የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ አገር የሚጫወተውን ሚና ለማጉላት በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ዘንድሮ ዓመት ከመንፈቅ ሆኖታል። አወቃቀሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ፣ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ሥራን ለማቀላጠፍ አግዞታል፤ ለሌሎች ባለድርሻ አካላትም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ከአዲሱ መዋቅር ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1 ሺ 647 ሴቶች በቀጥታ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል። 547 ሺ 927 ሴቶች ደግሞ በገቢ ማስገኛ የሥራ መስኮች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ተችሏል። ከተሰጠው ሰፊ ኃላፊነት አንፃር በዓመት ከመንፈቁ ውስጥ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ያከናወነው ስራ ‹‹አባይን በጭልፋ የመዝገን›› ያህል ቢሆንም በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት በ2014 ዓ.ም 38 ሚሊዮን 738 ሺ 181 የሚሆኑ ወጣቶችን በልዩ ልዩ የስራ መስኮች ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
በተለይ 19 ሚሊዮን 206 ሺ 442 ለሚሆኑ ሴት ወጣቶች በችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይስተጓጎሉ የትምህርት መርጃና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ከማቅረብ ጀምሮ በልዩ ሁኔታ እያበቃ መገኘቱ ትልቅ እምርታ ነው። ይህም ሴት አመራሮችን ማፍራትን ያካትታል።
ከዚህ ባሻገር ግን ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ በዚህ ጊዜ ውስጥ በተለይም በስድስት ወር አፈፃፀሙ ወቅት መዋቅራዊ አደረጃጀቱ እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር አለመውረድና በአዲስ አበባ ጎዳና የሚወጡ ዜጎች ቁጥር መበራከት ከገጠሙት ችግሮች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው። ለቀውስ የሚያጋልጡ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ታቅደው ስለማይመጡ በጀት መፈለጋቸውና ለበጀት ዓመቱ ደግሞ የተያዘው ዕቅድ በሰው ኃይል ስምሪት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርምና ይህንን በቀጣይ በሌላ ዕቅድ ለማካተት እየሰራ ይገኛል። በዚሁና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ እታገኝ አሰፋ የሚከተለውን ማብራሪያ ለአዲስ ዘመን ሰጥተዋል።
ኃላፊዋ እንደሚሉት፤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መላው የሀገሪቱን ዜጎችን እያገለገለ ይገኛል። ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አረጋዊያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ወጣቶችን እንደዚሁም ለተለያየ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብት በማስከበር፤ ሁለንተናዊ ተሳታፊነታቸውን ያረጋግጣል። በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያደርጋል። ከችግሩ ስፋት አኳያም በየዓመቱ በተያዘው ዕቅድ መሰረት እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊና ተጠቃሚና ለማድረግ ብሎም ለመብታቸው ስራዎች እየተሰሩ ነው። አደረጃጀቱም ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ሚናውን ለመወጣት የሚያስችለው ነው።
ኃላፊዋ እንደሚናገሩት፣ አሁን ባለው አደረጃጀት የሴቶችም፣ የወጣቶችም፣ የአካል ጉዳተኞችም ማህበራዊ ጉዳይ ነው የሚባለው። በፊት በነበረው አደረጃጀት ግን የሴቶች፣ የወጣቶችና ህፃናት ዘርፎች ለየብቻቸው ሆነው ነበር ስራቸውን የሚያከናውኑት። ይህም ለአገልግሎት አሰጣጥ አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በአንድ መጠቃለሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለመስራት አስችሏል። ለባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎም ምቹ መደላድልን ፈጥሮላቸዋል። ለሀብት አጠቃቀም ጥሩ ሁኔታ ፈጥሯል። ተጠቃሚውም ከአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሎታል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አሁን ባለው መንገድ ተደራጅቶ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ሆኖታል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። አደረጃጀቱም ለሀብት አጠቃቀምና ሥራን ለማቀላጠፍ አግዞታል። በፌዴራል ደረጃ ማህበራዊ ጉዳይ ፣ ሴቶችና ህፃናትና ወጣቶች በተለያዩ ሚንስቴር ዲኤታዎች ይመራሉ። በዚሁ መሰረት ሴቶች በሴትነታቸውና በወጣትነታቸው ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ይሰራል። የሴት ወጣቶችን ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር በሴትነታቸውና በወጣትነታቸው በኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል። ስራውም በዕቅድ ይከናወናል። ለአብነትም ሴቶች በወጣትነታቸው ተጠቃሚ
እንዲሆኑ ትምህርት ቤት ሲማሩ ለትምህርታቸው አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች ይደረግላቸዋል። ድጋፉም የሚደረገው አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ሲሆን በድርጅቶቹም ሴት ወጣቶቹ እንዳይቸገሩና በችግር ምክንያት ወደ ኋላ እንዳይቀሩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ይቀርብላቸዋል። በተጨማሪም ለሴቶች በተለየ መልኩ የሚያስፈልጉ እንደ የንፅህና መጠበቂያ አይነት ግብአቶች ይቀርቡላቸዋል። ክልሎችም ከሴቶች ጉዳይ ጋር በተያያዘ በዕውቀት እንዲጎለብቱ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል።
ለችግር ተጋላጭ የሆኑና በሴተኛ አዳሪነት የተሰማሩ ወጣት ሴቶችም አሉ። ምንም እንኳን ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በእዚህ ጉዳይ ላይ ባይሰራም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል የክህሎትና የተግባር ስልጠና ይሰጣል። ስልጠና ሰጥቶ በቀጥታ በሥራ ዕድል ፈጠራ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያደረጋቸው ችግረኛ ሴቶችም አሉ። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1 ሺ 647 ሴቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በገቢ ማስገኛ ሥራ መስኮቸ ላይ እንዲሳተፉም ተደርጓል።
ለማሳያም 547 ሺ 927 ሴቶች በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ መሰማራት የሚያስችላቸው ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል። ወደ ሥራ መግባት የሚያስችላቸው ብድርም እንዲመቻችላቸው ተደርጓል። እንዲሁም በየወረዳውና በየክልሉ፣ በከተማ አስተዳደር ደረጃ ያሉ ሴቶች በቁጠባ እንዲሳተፉ ተሰርቷል። ተተኪ አመራሮችን ማፍራት የሴቶች ተጠቃሚነት አንደኛው ስራ እንደመሆኑ ከኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት 1 ሺ 552 ሴቶች በሱሉልታ ማሰልጠኛ የተተኪ አመራርነት ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዳይፈፀምና ጾታዊ ጥቃት እንዳይደርስ ለማድረግም በየክልሉ ከወንድም ከሴትም የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ በ2014 ዓ.ም የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ መረጃ መሰረት አጠቃላይ የሀገሪቱ ወጣት ቁጥር 38 ሚሊዮን 738 ሺ 181 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 19 ሚሊዮን 206 ሺ 442 ያህሉ ወይም 50 ከመቶው ሴት ወጣቶች ናቸው። በፊት በነበረው የወጣቶች ፖሊሲ ወጣት የሚባለው የአድሜ እርከን ከ15 ዓመት እስከ 29 ዓመት ነበር። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር ላይ የፈረመበት የወጣቶች የእድሜ ክልልም ይኸው ነው።
ኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የወጣቶች ፖሊሲን እያሻሻለች ሲሆን በዚሁ ማሻሻያ ወቅት የሚወሰደው የዕድሜ ክልል በአፍሪካ ቻርተር የተቀመጠው ከ15 እስከ 35 ያለው ሲሆን በየመስኩ ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚደረጉት ሴት ወጣቶችም ዕድሜ ክልል ይኸው ነው። በዓመት አንዴ የሚከበረው የዓለም ሴቶች ቀንም እነዚህን ወጣት ሴቶችን ጨምሮ አጠቃላይ የሴቶችን ተሳታፊነት፣ መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።
ብዙዎች በዓሉ ዳቦና ኬክ ከመቁረስና ከፈንጠዝያ ያለፈ ፋይዳ የሌለው ይመስላቸዋል። አደባባይ ወጥቶ ማክበሩም አስፈላጊ አይደለም ብለው የሚያምኑ አሉ። ነገር ግን ሥራው ግንዛቤ የማስጨበጥ የንቅናቄ ስራ በመሆኑ ከቢሮ ወጥቶ መስራትን ይጠይቃል። ሁሉም አካላት መሳተፍ ይኖርባቸዋል። በንቅናቄ ደረጃ በመሰራቱ በዓሉ አሁን ላይ የሁሉም ሆኗል። መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ እንዲሁም ሌሎች አጋር አካላትም በዓሉን ያከብሩታል።
በዓሉ መከበሩና አደባባይ መውጣቱ በሴቶች ላይ የነበረውን የአትችልም አስተሳሰብ አስተካክሏል። ይህን አስተሳሰብ መቀየር በመቻሉም ሴቶች በተለየዩ የኃላፊነት ደረጃዎች እየታዩ መጥተዋል። ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጀምሮ የማይደፈሩ የስልጣን እርከኖችም በሴቶች እየተያዙ ነው። አትችልም የሚለውን አስተሳሰብ በዓሉን ለማክበር በሚደረግ ውይይት፣ በተደረጉ የተለያዩ የተሞክሮ ልውውጦችና በተሰሩ የአደረጃጀት ለውጦች መስበር ተችሏል።
ሴቷ እቤቷ ብትቀመጥ በተደራጀ መልኩ አደባባይ በመውጣት መብቷን ማስከብር አትችልም። በመሆኑም በዓሉ ሴቶች በተደራጀ አግባብ አደባባይ በመውጣት መብታቸውን የማስከበር ትልቅ ግንዛቤ አግኝተውበታል። በመደራጀት መብትን ማስከበር አስፈላጊ እንደሆነም አውቀዋል።
‹‹ከወንዶች ጋር በነበረ አንድ ስብሰባ ያልተደራጀች ሴት መብቷ አይከበርም ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱን የሚያስታውሱት ኃላፊዋ፤ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ መብታቸውን ለማስከብር ሲደራጁ እንጂ ካልተደራጁ ተደራሽ ሊያደርጋቸው እንደማይችልም ያስረዳሉ። ከዚህ አንፃር በዓሉ ሲከበር መደራጀት ምን ያህል ጥቅም እንዳለው
ሴቶቹ መገንዘባቸውን ይጠቅሳሉ። በዚህም መንግስታዊ የሆኑና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በየዓመቱ ለሴቶች የእውቅና መድረክ እያዘጋጁ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። የሚሰሩና አርአያ የሚሆኑ ሴቶችም በዓለም የሴቶች ቀን ብቅ እያሉ መምጣታቸውን ይጠቅሳሉ። ይህም ሌሎችም ሴቶች እነርሱን እንዲከተሉ እየገፋፋ መሆኑንም ይናገራሉ።
በቅርቡ በዓሉ በተከበረበት ሰሞን የዓለም የሴቶች ቀንን አስመልክቶ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የተሰጣትና ተሞክሮዋን ስታካፍል በመገናኛ ብዙሃን ያየናት ሴት ማሳያ ናትም ይላሉ ኃላፊዋ። ይሄ መድረክ ባይመቻች ኖሮ ይህች ሴት በየትኛው መድረክ ነበር ልትወጣ የምትችለው ሲሉም ይገልጻሉ። በተጨማሪም በዚሁ በዓል ታሪክ ሰርተው የነበሩ ሴቶች ተሳትፏቸው እንዲዘከር መደረጉንም ይጠቁማሉ።
እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ስለማይቻል የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወንዶችን በጉዳዩ ማሳተፍ ያስፈልጋል። ምንም እንኳን የሴቶች በዓል ሴቶችን በተለየ ሁኔታ የሚያጎላ ቢሆንም ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን ከማረጋገጥ አንፃር የወንድ አጋርነት የግድ ነው። ያለበለዚያ የሴቶች ተጠቃሚነት በቀላሉ ሊሳካ አይችልም። ሴት ብቻዋን ተሰብስባ እኩል ነኝ፤ እኩልነቴን በራሴ አረጋግጣለሁ ብትል ከወንዶች ተሳትፎ ውጪ አይሆንም።
በማህበራዊውና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ብሎም በስልጠናም ሆነ በሥራ ቦታ ከወንዶች ጋር አብሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ካልተሰራና ወንዶችን የመፍትሄው አካል ማድረግ ካልተቻለ ውጤት ማምጣት አይቻልም። በመሆኑም ለብቻ ተነጥሎ የሚመጣ ለውጥ የለምና በሴቶችም በወንዶችም አስተሳሰብ ላይ እኩል ስራ መሥራት ይገባል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት አፈፃፀሙ ከገጠመው ችግር ውስጥ አንዱ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ ታች እስከ ክልል፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደር አለመውረዱ ነው። በየክልሎች ሴቶችና ህፃናት ፤ወጣቶችና ስፖርት በተናጥል የመደራጀት ችግር ይታያል። በዚህ አሰራር አንድ ክልል ላይ ስብሰባ ለመጥራት አራት ቢሮ መጥራት የግድ ይሆናል። ሪፖርት ለመሰብሰብም ተመሳሳይ ሁኔታ ይጠይቃል። አወቃቀሩ አንድ ወጥ አለመሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ትልቅ ችግርም ፈጥሯል። ይህን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ማስተካከያ እንዲደረግ ለሚመለከተው አካል ሀሳብ ቀርቧል። በዚህም አወቃቀሩ ይስተካከላል፤ ችግሩንም ይፈታል ተብሎ ይታሰባል።
ሁለተኛው ችግር ደግሞ ከጎዳና የሚነሱ ዜጎች ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ሲሆን ከጎዳና አንስቶ ለማስቀመጥ የሚያስችል መጠለያና ማገገሚያ ማእከል አለመኖርም ችግሩን ድርብ አድርጎታል። የተወሰነ መጠለያ ቢኖርም በየጊዜው ጎዳና ከሚወጣው የሕብረተሰብ ክፍል አንጻር የሚመመጣጠን አለመሆኑም ራሱን የቻለ ችግር ሆኗል።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ አማካኝነት ያስጠናውንና በመዲናዋ አዲስ አበባ ከ50 ሺ በላይ ጎዳና የወጡ ዜጎች እንዳሉ የሚያመለክተውን ጥናት መሰረት በማድረግ የመወያያ ጽሑፍ ተዘጋጅቷል። ጽሑፉም ለሚመለከተው አካል ቀርቧል። ፅሁፉ የቀረበበት ዓላማ ዜጎች በየጊዜው ጎዳና የመውጣት ጉዳይ የአንድ መሥሪያ ቤት ወይም ከተማ አስተዳደር ስላልሆነ ሁሉም ኃላፊነት እንዲወስድበት ማድረግ ሲሆን የክልል ፕሬዚዳንቶች በሙሉ ባሉበት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት የመጨረሻ እልባት ይገኝበታል ተብሎ ታስቧል።
‹‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ጌጥ›› እንደሚባለው ሁሉም ሰው በጉዳዩ ላይ ከተረባረበበት ሊቀንስ ይችላል። ትልቁ ነገር ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ነው። ከምንጩ ለማድረቅ አንደኛው መፍትሄ ከተሞችን እኩል ማስፋትና ማበልፀግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ቤተሰብ ላይ መሥራት ነው። ዜጎች ወደ ጎዳና የሚወጡት በተለያየ መንገድ እንደመሆኑ ቤተሰብ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ለፍልሰቱም፤ ለጎዳና ሕይወቱም ምክንያት ስለሆኑ እነሱንም ተረባርቦ መቀነስ መፍትሄ ይሆናል። ለማህበራዊ ቀውስ የሚያጋልጡ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ለመቅረፍ ታቅደው ስለማይመጡ በጀት ይፈልጋል። በበጀት ዓመቱ የተያዘው ዕቅድ ላይም ተፅዕኖ ይፈጥራል። በሰው ኃይል ስምሪት ላይም ችግሮች ስለሚስተዋሉ ችግሮቹን በቀጣይ እቅድ አካቶ መስራት ያስፈልጋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም