በዛሬው የወጣቶች ዓምዳችን ዓርአያ አድርገን ያቀረብነው ወጣት አሕመድ ደሊል ይባላል። ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ ከሃዋሳ ዩኒቨርስቲ በ2013 ዓ.ም በኬሚካል ኢንጅነሪንግ የማዕረግ ተመራቂ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ በትምህርቱ ጎበዝ ተማሪ የነበረው ይህ ወጣት፤ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ከነጋዴ አባቱ ጋር በመዋሉ የንግድን ጽንሰ-ሃሳብ በሚገባ እንዲገነዘብ ያደረገው መሆኑን ይናገራል።
ወላጅ አባቱ የልጃቸውን የትምህርት ዓለም ጉብዝና ቢያውቁም፤ ወደ ንግድ እንዲገባ እና የእርሳቸውን ሥራ እንዲያግዛቸው ግፊት ያደርጉበት እንደነበረ ይጠቅሳል። በዚህ የተነሳ ምንም እንኳን በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆ እዚያው ዩኒቨርስቲ ውስጥ የማስተማር እድል ቢያገኝም፤ ተቀጥሮ የመሥራት ፍላጎት አልነበረውም። እንደተመረቀ ምንም ጊዜ ሳያባክን የራሱን ሥራ በመፍጠር ለማኅበረሰቡ አስተዋፅዖ ወደ ማበርከት ገባ።
በዩኒቨርስቲ እያለ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የተለያዩ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሠራ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከተለያዩ አትክልቶችን እና ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ወረቀትና መሰል ምርቶችን ማግኘታቸውን ይጠቅሳል። የተማሩበት አካባቢም የእንሰት ምርት በስፋት የሚገኝበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንሰትን በሳይንሳዊ መንገድ በማቀናበር የበለጠ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ጥናት ማካሄዳቸውን ወጣት አሕመድ ያስታውሳል። በተለይ ደግሞ እንሰት ድርቅ የሚቋቋምና ምርቶቹም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ሆነው ሳለ በደቡብ አካባቢ ብቻ መወሰኑና ወደ ሰሜኑ የሀገሪቱ አካባቢ ያልተስፋፋበትን ምክንያት በጥልቀት ማጥናታቸውን ይናገራል።
በሌላ በኩል አሁን ላይ እንሰት አምራች የሆኑ አርሶአደሮች በምርቱ የሚገባውን ያህል ጠቀሜታ እያገኙበት ባለመሆኑ ፊታቸውን ወደ ጫት ምርት ማዞራቸውን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን፤ ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች በርካታ የጤና በረከት ያሉትን ምርት ከገበያ እንዲወጣ ከማድረጉም ባሻገር ጫት ሊያስከትል የሚችለው ማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ጥናት በተሳካ ሁኔታ ማከናወናቸውን ያስረዳል።
ተመርቀው ከወጡ በኋላም በዚሁ ጥናታቸው ገፍተውበት ወደ ትግበራ የገቡት ወጣት አሕመድና ጓደኞቹ፤ በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በቴክኖሎጂና በሳይንስ የዳበረ የእንሰት ምርት ለማግኘት ከ24 ያላነሱ ምርምሮችን ማከናወናቸውን ይጠቅሳል። ከእነዚህም መካከል ከእንሰት ቡላ ለምግብ አገልግሎት የሚውል ‘ስታርች’ የተባለውን ንጥረ ነገር ማውጣት መቻላቸውን አስመልክቶ፤ ይህም ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውለውና ከውጭ ሃገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣውን የስታርች ንጥረ ነገር ለማስቀረት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ያብራራል።
እንደወጣት አሕመድ ገለፃ፤ አሁን ባለው ሁኔታ በሀገሪቱ ከበቆሎ የሚገኘውን የስታርች ዱቄት ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ለጨርቃ ጨርቅ፤ ለወረቀት አምራች ኢንዱስትሪ በተወሰነ መልኩ በግብዓትነት እየዋለ ይገኛል። ይሁንና አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች እያዋሉት ያለው ስታርች የሚመጣው ከቻይና እና ከሕንድ በውጭ ምንዛሪ እየተገዛ ነው። ለምግብ ፍጆታ የሚውለው ስታርች ደግሞ በከፍተኛ ወጪ የሚገኘው ከቱርክና ከሲዊዘርላንድ ነው። በአሁኑ ወቅት ለሕፃናት ምግብ ፍጆታ የሚለው 400 ግራም የበቆሎ ስታርች እስከ 135 ብር በመሸጥ ላይ ነው። በተመሳሳይ ትልልቅ ሆቴሎች ለሾርባ ግብዓትነት የሚጠቀሙትም ስታርች እንዲሁም የፓስታና መኮሮኒ፤ ብስኩት ፣ ጁስና ማልማላታ አምራች ኢንዱስትሪዎች በተመሳሳይ ከውጭ ሃገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚመጡ ናቸው ።
‹‹እኛ ያመረትነው ስታርች ግን የሚገኘው ከቡላ ምርት ሲሆን፤ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚመጣውን የበቆሎ ምርት ስታርችን ሙሉ ለሙሉ ለመተካት ያስችላል›› የሚለው ወጣት አሕመድ ቡላ በተለምዶ ጥቅም ላይ ከሚውልበት መንገድ በተጨማሪ አማራጮችን ማስፋት መቻላቸውን ይናገራል። ከዚህም ባሻገር የቡላውን ሽታ በመጥላት የማይጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ የምርምር ሥራ ማከናወናቸውን ጠቅሶ፤ አሁን ላይ ለሙከራ ያመረቱት የቡላ ስታርች ምንም አይነት ሽታ የሌለው በመሆኑ ከፍተኛ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚል ተስፋ እንዳለው ተናግሯል። ለናሙና ያህል በቡላ ስታርች የሠሩት ኩኪስም በአምራች ኢንዱስትሪዎችና በአከፋፋዮች ዘንድ ተወዳጅነት ማግኘቱን ነው ያመለከተው።
በጥራትም ሆነ ለእይታ የተሻለ ሆኖ የቀረበው ይኸው የቡላ ስታርች፣ ለኮስሞቲክስ ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት ማገልገል የሚችል መሆኑን ይጠቁማል። ከዚህም ባሻገር ‘ግሉተን’ የተባለ ጎጂ ንጥረ ነገር የሌለው በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚል እምነት አለው። የአንጀት ካንሰርና መሰል ከባድ በሽታዎችን ያመጣል ተብሎ የሚነገረው ይህ ‘ግሉተን’ ንጥረ ነገርን በመሸሽ በርካታ የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ከግሉተን ነፃ የሆኑ እንደጤፍ ያሉ ምርቶችን በስፋት የመጠቀም ባሕሉ እየዳበረ ስለመሆኑ ያብራራል። ልክ እንደጤፉ ሁሉ ከግሉተን ንጥረ ነገር ነፃ የሆነውን የእንሰት ምርት በአዓም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ ከተቻለ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ያብራራል።
እንደወጣት አሕመድ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰው የእንሰት ምርት ቋሚ ተመጋቢ እንዳለው ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁንና አሁን ያለውን ምርት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ እስከ 100 ሚሊዮን ሕዝብ መመገብ ይቻላል። በተጨማሪ ዓመቱን ሙሉ ውሃ ባያገኝም እንኳን ከፍተኛ ድርቅ የመቋቋም አቅም ያለው በመሆኑ ለሌሎች ሰብሎች የሚባክነውን ጊዜ፤ ጉልበትና ገንዘብ በመታደግ ረገድም ሚናው የላቀ ነው። እስካሁን ባለው ጊዜ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በሰጣቸው ቦታ ላይ የማምረቻ ሼድ ግንባታ ያጠናቀቁ ሲሆን፤ አስፈላጊ የሚባሉ አብዛኞቹ ግብዓቶችንም አሟልተዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከዚህ ፊት ለቡላ ስታርች ማምረቻ የሚሆን ማሽን ባለመኖሩ ራሳቸው ዲዛይን በማድረግ ማሽን በማሠራት ላይ ይገኛሉ።‹‹የቡላ ስታርችን በማምረት ለሃገራችን ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለመታደግ እየሠራን ነው፤ በአሁኑ ወቅት ለናሙና ያመረትነውን ምርት ለኢትዮጵያ ጥራትና ምዘና ድርጅት ተልኮ የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝቷል፤ በተጨማሪም የጀርመን ኢንተርናሽናል ቴስት ወደ ተባለ ተቋም ልከን ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ነን›› ይላል።
በቅርቡ በስፋት ለማምረት ዝግጅት ላይ ሲሆኑ፤ ከዚህ በፊት ግን ናሙና የሚሆኑ ምርቶችን በማምረት ለደንበኞችና ለአከፋፋይ ድርጅቶች ተደራሽ መደረጋቸውን ያስረዳል። ምርታቸውን ከቀመሱ አካላት በሙሉ ያገኙት አስተያየትና ምላሽ የሚያበረታታ መሆኑን በመጠቆም፤ ኢኮፒያ የተባለ ድርጅት ናሙናውን ካየ በኋላ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳሳያቸው ወጣት አሕመድ አመልክቷል ።
በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው በአነስተኛና ጥቃቅን ደረጃ የተደራጀ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ፤ በቀን እስከ 300 ኪሎ ግራም ለማምረት መዘጋጀቱን ይጠቁማል። ለዚህም እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ብለው ማቀዳቸውን፤ ግን ደግሞ ከዚህ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ብሩ ለማሽን ሥራው የሚፈጅባቸው መሆኑን ያስረዳል። በጅምር ደረጃ ሀዋሳ አካባቢ የሚገኙ የገበሬ ማኅበራትን ጨምሮ 25 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገረው። ‹‹ይሁንና አቅሙን እያሳደገ በመጣ ቁጥር በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአካባቢው ወጣቶች ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል›› ይላል።
እንደወጣት አሕመድ ገለፃ፤ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በስተቀር የትኛውም የመንግሥት አካል ተገቢውን ድጋፍ እያደረገላቸው አይደለም። 0ዩኒቨርስቲው ግን ከማምረቻ ቦታ ባሻገር የመብራትና የውሃ ወጪያቸውን በሙሉ እየሸፈነላቸው ይገኛል። ይሁንና እንደእነሱ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከራሳቸው አልፈው ለሃገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማበርከት የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን በመደገፍ ረገድ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍ በጣም ዝቅተኛ ነው። በተለይ ጥሩ የፕሮጀክት ሃሳብ ይዘው በፋይናንስ እጥረት ሥራ ለመጀመር ለተቸገሩ አካላት በቂ ድጋፍ አለመደረጉ ሀገሪቱም ጭምር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያሳጣት ነው።
‹‹እርግጥ ነው፤ ማንኛውም ወጣት ሥራ ለመፍጠር ሲነሳ ጀምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ያጋጥሙታል፤ ከቤተሰብ ጀምሮ ወዲያውኑ ተቀጥረን ገንዘብ እንድናመጣ እንጂ ወደፊት የተሻለ ደረጃ ይደርሳሉ ብሎ ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ውስን ነው›› ይላል። በተለይ አበዳሪ ተቋማት ፕሮጀክቶቻውን አይተው ብቻ ብድር ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆናቸው በርካታ ወጣቶችን ወደኋላ የጎተተ መሆኑን ያመለክታል። ከዚህም ባሻገር አንድ ጉዳይ ለማስፈፀም በመንግሥት ተቋማት በኩል ያለው ውስብስብና የተጓተተ አሠራር ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን ያነሳል። ‹‹ከእኛ እኩል ሥራ የጀመሩ በርካታ ወጣቶች መንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለውን ቢሮክራሲ በመሰልቸት ሥራ ያቆሙ አሉ›› ሲልም ያክላል።
በሌላ በኩል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቂ እውቀት ይዘው የማይወጡ በመሆኑ፤ በተማሩት ትምህርት ሥራ ለመፍጠር የሚቸገሩ መሆናቸውንም አልሸሸገም። በዚህ ረገድ እሱና ጓደኞቹ በትምህርት ቤት ካገኙት እውቀት ባሻገር በራሳቸው ጥረት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ክህሎታቸውን ማዳበራቸው አሁን ላይ ያላቸውን እውቀት በመጠቀም በድፍረት ሥራ ለመጀመር ያስቻላቸው መሆኑን ያስረዳል። ‹‹እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ግን የምናምንበት ዓላማ ካለ ያሰብንበት ለመድረስ ተቋቁሞ ማለፍ ይጠይቀናል፤ ተግዳሮቶችን ተወጥተን ካለፍነው በኋላ ከምንም በላይ አስደሳች መሆኑ አይቀርም።›› ይላል።
ወጣቶች ላይ የሚታየው ፍርሃት እና በራስ የመተማመን ችግር በመኖሩ የተማሩትን ነገር አውርደው ለመተግበር የሚያዳግታቸው መሆኑን የሚያነሳው ወጣት አሕመድ፤ ግን ደግሞ ያለመሰልቸት በመሞከር ያሰቡትን ዓላማ ማሳካት እንደሚችሉ ይናገራል። ከዚህም በተጨማሪ ከተማሩበት የትምህርት ዘርፍ ውጪ የሆኑ ሥልጠናዎችን በመውሰድ በተለይ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችሉ ክህሎቶችን ለማዳበር የራሳቸውን ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ያስገነዝባል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገረው። ‹‹የአመለካከት ለውጥ እስካላመጣን ድረስ የፈለገውን ያህል ከፍተኛ ውጤት ይዘን ከዩኒቨርሲቲ ብንወጣ ያለምነውን ወደተግባር ማምጣት አንችልም›› ሲል አክሏል።
በመንግሥት እና በፋይናንስ ተቋማት በኩል በተለይ በቅርቡ ልማት ባንክ እንደጀመረው አይነት የብድር አቅርቦት ሊመቻች እንደሚገባ ወጣት አሕመድ ይናገራል። ያሉትን ውስብስብና አታካች አሠራሮች በመቅረፍ ለሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ያሳስባል። በተለይ አሳማኝ የሆነ የሥራ ፕሮጀክት ይዞ ለሚመጣ ወጣት የወለድ መጠኑ ዝቅ ባለ ሁኔታ የብድር አቅርቦት እንዲመቻች በመጠየቅ፤ ከዚህም ባሻገር የሚያመጡት አዳዲስ ሃሳብ ለሌላ አካል ተላልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ያለው የአሠራር ሥርዓት ቢፈጠር የተሻለ እንደሆነ ይናገራል። ‹‹ወጣቶቹ የሚያፈልቁት አዳዲስ እና ችግር ፈቺ ሃሳብ በአዕምራዊ ንብረት በኩል ምዝገባና እውቅና የሚያገኝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት›› በማለትም አስገንዝቧል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ እነሱ ያመጡትና ሥራ ላይ ለማዋል እየተዘጋጁበት ያለው የቡላ ስታርች፤ ከሃገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ መንግሥት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል። በመጨረሻም እንሰት ድርቅ የሚቋቋም የሰብል ዝርያ እንደመሆኑ በተለይ እንደቦረና ባሉ አካባቢዎች ላይ በስፋት ተተክሎ በማኅበረሰቡ የሚለመድበት ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ነው ወጣት አሕመድ የተናገረው።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2015