂ የስራ ዕድልም መፍጠር ያልቻለ መሆኑ ተገለፀ።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክብርት ዶክተር ፍፁም አሰፋ፤ ትናንት በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ እስካሁን ሀገራዊ የረጅም ጊዜ ዕይታ ያለው የልማት ዕቅድ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የልማት ዕቅዱ በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በአሁን ወቅት አሉ የተባሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያሰችል ሀገራዊ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተናገረዋል።
እንደ ኮሚሽነሯ ገለፃ፤ ዕቅዱ በዋናነት ኢኮኖሚያዊናማህበራዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ በተለይም ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮችን፣ የአምራች ዘርፎችን፣ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት፣ የከተማ ልማትና ቤቶች፣ የስነ-ህዝብና ልማት፣ የሰው ሀብት ልማትና ሌሎች ቁልፍ ተግባራትን ጭምር በዝርዝር የሚቃኝ ነው። በመሆኑም፤ በቀጣይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሁሉንም ዜጋ ማዕከል ያደረገና እያንዳንዱን ማህበረሰብ እንዲያሳትፍ ሆኖ እየተሰራ ያለ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ መሆኑን ገልፀዋል።
ክብርት ዶክተር መሰረት መስቀሌ፤ በፕላንና ልማት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር በበኩላቸው፤ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በፍጥነት ከሚመጣው ትውልድና ተምሮ ከሚወጣው ስራ ፈላጊ ወጣት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አዝጋሚና ሁሉንም ዜጋ ተደራሽ ያላደረገ በመሆኑ በቂ የስራ ዕድል መፍጠር አልተቻለም።
የኢኮኖሚው መነቃቃት በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት ካለመመዝገቡም በላይ ያለውን የሰው ሀይል ውጤታማ አድርጎ ከመጠቀም አንፃር፤ ክህሎቱንና ተነሳሽነቱን በመጨመር፤ እንዲሁም ለስራ የሚመች አካባቢን ፈጥሮ ውጤታማ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ መጠነኛ መሻሻል እየታየበት እንዳለም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በአሁን ወቅት ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች የያዘ ሀገራዊ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ ዝግጅት፣ በሀገራዊ የልማት ዕቅድ አፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ስርዓትና በልማት ፕሮጀክቶች አመራርና አስተዳደር የህግ ማዕቀፍ ዝግጅቶችን መሰረት በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ በሚያስችል መልኩ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ ከሙያ ማህበራት ጀምሮ የልማት አጋሮችን ጭምር ተሳታፊ በማድረግ ሀገራዊ የአስር ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በፍሬህይወት አወቀ