የሰራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት፤ የመነሻ ደመወዝ ወለል አለመኖር፤ የሙያ ደህንነትና ጤንነት አለመጠበቅ ጉዳዮች በአሰሪና ሰራተኞች፤ እንዲሁም በመንግስት በኩል አነጋጋሪነታቸው እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ መደራጀት ህገ መንግስታዊ መብትና አለም አቀፍ ድንጋጌ ቢሆንም በአገር ውስጥ ባግባቡ እየተተገበረ እንዳልሆነ ይገለጻል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አበባው ዋለልኝ እና ዋና ጸሃፊው አቶ ታደሰ ጥበቡ፤ የሰራተኛ ማህበራት በርካታ ችግሮች እንደተደቀኑባቸው ይናገራሉ፡ ፡ በአንዳንድ ተቋማት ሠራተኞች እንዳይደራጁ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚደርግባቸውና ከተደራጁ በኋላም የሚፈርሱ እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራም ባግባቡ እንደማይሰራም ያመለክታሉ፡፡
መደራጀት ለአገር፤ ለሰራተኛውና ለአሰሪውም ጥቅም አለው፡፡ ለምርትና ምርታማነት ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ መብቱ እንዲከበር ትኩረት ማድረግ ይገባል፤ ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ ለሰራተኞች የሚከፈለው ደመወዝ እጅግ ትንሽና ኑሮን ለመቋቋም ያላስቻለው መሆኑን በማንሳትም፤ መንግስት ትኩረት በማድረግ ሊፈታው ይገባል ባይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤ የሰራተኞች የመደራጀትና የመደራደር መብት ጥያቄ ከፍተኛ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በውጭ ኩባንያዎች፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፤ በኢንዱስትሪ ዞኖችና በተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ሰራተኞች ባግባቡ በማህበር አለመደራጀታቸውን ያመለክታሉ፡፡ ችግሩ አሰሪዎቹ የሰራተኛውን የመደራጀትና የመደራደር መብት ስለማይቀበሉት የተፈጠረ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የመነሻ ደመወዝ ወለል አለመኖርም ችግር ፈጥሯል፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የመነሻ ደመወዝ በወር 750 ብር (ሰባት መቶ ሀምሳ ብር)፤ ከፍተኛው ደግሞ 860 ብር (ስምንት መቶ ስድሳ ብር) ነው፡፡ በዚህም ደመወዛቸው የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እንኳን ለመሸፈን ህይወትን አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል፡፡
የሙያ ደህንነትና ጤንነት ችግርም ሰራተኛውን እየተፈታተነ መሆኑን አቶ ካሳሁን ያነሱና፤ አዋጁ በአሰሪው ላይ የሙያ ደህንነት አልባሳትን ማቅረብና በጉዳዩ ላይም መረጃና ስልጠና መስጠትን በአሰሪው ላይ የሚጣል ግዴታ ቢያደርገውም ባለመተግበሩ በስራ ላይ አደጋም ብዙ ሰራተኞች ህይወታቸውን እንደሚያጡና ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ አቶ ካሳሁን ይናገራሉ።
አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሰራተኛው ጉልበት እየነገዱ መሆኑን፤ በህጋዊ ሽፋን ህገ ወጥ ድርጊት እንደሚፈጸም፤ አንድ ሰራተኛ ሊከፈለው ይገባ የነበረን ገንዘብ ቀንሰው ክፍያ የመፈጸም ችግር መኖሩን፤ አሰሪና ሰራተኛ አገናኞች አንድ ጊዜ ብቻ ኮሚሽን መውሰድ ሲገባቸው በየጊዜው ከሰራተኛው ደመወዝ እንደሚቀበሉ ያመለክታሉ፡፡
ኢትዮጵያውያውያን መስራት በሚችሏቸው እንደ ጥበቃ፤ ጽዳት፤ የሂሳብ ሙያ፤ ከባድና ቀላል መኪና አሽከርካሪ የመሳሰሉ አነስተኛ የስራ መደቦች ላይ የውጭ አገር ሰራተኞች ቅጥር እንደሚፈጸምም ነው የሚናገሩት፤ መስፈርቱን የሚያሟሉ ስራ አጥ ወጣቶች እድሉን ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ ሰራተኞች በማህበር ሲደራጁ የማህበር መሪዎች ስራ እንዲለቅቁና የስራ ቦታ ዝውውር በማድረግ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩባቸው ይጠቅሱና፤ መስተካከል እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡
መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡ ፡ ኮሚቴው በውጭ ኩባንያ ያሉ ሰራተኞች እንዲደራጁ ይሰራል፡፡ አሰሪውንና ሰራተኞቹን ያነጋግራል፡፡ ሰራተኞች ሲደራጁ መብትና ጥቅማቸውን እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡ ሰራተኞች ለምርትና ምርታማነት ትኩረት እንዲሰጡ የማንቃት ስራ ይሰራል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡
በ2008 ዓ.ም ሊወጣ በነበረው የአሰሪና ሰራተኞች አዋጅ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ መነጋገራቸውን፤ የደመወዝ የመነሻ ወለል እንዲቀመጥ ሃሳብ አቅርበው ተቀባይነት እንዳላገኙና በልዩነት መውጣታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ከለውጡ በኋላ አጠቃላይ አንቀጾቹ ላይ መወያየታቸውን፤ በየዓመቱ የመነሻ ደመወዝ ወለል እየመዘነ የሚወስን ኮሚቴ ከአሰሪ፣ ከሰራተኛና ከመንግስት ተወካዮች የሚወከሉበት ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚፈቅድ አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ተካትቶ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ያመለክታሉ፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ መደራጀት ህገ መንግስታዊ መብትና ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ነው፡፡ ይህንን በመረዳት አሰሪዎች የሰራተኞችን መደራጀት ሊፈቅዱ፤ መደራጀታቸውንም የግጭት ማስወገጃ፣ ምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ ሊያደርጉት ይገባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ኢሰማኮም ማደራጀቱን ይቀጥላል፡፡ መብቱም በማንኛውም መንገድ እንዲከበር ይደረጋል ብለዋል።
አለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ44ኛ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ130ኛ ጊዜ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2011
በዘላለም ግዛው