በቀኑ የሥራ ውሎ የተዳከመው ሠራተኛ ወደ ሰፈሩ የሚያደርሰውን ትራንስፖርት መጠበቅ ይዟል:: አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞችን አውቶቡስ የሚጠብቅ ነው:: የተቀረው የታክሲ ሰልፍ ይዞ ከወረፋው በተጠንቀቅ ቆሟል:: የሰሞኑ ዝናብ እንደልማዱ ‹‹መጣሁ›› እያለ ማስፈራራት ጀምሯል:: በስፍራው የቆምን አንዳንዶች ሰማዩን አንጋጠን እናያለን:: ካሁን አሁን ዳመናው ዝናብ ሆኖ ጉድ እንዳይሠራን ሳንፈራ አልቀረንም::
ደግነቱ በስሱ የጀመረው ካፊያ ብዙ አልቆየም:: እንዳመጣጡ ጥቂት ጎብኝቶን አልፎን ሄዷል:: የአውቶቡሱ ሰልፍ ቀስ በቀስ ተቀጣጥሎ አስፓልቱን ሊሻገር ነው:: ለዓይን የዘገየው ሰማያዊ አውቶቡስ እስካሁን ብቅ አላለም:: ጊዜው እስኪደርስ የሞባይሉን ሰዓት የሚቆጥረው ተሳፋሪ መበርከቱን አስተዋልኩ:: የልምድ ሆኖ እንጂ ሁሉም መነሻ ሰዓቱን ያውቀዋል::
ከሰልፈኞች መሀል አንዳንዱ አስር ሰዓት ሳይሞላ ከሥራው የወጣ ነው:: የአውቶቡሶች መንቀሳቀሻ ሰዓት ቢታወቅም ቀድመው መሰለፍ ሱስ የሆነባቸው ሞልተዋል:: ከቆምነው መሀል አብዛኞች ለመሄድ የቸኮሉ ይመስላል:: ያም ቢሆን ሾፌሮቹ ከሰዓታቸው ቀድመው አያሳፍሩም:: ይሄ እውነት ቢታወቅም አንዳንዶች መቁነጥነጥ፣ መጣደፍ ልማዳቸው ነው:: መቆም መቀመጡ የሰለቻቸው ጥቂቶች ቶሎ ተሳፍረው ለመሄድ ይቸኩላሉ:: እኔም ብሆን ስሜቱ ሳይጋባብኝ አልቀረም:: በየአፍታው ዓይኔን እየጣልኩ ማንጋጠጡን ይዣለሁ::
አሁን ጥቂት አውቶቡሶች መታየት ጀምረዋል:: አጠገባችን ሲደርሱ የያዙትን ይዘው እብስ ይላሉ:: የእኛው ሰማያዊ ፈረስ እስካሁን አልመጣም:: ሁላችንም በእጆቻችን መታወቂያዎች ይዘን እየጠበቅን ነው:: ጥቂት ደቂቃዎች አለፍ እንዳሉ ሲጠበቅ የነበረው አውቶቡስ ከች አለ:: ወዲያው በሁሉም ሰው ገጽታ የእፎይታ ፈገግታ ተስተዋለ::
ከሠራተኞች የተመረጠው ቋሚ አስተባባሪ መታወቂያ እያየ ለማስገባት ስፍራውን ይዟል:: ተሳፋሪው አንድ በአንድ ወደውስጥ መግባት እንደጀመረ አንዳንዶቹ ሲያጉረመርሙ ተሰማኝ:: ቀደም ሲል በቦታው ያልነበሩ ሁለት ሰዎች በ‹‹እንግባ አትገቡም›› ውዝግብ እየተጨቃጨቁ ነው::
አብዛኛው ሰልፈኛ ጣልቃ ገብቶ ሁለቱን ሴትና ወንድ እየገሰጸ ነው:: እውነት ለመናገር እኔም ብሆን ሰዎቹን አስቀድሜ አላየኋቸውም:: ቆይታዬ ጥቂት ባለመሆኑ መኖር አለመኖራቸውን ለመለየት አልቸገረኝም:: ከየት እንደመጡ ባላውቅም ‹‹እዚሁ ነበርን ሲሉ መከራከራቸው አሳፍሮኛል:: አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ደፋሮች አይጠፉም:: ዓይናቸውን በጨው አጥበው ከፊት ለመቅደም የሚያህላቸው የለም::
ለእንዲህ ዓይነቶቹ በይሉኝታ ይለፍ የሚሰጧቸው እንዳሉ ሁሉ አመናጭቀውና አዋርደው የሚያስወጧቸው አይጠፉም:: የሁለቱ ሰዎች ዕጣ ፈንታም ከዚህ አላለፈም:: አስቀድመው በስፍራው እንዳልነበሩ ተመስክሮባቸው ወደመጡበት ተመልሰዋል::
ድርጊታቸው እያስገረመኝ ወደውስጥ ማለፍ ጀምሬያለሁ:: ጥሎብኝ የምመርጠው ቦታ የጥጉን አቅጣጫ ነው:: አጋጣሚ ሆኖ ለዛሬ በጥግ ያሉት ወንበሮች በሙሉ ተይዘዋል:: ክፍት፣ ድብር አለኝ:: ሁሌም በመስታወቱ በኩል መቀመጥ ምቾት አለው:: ይህን የምናውቅ አብዛኞቻችን እነዚህን ቦታዎች እንመርጣለን::
ሰዓቱ ሲደርስ የሰፈራችን አውቶቡሱ ተንቀሳቀሰ:: ወንበር የያዘው እንዳለ ሆኖ ቆሞ ለመሄድ የተዘጋጀው ጥቂት አልሆነም:: ጥቂት አለፍ እንዳልን ያቆመ የመሰለው ዝናብ ማካፋት ጀመረ:: በዚህ ብቻ አልበቃውም:: መጠኑን ጨምሮ ያወርደው ጀመር:: በዚህ ከቀጠለ ሰበብ ፈላጊው መንገድ መዘጋጋቱ አይቀረም:: እኛስ ወንበር ይዘናል :: ‹‹ይብላኝ.›› ቆመው ለሚጓዙት:: አሳዘኑኝ::
ምስጋና ለሚገባቸው ሁሉ ይሁንና ይህ የመንግሥት ሠራተኞች አውቶቡስ ያላቃለለው የለም:: ተጠቃሚውን ከእንግልት ወጪ ታድጓል:: ሁሉም በጊዜ ወጥቶ ለሥራውና ለቤቱ እንዲደርስ አግዟል:: ይህን እያሰብኩ ዓይኖቼን ወደውጭ ወረወርኩ:: በርካታ ታክሲ ጠባቂ ዝናብ እየደበደበው ቆሟል:: የጫፉን መጨረሻ በወጉ ያላየሁት ረጅሙ ሰልፍ ማብቂያ ያለው አይመስልም::
ጉዞ የቀጠለው አውቶቡሳችን በጀመረው ፍጥነት ላይ ነው:: የባስ ካፒቴናችን እንደተለመደው በየምክንያቱ መነጫነጭ ይዘዋል:: ለምን እንደሆነ ባላውቅም ለመቆጣት ሰበብ አያጡም:: ሲሻቸው ከተሳፋሪው ጋር ሙግት ይዘው ይጋጫሉ:: ሲላቸው ደግሞ አንገታቸው አውጥተው ከሌሎች ሾፌሮች ጋር ይሰዳደባሉ::
ከሁሉም ግን አንድ ማለዳ የሆነውን እውነት ፈጽሞ አልረሳም:: በጠዋቱ ከቤት ወደሥራ መንገድ የጀመረው ሠራተኛ በካፒቴናችን ይሁንታና ምሪት እየተጓዘ ነው:: ጊዜው ባለመርፈዱ መንገዱ ነፃ ነበር:: እንዲህ ሲሆን በጊዜ ለመድረስ አይቸግርም:: ትልቁ ሾፌራችን ግን ዛሬም መንገዱ የጠበባቸው ይመስላል:: በቅርባቸው ያሉ ትናንሽ መኪኖችን በ‹‹አትድረሱብኝ›› ጡሩንባ እያንቧረቁ መድረሻ አሳጥተዋቸዋል::
አንዳንድ ትናንሽ መኪኖች የአውቶቡሱን ግዝፈት እያዩ ጥግ ይይዛሉ:: ሌሎች ደግሞ መንገዳቸውን ጠብቀው በወጉ ይጓዛሉ :: ቁንጥንጡ ሾፌር ይህ ዓይነቱ እውነት ሁሌም ያናድዳቸው ይመስላል:: መንገዱ የጋራ እንዳልሆነ ‹‹የእኔ ብቻ ይሁን›› ማለትን ለምደዋል::
የዚያን ዕለት ማለዳም የሆነው እንዲሁ ነው:: አንድ መለስተኛ የጭነት መኪና ከጎናቸው ቆሞ ይቆይና ቀድሟቸው ያልፋል:: አስቀድሞ ቦታ እንዲለቅላቸው ሲጋፉት የቆዩት ካፒቴን ታዲያ እልህ ይይዛቸዋል:: መሪውን እየደበደቡ፣ አንገታቸውን እያወጡ እንደልማዳቸው አንባረቁ::
ጥቂት ቆይቶ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ስድብ ከሁላችን ዘንድ ደረሰ:: የሬዲዮው ድምጽ ከፍ ያለ ቢሆንም አስደንጋጩ ቃል ጎልቶ ለመሰማት ኃይል አላጣም:: ክፉ ቃልና ክፉ ሽታ ቶሎ ለመድረስ ይፈጥናል ልበል? ዞር ብዬ የሌሎችን ፊት ቃኘሁ:: አብዛኞቹ በሀፍረት እጃቸውን ከአፋቸው ጭነዋል:: መኪናው ርቋቸው ቢሄድም በዋዛ ሊተዉት አልፈለጉም:: ሰውዬው ፍጥነት ጨምረው ከኋላው ተከተሉት::
ሁሉም በድንጋጤና ስጋት ተያየ :: ሾፌሩ ያሰቡት አልቀረም:: ከመኪናው እንደምንም ተሽሎክሉከው ደረሱበትና ከጎኑ ተገሸሩ:: አንዳንዶች ድርጊታቸውን መታገስ አልቻሉም:: ሰውዬው ባይሰሟቸውም በግልጽ ተቃወሟቸው::
የጭነት መኪናው ሾፌር ሮጦ ያልጠገበ ጎረምሳ ነው:: የእኛን መኪና እንዳየ ከሰውዬው ጋር የእልህ ጨዋታ ጀመረ:: አሁንም መንገዱን ላለመልቀቅ ተገዳደራቸው:: ምክንያት ፈላጊው ካፒቴን በንዴት እንደጨሱ መንቀሳቀስ የጀመረውን መኪና ተከተሉት:: በጣም እየፈጠኑ ነው:: ሁላችንም በጩኸት ተንጫጫን:: መኪናው ፍጥነቱን አልቀነሰም:: የሌባና ፖሊስ የሚመስለው አባሮሽ ዋና መንገዱን ለቆ ውስጥ ውስጡን ቀጠለ::
አሁን ጎረምሳው ሾፌር የደነገጠ ይመስላል:: መኪናውን በፍጥነት እያከነፈው ነው:: የሁላችንም ድንጋጤ ከቀድሞው ይበልጥ አይሏል:: ሽማግሌው ደንታ አልሰጣቸውም:: ሾፌሩን ለመድረስ የእርምጃ ርቀት ቀርቷቸዋል:: ሁሉም ሰው ሁለቱ ቢገናኙ የሚፈጠረውን እያሰበ ተሳቀቀ ::
የፊትና ኋላው ግብግብ በአጭር ርቀት ቀጠለ:: ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ መልካም አጋጣሚው ተፈጠረ:: ለማቋረጥ በሁለቱ መካከል የገቡት ጥቂት መኪኖች ታሪክ ቀየሩ:: ተሯሯጮቹ ኃያላን ርቀታቸው ሰፍቶ በድንገት ተለያዩ:: ሽማግሌው ሾፌራችን ግዳይ አልቀናቸውም:: መሪውን እየደበደቡ ስድባቸውን ቀጥለው መንገዳቸውን ይዘዋል::
ጥቂት ስረጋጋ ያለሁበትን አካባቢ ቃኘሁ ከዚህ ቀድሞ ያልሄድንበት የውስጥ ለውስጥ መንገድ ላይ ነበርን:: ዞር ብዬ ሌሎችን አስዋልኩ በኀዘኔታና በሀፍረትና ድንጋጤ ተሸማቀዋል::
ይህ ዓይነቱን ድርጊት የለመደው ተሳፋሪ ከመታዘብ ውጪ አስተያየት ለመስጠት አይደፍርም:: ልናገር ቢል ደግሞ የሚደርስበትን አሳምሮ ያውቃል:: ነጭናጫውና ቁጡው ሾፌር ለእሱም የሚተርፍ የነገር ዱላ አያጡለትም:: ባጋጣሚ ዕለቱ እንዲህ ቢያልፍም ሊሆንና ሊከሰት የሚችለውን አደጋ መገመት አይቸግርም::
በእርግጥ እጅግ መልካም ሥነምግባር ያላቸው የአውቶቡስ ሾፌሮች አሉ:: በዚህ እውነታ ደግሞ አብዛኛው ተጠቃሚ ይስማማል:: እንደዛሬው ሳይሆን ከጥቂት ጊዜያት በፊት ለእንዲህ ዓይነቶቹ ልበ መልካሞች ሽልማትና ስጦታ ይበረከት ነበር:: እንዲህ ሲደረግ አብዛኛው ተሳፋሪ አይሰስትም፣ በራሱ ይሁንታ ተነሳስቶ አክብሮቱን ያሳያል::
ዛሬ ይህን ጉዳይ ሳነሳ መልካም ሥነምግባር ላላቸው በጎ ካፒቴኖቻችን ምስጋናንን በመቸር ነው:: እኛም በሥነምግባራቸው የሚታወሱ፣ በተባባሪነታቸው የሚሞገሱ፣ በሠሩት ድንቅ ተግባር ተቋማቸው ጭምር የሸለማቸውን ጀግኖች ሁሌም እናደንቃለን:: አሁንም በያሉበት ሰላማቸው ይብዛ:: አንዳንዴ ደግሞ በስንዴ መሀል እንክርዳድ አይጠፋምና ከትዝብቱ፣ ለእርምቱ ይህን ብለናል:: መልካም መንገድ ::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23/2015