የትምህርት ቤት እርሻዎች ወይም ግብርና ተግባራዊ የሆነ የትምህርት ልምድን ለተማሪዎች የሚሰጥ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመንበታል:: ምክንያቱም እነዚህ ቦታዎች ትምህርታዊ ቦታዎች ቃለ ነቢብ ወደ ገቢር የሚቀየርባቸው ስፍራዎች በመሆን አገልግሎት ይሰጣሉ። እነዚህ እርሻዎች ብዙውን ጊዜ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ወይም አቅራቢያ እንዲኖሩ ተደርገው የሚፈጠሩ ስለሆኑም ለተማሪዎች የሚሰጡት ጥቅም ከዚህ መለስ የማይባል ሲሆን፤ አንዱም የመማር-ማስተማር ሥራውን መደገፍ እንደሆነ ታምኖበታል::
ተማሪዎች ስለ ምግብ ምርት እና ስለ ጤናማ አመጋገብ አስፈላጊውን እውቀት እንዲጨብጡ በማድረግ፣ ስለ እንስሳት ሕይወት እና ዑደቶች፤ እንዲሁም፣ ስለ ምግብ አመራረት ሂደቶች፣ ስለ ምርት መሰብሰብ፣ ማከማቻ እና ወደ ምግብነት መቀየርን እንዲማሩበት ዕድል በመስጠት፤ ስለ ተፈጥሮና አካባቢ እንክብካቤ፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቅሞች፤ ኃላፊነት መውሰድን የመሳሰሉ ተግባራትን እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል:: የግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላይ ኅብረተሰቡና ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ያለውን ፋይዳ ይረዱ ዘንድ ያስችላቸዋል::
በትምህርት ቤት እርሻ ላይ የመሥራት ልምድ የቡድን ሥራን ለማዳበርም ሁነኛ መንገድ ነው:: ለሌሎች ያለን አክብሮት፣ ኃላፊነት መውሰድና ለማኅበረሰቡ ቁርጠኝነትን ማሳየትም የሚቻልባቸው ቦታዎች ናቸው:: በተጨማሪም ተማሪዎች ተግባራዊ ችሎታዎችን የሚያውቁባቸው የትምህርት ስፍራዎች ሲሆኑ፤ በተግባር ውስጥ ደግሞ ችግር መፍታትን፣ ውሳኔ መስጠትን፣ እቅድ ማውጣትንና የመሳሰሉትን ይማራሉ:: በእነዚህ ልምዶችም ተማሪዎች ለግል እድገታቸው እና ለኅብረተሰቡ ደህንነት ፍቱን መድኃኒት ይሰጣሉ:: ስለዚህም የእነዚህ ቦታዎች ዋና ግብ ለተማሪዎች የተግባር ልምድ መስጠት ነው::
የምግብ ምርት፣ ዘላቂ ግብርና እና ጤናማ አመጋገብ ደግሞ በእነዚህ ልምዶች የተማሪዎችን ግላዊ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ እድገትን የሚያመጣ አጠቃላይ ትምህርት ነውና ይህንን አውቀው እንዲራመዱ ያስችላቸዋል:: ታዲያ እነዚህና መሰል ልምዶች በአገራችን ደረጃ እንዴት እየተተገበሩ ናቸው ከተባለ ለዛሬ ከተለመደው የገጠር ግብርና ወጣ ብለን የከተማውን፤ ከከተማም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያለውን እንቅስቃሴ እንመልከት:: ይህም ሰፊ ስለሚሆን ወስነን በትምህርት ቤት ያለውን የከተማ ግብርና እናንሳ::
በ2014 አ.ም በ138 ትምህርት ቤቶች 147ሺህ 971 ነጥብ 38 ካሬ ቦታ ለማልማት ታቅዶ በ333 ትምህርት ቤቶች 279ሺህ 857 ካሬ ሜትር ማልማት ተችሏል:: በዚህ ሥራ ላይ ደግሞ 5ሺህ 187 ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ሆነዋል:: በ254 ትምህርት ቤቶችም የኮምፖስት ማዘጋጀት ሥራ የተከናወነ ሲሆን፤ ለጓሮ አትክልት ብቻ ሳይሆን ለመማር-ማስተማሩ ሥራም እጅጉን ጠቅሟል:: እንደ አጠቃላይ በትምህርት ቤት ግብርናው 1ሚሊዮን 122ሺህ 180 ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ አብዛኛው ወደ ምርትነት እንደተቀየረና ጥቅም ላይ እንደዋለ፤ በተፈጠረው የአመለካከት ለውጥም ሥራዎቹ እንደቀጠሉ የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል::
የትምህርት ቤት ግብርናን እውን አድርገው እውቅናን ካገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ደግሞ ገላን የወንዶች ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትና ደጃዝማች ወንድይራድ አጸደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይጠቀሳሉ::
ገላን ልዩ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት መጀመሪያ ያየነው ሲሆን፤ በከተማ ግብርና በተደጋጋሚ ሽልማት አግኝቷል:: ለዚህ ያበቃው ደግሞ የሥራ ድባቡን ከተማሪዎች እስከ መምህራን፤ ከጽዳትና ጥበቃ እስከ ጸሐፊና ርዕሰ መምህራን፤ ከምገባ ሠራተኞች እስከ የዶርም ተቆጣጣሪዎች ድረስ ለሁሉም የራሳቸው የሆነ የእርሻ ቦታ በመስጠት ወደ ተግባር ተገብቷል:: በዚህ ደግሞ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ትምህርትም፣ ገንዘብም ማስገኘት ችሏል::
ትምህርት ቤቱ ከሁሉም በላይ በዚህ ሥራው ማህበረሰቡን ጭምር ማቅረብ ችሎበታል:: ምክንያቱም በግቢው ውስጥ የተመረተውን ምርት ከሽያጭ ይልቅ በስጦታ መልክ ያቀርባል:: በተለይም ርዕሳነ መምህራን የያዙት የእርሻ ስፍራ ብዙ አትክልትና ፍራፍሬዎችን የያዘ ሲሆን፤ ለተቸገረው የሚሰጥ፣ በአማረው ተቀጥፎ የሚበላ ነው:: የሌሎቹ መምህራንም ቢሆን ይህንኑ መልክ የያዘ ነው::
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ ከሌሎቹ ጭምር ወስደው ሸጠው ቤታቸውን እንዲደጉሙበት ይደረጋሉ:: በመሆኑም ለምግብ ፍጆታቸው ከጓሯቸው ውጪ ብዙም አይገዙም:: አብዛኛውን ፍጆታቸውን ከዚያው ይጠቀማሉ። ወጪያቸውንም ይቀንሳሉ:: ይህንን ትምህርት ቤት ከሌላው ለየት የሚያደርገው ነገር የውሃ አጠቃቀሙ ሲሆን፤ ንጹህ ውሃን ሳይሆን ቆሻሻ ውሃን አጣርቶ በማቆር ነው ሥራ ላይ የሚያውለው:: በዚህ ምክንያትም ከግቢ ውጪ የሚፈስ አንድ ጠብታ ውሃ የለም::
አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ እርሻዎች በርካታ ጠቀሜታዎች ያሏቸው ሲሆን፤ ዋነኛ አላማቸውም ጤናማ የአመጋገብ ልምዶችን ተማሪዎች እንዲያውቁ ማድረግ ነው:: ተማሪዎች ስለ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ፣ ተገቢ የአፈር አያያዝን መማር ማስቻልም ነው:: ይህ ልምድ ደግሞ ተማሪዎች ግላዊ እና ማህበራዊ እድገትን እንዲያመጡ ያስችላቸዋል:: ጠቃሚ እሴቶችን እና ክሂሎትን እንዲያዳብሩም ይረዳቸዋል:: የወደፊት ፍላጎታቸውንም ለመወሰን አቅጣጫ ይጠቁማቸዋል::
በትምህርት ቤት እርሻዎች ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት እንደ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የሚወሰኑ ሲሆን፤ በገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ያለው የመልከአ ምድር ሁኔታ ለጥ ያለ ሜዳ ቢሆንም ብዙ ሥራን ግን የጠየቀ ነው:: ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ስፍራዎች ድንጋያማና ቆሻሻ መድፊያ ነበሩ:: ስለዚህም እነዚህን የእርሻ ቦታዎች ብዙ በመድከም ምርት ሰጪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:: ስለሆነም ከቆሻሻ ማንሳትና ማጽዳት ባሻገር ድንጋያማውን ስፍራ ወደ ለም መሬት የመለወጡ ተግባራት በስፋት ተከናውኗል:: ይህንን በማድረጋቸው ደግሞ ውጤታማ ለመሆን በቅተዋል:: ከምድሩ በረከትም ማፈስ ችለዋል::
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ካሳሁን መርጋ እንዳሉን፤ ትምህርት ቤቱ ከችግኝ ጋር በተያያዘ ታሪካዊ ዳራ ያለው ነው:: ምክንያቱም ታውቋቸው ሊሆን ይችላል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1997 ዓ.ም በቦታው ተገኝተው ችግኞችን ተክለዋል:: በዚህም ዓመታትን ያስቆጠረ የግራር ዛፍ ምቹ ሆኗል:: ግራር ካለ ደግሞ ቡና ግድ ነውና ትምህርት ቤቱ በቡና ተክል እንዲታወቅና ከዛፉ ፍሬ እንዲቀምስ ሆኗል:: እንደ ሌሎቹ ትምህርት ቤቶች በአትክልትና ፍራፍሬም ተጠቃሚ ነው:: ከዚህ ሻገር ሲልም ንብ የማነብ ተግባርን ያከናውናል::
የትምህርት ቤት ግብርና በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት:: አንዱ የመማር ማስተማር ሥራውን መደገፍ ነው:: በዚህም ተማሪዎች ስለ እንስሳት የሕይወት ዑደት፣ ምርት መሰብሰብ እና ማቀናበር፤ በምርቶቹ ንግድ ውስጥ መሳተፍን ተማሪዎች እንዲያውቁ አስችሏል:: ትምህርታቸውን አጠናቀው ቢወጡም እንዳይቸገሩ ያደርጋቸዋል:: ምክንያቱም ኢንዱስትሪውን በእጅጉ የሚደግፈው እርሱ እንደሆነ በሚገባ ተረድተዋል:: በትምህርት ውስጥ የሙያ አማራጮችን ለማየትም ችለውበታል ብለውናልም::
ግብርና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን እና የእንስሳት ምርምር እና ልማትን የሚያካትት ሳይንስ እንደሆነ ያነሱት ደግሞ የትምህርት ቤቱ የተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ መስፍን መኩሪያ ናቸው። እሳቸው እንዳሉንም ሆነ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የግብርና ሳይንስ ባለሙያዎች በኅብረተሰባችን ውስጥ ያለውን የምግብ አቅርቦት ሳይቀር መፍትሄ ሰጥተዋል:: በምገባ ሥርዓቱ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ብናነሳ እንኳን ሚናቸው የላቀ ነው:: ለአብነት እንደ አገር 1ነጥብ5 ሚሊዮን ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራም ውስጥ ተካተዋል::
ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ደግሞ ከ700ሺህ በላይ ተማሪዎች በፕሮግራሙ ተካትተዋል:: ይህንን የምገባ ፕሮግራም ለመሸፈን ደግሞ እጅግ አዳጋች ነው:: ዋነኛው የገንዘብ ምንጫችን ደግሞ የዓለም ባንክ ነው:: ይህንን ቢያቆም ተማሪዎችን ለመመገብ አስቸጋሪ ይሆናል:: እናም ይህንን መተካት የሚቻለው በትምህርት ቤቶች ግብርናና ምርት ስለሆነ በስፋት ሊሠራበት ይገባል::
እንደ ትምህርት ቤት በከተማ ግብርና ብቻ ሳይሆን አዲስ በመጣው የሌማት ቱሩፋት ሳይቀር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው:: ለዚህ ማሳያው ደግሞ ንብ ማነብና አትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ በስፋት መሥራታችን ሲሆን፤ ዶሮ እርባታም የቅርብ ሥራችን ይሆናል:: እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ በቅንጅት ለመሥራት የመፈልፈያ ማሽን መግዛት ተችሏል:: በቀጣይ ደግሞ የእንስሳት እርባታ የሚጀመር ይሆናል:: ሁሉንም በማቀናጀት ተማሪዎቻችንን ጤናማ አድርገን ውጤታማ እንዲሆኑ እንሠራለን::
የትምህርት ቤት ግብርና የትምህርት ላብራቶሪ ነው:: ምክንያቱም በሙከራና በእይታ ነገሮችን ማረጋገጥ ይቻልበታል:: በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ለሚማሩ ተማሪዎች መሠረት የሚሆን እውቀት የሚያስጨብጥ ነው:: ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ቢሆን ቀጣይ የሕይወት ማረፊያቸውና መተዳደሪያቸውን የሚወስን ነው:: ምክንያቱም ተማሪዎች የአትክልትና ፍራፍሬን አበቃቀል፤ ዓይነቶችን፤ የአፈር ዝግጅት፣ መትከል፣ ውሃ ማጠጣት፣ ማዳበሪያ፣ ተባዮችን እና በሽታን መቆጣጠር እንዴት እንደሚቻል ይማሩበታል:: መሥራትን ልምድ ያደርጉበታልም ሲሉ ያብራራሉ::
ሌላኛው የተመለከትነው ትምህርት ቤት ደግሞ ደጅአዝማች ወንድይራድ የአጸደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ልክ እንደ ገላን ሁሉ በትምህርት ቤት ግብርና የላቀ ተሸላሚ ነው:: ትምህርት ቤቱ በቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት የብዙዎችን ሕይወት ሊታደግ የሚችል እና በከተማ እየተከናወነ ላለው የጓሮ አትክልት ልማት ሥራ ማዳበርያ ማቅረብ ያስቻለ በመሆኑ ተሸልሟል::
ይህ ት/ቤት ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት በመቀየርም የገቢ ማስገኛ ሥራን ያከናወነ ተቋም ነው:: ይህ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ተስማሚ እና መልሶ የመጠቀም አሠራርን ያመጣል:: ለአረንጓዴና ጤናማ የከተማ ግንባታ ሂደትም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው:: እናም ይህን በማድረጉ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል::
የዚህ ትምህርት ቤት የከተማ ግብርና ውጤት በአንድ በኩል ለተማሪዎች ምገባ ሲውል በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በዚህ በኑሮ ውድነት ወቅት ለማኅበረሰቡ አለኝታ መሆን ችሏል:: እንዴት ከተባለ ምርቱን በቀላል ዋጋ በማቅረብ ችግር ፈቺነቱን አሳይቷል:: ሌላውና ዋነኛ አላማው ደግሞ ተማሪዎች በግብርናው ዘርፍ በቂ እውቀት እንዲጨብጡ ማስቻሉ ነው:: ለአብነት ተማሪዎች ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት መቀየር የሚችሉበትን እውቀት ቸሯቸዋል:: ተፈጥሮን የሚያክም፤ ቆሻሻን ወደ ሀብትነት የሚቀይር አቅም እንዳላቸውም አሳይቷቸዋል::
ይህ ደግሞ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን የአምስት ዓመት የከተማ ግብርና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሠርተው ነው:: በዚህ እቅዳቸው የመጀመሪያው ዓመት የጓሮ አትክልት፤ በሚቀጥለው ዓመት ዶሮ፣ በሌሎቹ ዓመታት ደግሞ የዓሣ፣ ንብ ማነብና የእንስሳት ርባታን አካቶ ለመሥራት አስቦ ብዙዎቹን ተግብሯል:: ቀጣይ ዓመት እቅዱም ዓሣውን ማስጀመር መሆኑን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ሰለሞን ክቤ ነግረውናል::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሁን በተሠሩት ተግባራት ከራስ አልፎ ለአካባቢው ማህበረሰብ መድረስ ተችሏል። ሥራውን የሚያከናውነው ምርቶቹን በግቢው ውስጥ ባለው ሱቅ አርብ አርብ ለማህበረሰቡ በማቅረብ ሲሆን፤ በዚህም ትምህርት ቤቱ በወር በአማካኝ ከ18ሺህ ብር በላይ ገቢ እንዲያገኝ ሆኗል::
ትምህርት ቤቶች ግብርና ላይ መሥራታቸው በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚያነሱት ርዕሰ መምህሩ፤ በተለይም የከተማ ግብርና ለከተማ ልጆች እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ያስረዳሉ:: ምክንያታቸው ደግሞ የከተማ ልጅ በቤቱ ብዙ ነገሮችን የማወቅ ዕድል የለውም የሚለው ነው:: እንስሳትንና እጽዋትን ሳይቀር የማየት ዕድል ያለው በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ነው:: ስለዚህም የትምህርት ቤት የእርሻ ቦታዎች ይህንን ችግራቸውን ከመፍታት አኳያ የማይተካ ሚና አላቸው:: በተግባራዊ ልምምድም መፍትሄ ያገኙባቸዋል::
ይህ ብቻም አይደለም፤ ከእርሻ እስከ አጨዳ እና አቀነባበር ድረስ ያለውን የግብርና ሂደት ይረዱበታል:: ምግብ ከየት፣ እንዴት እንደሚመጣ እና ለማምረት ምን እንደሚያስፈልግ ይገነዘቡበታል:: ጤናማ የአመጋገብ ልምዶችን ይቀስሙበታል:: ማለትም ተማሪዎች ስለ ጤናማና የተመጣጠነ አመጋገብ አስፈላጊነት በትምህርት ቤት በንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም እያወቁ ይሄዱበታል:: ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያጠናክሩበታልም:: አካባቢያቸውን የመንከባከብ አስፈላጊነትንም ይረዱበታል::
ልጆች ከእፅዋትና ከእንስሳት ጋር በመገናኘት ስለ ብዝኃሕይወት አስፈላጊነት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ግንዛቤ ይይዙበታል:: ሌላው የማህበራዊ ክሂሎት እድገትን ያመጡበታል:: ማለትም በቡድን መሥራት ምን ያህል እንደሚጠቅም ያረጋግጡበታል:: ችግር መፍታትንም ይማሩበታል:: እነዚህ ማህበራዊ ክሂሎቶችን ማዳበር ከቻሉ ደግሞ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እና በወደፊት ሥራዎቻቸው ላይ ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ:: እሴቶችን እና አዎንታዊ አመለካከቶችን ያዳብራሉም:: ኃላፊነት መውሰድን ያውቃሉ:: አወንታዊ እሴቶች እና አመለካከቶችን ከማዳበር አልፈው ለግላዊ እና ማህበራዊ እድገታቸው ይጠቀሙበታል ይላሉ::
አዎ፣ የትምህርት ቤት ግብርና ለተማሪዎች የትምህርት አቅም ማጎልበቻ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ እረፍትም መስጪያ ስፍራ ነው:: ምክንያቱም ቤተሰባቸው በኑሮ ውድነቱ እንዳይሰቃዩ ልምዱን በቤታቸው በማስፋት ተጠቃሚ ያደርጉበታል:: ራሳቸውም ጤናማ የመማር-ማስተማር ሥራ ውስጥ እንዲገቡ ያስችላቸዋል:: እናም ይህ አካዳሚያዊና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል በማለት ሀሳባችንን ቋጨን::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2015