በአከራይና ተከራይ ዙሪያ ብዙ ተብሏል፤ እኔን ጨምሮ በዚሁ በትዝብት ዓምድ እንኳን ብዙ ተብሏል። በየመገናኛ ብዙኃኑ የሚሰጠው የአከራይና ተከራይ ትዝብት ግን የአከራዮች ክፋትና ጭካኔ ላይ የሚያተኩር ነው። በአከራዮች በኩል ያለው ችግር ብዙ ስለተባለበት እስኪ ዛሬ ደግሞ በተከራዮች በኩል ያለውን ችግር እንታዘብ።
አንዳንዴ በአከራይ ቦታ ሆኜ አስበውና ‹‹እኔ ብሆን ይህን እታገስ ነበር?›› ብዬ አስቤ አውቃለሁ። ይህን የምለው በተከራየሁበት ግቢ ውስጥም ሆነ በተለያዩ ጓደኞቼ የአንዳንድ ተከራዮችን ድርጊት በማየት ነው። አንዳንዴ ደግሞ በዚያ ልክ እንዴት ድፍረት ሊያገኙ ቻሉ? የሚለው ያስገርመኛል። ከእኔ ግላዊ ባህሪ አንፃር እያየሁት ነው መሰለኝ ለመቅናትም ይቃጣኛል። በዚህ ልክ ድፍረት ቢኖረኝ እላለሁ።
ለምሳሌ፤ የሚከፍቱት ሙዚቃ ልክ በጎዳናዎች ላይ የበዓል ሰሞን በሞንታርቦ የሚለቀቁ ማስታወቂያዎችን ይመስላል። ከመረበሽ አልፎ ጎረቤት ያለ ሰው ለማውራት እስከሚቸገር ድረስ(ባለመሰማማት) የሚያስጮሁ አሉ።
ሲወጡና ሲገቡ የውጭውን በር ሲዘጉት የሚጠቀሙት ኃይል ግንብ ካልሆነ አጥሩን ሁሉ ያነቃንቀዋል። አንዳንዴ እንዲያውም በግዴለሽነት ብቻ ሳይሆን ሆን ብለው ሁሉ ይመስለኛል፤ በሩን በእጅ ተከትሎ ቀስ ብሎ መዝጋት እየተቻለ ይወረውሩታል።
ግዴለሽነቱ አብሮ ያደገ እንዝላልነት ነው እንበል፤ ተከራይ መሆኑ ግን ይረሳል? በዚህ የቤት መጥፋትና መወደድ ዘመን ይህ ችግር መረሳት ነበረበት? ‹‹ውጡ!›› ከተባለ በኋላ ከማማረር በሥነ ሥርዓት መኖር አይሻልም? እዚህ ላይ ግን አንድ ልብ መባል ያለበት ነገር ‹‹ውጡ!›› የሚባለው በተከራዮች የሥነ ምግባር ችግር ብቻ አይደለም፤ አከራዮች የተጋነነ ዋጋ ሊጨምሩ ሲያስቡ መሆኑ አሁን አሁን የተረጋገጠ ሀቅ ሆኗል!
የአንዳንድ ተከራዮች ባህሪ አከራዮችን ብቻ ሳይሆን ሌላውን ሥነ ሥርዓት ያለውን ተከራይ ሁሉ የሚረብሽ ነው። አንድ የራሴን ገጠመኝ እንደ ማሳያ ልጠቀም። በአንድ በተከራየሁበት ግቢ ውስጥ የፍሳሽ ቆሻሻ መድፊያ ቱቦ ነበር። በግቢው ውስጥ አጥሩ ሥር ነው መድፊያው። መድፊያው የሽቦ ወንፊት መሰል ነገር ሲሆን ፍሳሽ ነገር ብቻ እንደሚያስተላልፍ ለማንም ግልጽ ነው። ደረቅ ቆሻሻ በፌስታል ወይም ማዳበሪያ አጠራቅሞ ቆሻሻ የሚያነሱ ሠራተኞች በሚመጡ ቀን ነው ጎዳናው ላይ የሚደረግ።
ዳሩ ግን ያንን የሽቦ ወንፊት መሰል የፍሳሽ ብቻ መድፊያ ጠጣር ነገር ይጥሉበት ጀመር። ተረፈ ምግብ፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ፌስታል ሁሉ ሳይቀር ይጣልበታል። በተደጋጋሚ ቢነገር፣ ማሳሰቢያ ቢጻፍበት ችግሩ ሊቀረፍ አልቻለም። በመጨረሻም የሽቦ ወንፊቱ ተቀዳዶ የሚጣልበትን ጠጣር ነገር ማሳለፍ ጀመረ፤ ቱቦውም ተደፈነ። ባለቤቱ ቦታውን በቆርቆሮ ደፍኖ ‹‹ከዚህ በኋላ ወንዝ እየሄዳችሁ ድፉ›› አለ።
እስኪ አሁን እንግዲህ በማን ይፈረዳል? በቀላል ዘዴ መጠቀም እየተቻለ ባልዲ ሙሉ ቆሻሻ ውሃ ተሸክሞ መጓዝ ተጀመረ ማለት ነው። ቶሎ ቶሎ መድፋት ይቻል የነበረበትን አሠራር በማበላሸት ቆሻሻ ውሃ ታቅፎ መቆየት መጣ ማለት ነው። በእንዲህ ዓይነት ሰዎች ምክንያት በነፃነት መኖር ይችሉ የነበሩ አከራዮች በራሳቸው ግቢ መጉላላትና መቸገር ጀመሩ ማለት ነው።
አንዳንድ የተከራይ ድርጊቶችን ሳይ ‹‹እውነት የራሳቸው ቢሆን እንዲህ ያደርጋሉ?›› እላለሁ። በእርግጥ እስከኖሩበት ድረስ የተከራዩበትም የራሳቸው ነው። ግን ግዴለሽነታቸው ሲታይ ደግሞ የራሳቸው ቢሆን እንዲህ አያደርጉትም ብሎ ለመገመት ያስገድዳል።
እንዲህ ነው እንግዲህ በአከራይም በተከራይም ከሰዋዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ ድርጊቶች የሚታዩ። ለተከራይ መብት የጮህነውን ያህል ለአከራዮች ነፃነትም ማሰብ አለብን። ባለቤት ስለሆኑ የተለየ ነፃነትና ከልክ ያለፈ አክብሮት ይኑረን ባይባልም ቢያንስ ግን እየተማረሩ የሚኖሩበትን ድርጊት መፈጸም ልክ አይደለም። ምንም እንኳን አለመሰልጠን እንደ አገር ያለብን ችግር ቢሆንም አከራዮች ግን ግለሰብ ናቸውና ‹‹ምን አገባህ!›› ልንላቸው አንችልም፤ ምክንያቱም ግለሰብ ስለሆኑ የማስወጣት ድርጊት ይፈጽማሉ።
ይህን ያህል ለአከራይ ስቆረቆር አከራይ እመስላለሁ አይደል?(ፌስቡክ ቢሆን የሳቅ ‹‹ኢሞጅ›› በተጠቀምኩ ነበር) ይግረማችሁ አከራይ ዘመድ እንኳን የለኝም። ዳሩ ግን ከላይ የጠቀስኳቸውን ዓይነት ተከራይ አይደለሁም፤ እነዚያን ድርጊቶች የማላደርጋቸው አከራዮቼን በመፍራት ሳይሆን ድርጊቶቹ ራሴን ስለሚረብሹኝ ነው። ቤት ቢኖረኝ የማላደርጋቸውን ነገሮች ስለማላደርግ ነው።
ከብዙ ተከራይ ጓደኞቼ ጋር የምጣላበት ነገር ቢኖር ‹‹ከፍዬ ነው እኮ የምኖር!›› ሲሉኝ ነው። በነፃ የሚኖር ከሆነ በሥነ ሥርዓት ሊኖር፣ ከፍሎ የሚኖር ከሆነ ግን እየረበሸ ሊኖር ማለት ነው? አከራዮቹ እኮ ቢያስወጡት ቀጣዩ ተከራይም ከፍሎ ነው የሚኖር። መከራከሪያው መሆን የነበረበት መብቱ የሆነውን ነገር እንዳይከለከል እንጂ ስለከፈለ ብቻ የትኛውንም ረባሽ ድርጊት ይፈጽማል ማለት አይደለም።
ሥነ ምግባር የሌላቸው ተከራዮች አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንጀቴን ያሽሩኛል። እንዲህ ዓይነት ተከራዮችን የማመሰግናቸው ክብር የማይወድላቸው አከራዮችን ልክ ሲያስገቧቸው ነው። በጣም ተለሳላሽ የሆነውን ተከራይ በውሃ ቀጠነ ምክንያት ቁም ስቅል ሲያሳዩት ይከርማሉ፤ ይባስ ብሎ የተጋነነ ዋጋ ጨምሮ ለማከራየት ያስወጡታል።
ቀጣዩ ተከራይ የሙሉ ጊዜ ሰካራም ይሆናል። ልቀቅ ሲሉት ‹‹ማን ለቃቂ ማን አስለቃቂ እንደሚሆን እናያለን!›› እያለ ይፎክራል። በደረቀ ሌሊት እየመጣ በሩን ይነርተዋል። የሚገርመው ለእንዲህ ዓይነቱ ተከራይ ተሽቆጥቁጠው ነው የሚከፍቱለት። የሚነጫነጩት እንኳን ቤት ገብተው ለብቻቸው ነው። ከፊቱ የመናገር ነፃነት እንኳን የላቸውም። ይህ የሚሆነው ምናልባትም በተለሳላሹ ተከራይ ግፍ ሊሆን ይችላል።
የዛሬው ትዝብቴ ተከራዩ ላይ ብቻ ስለሆነ ወደዚያው ልመለስ። ተከራዮች ቤት ስንፈልግ እኛም እንደ አቅማችን ብዙ መስፈርት እናወጣለን። ለዋና መስመር ቅርብ የሆነ፣ በአካባቢው የሚረብሽ ነገር የሌለበት፣ ከዚያም አለፍ ሲል ተከራይ የማይበዛበት እንመርጣለን። ይህ ሁሉ የሚሆነው ምቾት ፍለጋ ነው፤ ነፃነት ለማግኘት ነው። በዚህ ልክ ለራሳችን ነፃነትና ምቾት ስንፈልግ ለአከራዮች ነፃነትም መታሰብ አለበት።
እውነቱን እንናገር ከተባለ፤ እኛ ተከራዮች እንኳን የማናውቀው ሰው በር ከፍቶ ሲገባ ምቾት አይሰጠንም፤ ነፃነት አይሰጠንም። ስለዚህ አንድ ተከራይ ጫት የሚቅሙ ብዙ ጓደኞችን ይዞ ቢመጣ አከራዮች ደህንነት አይሰማቸውም። ማንም እያንኳኳ ‹‹እገሌን ፈልጌ ነው!›› እያለ ሲገባ ነፃነት አይሰጣቸውም። ምክንያቱም ዘመኑም የማጭበርበርና የዝርፊያ ወንጀሎች የበዙበት ነው።
አንድ ተከራይ በአከራዮቹ ላይ እምነት የሚጣልበት መሆን አለበት፤ ከዚያ በኋላ ሰፊ ነፃነት ነው የሚኖረው። መጀመሪያ በሚረብሹ ነገሮች ከታወቀ ግን በጥርጣሬ ነው የሚያዩት። በአጠቃላይ ለራሳችን ነፃነት እንደምንፈልግ ሁሉ ለአከራዮችም ነፃነት እያሰብን ይሁን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2015