ኢትዮጵያ ለምጣኔ ሀብት እድገቷ ትኩረት ሰጥታ ከምትንቀሳቀስባቸው ዘርፎች ማዕድን አንዱ እንደሆነ ይታወቃል:: በተለይም ካለፉት አራት አመታት ወዲህ እንደአገር በተወሰደው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ከተለዩት አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል የማዕድን ዘርፉ ይጠቀሳል::
ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ለማድረግ የሚያሠራ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ፣ ከተቋማዊ አደረጃጀት ጀምሮ እንደ ወርቅ፣ የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ የተፈጥሮ ነዳጅና ጋዝ፣ የብረት ማዕድናት የመሳሰሉ አንኳር የማዕድን ሀብቶችን ለይቶ ለኢንቨስትመንት ምቹ በማድረግ፣ዘርፉ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ጋር በጋራ የሚሠራበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሲሠራ ቆይቷል:: የተከናወኑት ተግባራትም ዘርፉን አነቃቅተዋል::
በአገር ውስጥ የነበረው አለመረጋጋት፣ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው ጦርነት፣ እና ዓለም አቀፍ ጫናዎች በማዕድን ልማቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፋቸው ይታወቃል:: በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ከዘርፉ የተገኘው ውጤት የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም፣ ዘርፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖም ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው::
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ ባለፉት ጊዜያቶች ትኩረት ሰጥታ ስታከናውን የነበረቻቸው ጥረቶችም በተለያዩ ባለድርሻዎች ተወድሰዋል:: እኛም በመንግሥት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችንና ዘርፉ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ መሠረት በማድረግ በተለይም እየተገባደደ ባለው በጀት አመት ዘርፉ ያስገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝትና በቀጣይ ምን መሠራት አለበት በሚል ዘርፉን የዳሰስንበትን ጽሑፍ እንደሚከተለው አቅርበናል::
እየተገባደደ ባለው በዚህ በ2015 በጀት አመት አስፈጻሚ ተቋማት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወኗቸውን ሥራዎች፣ በሥራቸው የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችና በሥራ የተገኙ ውጤቶችን የሚገመግሙበት ወቅት ነው:: በተለይ ደግሞ በአገር የምጣኔ እድገት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብለው የተለዩት የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የነበራቸው ሚና ከሚጠበቁ የሥራ ውጤቶች ውስጥ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል:: በዚህም የማዕድን ዘርፍ ድርሻ ይነሳል::
ኢትዮጵያ በ2015 በጀት አመት በዘጠኝ ወር ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ሁለት ነጥብ 64 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል:: ይህ ገቢ የተገኘው በዘጠኝ ወሩ ከወጪ ንግድ ለማግኘት ከታቀደው ሦስት ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል:: ለውጭ ገበያ ተልከው ገቢ ካስገኙ ዘርፎች መካከልም ማዕድን ስድስት ነጥብ 53 በመቶ ድርሻ አለው:: ይህም በወርቅ፣ ታንታለምና በሌሎች የማዕድን ዓይነቶች የተገኘ ውጤት መሆኑም ተጠቅሷል::
የዘርፉን ድርሻ መሠረት አድርገን ሀሳባቸውን እንዲሰጡን ካነጋገርናቸው መካከል በማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሠ አንዱ ናቸው::እርሳቸው እንዳሉት የማዕድን ዘርፍ ከአመት በፊት በወጪ ንግድ የነበረው ድርሻ በአማካይ ከ15 እስከ 20 በመቶ እንደነበር ነው ያስታወሱት:: በተያዘው በጀት አመት በዘጠኝ ወር 6 ነጥብ 53 በመቶ ድርሻ መያዙ ከፍተኛ ጉደለት መኖሩን እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል:: ዶክተር ጉታ ለዚህ ምክንያት ናቸው ያሏቸውንም ሲገልፁ፣ የማዕድን ልማት ሥራው በተሰጠው ትኩረትና በተሠራው ሥራ ልክ ውጤት ተገኝቶበታል ወይንም ገቢ አስገኝቷል የሚል እምነት የላቸውም:: ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ የማዕድን ዓይነቶች ላይ የሚጠበቀው ገቢ ቀንሷል፤ በተለይም ከወርቅ የሚጠበቀው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ሲሉ ያብራራሉ::
እንደ ዶክተር ጉታ ገለጻ፤ ችግሩን በጥናት ለመለየት በተደረገው ጥረትም በጥናቱ ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ተለይተዋል:: በዚሁ መሠረትም አንዱ እንደአገር የነበረው አለመረጋጋት የፀጥታና የደህንነት ሥጋት መፈጠር ሲሆን፣ በዚህ ምክንያትም የሚመረተውን ወርቅና ሌሎች ማዕድናት ለመከታተልና ግብይት ለማድረግ ከፍተኛ ማነቆ በመሆኑ ተጽእኖ አሳድሯል::
አንዳንድ የወርቅ ማምረቻዎች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆኑበት አጋጣሚዎችም ተፈጥሮም ነበር:: በተለይ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በነበሩ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ ትግራይ ክልል ውስጥ የወርቅ ማዕድን ልማቱ ሙሉ ለሙሉ የተቋረጠበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው:: ልማቱ ይከናወንባቸው የነበሩ የጠረፍ አካባቢዎችም ቢሆኑ በተመሳሳይ ለቁጥጥርና ክትትል ምቹ ባለመሆናቸው በስፍራው በማዕድን ልማቱ ላይ የተሰማሩት ያለሙትን በአካባቢው ላይ ለሚንቀሳቀስ ብቻ ነበር ሲሸጡ የነበረው:: ይህም ሁኔታ ዘርፉን ለሕገወጥ የማዕድን አዘዋዋሪዎች መንገድ በመክፈቱ፣ አገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ጥቅም ወይንም ገቢ አሳጥቷታል::
ከፀጥታ ስጋቱ ቀጥሎ የነበረው ችግር ደግሞ በተለይ ከወርቅ ግብይት ጋር ተያይዞ ትልቅ ችግር የነበረው የወርቅ የመሸጫ ዋጋ ተመን ጋር የተያያዘው ነው:: መንግሥት የወርቅ ግብይት የሚፈጽመው የዓለም አቀፍ ዋጋን መሠረት በማድረግ ነው:: ሕገወጥ ግብይቱ ያስቀመጠው ዋጋ ደግሞ ከዚህ ከፍ ይላል:: በሕጋዊና በጥቁር ገበያ ግብይት መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ከፍተኛ እየሆነ መምጣት በግብይቱ ላይ ከዕለት ተዕለት አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መጥቷል:: ግብይቱ ላይ የመፍትሄ እርምጃ ባለመወሰዱ ለሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት መንገድ ከፍቷል:: የፀጥታ ስጋትና የዋጋ ተመን ጉዳይ ቁልፍ ችግሮች ቢሆኑም የአምራቾችን አቅም አለመደገፍም በሦስተኛ ደረጃ እንደ ችግር ተለይቷል::
ለዘርፉ እንቅስቃሴ እንቅፋት ሆነው የቆዩ ችግሮች እንደማይቀጥሉ ተስፋ ያደረጉት ዶክተር ጉታ፤ችግሮች ሲቀረፉ በተለይ አዳዲሶች ወደ ልማቱ ሲገቡ ነገሮች ተስተካክለው ዘርፉ እድገት እንደሚያስመዘግብ ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል:: ቅንጅታዊ ሥራ፣ በዘርፉ የሚሰማሩ በተለይም በልማቱ ላይ በስፋት የሚሠሩትን ወጣቶች በስልጠና ማብቃት፣ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ በፖሊሲ የሚፈቱትንም በመንግሥት በኩል በመሥራት መፍታት፣ ወርቅን በተመለከተም የተሻለ የአስተዳደርና ከግዥ ጋርም ያለውን የሌሎችን አገሮች ልምድ በመቀመር መሠራት እንዳለበት ታምኖበት በማዕድን ሚኒስቴር በኩል ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ሥራ መገባቱንም አስረድተዋል::
ዶክተር ጉታ ወርቅ ላይ ትኩረት ያደረጉት ክፍተቱ ጎልቶ የታየበት በመሆኑ እንጂ እንደአጠቃላይ የማዕድን ዘርፉን የማዘመንና ተጠቃሚ ለመሆን ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ይናገራሉ::ለአብነትም የጌጣጌጥ የከበሩ ማዕድናትን በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ፣ እሴት በመጨመር ማቅረቡ በኢኮኖሚ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚያስችል ግንዛቤ ተይዞ የአደረጃጀት፣ የፖሊሲ፣ የአቅም ማጎልበት ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸውም ያመለክታሉ::
እርሳቸው የሚመሩት የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዘርፉን በመደገፍ ረገድ እያከናወነ ስላለው ተግባርም ሲናገሩ እንደገለጹት፤ አቅም በማጎልበትና መለስተኛ የጥናት ሥራ በማከናወን፣ አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ይሠራል:: በእስካሁኑ ሥራም የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናት በጥሬ ለገበያ እንዳይቀርቡና እሴት የተጨመረባቸው ቢሆኑ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል፣ ይህም በፖሊሲ እንዲደገፍ የማድረግ ተግባር ተከናውኗል፤ የፖሊሲ ዝግጅቱም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል::
የማዕድን ክፍለኢኮኖሚውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ዘርፉም በምጣኔ ሀብት ውስጥ ድርሻው ከፍ እንዲል በማድረግ ዘርፉን ከሚመራው ማዕድን ሚኒስቴር ጋር እየሠሩ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው:: በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓለሙ ዲሳሳ እንደሚሉት፤ የማዕድን ዘርፉ ትኩረት ያገኘው ካለፉት አራት አመታት ወዲህ ነው::
መንግሥት ከግብርናው እና ከሌሎች ዘርፎች ባልተናነሰ ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረትም ያስመሰግነዋል የሚሉት ዶክተር አለሙ፣ መንግሥት በሰጠው ትኩረት ልክ እና ዘርፉ ከግብርናው ባልተናነሰ መልኩ ውጤት አለማስመዝገቡ እንደ ክፍተት መታየት አለበት ብለው አያምኑም:: እንደ ዶክተር ዓለሙ ገለጻ፤ ዘርፉ ለረጅም ጊዜ ትኩረት የተነፈገው በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ሥራ አልተሠራም:: በአራትና አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ያለፉ ተሞክሮዎች መሠረት የጣሉ አይደሉም:: ይህም የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ አምጥቶ በዘርፉ ገቢ ላለማስገኘቱ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል::
ሌላው ግንዛቤ መያዝ ያለበት ማዕድንን እንደ ሌሎች ዘርፎች በቀላሉ አልምቶ ለውጤት ማዘጋጀት የማይቻል መሆኑ ሲሉ ይገልጻሉ:: ዘርፉን ለማልማት ቴክኖሎጂ፣ በቴክኖሎጂው ለማልማትና ቴክኖሎጂውን ለማሻገር የሰለጠነ የሰው ኃይል ይፈልጋል:: ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ይጠይቃል ሲሉም ያብራራሉ:: እነዚህን ፍላጎቶች ማሟላት የአገርን አቅም እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ማዕድን የፖለቲካ አንድምታም ስላለው ብዙ ጣልቃገብነት ይበዛዋል ይላሉ:: እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተደምረው ልማቱና ተጠቃሚነቱን ውስብስብ እንደሚያደርጉት ነው የሚናገሩት::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ መንግሥት ባለፉት ሦስትና አራት አመታት የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት ተንቀሳቅሷል:: ሀብቱንም ለይቶ በሙዚየም በማደራጀት ያደረገው ጥረት ከሚጠቀሱ ሥራዎች መካከል ሲሆን፣ ይህም ዘርፉን ለማልማት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል:: ይህም ተስፋ ሰጪ ሥራ ተደርጎም መወሰድ ይኖርበታል::
ዘርፉ ቀደም ሲልም በተግዳሮቶች ውስጥ ማለፉን ጠቅሰው፣ ወደፊትም ነፃ ሊሆን አይችልም ሲሉ ይናገራሉ:: እንዲያም ሆኖ ግን መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ይዞ ዘርፉ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል::
ሥራውም በውጤት መለካቱ የግድ መሆኑን ተናግረው፣ ለችግሮች መፍትሄ እየሰጡ ውጤት ላይ ማተኮር ይጠበቃል ይላሉ:: ዘርፉን ለውጤት ማብቃት ደግሞ ድርሻው የመንግሥት ብቻ መሆን እንደሌለበት ይታመናል:: ከዚህ አኳያ ዩኒቨርሲቲዎች ስላላቸው ሚናም ዶክተር ዓለሙ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አዳማ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ከማፍራት ጀምሮ በዘርፉ ላይ በተለያዩ የጥናት ሥራዎች ያለውን የማዕድን ሀብት በመለየት፣ እንዲሁም የዘርፉን ባለድርሻዎች በማማከርና ዘርፉን የሚመራውን አካል በማገዝ በቅርበት በመሥራት አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል::
እንደ ዶክተር አለሙ ገለጻ፤ አስፈጻሚው ተቋም በሚያስፈልጉት ጉዳዮች ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ መሥራቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሥርዓተ ትምህርት ለመቅረጽም ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል:: የዘርፉ አስፈፃሚ ተቋማት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል:: ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ ወደ ተቋማት የሚሄዱት:: የማዕድን ሚኒስቴር ተሞክሮ የሚያሳየው ግን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ አብሮ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረም ወደ ተግባር ሥራ መግባቱን ነው:: የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በምርምርና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ በጋራ የመሥራቱ ሥራም ተጀምሯል:: እንዲህ ያለው የጋራ ሥራ ከተጠናከረ ባለሙያን ማፍራት ብቻ ሳይሆን፤ እንደ አገር በኢኮኖሚው ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ተያያዥ ሥራዎችንም የበለጠ አጠናክሮ በመሥራት ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል::
በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም የማስተዋወቅ ሥራ መጠናከር እንዳለበት የሚገልጹት ዶክተር ዓለሙ፤ ዘርፉ የተረጋጋና አስተማማኝ ደህንነት የሚፈልግ እንደሆነና በዚህ ረገድም የተጠናከረ ሥራ እንደሚጠበቅ ነው ያስገነዘቡት:: በአጠቃላይ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ጥቅም እንዲገኝበት ለማድረግ ከመንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015