አዲስ አበባ፦ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እሳት በማጥፋት ስራ ላይ ከማተኮር ይልቅ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስልት በመከተል ችግሮችን ከምንጫቸው ማድረቅን ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ የኮሚሽኑን የእስካሁን የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ በመግለጫቸው እንዳሉት፤ የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር በመነሳት ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው በግጭቶቹ መሰረታዊ መንስኤዎች ላይ ነው። በዚህ መሰረት የህዝቦችን ዘላቂ ሰላምና በእውነትና በፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቅ ለማምጣት የሚያስችሉ ግብዓቶችን እስከ ማሟላት የሚያደርሱ ልዩ ልዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ኮሚሽኑ ትኩረት የሚያደርገውም እሳት በማጥፋት ስራ ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስልት በመከተል ችግሮችን ከምንጫቸው በማድረቅ ላይ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል ያደሩትንና የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶች ለማከም፤ በእውነትና በፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት የተጣለበትን ሀላፊነት ለመወጣት ቅድመ ሁኔታዎችን እያሟላ መሆኑን በመግለጫው አመልክተዋል።
ኮሚሽኑ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል የቀረቡ አቤቱታዎችን መነሻ በማድረግ የዜጎችን የመደመጥና በተገቢው መንገድ ፍትህ የማግኘት መብት ለማመቻቸት የሚያስችል የባለሙያ ስብስብ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ይገኛል። ይህ የባለሙያዎች ስብስብ በተለያዩ ጊዜያትና ሀገራት የተከናወኑ የእርቀ ሰላም ሂደቶችን በመፈተሽ ለሀገራችን ይበጃል የሚለውን አቅጣጫ የሚያመላክት ይሆናል።
የእርቀ ሰላም ሂደቱን የተሳካና ውጤታማ ለማድረግ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ልዩ ልዩ የመገናኛ አውታሮችን በመጠቀም በሀገር ውስጥና በውጪ አገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ባደረገው ግንኙነት ዜጎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውና ኮሚሽኑን ለመደገፍ ያሳዩት ቁርጠኝነት አበረታች መሆኑም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በዳንኤል ዘነበ