እንደ አጠቃላይ ሲታይ፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ ይሳናቸዋል፤ ብቸኝነት ያስደስታቸዋል። እንዲሁም፣ ሰርክ የሚያስደስቷቸውና የሚወዷቸው ነገሮች አንዳንዴ የሚረብሿቸው፤ በተጨማሪም የሚያስፈሯቸው ጊዜ አለ። እነዚህ ችግሮች በማህበረሰቡ ውስጥ ድርብርብ ኃላፊነት ባለባቸው ሴቶች ላይ ሲከሰቱ ደግሞ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን ታሳቢ በማድረግ ከሰሞኑ በስካይላይት ሆቴል፣ “ከሚያዝያ 2015 እስከ ሚያዝያ 2016 ዓ.ም” የሚዘልቅ የፀረ አደንዛዥ ዕፆች የንቅናቄ መድረክ ይፋ አድርጎ ነበር። ወጣት ሴቶችን፣ እንዲሁም አጠቃላይ ወጣቶችን ለመታደግ በተጀመረው በዚህ የንቅናቄ መድረክ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሙና አህመድም የተገኙ ሲሆን ሁለቱም በየፊናቸው ባስተላለፉት መልክት መጤ ባህሎችም ሆኑ አደገኛ ዕጾችና የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች በይበልጥ ሴቶችን የሚጎዱበት ሁኔታ መኖራቸውን አንስተዋል። ከሴቶች ጋር ተያይዞም ሴቶች በማህበረሰብ ውስጥ ካላቸው ከፍተኛ ኃላፊነት አንፃር በችግሩ መጠመዳቸው፤ ማህበረሰቡም ለቀውስ የሚዳረግበት ሁኔታም እንደሚፈጠር ተናግረዋል። ሴቶች በተፈጥሮ ባገኙት ልጅ በመውለድ ሕይወትን ከማስቀጠል ታላቅ ፀጋ ጋር ተያይዞ ሱሰኛና ጤናማ ያልሆነ ልጅ ከመውለድ ጀምሮ ቀውሱ የሚባባስበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ያወሳሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የሕብረተሰብ ክፍል የሴቶች ቁጥር ከግማሽ በላይ እንደሆነ ያወሱት ሚኒስትር ኤርጎጌ ሚኒስቴር መሥርያ ቤታቸው የእነዚህ ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ደፋ ቀና እያለ መገኘቱንም ጠቁመዋል። ‹‹ይህንን ከግብ ለማድረስ አሁን ላይ በአገራችን ከፊተኞቹ ዘመናት የተሻለ ምቹ ሁኔታ አለ›› ይላሉም።
ከፖለቲካዊ ምቹ ሁኔታዎች መካከልም የሴቶችን መብትና ጥቅሞች ማስከበርና ማረጋገጥ አስመልክቶ ኢትየጵያ የተቀበለቻቸውንና የፈረመቻቸው ሕጎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ ባይ ናቸው። በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ካሉት 20 የካቢኔ አባላት 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም በማሳያነት ያነሳሉ። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋን ጨምሮ ቁጥራቸው በርከትከት ያለ ሴቶች በየደረጃው መቀመጣቸውም ከዚሁ ምቹ ሁኔታ የሚደመር መሆኑን ያወሳሉ። እንዲህም ሆኖ በክልል፤ በዞንና በወረዳ ደረጃ የሴቶች ቁጥር ከላይ በመጣበት አግባብ የሚሄድበት ሁኔታ አለመኖሩ ሌላው ብዙ ትግልና ሥራ የሚጠይቅ ፈተና መሆኑንም ይጠቁማሉ።
እዚህ ላይ ሴቶች በአብዛኛውም ወጣት ሴቶች የወንዶቹን ያህል እንኳን ባይሆንም በትንሹም ቢሆን በመጤ ባህል፤ የአልኮል ይዘት ባላቸው መጠጦችና በአደገኛ እጾች ሱሰኝነት ተጠምደው መገኘታቸውን፤ በዚሁ ሰበብም ማህበረሰባዊ ቀውስ መፈጠሩ ፈተናውን በእጅጉ የሚያከብደው መሆኑንም ይጠቁማሉ። ችግሩ በራሳቸው፤ በጤናቸው፤ በትምህርታቸው፤ በውሳኔ ሰጪነታቸው፤ በኑሯቸው፤ በሚተኩት ልጅ (ትውልድ) ብሎም በሕብረተሰቡ፤ እንደ አጠቃላይም በአገር ላይ ስር የሰደደ ጉዳት ያደርሳል።
ሴቶችን ለማብቃት፤ የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ለማሳደግና የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በማጎልበት በሁሉም የልማት ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ፤ እንዲሁም፣ ለአገሪቱ ልማት እና እድገት መሰረት እንዲሆኑ ለማስቻል የግድ አስቀድሞ በሱሰኝነት ችግር እንዳይወድቁ መሥራት ያስፈልጋል። የገቡት እንዲወጡ መስራትም ለነገ የማይባልና በርብርብ የሚከናወን የዛሬ የቤት ሥራ መሆን ይኖርበታል። የንቅናቄ መድረኩን እንደ አገር ማስጀመር ያስፈለገውም አጠቃላይ ወጣቱን፤ በዚሁ ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣት ሴቶችን እንዲሁም አጠቃላይ ተጋላጭና ሰለባ የሆኑ ሴቶችንና ሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎችን ለማዳንም እንደሆነ ሚኒስትሯ አስምረውበታል።
የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድም የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች፤ አደገኛ ዕጾችና መጤ ባህሎች አነሰም በዛ በሴቶች ላይ፣ በተለይም በሴት ወጣቶች ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ ሰፊ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ፈጣን መፍትሄ የሚሻ መሆኑን ነበር በመልክታቸው የተናገሩት። ‹‹ወጣት በማንኛውም ሕብረተሰብ ውስጥ የአፍላ ጉልበት፤ የብሩህ አእምሮና የእምቅ ኃይል ባለቤት ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሆኖ መገኘት የሚችለው ይሄን ፀጋውን በአግባቡ ተግባር ላይ ሲያውለው ነውም ባይ ናቸው።
እንደ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና ገለፃ ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ የስብዕና ግንባታ ወይም የመዝናኛ ማዕከላት መገንባትና ሴት ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም በሱስ የተጠመዱ ወጣቶች በፍትሀዊነት ከሱስ እንዲላቀቁ ማድረግ ያስፈልጋል። መፍትሄውም ይኸው ነው። በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት 113 ስብዕና ማእከላት ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ እንደሆነም በመድረኩ ላይ ተነግሯል። እንደ አገር ሲታይ ደግሞ ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ ማዕከላት መኖራቸውንና ማዕከላቱ በትክክል ለወጣቱ፣ በተለይም ከመረጃ ለራቁት ሴቶች መረጃ በማቀበል፣ ስልጠና በመስጠትና የሚፈለጉትን ሥራዎች በመሥራት ረገድ ሁሉም የሚጠበቅባቸውን በእኩል ደረጃ ተወጥተዋል ማለት እንደማይቻልም ይጠቅሳሉ።
ከ3ሺህ በላይ የስብዕና ግንባታ ማዕከላት ቢኖሩም ሥራ ላይ የዋሉት 1ሺ 545 ብቻ በመሆናቸው እነዚህን የማጠናከር ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትር ዴኤታዋ ያሳስባሉ። ጾታ ሳይለይ ሁለቱም ወጣቶች አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ስብዕና ማዕከላት ሄደው የ“ዋይፋይ”፤ የቤተ መጽሐፍት፤ ስልጠናና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ እየተሰራ የተመጣበት ሁኔታ መኖሩንም የተናገሩ ሲሆን፤ አደንዛዥ ዕጾች፤ ከኛ ባህሎች ጋር የሚቃረኑ መጤ ባህሎችን በተመለከተ የሚያስከትሉትን ጉዳት የማስተማር ሥራም እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሆኖም፣ በግምገማቸው እንዳረጋገጡት የተሰራው ስራ በቂ አለመሆኑን፤ ለዚህም ማሳያው ሱሰኝነት እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ መምጣቱ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም፣ በቀጣይ ሕይወት አስቀጣይ ሱሰኛ ሴት ወጣቶችም ላይ ሆነ በአጠቃላይ ወጣቶች ላይ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል። እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ከሆነ፣ ወጣት ሴት ስትሆን ደግሞ ሴቲቱ በማህበረሰብ ውስጥ ካላት ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት አንፃር ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው የሚሆነው። በመሆኑም ንቅናቄው በሁሉም አካላት ርብርብ ታግዞ ሊካሄድ ይገባል ሲሉም ወይዘሮ ሙና አህመድ ሕዝባዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ወይዘሮ ባንቹ ሙሉጌታ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ማብቃት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አደንዛዥ ዕጾችና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ። ሴቶችን ለመጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች የሚያጋልጡም ሁኔታዎች መኖራቸውንም ያነሳሉ። በዚሁ ዙርያ የተሰሩ ጥናቶችን መሰረት አድርገው እንዳብራሩት ወሲባዊ ፊልም፤ የምሽትና የቀን ጭፈራ ቤቶች፤ የጫት መቃሚያና ሲሻ ቤቶች፤ የመዝናኛ፣ የመገናኛና በይነ መረቦች ይጠቀሳሉ።
መሪ ሥራ አስፈፃሚዋ ዓለማቀፋዊነት የቤተሰብ ትስስር መላላት፤ የወንድ አቻ ግፊትና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ሁኔታም ለችግሩ አጋላጭ ምክንያቶች እንደሆኑ ተናግረዋል። የወንዶች ብቻ ሳይሆን የአልኮል መጠጦችና የፀረ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ ሴቶችና ሴት ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ በመምጣቱ አንድ ዓመት የዘለቀ የንቅናቄ መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። አብዛኛው የችግሩ ሰለባዎች ወንዶች መሆናቸው በጥናት መመላከቱን ወይዘሮ ባንቹ ያወሳሉ። ሆኖም ወንዶች ናቸው ሰለባዎቹ ሲባል ሴቶች ሰለባ አይደሉም ማለት እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።
ሁሉንም ማህበረሰብ፤ በተለይም ሴቶችን የሚመለከት ክፍል በመኖሩ ሴቶች ከዚህ ችግር እንዲወጡ ይሰራል። በጥናቱ ላይ 4 ነጥብ 4 በመቶው በአጠቃላይ ካለው ወጣት አንፃር ሁሉም ሱሰኛ ነው ባይባልም ተጠቃሚ መሆኑን እንደሚያሳይ ይጠቅሳሉ። ከስብዕና ግንባታቸው ጋር ተያይዞ አደንዛዥ ዕፅን መጠቀም የጤና፤ የስነ ልቦናና የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ቀውሶችንም ያስከትላል። ከእነዚህ ቀውሶች ለመታደግ ስብዕና ግንባታ ላይ መሥራት ይገባል።
መሪ ሥራ አስፈፃሚ ባንቹ እንደሚሉት ሁሉም የችግሩን አሳሳቢነት እያየ ነው ያለው። ቁርጠኝነቱ የሚረጋገጠው እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በቀጣይ እንዴት ይፈፀማል ብሎ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን ሲሰራ ነውና ይህንን ይሰራል። ከዚህ በፊት ሥራዎች አልተሰሩም ሳይሆን ሚኒስቴሩ በየዓመቱም ሲሰራ ነው የቆየው፤ ክልሎችም እንዲሁ። አሁንም ሚኒስቴሩ አፈፃፀሙን ይከታተልና ይቆጣጠራል።
ክፍተቶችም ካሉ የእርምት ሥራ ይሰራል። ተጨባጭ ለውጥ ማምጣትም ተችሏል። በችግር ውስጥ የነበሩና ከችግር በመውጣታቸው በንቅናቄው መድረክ ለመሳተፍ የቻሉ ማሳያ ናቸው። ሆኖም የመጣው ለውጥ አሁን ባለው ሁኔታ በሚፈለገው ልክ አይደለም። ሌላው ጥናት አቅራቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (ጥቁር አንበሳ) የአእምሮ ሕክምና ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ናቸው። በግል የሬናሰንት የአእምሮ ሕክምናና ተሀድሶ ማዕከል መሥራችና ዋና ሥራ እስኪያጅ ናቸው። በችግሩም ላይ ለበርካታ ዓመታት በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል።
ፕሮፌሰር ሰለሞን ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከጥናታቸው ተነስተው እንደሚሉት መጤ ባህሎች፤ በፋብሪካና በቤት ውስጥ በጎጆ ኢንዱስትሪ በሚመረቱ የአልኮል መጠጦች፤ እንዲሁም፣ በአደገኛ ዕጾች ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ተጎጂዎች ናቸው። ይሄ በሳይንሱም የተረጋገጠ ዕውነታ ነው። ለምሳሌ የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች አብዝተው የሚጠቀሙ ሴቶች በጽንስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ አለባቸው።
እንደውም በአሁኑ ሰዓት ዓለም ዓቀፍ ጥናቶች ላይ ተመስርቶ የወጣው መመሪያ ነፍሰ ጡር ሴት የአልኮል ይዘት ያለባቸውን መጠጦች ፈጽሞ መጠቀም የለባትም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የትኛውም የአልኮል ይዘት ያለው መጠጥ ጽንስን ስለሚጎዳ ነው። ነፍሰ ጡር ሆነው መጠጥ የሚጠጡ ሴቶች የእርግዝና ወቅት ከጠላና ጠጅ ጀምሮ በቤት ውስጥ የሚመረት ቢራም ሆነ ጠጅና አረቄ በየትኛው መጠን መጠቀም በጽንሱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት በመረጋገጡ ተከልክሏል።
በርካታ ሴቶች በእርግዝና ወቅት፣ በተለይም የበዓላት ሰሞን የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች እንደሚጠጡ ይታወቃል የሚሉት ፕሮፌሰሩ ለነዚህ ነፍሰ ጡር ሴቶች ሲመክሩም፣ “በልጃችሁ አእምሮ እድገት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል። ለከፍተኛ ጉዳትም ይዳርጋቸዋል። በመሆኑም መጠጦቹን ከመጠጣት ራሳችሁን አቅቡ” ብለዋል። ቀጥለውም አደገኛ ዕጾችን፣ ለምሳሌ ጫትን በእርግዝና ወቅት መጠቀም ከጽንስ መጨንገፍ ጀምሮ የጽንስ መቀጨጭን ሁሉ እንደሚያስከትል በጥናቶች ተረጋግጧል።
ሌሎች አደንዛዥ ዕጾችን መጠቀምም በሆድ ውስጥ እያለ ጭምር ሱሰኛ ሆኖ እንደሚወለድ የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። ለአብነት ሄሮይን፤ ክራማዶንና ሌሎች አደገኛ ዕጾችና መድሃኒቶችን በእርግዝና ወቅት መጠቀም በቀጥታ በህፃኑ ላይ ሱሰኝነትን እንደሚያስከትል በጥናት ተረጋግጧል። በመሆኑም የትኛውንም ዓይነት አእምሮን የሚለውጥ መድሃኒት፣ የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች፣ ጫት፣ ትምባሆና ሌሎች አደንዛዥ ዕጾችን በእርግዝና ወቅት መጠቀም በጽንስ ላይ ችግር ያስከትላልና ታቀቡ በማለት ደጋግመው ነፍሰ ጡርና ሌሎች ሱስ አስያዥ እፆችን ተጠቃሚ ሴቶች ይመክራሉ።
ልማዳዊ ድርጊቶች
አቶ ኤሊያስ ካላይ ከዚሁ ከሱሰኝነት መከላከል ጋር በተያያዘ እየሰራ ያለ ተቋም (መቋሚያ) ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት ቅድመ መከላከል ባለሙያ ሲሆኑ “መቋሚያ የሱስ ሳይንስ” የሚል መጽሐፍም ደርሰዋል። አቶ ኤሊያስ እንደሚሉት በአገራችን አደገኛ አደንዛዥ ዕጾችና የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች፤ እንዲሁም ፊልሞችና የመሳሰሉት መስፋፋት አደንዛዥ ዕጾችና የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች ተጠቃሚ ቁጥር እንዲጨምር እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ ለማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ስነልቦናዊና አእምሯዊ ችግሮች በበለጠ ሰለባ የሚሆኑት በሴትነታቸው ሰፊ ማህበራዊ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሴቶች ናቸው።
ሱሰኝነት ሴቷን ብቻ ሳይሆን የምትወልደውን ልጅም ጭምር ይጎዳል። ቀስ በቀስ የቤተሰብን፤ የወዳጅ ዘመድ የሰላምና የተረጋጋ ህይወት ጠንቅም ይሆናል። እንዲሁም በቤተሰብ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳድራል። የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በ2002 ዓ.ም ያወጣውን፣ በወቅቱ የነበረ የአደገኛ ዕጾች መሸጫ ዋጋን ሪፖርትን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት፣ ግማሽ ሺሻ ለማጨስ 30 ብር፤ ሙሉ ሺሻ ለማጨስ ደግሞ 60 ብር ይጠይቃል።
ይህም እንደሚጨስበት ቤትና በተጨማሪ እንደሚወሰደው ሱስ አስያዥ የዕፅ ዓይነት ይለያያል። እንደ ጫትና ሌላም ሱስ አስያዥ ዕፅ ከሺሻው በተጨማሪ ከተወሰደ ደግሞ፤ ክፍያው እስከ ብር 100 እና በላይ ይደርሳል። ከዚህም በተጨማሪ ሌላ ሱስ አስያዥ ዕፅ ሳይጨመር ሺሻን ብቻ በወር አራት ቀን የሚያጨስ ተጠቃሚ በወር በአማካይ ከብር 120 እሰከ 240፤ አዘውትሮ የሚጠቀም ደግሞ በትንሹ ከብር 600 እሰከ ብር 1000 ያወጣል።
ይህም ተጠቃሚው ሴትም ሆነ ወንድ በቤተሰቡ ኑሮ ላይ የኢኮኖሚ መናጋት ያስከትላል። በማጨስ የሚባክነው ገንዘብም እንዲሁ የገቢ መቀነስን ያስከትላል። ተጠቃሚዋ ሴት በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ ካላት ሰፊ ኃላፊነት አንፃር ተጽዕኖው በእጅጉ ይገዝፋል። ተቋማቸው ተፅዕኖውን በመቀነስ ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ በተለይ ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።
የገቡት እንዲወጡ፤ ያልገቡት እንዳያገቡ ቅድመ መከላከል ላይ የሚሰራውንም በማሳያነት ያነሳሉ። መጤ ባህል ኩረጃ የሚዘወተርባቸውና አደገኛ አደንዛዥ እጾችን መጠቀም ባህል ያደረጉ አካባቢዎች ከዚህ ልማዳቸው እንዲላቀቁ ለማድረግ ረጅም ጊዜ ቢፈጅም ባህልና ልምዱን ባከበረ መልኩ ሱሰኝነትና ጉዳቱን ነጥሎ የማውጣት ሙከራ እየተደረገ መገኘቱንም አቶ ኤልያስ ያወሳሉ።
ለአብነትም በምስራቁ የአገራችን ክፍል ጫት በተዘጋ ቤት ውስጥ፤ እንዲሁም፣ ከኮካ ኮላና ከአልኮል መጠጥ ጋር ሳይሆን እንዲሁ እየተናፈሱ ውጪ ሆነው እንዲቅሙ በማስለመድ ከመቃም ጋር ተያይዞ የሚመጣን ጉዳቱ ለማስቀረት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያነሳሉ። እኛም ከማንኛው ሱስ ነፃ የሆነ ህብረተሰን ይፈጠር ዘንድ በመመኘት ዝግጅታችንን በዚሁ እናጠናቅቃለን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም