ወጣት ዳዊት ከተማ ይባላል፤ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ አግኝቷል:: ከልጅነቱ ጀምሮ የራሱን የንግድ ድርጅት የመክፈት ህልም አለው:: ወጣቱ እንደሚያነሳው፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ጀምሮ ህልሙን ለማሳካት በተለያዩ ሶስት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ የራሱን ገቢ ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል:: የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ትምህርት ሲዘጋ፤ ከጓደኞቹ ጋር የዶሮ እርባታ ሥራ ጀመረ:: ይሁንና እንዳሰበው ውጤታማ አልሆነም:: ስለዚህ ፈሳሽ ሳሙና ወደ ማምረት ሥራ ገባ::
ፈሳሽ ሳሙና ማምረት አትራፊ ቢሆንም ከሰዎች ጋር የሚሰራው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አለመግባባት ይፈጠርና ይህንንም ሥራ ለመተው ተገደደ:: በዚህ ተስፋ አልቆረጠም፤ ይልቁኑ በተወለደበት ባሌ አካባቢ በመስኖ ሽንኩርት ማልማት ጀመረ:: በአጭር ጊዜ በትንሽ መሬት ላይ የጀመረው ምርት ውጤታማ አደረገው:: የማምረቻ መሬቱን ወደ ሁለት ሄክታር በማሳደግ ምርቱን ለማስፋት ወስኖ ሥራ ጀመረ:: ይሁንና ለመስኖ የሚጠቀምበት ወንዝ ከምንጩ የመድረቅ አደጋ አጋጠመው፤ በዚህ ምክንያት የሽንኩርት ማሳው ሙሉ ለሙሉ ደረቀበት::
ተስፋ መቁረጥ የማያውቀው ይህ ወጣት በድጋሚ ሌላ የቢዝነስ አማራጭ በአካባቢው አማተረ:: ህብረተሰቡ በተለምዶ ”ቁጢ” እያለ በሻይ መልክ የሚጠጣውን የቡና ቅጠል በዘመናዊ መንገድ አሽጎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አሰበ:: እናም የመጀመሪያ ሥራው ቡና የሚያመርቱ ገበሬዎችን እየዞረ ማናገር ነበር:: የተወሰኑ አርሶ አደሮችን አሳምኖ ወደ ምርት ገባ:: እየዋለ ሲያድር አርሶ አደሮቹ “ለቁጢ” የሚውለው የቡና ቅጠል በተቆረጠ ቁጥር ምርታችን ይቀንሳል ብለው በመስጋታቸው ምርቱን እንዳሰበው በስፋት ለማምረት ተቸገረ:: በተለይ ጥራት ያለውን ቅጠል በስፋት ማግኘት ፈተና ሆነበት:: ለአንድ ኪሎ ግራም በርካታ የቡና ቅጠል እና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ በመሆኑ፤ ካለው አቅም ጋር የሚመጣጠን እና አዋጭ ሆኖ እንዳላገኘው ያስረዳል::
‹‹እርግጥ የራሴ እርሻ ኖሮኝ ብሰራ ኖሮ የተሻለ ትርፋማ እሆን ነበር፤ ግን በተማሪ አቅም መሬት ገዝቶ ወይም ተከራይቶ ማልማት የማይቻል በመሆኑ ሥራውን ለማቆም ተገድጃለሁ›› የሚለው ወጣት፤ አክሎም ‹‹ይህንን ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የሚያግዝ አካል ቢኖር ግን ከቡናው ባሻገር በቅጠሉም (በቁጢው) ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገባት በተቻለ ነበር›› ሲል በቁጭት ይናራል:: በሌላ በኩል ይህ ቅጠል ለደም ግፊት እና ለልብ ህመም በመድሃኒትነት የሚያገለግል በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ለሚያለሙ አካላት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል። የቁጢውን የጥራት ደረጃ የሚለካ ስርዓት በኢትዮጵያ ባለመዘርጋቱ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ አዳጋች መሆኑን ይጠቁማል::
ዳግም ወረርሽኙ ጋብ ሲል ወጣት ዳዊት ትምህርቱን አጠናቀቀ፤ እዛው አዳማ ላይ ሆኖ በቀጥታ የራሱን ስራ ወደ መፍጠር መግባቱን ያነሳል:: ቀደም ሲል ሥራ ለመፍጠር ባደረገው ጥረት በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሙትም አዳዲስ የሥራ ሃሳቦችን ለማፍለቅ እና በአዲስ መንፈስ ለመነሳት ረዱት እንጂ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ አላደረጉትም:: ግን ደግሞ ተሞክሮዎቹን በመቀመር ወደ ፊት ላለመው ትልቅ አላማ መነሻ የሚሆነውን እና በአነስተኛ መዋእለንዋይ የሚሰራ ሥራ አሰበ፤ በተለይ ደግሞ ወደ ተማረው የኬሚካል ኢንጀነሪንግ ዘርፍ ጋር ቅርበት ያለውን የፕሮጀክት ንድፍ ቀረፀ:: ይኸውም በየመንግስት ተቋማት እና ትልልቅ ድርጅቶች ላይ በስፋት መጠቀም የተጀመረውን እና በፋይበር የሚሰራውን የአበባ ማስቀመጫ እና መሰል ምርቶችን በተለየ መንገድ ሰርቶ ማቅረብ ነበር:: ግን ደግሞ ሥራውን በተጨባጭ ለማወቅ ስልጠና የሚያስፈልገው በመሆኑ የተወሰኑ ቦታዎች ጠየቀ፤ ለአንድ ሳምንት ስልጠና 10 ሺ ብር እንደሚያስፈልገው ተነገረው:: ይህንን ለመክፈል ደግሞ አቅሙ ስላልነበረው ፋይበር የሚያመርቱ ድርጅቶች ጋር ለጥቂት ጊዜ ተቀጥሮ ልምድ ለማካበት ወሰነ::
ይህም እንዳሰበው ቀላል አልሆነለትም፤ ለመቀጠር ያመለከተባቸው ድርጅቶች አልተቀበሉትም:: በዚህም ተስፋ አልቆረጠም፤ አንድ መላ ዘየደ፤ ይኸውም የተማረውን ትምህርት በመጠቀም፤ በራሱ መንገድ መርምር በማድረግ ፋይበሩን መስራት ጀመረ:: ይሕ ትጉህና ጉጉ ወጣት በተደጋጋሚ ምርምር አድርጎ በራሱ መንገድ የፋይበር አበባ መትከያና ሌሎች ግብዓቶችን ማምረት ቻለ:: ከትንሽ ጀምሮ ተለቅ ወዳሉት ሥራዎች ለመግባት ግን ሰፊ የማምረቻ ቦታ፤ ግብዓትም ሆነ ገበያ እንደልብ የሚገኝበትን ሁኔታ ማሰብ ያዘ:: ወደ ተወለደበት ባሌ ቢሄድ የተሻለ ሆኖ አገኘው:: በቅድሚያ ገበያውን ለማጥናት መሞከሩን የሚናገረው ወጣት ዳዊት፤ በሽያጭ ደረጃ ሳይሆን በመንግስት ተገዝተው የእግረኛ መንገዶች አካባቢ አበባ ተተክሎባቸው የተቀመጡ መሆናቸውን ማስተዋሉን ይናገራል::
‹‹ይህ የፋይበር ምርት ምንም እንኳን ገበያ ላይ ባይኖርም ለህብረተሰቡ አዲስ ባለመሆኑ ለማስተዋወቅ እንደማልቸገር አምኜ በቀጥታ ማምረት ጀመርኩኝ›› ይላል:: በመቀጠልም ሆቴሎችን እና ትልልቅ ድርጅቶችን በማነጋገር ምርቱን ማስተዋወቁን ይጠቅሳል:: አብዛኞቹ ሆቴሎች እና ድርጅቶች ምርቱን አይተው የመግዛት ፍላጎት ማሳደራቸውን፤ ይሁንና የፋይበር ምርቱን ለመስራት የሚጠቀምበት ኬሚካል ዋጋ ውድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአበባ ማስቀመጫዎቹም ዋጋ የዚያኑ ያህል ከፍ ስለሚል ወስኖ ለመግዛት የሚያቅማሙ መኖራቸውን ነው የጠቆመው::
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዲዛይኖች፤ መጠንና ቀለም የሚያመርታቸው የፋይበር የአበባ መትከያ ሳህኖቹ እየተለመዱ እና ተቀባይነት እያገኘ መምጣታቸውን ይናገራል:: ከዚያም ባሻገር የሻወር ቤት ትሪ በማምረት ለሆቴሎች ማከፋፈል መጀመሩን ይጠቅሳል:: ወጣቱ ስራ ፈጣሪ ሥራውን በጥቂቱ ይጀምር እንጂ የማምረቻ ቦታውን በማስፋት፤ ዘመናዊ እና ትልልቅ ማሽኖችን በማስገባት ሮቶ (የውሃ ማጠራቀሚያ)፤ የመታጠቢያ ቤት ገንዳ የመሳሰሉ ለሆቴሎች፤ ለተለያዩ ድርጅቶች ግብዓትነት የሚውሉ የፋይበር ምርቶችን የማምረት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ያስረዳል::
ሥራውን ሲጀምር ከመስሪያ ማሽንና ግብዓት ውጪ በ46 ሺ ብር መነሻ ካፒታል መሆኑን የሚናገረው ወጣት ዳዊት፤ ለሶስት የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩን ይጠቁማል:: ድርጅቱን እያሰፋ በመጣ ቁጥር ግን በርካታ የአካባቢውን ሥራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ ያለው መሆኑን ያነሳል::
ከሁሉ በላይ እየሰራቸው የሚገኙት ሥራዎች ወደፊት ላሰበው አዲስ ፕሮጀክት መንደርደሪያ፤ አቅም ማጎልበቻ ይሆኑኛል ብሎ መጀመሩን ነው ያጫወተን:: በተለይ ኢኮኖሚው ሲዳብር በፍጥነት አዲሱን ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ መጓጓቱን የሚናገረው ወጣት ዳዊት፤ ይህም ከራሱ አልፎ አገርን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል የሚል እምነት ይዟል:: ወጣቱ ትልቅ ህልሙ እስካሁን ባሳለፋቸው ውጣ ውረዶች ሁሉ ተስፋ እንዳይቆርጥ ምክንያት እንደሆነው ያስረዳል:: ‹‹ከዚህ ቀደም ያደረኳቸው ሙከራዎቼ ሁሉ ባይሳኩልኝም በቀላሉ ከአንዱ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ መስራት አያቅተኝም ነበር፤ ሆኖም የእኔ ህልም በራሴ መንገድ አገሬን ተጠቃሚ የሚያደርግ ራዕይ ሰንቄ በመስራቴ ተስፋ እንዳልቆርጥ አድርጎኛል›› ሲል ያብራራል::
ወጣት ዳዊት እንደሚለው፤ በኢትዮጵያ ለምሩቃን የሚሆኑ ሥራዎችን ማግኘት ከባድ ነው:: ከተማረው ወጣት ጋር የሚመጣጠኑ የሥራ በሮች እምብዛም አይታዩም:: ከዚህ የተነሳ በርካታ ወጣቶች ተስፋ ቆርጠው ወደ ተለያዩ ሱሶችና አልባሌ ሁኔታዎች ለመግባት ይገደዳሉ:: ይሁንና ወጣቱ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች በፅናት ካለፈ፤ የራሱን እና አዲስ እሴት የታከለበት ሥራ መስራት ከቻለ ተቀባይነቱ በአንድ ጊዜም ባይሆን በሂደት መምጣቱ አይቀሬ ነው::
አንድ አንድ ጊዜ ወጣቶች በስሜታዊነት ተነሳስተው የሚጀምሩት ሥራ ሊከሽፍባቸው ቢችልም፤ ዳግሞ መነሳት እና የሚፈልጉትን ህልም ማሳካት እንደሚችሉ ማመን ይገባቸዋል:: ሁሉም ሥራ ያለፈተና እና መሰናክል ሊሳካ እንደማይችል ራስን አሳምኖ መግባትን ይጠይቃል ይላል::
አዳማ ዩኒቨርሲቲ ሳለ ተቋሙ ለእንደእርሱ አይነቱ ሥራ ፈጣሪ ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርግበት መርሃ ግብር እንደነበረው ወጣት ዳዊት አስታውሶ፤ ይህንን እድል ተጠቅሞ ከጓደኞቹ ጋር የተለያዩ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለመስራት እንዳስቻላቸው ይጠቁማል:: ይሁንና ይህንን የሥራ መፍጠር አቅም ከዩኒቨርሲቲው ከወጡም በኋላ በተጨባጭ ተግባር ላይ እንዲያውሉት በማድረግ ረገድ ተቋሙ ድጋፍ የሚያደርግበት ሥርዓት አለመኖሩን ይናገራል:: በዚህም ምክንያት ብዙ ወጣቶች በርካታ አዳዲስ ርዕዮች እና የልማት ፕሮጀክቶች ቢኖራቸውም በፋይናንስ ረገድ የሚረዱበት አግባብ ባለመኖሩ ተመልሰው የቤተሰቦቻቸው እጅ ጠባቂ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ነው ያብራራው::
በሌላ በኩል ልክ እንደእርሱ ሁሉ የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች በፅናት አልፈው ራዕያቸውን እውን ላደረጉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚደረግላቸው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የራሱን ተሞክሮ በማንሳት ይናገራል:: ‹‹የእኔን ተሞክሮ ለአብነት ሳነሳ ስራ ለመጀመር ባሳለፍኳቸው ውጣ ውረዶች ውስጥ በየትኛውም አካል ድጋፍ ተደርጎልኝ አያውቅም፤ በተለይ በመንግስት በኩል ደግሞ ጅምር ጥረቴን አይቶ የማምረቻ ቦታ፤ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳገኝ ምንም አይነት ጥረት አልተደረገልኝም›› ሲል ያስረዳል::
ይሁንና በትምህርት ቤት ሳለ ያደርጋቸው ለነበሩ የምርምር ስራዎች በተቋሙ ድጋፍ ተደርጎለት እንደነበር፤ ከዚያም ባሻገር የውድድር መድረክ በማዘጋጀትና አሸናፊ ለሆኑ ፕሮጀክቶች ሽልማት በመስጠት የሚበረታታበት ሁኔታ እንደነበር አልሸሸገም:: ያም ቢሆን እሱም ሆነ ሌሎች ተማሪዎች ያደረጉትን ምርምር ፍሬ እስኪያፈራ እና ወደ ምርት እስኪገባ ድረስ ድጋፍ የሚደረግበት የአሰራር ስርዓት ባለመኖሩ ብዙ አገርን የሚለውጡ ፕሮጀክቶች ሼልፍ ላይ የሚቀሩበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ይገልፃል:: የሚደግፋቸው በማጣት እና ተስፋ በመቁረጥ በማይፈልጉት እና ባልተማሩበት የሙያ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሰሩ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውንም ነው የጠቀሰው::
በመሆኑም ወጣት ተመራማሪዎችን እና ሥራ ፈጣሪዎችን በተጨባጭ ለአገር የሚያበረክቱትን አስተዋፅዖ በመረዳት አስፈላጊውን የፋይንናስ፤ የብድር አቅርቦት፤ የማምረቻ ቦታ እና የገበያ ትስስር በመንግስት በኩል ሊደረግ እንደሚገባ ያስገነዝባል:: በተለይም በገጠር ከተሞች አካባቢ ለሚሰሩ ወጣት ተመራማሪዎች ወደ እነሱ መስመር የሚመሩት በርካታ ወጣት እና የሥራ እድል የሚፈጥሩለት ዜጋ እንደሚኖር በማመን ከሁሉ በላይ አገሪቱ እየተፈተነችበት ያለውን ሥራአጥ ተመራቂ ተማሪዎችን ችግር የሚያቃልል መሆኑን መገንዘብ እና አፋጣኝ ድጋፍ ማድረግ የመንግስት ቀዳሚ ሥራ እንዲሆን ነው ያሳሰበው:: ከዚህም ባሻገር ባለሃብቶች እና ትልልቅ ድርጅቶች የወጣቶች የምርምር ሥራ በተጨባጭ እውን ሆኖ ለአገር ፋይዳ ያለው አስተዋፅኦ ያበረክት ዘንድ በጋራ እንዲሰሩ ወጣት ዳዊት ጥሪ አቅርቧል::
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015