አዲስ አበባ፦ የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ዕለት ከዕለት ቅናሽ እያሳየ በመሆኑ በኤክስፖርቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ተባለ።
አቶ ትዕዛዙ ኢዶሳ፤ በቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ መረጃና ቁጥጥር ተወካይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ከአሥራ አንድ ዓመት ወዲህ የዓለም የቡና ዋጋ ዕለት ከዕለት እየቀነሰ በመምጣቱ በኤክስፖርቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በመጠን 195 ሺህ አምስት መቶ 74 ቶን ቡና ኤክስፖርት ለማድረግ ታቅዶ፤ 151 ሺህ 211 ነጥብ አምስት ቶን ኤክስፖርት ማድረግ ተችሏል። ይህም ከገቢ አንፃር ሲታይ 498 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የምርትም ሆነ የስቶክ ችግር የሌለ በመሆኑ በመጠን የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በዓለም የቡና ዋጋ ከዕለት ዕለት በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ በገቢ ረገድ የቡና ዋጋ በከፍተኛ መጠን ቅናሽ አሳይቷል። የኒዎርክን ገበያ ስንመለከት የቡና ዋጋ ከአሥራ አንድ ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ቅናሽ እያስመዘገበ ይገኛል። ይህም እንደ ሀገር ኤክስፖርቱ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑን አቶ ትዕዛዙ ገልፀዋል።
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ቡና፤ ቅመማ ቅመምና ሻይ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ እንደመሆኑ አጠቃላይ በሦስቱ ምርቶች በዘጠኝ ወራት ውስጥ በመጠን 158‚039 ነጥብ ዘጠኝ ቶን ምርት ኤክስፖርት በማድረግ 507 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። ምንም እንኳን የቡና ዋጋ ዕለት ከዕለት ቅናሽ እያሳየ የመጣ ቢሆንም ከሦስቱ የምርት ዓይነቶች በኤክስፖርት መጠኑ ቡና ቀዳሚ ሲሆን፤ ሻይ ሁለተኛ ደረጃ፤ ቅመማ ቅመም ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አቶ ትዕዛዙ አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በፍሬህይወት አወቀ