አዲስ አበባ፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ከቀናት በፊት ግጭት መከሰቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስና የዜጎች የፀጥታ ዋስትና ለማረጋገጥ በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑ ተገለፀ።
የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገለታ ሃይሉ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልል የጸጥታ ኃይሎች የዜጎች አስተማማኝ የፀጥታ ዋስትና ለማረጋገጥ በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛሉ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በተገኙበት ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በመድረኩም የአገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በተለይ ግጭቱ ከተከሰተ ወዲህ እስከ ትላንት ድረስ መተከል አካባቢ ለሁለት ቀናት የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት ሃላፊው፤ይሁንና በአጎራባች በተለይ ዳንጉር ወረዳ ሌሎችም ከአማራ ክልል ጋር የሚያዋስኑ ጃዊ አካባቢዎች የፀጥታ መደፈረስ እንደሚስተዋል አስታውቀዋል።በአካባቢዎቹ የሚስተዋለው የፀጥታ መደፍረስም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ መረጃ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
ግጭቱን ከማስወገድ በተጓዳኝ አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ረገድ ከግጭቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ የተጠረጠሩ 15 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያመላከቱት ፅህፈት ቤት ሃላፊው፤የተጠርጣሪዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በመግለጽ ምርመራው ኅብረተሰቡን ባሳተፈ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
የሁለቱ ክልሎች መንግስታት ዜጎችን ከጉዳት ለመጠበቅ፤ ህብረተሰቡን ለማረጋጋትና አንድነቱን ወደ ቀድሞው ለመመለስ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ እቅድ ማውጣታቸውን አመልክተዋል።
ሚያዚያ 17 ቀን 2011 ምሽት በክልሉ ዳንጉር ወረዳ ማምቡክ ከተማ አቅራቢያ አይሲካ ቀበሌ በግለሰቦች መካከል በተከሰተ ግጭት የዜጎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በታምራት ተስፋዬ