ነዋሪው ዓመታትን በጥያቄ የተጋበት ጉዳይ ዘንድሮ ዕልባት ማግኘቱ አስደስቶታል። አብዛኛው በወጣ በገባ ቁጥር ዓይኑን ከመንገዱ አይነቅልም። በየቀኑ የግንባታውን ለውጥ በአትኩሮት ይቃኛል። የታከለውን አዲስ ነገር እያስተዋለ ቀጣዩን በጎነት ይመኛል።
ማልደው በስፍራው የሚደርሱ ሠራተኞች ለነዋሪው የዓይኑ ርሀብ ናቸው። ከሰዓታቸው አለፍ ካሉ ሁሉም ደስ አይለውም። በርከት ብለው ሲመጡ ፈገግታው ይበራል፣ መቆፈሪያ ቡልደዘራቸውን፣ አካፋ ዶማቸውን ማየት የልብ ደስታው ከሆነ ቆይቷል። የእነሱ ድካም የአብዛኛው ሰው ብርታትና ተስፋ ነው። የእነሱ መታየት ለነገው ዓለም ብርሃን ነው።
ለአካባቢው ከዚህ እውነታዎች ማዶ ነገ ሲታሰብ ብዙ ትርጉሞች አሉት። ሁሉም ትናንት የሆነበትን አይረሳም። በዚህ ጎዳና የተከለሉ፣ በጥሻው የተደበቁ፣ ጨለማን የተተገኑ ጨካኞች ብዙ ፈጽመውበታል። ከጉድባው ተሸሽገው፣ ኪሱን አራቁተዋል፣ ንብረቱን ዘርፈዋል። አለፍ ሲልም ስለት ድንጋይ ጨብጠው ነፍስ የቀጠፉ፣ አካል የጎዱ አይጠፉም። ዛሬ ደግሞ ለአካባቢውና ዙሪያው ደማቅ ፀሐይ የወጣ፣ መልካም ቀን የመጣ ይመስላል። የነዋሪው የዓመታት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ የመንገዱ ግንባታ ተጀምሯል። እንዲህ በሆነ ማግስት የነበረው ደስታም ‹‹አጀብ›› የሚያስብል ነበር።
ይህ ያልተመቸ መንገድ ለዓመታት በርካቶችን አመላልሷል። መኪኖችን፣ ባጃጆችን፣ ጋሪዎችን በእኩል አጋፍቷል። የአካባቢው ህልም ይህ አልነበረም። መንገዱ እንደታሰበው በአስፓልት ተለውጦ፣ ማየትን ሲሻ ኖሯል። መብራቱ ገብቶለት፣ የተዘጉት ንግድ ቤቶች በወጉ ሥራ ጀምረው መመልከትን ተመኝቷል።
ይህ ይሆን ዘንድ ነዋሪው ኮሚቴ ያላዋቀረበት፣ በየስብሰባው መድረክ ያልተናገረበት፣ ያልጮኸበት ጊዜ የለም። የመንገዱ ጉዳይ ሁሌም የዓመቱ ስብሰባዎች አጀንዳ መክፈቻና መዝጊያ ነው። ጥያቄ ይነሳበታል፣ አስተያየት ይታከልበታል፣ በመጨረሻ የተለመደው ተስፋ ተቋጥሮበት በይደር ይታለፋል።
የሚገርመው የነዋሪው ተስፋ አለመቁረጥ ነው። ሁሌም ከመንገዱ መገንባት ጋር የሚሠራውን ድንቅ ተግባር ከማለም አይቦዝንም። አካባቢው የጋራ መኖሪያ እንደመሆኑ የነገው ትልሙ ከዕድገት ጋር የተያያዘ ነው። በነዚህ ሕንፃዎች ስር በጨረታ የተገዙት የንግድ ቤቶች ለዓመታት ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ ባክነዋል። የዛሬን አያድርገውና ቤቶቹ ከፍ ባለ ዋጋ ለገዢዎች ሲተላለፉ የመንገዱ አስፓልት መሆን ታሳቢ ተደርጎ ነበር።
ዛሬ ግን አብዛኞቹ ስማቸውን አልተሸከሙም። እንኳን ለንግድ ለመኖሪያነት አልተመረጡም። ሁሉም በሚባል መልኩ የጥርጊያውን አቧራ እንደ ጋቢ መከናነብ ግዴታቸው ሆኗል። በጋው አልፎ ክረምቱ ሲመጣ ደግሞ ጭቃ፣ ዝናብና ጎርፍ ሳይጎበኛቸው አያልፍም። ችግሩ በእነሱ ብቻ አይቆምም። የዝናቡና የጎርፉ መጥለቅለቅ የሕንፃውን አጠቃላይ ህልውና ለከባድ ስጋት ሲያጋልጠው ኖሯል።
አሁን ደግሞ ነዋሪው ያላሰለሰ ምስጋናና ውዳሴ በአፉ ይመላለስ ጀምሯል። የዓመታት ደጅ ጥናቱ፣ ጥያቄና ልመናው ጫፍ ይዟልና ግንባታውን የሚያየው በተለየ ስስትና አትኩሮት ነው። ይኸው እንግዲህ ትራክተር፣ ቡልደዞር፣ ሲኖትራክ፣ ግሬደር መርመስመስ ይዘዋል።
ማለዳውን ብቅ የሚለው አንገተ ረጅሙ ሎደር ጎንበስ ቀና የሚለው ብቻውን አልሆነም። ነዋሪውም አብሮት በድካም ሲዋትት ይውላል። ለሥራው አንዳች ነገር ባይፈይድም ሁሌም ለበጎ ሀሳብ ከአካባቢው አይርቅም።
የግንባታ መኪኖቹ ድንጋዩን ዘርግፈው፣ ጠጠሩን አፍሰው መንገዱን ባሰለጡት ቀን ሁሉም የዕድገቱን ለውጥ እያሰበ የቀጣዩን ቀን ውሎ ያልማል። ከዚህ በኋላ ሊቀር የሚችለው ሥራ ጥቂት እንደሚሆን የሚገምተውም ይበዛል። ማግስቱን ዓይኑን ከስፍራው የሚጥለው ተመልካች እንደልማዱ የመኪኖቹን መምጣት ሲጠብቅ፣ ሲናፍቅ ያረፍዳል።
መንገዱ ደግሞ አንደሰሞኑ አልሆነም። ሆዱ እንደተገመሰ፣ ጎኑ እንደተቆረሰ ያለአንዳች ድምጽ ረጭ ብሎ ይውላል። ተመልካቹ ተስፋ አይቆርጥም። ቀጣዩን ቀን በጉጉት ይጠብቃል። አሁንም አንዳች አካል ዝር ሳይል መዋል ማርፈዱን ያስተውላል። አንድ ቀን ብቅ ያሉት የመንገዱ ሠራተኞች ዝር ሳይሉ አስር ቀናት ይቆጠራሉ። ይቀጥላል። ቀናቶች በእጥፍ ይጨምራሉ።
የነዋሪው ዓይኖች ፈጽሞ ተስፋ አይቆርጡም። ባሻገር እያስተዋሉ፣ የመኪኖቹኑ መምጣት፣ የሠራተኞቹን ድረስ ይናፍቃሉ። ተናፋቂዎቹ ግን ጅምራቸውን እንዳዝረከረኩት ድራሻቸው ይጠፋል።
ቀናት ለወራት እየተጠጉ ይገሰግሳሉ። ተፈላጊዎቹ ብቅ ዝር አይሉም። ወቅቱ እንደሁ ሰዓቱን አይስትም። ፀሐይ ትደበዝዛለች፣ ዳመናው ያንዣብባል፣ ዝናቡ ማከፋት ይጀምራል። ካፊያው አምርሮ ዶፍ ዝናቡ ሲቀጥል፣ የከረመው ውሃ ደራሽ ወንዝ ሆኖ በጎርፍ መጥለቅለቁ ይፋጠናል። ይህኔ ጠፍተው የከረሙት ተናፋቂዎች በድንገት ከቡልደዘር፣ ሎደራቸው ጋር ይከሰታሉ።
የሚገርመው ሲመጡ ባዷቸውን አይደለም። ሲኖዎቹ ድንጋይ አሸዋ ጭነው፣ አይሱዚዎቹ ጠጠር ኮረት አጭቀው ነው። ቀድሞ የመጣው ግብአት አፈርና ጭቃ ሆኗል። እነሱም አይተዋል። ደንታ አይሰጣቸውም። የጫኑትን ዘርግፈው ሌላ ክምር ሊያመጡ በፍጥነት ይከንፋሉ።
አሁንም ነዋሪው የመጣውን አይቶ ሌላን የለውጥ ቀን ይናፍቃል። ቀናት እንደዋዛ አልፈው ወራት መቆጠር ይይዛሉ። አሸዋው ኮረትና ድንገጋዩ እየታየ ደልዳላ መሬት ይሆናል። አካባቢው በውሃ ጭቃ ይጨቀያል፣ እግረኞች መንገድ ፍለጋ ሌላ መንገድ እያበጁ አዲስ ጎዳና ይቀይሳሉ።
ደግሞ በሌላ ቀን ተናፋቂዎቹ እንደዋዛ ብቅ ይላሉ። ሳር የበቀለበትን ደልዳላ መንገድ በመዛቂያቸው ቆፈር ቆፈር አድርገው መለስ ቀለስ ይሉና ድራሻቸው ይጠፋል። ጥቂት ቀናት ቆይተው ያው ዝናቡ ሲመጣ ትላልቅ ቱቦዎችን ይዘው ይደርሳሉ። ተስፋ የማይቆርጡ ፊታቸው በፈገግታ በርቶ መንገዱ ሊያልቅ መሆኑን ያስባሉ።
ተናፋቂዎቹ አንድ ወደፊት አስር ወደኋላ ማለታቸውን አይስቱም። ግዙፎቹን ቱቦዎች ግራና ቀኝ ከምረው፣ ደርድረው ይጠፋሉ። ቱቦዎቹ ጥቂት ቀናት ቆይተው የጎዳና ልጆች ማደሪያ፣ የማጅራት መቺዎች መደበቂያ ይሆናሉ። ቋጥኝ የሚያህሉት ቱቦዎች ከፍ ያለ ገንዘብ የወጣባቸው የአገር ሀብቶች እንዲህ መባከናቸውን ያዩ እርር፣ ትክን፣ ድብን ይላሉ።
ጉደኞቹ ተናፋቂዎች ይህም ስሜት አይሰጣቸውም። ከጣሏቸው ወራት ያስቆጠሩትን ግዙፍ ቱቦዎች እንደነገሩ በየጉድጓዱ ወሽቀው ሌሎች ቀናትን በዝምታ ያደፍጣሉ።
እነሆ ! ዛሬም ይህ ተስፈኛ መንገድ ሌላው ክረምት ደርሶበታል። ከሰሞኑ የተዘረገፈለት ትላልቅ ኮረትና ድንጋይ ተከትሮ መጪውን ጎርፍ ለመስኖ ያዘጋጀው ይመስላል። ከሰሞኑ ብቅ ያለ ባለግሬደር፣ ዝር ያለ ባለ ሎደር የለም። አሁንም ዝናቡ፣ አይቀሬው ክረምቱ ‹‹መጣሁ፣ደረስኩ›› እያለ ነው።
ብቅ እያሉ የሚጠፉት የመንገዱ ባለሙያዎች ንብረቱን ፣ መንገዱንና የአገር ፣ ሀብቱን እንደዋዛ በትነው ኮሽታቸው ጠፍቷል። አንድ ወደፊት የመራመዳቸው እውነት ተጠናክሮም እርምጃቸው የኋሊት በአስር ተባዝቷል። ‹‹አንድ ወደፊት አስር ወደኋላ›› እንዲሉ ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2015