በአገር አቀፍ ደረጃ ለቅድመ ልጅነት እንክብካቤ አገልግሎት የሚደረጉ የፖሊሲ፣ የአሠራርና ሌሎች ሁኔታዎች እንደ አገር በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የትምህርትም ሆነ ሌላ የተሳትፎና ተጠቃሚነት ክፍተት በመሙላት እንዲመጣጠን በብርቱ ያግዛሉ ተብሎ ይታሰባል::
አሁን ላይ እንደ አገር ጎልተው የሚታዩት በሥርዓተ ጾታ መካከል ያሉ ክፍተቶች የመጡት ከቀዳማይ የዕድሜ ክልል ጀምሮ በሕፃናት ላይ ባለመሠራቱ መሆኑም ሲነገር ይደመጣል:: ለወንድና ለሴት ልጆች ከጨቅላ የዕድሜ ዘመን ጀምሮ በቤት ውስጥ በወላጆችና በአሳዳጊዎች እኩል የጨዋታና የትምህርት ዕድል ባለመሥጠት፤ እኩል ተጠቃሚ ባለማድረግ፤ እኩል የሚሳተፉበትን ምቹ ሁኔታዎች ባለመፍጠር እንዲሁም በተዛቡ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ሳቢያ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ በማየትና ትኩረት መንፈግ መሆናቸውም ይወሳል::
ትምህርት ሚኒስቴር ይሄን ችግር እንደ አገር ከሥር መሠረቱ መቅረፍን ታሳቢ በማድረግ ጭምር ሰሞኑን የቅድመ ልጅነት ዘመን ፖሊሲ ማዕቀፍን ይፋ አድርጎ ነበር:: ትግበራው ውጤታማ ይሆን ዘንድም ሥራውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ከጤና ሚኒስቴርና ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑና የሆኑ ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ለመሥራትም ወስኖ በአዲስ መልክ ወደ ሥራ ገብቷል::
ጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጥምረት ከሚሠሩ ተቋማት አንዱ ሲሆን፤ በዚሁ ዙሪያ በጤናው ዘርፍ ምን እየተሠራ እንዳለና ምን ለመሥራት እንደታሰበ በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፤ የሕፃናትና የአፍላ ወጣቶች ጤና መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር መሠረት ዘለዓለምን እና የሌሎች ተቋማት ኃላፊዎችን አነጋግረን ያጠናቀርነውን ጽሑፍ ልናስነብባችሁ ወድደናል::
ዶክተር መሠረት እንደሚሉት ጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚሠራው ሥራ አለው:: ሚኒስቴሩ በማህበረሰብም ሆነ በተቋማት ዘንድ የጤናውን ዘርፍ ፍትሃዊና ተደራሽ ለማድረግ በእናቶችና በጨቅላ ሕፃናት እንዲሁም በአፍላ ወጣቶች ላይ የሚሠራውን ሥራ የበለጠ አጠናክሮ በዘላቂነት የሚቀጥልበት መርሐ ግብር እንደሆነ ነው የሚናገሩት::
በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት በሥነ ምግብና ሌሎች ተያያዥነት ባላቸው የጤና አጠባበቅ ሂደቶች ላይ ዛሬ የሚሠራው ሥራ ትውልዱን የተሻለ አድርጎ ለማሳደግ ይረዳል ባይ ናቸው:: በተለይ በትምህርት ዝግጁና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: በዚህ መሠረት ሁሉንም ሕፃናት ለትምህርት ዝግጁ ማድረግ መቻል የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ያሰፍናል:: አሁን ላይ በአገራችንም ሆነ በዓለማችን በየመስኩ የምናየውን በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን ሰፊ የልዩነት በእጅጉ ለማጥበብ ይረዳል::
ሴቶች ከወንዶች ጋር የተመጣጠነ ብቃት፤ ችሎታ፤ ክህሎትና አፈፃፀም እንዲኖራቸው በማድረግ ከወንዶች እኩል እንዲወዳደሩና እኩል ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል:: ይሁንና ጤና ሚኒስቴር ፖሊሲ ያውጣ፤ ስትራቴጂ ነድፎ ከሌሎች አካላት ጋር ይሥራ እንጂ ለአንድ ልጅ መሠረት የሚጣልበት ቤት ውስጥ በመሆኑ በይበልጥ የትግበራው ባለቤት ወላጆችና አሳዳጊዎች እንደሆኑ ዶክተር መሠረት ይናገራሉ:: ሆኖም ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባር ለእናቶችና ለአሳዳጊዎች ብቻ የሚጣል ሳይሆን አባቶችም ከእናቶች እኩል ሕፃናትን ከመንከባከብ ጀምሮ በማስከተብ፤ ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኙና ምቹና ተስማሚ አካባቢ እንዲኖሩ በማድረግ፤ በተለያየ መንገድ በማጫወት ለትምህርት ዝግጁ እንዲሆኑ ኃላፊነቱን ወስደው መንቀሳቀስ አንዳለባቸውም ይመክራሉ::
«ሕፃናት እየተጫወቱ፤ በጨዋታ ነው እየተማሩ የሚያድጉት:: ብዙ እንደ አዲስ ዓለም የሚያዩትንና የሚቆጥሩትን የዓለማችንን ብሎም የአኗኗራችንን ሁኔታ እየተገነዘቡና እየተለማመዱ የሚመጡት በጨዋታ ነው» ይላሉ:: ሆኖም በዚህ በቅድመ ልጅነት ዘመን ሁሉም ሕፃን እንደመሆናቸው የጾታ ልዩነት ሳናደርግ እኩል የመመገብ፤ የመንከባከብና የጨዋታ ዕድል መስጠት አለብን::
ጨዋታዎችንም የወንድ የሴት እያልን መከፋፈል የለብንም:: ወንዱ የሚጫወተውን ሴቷም እንድትጫወት፤ ልጅ ማዘልን ጨምሮ ሴቷ በጨዋታዋ ውስጥ የምታደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ወንዱም እንዲያደርግ ማድረግ ያስፈልጋል::
ይሄን ካደረግን የዛሬው ሕፃን ወንዱ ልጅ ወደፊት አድጎ ትዳር በሚመሠርትበት ጊዜ ልጅ የማሳደጉና የመንከባከቡ ጉዳይ የሴቷ ብቻ አድርጎ አይተወውም:: ቀድሞ ግንዛቤው ካለው ግን እነሱ የሚወልዷቸው ሕፃናት የሁለቱንም ወላጆቻቸውን እንክብካቤ አግኝተው ያደጉ በመሆናቸው ስብዕናቸውም ሆነ ሁለንተናዊ አቋማቸው የተስተካከለ ይሆናል:: እስከ አሁን በመጣንበት በማህበረሰባዊ አኗኗራችን፤ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን የወንድ የሴት እያልን በመከፋፈል ወንዱ የበላይ ሴቷ ደግሞ የበታች ሆነው እኩል እንዳይሳተፉ፤ እኩል እንዳይጠቀሙ ስናደርግ የመጣንበትን የተዛባ ሁኔታ በብርቱ ያስተካክልልናል::
እንደ ዶክተር መሠረት ይሄን ለማሳካት ገና ከጠዋቱ እናት ልጅ ለመውለድ በዕድሜና በሥነ ልቦና ዝግጁ መሆኗ ፤ ልጅ ታቅዶ መወለዱ መታየት ያለበት ነው:: በዚህ በቅድመ ልጅነት ትግበራ ዘመን ከሕፃናት ጽንስ ጀምሮ እናት በጤና ተቋም ሁለንተናዊ ጤናና የሥነ ምግብ ክትትል ማድረግ ይጠበቅባታል:: በተጨማሪም ከዚሁ ከቅድመ ልጅነት ትግበራ ጋር ተያይዞ እናቶች በጤና ተቋም የቅድመ ወሊድ፤ የወሊድና የድህረ ወሊድ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ፤ የጤና ተቋማትም ለትግበራው ምቹ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ በስፋት እንደሚሠራም ዶክተር መሠረት ያወሳሉ:: የፖሊሲ ማዕቀፉ ይፋ ከመደረጉ በፊት በቅድመ ልጅነት ዙሪያ አዲስ አበባና አንዳንድ ክልሎች ላይ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉም ነው ያነሱት::
«ገጠር ላይ ልጅ እርሻ ቦታ ስትሄድም ሆነ ሥራ ስትሠራ እናቱ አዝላው እያጫወተችው የእሷን ድምፅ እየሰማ ነው የሚያድገው:: አዲስ አበባ ውስጥ እናት ከልጇ ጋር ነው ወይ የምትውለው ልጅ ቤት ተቆልፎበት እናት ሌላ ቦታ አትሄድም ወይ ? » ይላሉ:: እንዳከሉትም ከተማ ውስጥ ያለ ወላጅ ወይም አሳዳጊ ሞባይል በመስጠት ነው ልጆች የሚያሳድገው፤ ጥሩ ልብስ ስለገዛንላቸውና ጥሩ ትምህርት ቤት ስላስገባናቸው ነው ወይ ልጆች የሚያድጉት ብሎ እያንዳንዱ ወላጅ ራሱን መጠየቅ አለበት::
ይሄ ውጫዊውን ማሳመር እንዳለ ሆኖ መሠረት የሚጣለው ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ መሆን እንዳለበት ሊገነዘቡ እንደሚገባ ይገልፃሉ:: ጎን ለጎን የልጆች አእምሮ እንዲጎለብት፤ እንዲበለፅግ ማድረግ የሚችሉት በሥነ ልቦና ድጋፍ ሲያደርጉ መሆኑን ማወቅ አለባቸው:: ወላጆች ሕፃናትን በሥነ ምግብ፤ በጤና በሁለንተናዊ ደህንነት የተጠበቁ እንዲሆኑ ሲያደርጉ ለትምህርት ብቁና ዝግጁ እንዲሁም ተወዳዳሪ ይሆናሉ:: «ማዕቀፍ ትግበራ ሂደቱ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ከማምጣት አንፃር ጎልህ ሚና ይኖረዋል» ይላሉ::
በመጀመሪያ ስድስት ዓመት ውስጥ ወንድ ልጆችም ሴት ልጆችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠራቱን በማሳያነት ያቀርባሉ:: ሥራው ውጤታማ ይሆን ዘንድም አብዛኛው ሥራ ለእናቶችና ለአሳዳጊዎች የሚሰጥ መሆኑን ይጠቁማሉ:: ሥራው ከአጠቃላይ ዕድገት ብልጽግና ጋር የሚሔድ መሆኑንም ያወሳሉ:: በመጀመሪያዎቹ ስድስት ዓመታት ላይ ነፍሰ ጡር ከመሆኗ በፊት ያለውን ጊዜ አንድ ሺ ቀናት ከዚያ እስከ ስድስት ዓመት የሚሠራው ሥራ አዋጭ ኢንቨስትመንት ነውና እንስራበት ሲሉም ለባለድርሻ አካላቱ በሙሉ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ::
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና የሕፃናት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ ወይዘሮ ዘብይደር ቦጋለ እንደሚሉት፤ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት የትምህርት ፖሊሲ በ2005 ቢጀመርም የተለያዩ ክፍተቶች ነበሩበት:: አሁን ከደረስንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ዓለምአቀፍ ሁኔታዎችንም አለማካተቱ አንዱ ነው:: ተከልሶ በአዲስ መልክ ሊቀርብ የቻለው ከዚህ አንፃር ማሻሻያ ተደርጎበት እንደሆነም ያስታውሳሉ:: ሕፃናት ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት በዕድሜያቸው ማወቅ የሚገባቸውን የሚነቃቁበትንና ምቹ የሕፃናት ማቆያ አካባቢዎች እንዲኖሩ እንደሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ይሠራልም ይላሉ::
እንደ አማካሪዋ በተለይ የሕፃናት ማቆያን ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ይደረጋል:: ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ እንዲኖራቸው በአዋጅ እንደ መደንገጉ ይኸው የሚተገበር ይሆናል:: በተለይ አሁን ላይ እናቶች ሕፃናትን የሚያቆዩበት ቦታ የሚያጡበት ሁኔታ አለ:: በግል የሕፃናት ማቆያ ለመገልገል ደግሞ የገንዘብ አቅማቸው አይፈቅድም:: በዚህ የተነሳ ሕፃናትን ይዘው ቤት ውስጥ ታስረው የተቀመጡ እናቶች አሉ:: የሕፃናት ማቆያን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድረጉ ሕፃናት ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲውሉ በማድረግ የነዚህን እናቶች ችግር ይፈታል:: ለእናቶች ትልቅ የአእምሮ እረፍት የሚሰጥ ነው::
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያደጉ ሕፃናት በትምህርታቸው ውጤታማ ይሆናሉ:: በሥነ ምግባር፤ በአገር ፍቅርና በተለያየ ሁኔታ የተሻሉ ዜጎች ይሆናሉ:: አማካሪዋ እንደሚሉት ፖሊሲው ወደፊት የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከማድረግ አንፃር ተስፋ የሚጣልበት ነው:: መርሁ «የቀዳማይ ልጅነት ትምህርት ለሁሉም ሕፃናት» የሚል እንደመሆኑ ሁሉም ከስድስት ወር እስከ አራት ዓመት ያሉ ሕፃናት ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ወደፊት ለሴቶች ልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት በተለይም አሁን ያለውን በሥርዓተ ጾታ ዙሪያ ያለ ክፍተት ለመሙላት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል:: በተለይ እናቶች ያለምንም ስጋት ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላል:: ልጆቻቸውን በቅርብ አግኝተው ጡት በማጥባትና በማጫወት እንዲንከባከቡ ያግዛል::
«የተሻሻለው አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ እናቶችና አሳዳጊዎች ይሄን ማድረግ ይችሉ ዘንድ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነው» ያሉን ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ግርማ ናቸው:: እንደሳቸው ፖሊሲው ሁሉም ልጆች የመማር መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል:: በዚህ ፖሊሲ በተለይ በገጠሩና 85 በመቶው ሕዝብ በሚኖርበት አካባቢ ከግንዛቤም ሆነ ከተለያየ አመለካከት የተነሳ ሴት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ያለመላክ ልምድ ተቀባይነት የለውም ወንዱም ሆነ ሴቷ ሕፃን እኩል ዕድል እንዲያገኙ ተደርጓል::
ከዚህ በፊት በተለይም 2005 ዓ∙ም የቅድመ ልጅነት ዘመን ፖሊሲ እንደወጣ እስከ ተወሰኑ ዓመታት ትምህርት ተሳትፎው ሲታይ ገንዘብ ያለው የሚማርበት፤ በአካባቢው ትምህርት ቤት ያለው ትምህርት ቤት የሚገባበት ብቻ ነበር:: በመሆኑም ትምህርት በሁሉም አካባቢዎች ፍትሀዊና ተደራሽ ነበር ማለት አይቻልም:: ተደራሽ አልሆነም ሲባል ከሴቶች አንፃርም እንደሆነ የሚጠቁሙት ኃላፊው ለሴቶች ሕፃናት የሰጠው እኩል የትምህርት ዕድል ተፈፃሚና ውጤታማ እንዳልነበረም ያወሳሉ::
አሁን የሚተገበረው የቅድመ ልጅነት ፖሊሲ ማዕቀፍ እኩል ዕድል ለሁሉም ልጆች ከመስጠት በዘለለ ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ ሴቶች ሕፃናትን ታሳቢ ባደረገና ለእነሱ በሚመች መልኩ መሆን እንዳለበትም ያስቀምጣል:: ከፍ እያሉ ሲመጡ በተለየ ሁኔታ ለሴቶች ሕፃናት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ የውሃ አቅርቦት ሊኖራቸው ይገባል:: ከባህል ተፅዕኖ የሚያወጧቸው መሆን አለባቸው:: ብዙ ክፍተቶችን የሚሞላ ነው::
በኢማጅናል ዴይ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ማናጀር ወጣት ሀዊ ዓለሙ እንደምትለው በ2010 ዓ.ም በትምህርት ሚኒስቴርና በዩኤስኤ በተደረገው ጥናት 34 በመቶው ሁለተኛ ክፍል የጨረሱ ሕፃናት ማንበብ እንደማይችሉ ያመለክታል:: በዚህ ወቅት የአገሪቱ የንባብ ደረጃ 60 ቃላት በአንድ ደቂቃ ማንበብ ነበር:: ‹‹ይሄኔ በእኛ ድርጅት በሚደገፉ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሕፃናት ግን በደቂቃ 150 ቃላት ማንበብ ይችሉ ነበር›› ትላለች::
በዚህና በቅድመ ልጅነት እድገት ዘመን በሠራቸው የተሻሉ ሥራዎች ድርጅቱ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በተገኙበት ዕውቅና ማግኘት የደረሰ ውጤት ማምጣት መቻሉንም ታነሳለች:: ለዚህ ውጤት ያበቃችው በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በተገኙበት በደቂቃ ውስጥ 150 ቃላትን ማንበብ የቻለች የሁለተኛ ክፍል ሴት ሕፃን ተማሪ መሆኗ የፖሊሲው ትግበራ እንዴት ገና ከመሠረቱ ጀምሮ ሴቶችን ተጠቃሚ፤ ተሳታፊና ውጤታማ እንደሚያደርግ ማመልከቱንም ወጣት ሀዊ ታወሳለች::
ወጣቷ የሕፃናትን በንባብ ላይ ያለ ክፍተት ያለ ልዩነት እኩል ዕድል በመስጠት ለማሻሻል እነሱ በሚደግፏቸውና በአገሪቱ ስድስት ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ለሚማሩ ሕፃናት ክፍል ውስጥ ጥግ ላይ ሳጥኖች ይቀመጡላቸዋል:: በሳጥኖቹ ውስጥ ለዕድሜያቸውና ለትምህርታቸው የሚመጥኑ መጽሐፍቶችም ይኖራሉ:: ይሄ እንደ አገር ያለው የማንበብ ልማድ ደካማ ስለሆነ የማንበብ ልማዳቸውን እያዳበሩ እንዲያድጉ ያደርጋል::
ሁለተኛ ሁለቱም ተማሪዎች በተለይም ከፍ ስትል ጀምሮ አብዛኛውን ጊዜዋን በቤት ውስጥ ሥራ እንድታሳልፍ የምትገደደው ሴት በትምህርት አቀባበል ደካማ ሆና ክፍል እንዳትደግም ፤ ትምህርት እንዳታቋርጥ ውጤታማ እንድትሆን ያስችላል:: እኛም ሴትና ወንድ ሕፃናት እኩል ዕድል እየተሰጣቸው በመምጣት በ2030 ከውጭ ድጋፍ ነፃ የሆነ ትምህርት እንዲያገኙና በሥርዓተ ጾታ መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት ማመጣጠን በመቻል ለአገራቸው እኩል አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በመመኘት ጽሑፋችንን ደመደምን::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2015