ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ጨው በረንዳ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሃሌሉያና አፍሪካ በሚባሉ ትምህርት ቤቶች የተከታተለ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በመድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማረው፡፡ ጎልደን ብሪጅ ከተባለ ኮሌጅ ደግሞ በሊደርሺፕ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ወላጅ አባቱ በመሞታቸው ምክንያት በተለያዩ የኑሮ ውጣ ውረዶች ለማለፍ የተገደደው ይህ ሰው በተለይም ደግሞ ለመማርም ሆነ ቤተሰቡን ለመደጎም ከሚኖርበት ጨው በረንዳ እስከ ስታዲየምና ሌሎችም ራቅ ያሉ ስፍራዎች በእግሩ በመጓዝ ማስቲካና መሰል ሸቀጦችን እያዞረ በመሸጥ በልጅ አቅም የማይቻሉ ፈተናዎችን አልፏል፡፡
ይህ የልጅነቱ ችግር ደግሞ በተለይ አባት የሌላቸውን ልጆችንና ባሎቻቸው ሞተውባቸው ጧሪ ቀባሪ ያጡ እናቶችን ለመርዳት መነሻ እንደሆነው ይናገራል፡፡ እሱ ያለፋቸውን ውጣ ውረዶች ሌሎች ሕፃናት ማለፍ የለባቸውም ሲል በ2004 ዓ.ም የሲር ለና የተባለ የበጎ አድራት ድርጅት ከፈተ፡፡ ይሁንና ብዙም ሳይጓዝ በሀገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ለእስር በመዳረጉ ድርጅቱ ሥራውን አቆመ። ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ እሱን ጨምሮ ሌሎችም የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከወህኒ መለቀቃቸውን ተከትሎ ድርጅቱን ዳግሞ በመክፈት የበጎአድራጎት ሥራውን ቀጥሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ1ሺ200 በላይ ለሚልቁ ቤተሰቦችን የሚደግፈው ይህ ድርጅት፤ ከምግብ አስቤዛ ጀምሮ አልባሳት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የገንዘብ ድጋፎችን ለችግረኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በቋሚነት እየረዳ ይገኛል፡፡ በተለይም በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው የኮቪድ ወረርሽኝና የሰሜን ጦርነት ጋር ተያይዞ በመላ ሃገሪቱ ያደረጋቸው አስተዋፅዖ በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ዘንድሮ ለ1ሺ44ኛ ጊዜ በተካሄደው ከረመዳን ፆም ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ በርካታ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የምግብ አስቤዛ፤ ማስፈጠርና የገንዘብ ድጎማ በማድረግ አለኝታነቱን አረጋግጧል፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣም የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የድርጅቱን መሥራች ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪን የዛሬው የወጣቶች ዓምዳችን እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የበጎአድራጎት ሥራ የጀመርክበትን አጋጣሚ አስታውሰንና ውይይታችንን እንጀምር?
ኡስታዝ ኑሩ፡- የበጎ አድራት ሥራ እንድጀምር ምክንያት የሆኑኝ ምክንያቶች ወይም አጋጣሚዎች ሁለት ሲሆኑ አንደኛው የኖርኩበት አካባቢ በኢኮኖሚ ዝቅ ያለ ማኅበረሰብ የሚገኝበትና የብዙዎችን የእርዳታ እጆች የሚጠብቁ፤ በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እያየሁ በማደጌ እነዚህን ሰዎች የመርዳት ፍላጎት ስላደረብኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል እኔም ብሆን አባቴ በሰባት ዓመት እድሜ ስለሞተብኝ መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶችን እንኳን የሚያሟልኝ አጥቼ በከፍተኛ ችግር ውስጥ በማደጌ ልክ እንደእኔ ሌሎች እንዳይቸገሩ በማሰብ ነው ወደዚህ ሥራ የገባሁት፡፡ በተጨማሪም ሃይማኖቴ ከራስ ይልቅ ለሌሎች መኖር ያስተማረኝና የሚያስገድደኝ በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ድርጅታችን በአዲስ አበባ 11ንዱም ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ጭምር በስፋት ይሠራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዝቅተኛ ኢኮኖሚ ካለው ማኅበረሰብ እንደመውጣትህ የራስህን ገቢ ከማሳደግ ይልቅ የተቸገሩትን ለመደገፍ መነሳት የቻልከው በምን መልኩ ነው?
ኡስታዝ ኑሩ፡- በነገራችን ላይ ከምንም ተነስቶ የበጎ አድራጎት ሥራ መጀመር በራሱ ከባድና ፈታኝ ነው። መስመር እስኪገባና ሰዎች እስኪረዱልሽ ድረስ ሰው ፊት መቆም በራሱ አስጨናቂ ነገር ነው፡፡ እኛ ስንነሳም የያዝነው ካፒታል አልነበረም፤ የእኛ በጀታችን ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ መጥቶ ሥራችንን እንዲያይ በማድረግ በዚያ መነሻ አድርገን በመሥራት ነው እያስፋፋን የመጣነው። በእርግጥ ትዕግስቱ የሌለው ሰው ከመጀመሪያውም ባይጀምረው ይሻላል፡፡ ገንዘብ ማሰባሰቡም ሆነ ለትክክለኛ ችግርተኛ መስጠቱ በራሱ ፈታኝ ነው። አብዛኛውን የወጣትነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት አባት ከሞተባቸው ሕፃናትና በችግር ምክንያት ከተጎሳቆሉና ከተሰበሩ እናቶች ጋር ነው፡፡
በመሠረቱ የሆይታ ሥራ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ድረስ ባልዘለቀ ነበር፡፡ ልክ በኮቪድ ወቅት እንደ ታየው የወጣቱ እንቅስቃሴ ወረት ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ማኅበረሰባችን እየተጋፈጠ ያለው ችግር ከኮቪድም የከፋ በመሆኑ ሥራችን ከአንድ ሰሞን የወረት ሥራ አልፎ በዘላቂነት ወገኖቻችን ከድህነት የሚወጡበት ሁኔታ ለማመቻቸት ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ምክንያቱም ይሄ ሥራ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንጂ፡፡ እለት እለት በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ስንመለከት የበለጠ መሥራት እንዳለብን አምነን ነው የቀጠልነው፡፡
እርግጥ ነው፤ ብዙ ወጣቶች እንዲህ አይነት የበጎ አድራጎት ሥራ ለመጀመር ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ሊኖር እንደሚገባ ነው የሚያምኑት፤ በእኔ እምነት ግን የችግሩን ሁኔታ ተረድቶ ከልብ በመነጨ ሁኔታ ለመርዳት ራዕዩ ከሌለን የተስተካከለ ማኔጅመንት በሌለበት ሁኔታ ብሩንም ብናገኝ ውጤታማ ልንሆን አንችልም፡፡ እኛ የምንሠራው ሥራ የሰዎችን ልብ ነክቶ የተቸገሩትን ሕይወት በዘላቂነት ለመቀየር ነው፡፡ አሁን ከምንረዳቸው 1ሺ 200 ቤተሰቦች ውስጥ 62 በመቶ የሚሆኑት አባቶቻቸው የሞቱባቸው ናቸው፡፡
እነዚህን ሕፃናት ከእለት ቀለባቸው ጀምሮ አልባሳትና ሌሎችንም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን የሚሟሉባቸው ሥርዓት ፈጥረን ነው እየሠራን ያለነው። በአሁኑ ወቅትም ረመዳን ምክንያት በማድረግ 1ሚሊዮን 844 ሺ ብር በማውጣት ለ628 ሕፃናት ልብስ ገዝተንላቸዋል፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ ለፋሲካ በዓል 22 በመቶ ለሚሆኑት ሕፃናት ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገናል። ፈጣሪ ከፈቀደ ከዚህም በላይ ተደራሽ እንሆናለን ብለን እናስባለን፡፡ አሁን ቢሆን ልጆቻችን የተሻለ ቦታ ላይ ባይሆንም እንኳን ጎዳና ከመውጣትና መስኪድ ወይም ቤተክርስቲያን በር ላይ ቆመው ከመለመን ስለታደግናቸው ደስተኞች ነን። የምንሠራውን ሥራ ያዩ ሰዎች ዓላማችንን በመደገፍ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ቤተሰብ በቋሚነት ይደግፉናል። ግን ደግሞ ይህንን ሥራ ለማስቀጠል የማኅበረሰቡ ቀጣይ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ ገቢ የሚያገኘው በምን መንገድ ነው?
ኡስታዝ ኑር፡- እኛ አራት አይነት የገቢ ምንጮች አሉን፡፡ የመጀመሪያው የሙስሊሙ ኅብረተሰብ በረመዳን ከሚያወጣቸው ዘካዎች ገንዘብ ይሰበሰባል። ሁለተኛው ደግሞ ችግረኞችን ስፖንሰር ከሚያደርጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ እንዲሁም ማንኛውም ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ የኅብረተሰብ ክፍል ከ200 ብር ጀምሮ እገዛ የሚያደርግበት ሥርዓት አለ፡፡ በሌላ በኩል ከቴሌ ጋር በመነጋገር “9757” በአጭር የስልክ ቁጥር ገቢ የሚሰበሰብበት መንገድ አለ፡፡ ድርጅቱ በቦርድ የሚመራ ሲሆን 741 የሚሆኑ አባላት አሉት። ከእነዚህ ጋር ደግሞ እድር በማቋቋም እርስበርስ የምንደጋገፍበት ሥርዓት ዘርግተናል፡፡ በመሆኑም ነገ እኔ ባልኖርም ተቋሙ ግን በእነዚህ ዓላማችንን በደገፉ አካላት የሚቀጥል ነው የሚሆነው፡፡
በነገራችን ላይ ድርጅታችን ከድጋፍ ባሻገር ለሥራአጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል በማመቻቸት እንዲሁም እንደ ልብስ ማጠቢያ ማሽንና ማቀዝቀዣ በመግዛት የራሳቸውን ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ 162 የሚሆኑ ሰዎች ከእርዳታ ጠባቂነት የተላቀቁ የሚሆኑ ናቸው፡፡ በተጨማሪም 168 ጉድጓዶችን በመቆፈር በገጠርና በከተማ ያሉ በርካታ የውሃ ችግር ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች መታደግ ችለናል፡፡ ከእነዚህም መካከል በምዕራብ አርሲ፤ ኮፈሌ፤ ወንዶ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የልብስ ባንክ ከፍተን በገጠር ፤ በወህኒ ቤት ያሉ፤ በድርቅና በመሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጋለጡና በከተማ በጎዳና ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልብስ በየጊዜው እናከፋፍላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተረጂዎችን የምትመርጡበት መስፈርት ምንድን ነው?
ኡስታዝ ኑሩ፡- ባሏ የሞተባት ሴት ከፍርድ ቤት የሞግዚትነት ወረቀት ይዛ ስትመጣ አልያም የባሏን መሞት የሚያረጋግጥ የሞት ሰርተፍኬት ካላት እንዲሁም ከቀበሌ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ የማረጋገጫ ደብዳቤ ይዘው ከመጡ እንቀበላቸዋለን፡፡ ከዚህ ውጭ በጣም ችግር ላይ ሆነው መታወቂያ የሌላቸው ሁለት ምስክሮችን አስፈርመው እንዲታገዙ ይደረጋል፡፡ ግን ደግሞ ችግረኛ ነን ስላሉ ብቻ መርዳት አንችልም፤ በመሆኑም በትክክል ችግረኛ መሆናቸውን የሚያጣራ ቡድን አቋቁመን አረጋግጠን እርዳታ የሚያኙበት ሁኔታ ይመቻችላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ በኅብረተሰቡ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል ብለህ ታምናለህ?
ኡስታዝ ኑሩ፡- ድርጅታችን በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ትልልቅ ሥራዎችን ሰርቶ ከቀበሌ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ለአብነት ያህልም ድርጅታችን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ ለተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በመሆን ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ደሴ፤ ሃርቡ፤ ኮምቦልቻ ፤ ደጋን፤ ሐይቅ ከተሞች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አድርገናል። ከኮቪድና ከኑሮ መወደድ ጋር ተያይዞ ችግረኞችን ማዕከል ያደረጉ ትልልቅ ሥራዎችን በመሥራታችን በኅብረተሰቡ ዘንድ ሥራችንም ሆነ ተቋማችን መታወቅ ችሏል፡፡
ድጋፍ የምናደርገውም ለሁሉም ኃይማኖት ተከታዮች ነው፡፡ እምነት፤ዘር የሚባሉ መስፈርቶች የሉንም። የተቸገረን በሙሉ ለመርዳት ነው ፍላጎታችን። ይህ መሆኑ ደግሞ በሁሉም ዘንድ መልካም የሚባል ግንኙነት ለመፍጠር አስችሎናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኅብረተሰቡም ሆነ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ የመንግሥት አመራሮች ድጋፍ እየሰጡን ይገኛሉ፡፡ በነገራችን ላይ ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥራችንን በማየት ብቻ እዚህ ድረስ በመምጣት አባቶቻቸው ከሞቱባቸው ሕፃናት ጋር አሳልፈዋል፡፡ ይህም በአጠቃላይ ሥራችን በኅብረተሰቡ ልብ ውስጥ እያገኘ ያለውን ተቀባይነት ያመላክታል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዘንድሮ የረመዳን ወር ያከናወናቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው?
ኡስታዝ ኑሩ፡- በዚህ የረመዳን ወር በዋናነት አራት አይነት ሥራዎች የሠራን ሲሆን የመጀመሪያው ፆሙ አስር ቀን ሲቀረው በድርጅታችን ውስጥ የታቀፉ ክርስቲያኖች ለሙስሊሞቹ ድጋፍ ሲደረግ እንዳይጓጉ በማሰብ አስቤዛ ሰጥተናቸዋል፡፡ ፆሙ ሊጀመር አንድ ቀን ሲቀረው ደግሞ ለሙስሊም ተረጂዎቻችን በተመሳሳይ የወር አስቤዛ አድርገንላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ማብሰል ለማይችሉ ፆመኞች በየቀኑ ለ400 ሰዎች የተዘጋጁ ምግቦችን ከውሃ ጋር ስናድል ነው የቆየነው፡፡ 628 አባታቸው የሞቱባቸው እንዲሁም አባት እያላቸው ከእጅ ወደአፍ የሆነ ኑሮ የሚኖሩ ልጆችን የኢድ ልብስ ገዝተንላቸዋል፡፡ ለዚህም 1ሚሊዮን 664 ሺ ብር ነው ወጪ ያደረግነው። ከዚህ በተጨማሪ በኢድ ዋዜማ ማንኛውም ሰው በበዓሉ ከፍቶት እንዳይውል የተለያዩ ስጦታዎች እንዲሰጥ ነው የተደረገው፡፡ በተመሳሳይ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለፋሲካ ዋዜማ አስቤዛ ለሁለተኛ ጊዜ ሰጥተናቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣው የጎዳና ላይ የኢፍጣር ሥርዓት ሰዎችን ከመመገብ ባለፈ ምን ፋይዳ አለው ብለህ ታምናለህ?
ኡስታዝ ኑሩ፡- በእኛ ሃገር አዲስ ልምድ ይሁን እንጂ በጎረቤታችን ሱዳን የቆየ ተግባር ነው፡፡ ባልና ሚስት ብቻቸውን ሳይሆን የሚያፈጥሩት ጎዳና ላይ በመውጣት ከተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ነው፡፡ ይህም አንዱ ለሌላው በማካፈል ፍቅርንና መተሳሰብን ለመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ወንድማማችነታችንም የምናጠናክርበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ማካፈልና መደጋገፍ የእኛ የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ይህንን ባሕል ማስፋፋቱና ማስቀጠሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዘንድሮ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ደግሞ ለየት ባለ መልኩ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ፤ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የልብስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ይህ ልምድ መጠናከር አለበት ብዬ አምናለሁ፤ ለመደገፍ ግን የግድ አደባባይ ላይ መውጣት አይጠበቅንም በቤታችንም ጭምር የተቸገሩትን በመጋበዝ አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል፡፡
ከዚህ ባሻገር በተለያዩ የእምነት ተከታዮች መካከል ያለውን የመቻቻልና የመከባበር እሴት እንዲቀጥል ብሎም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በሃገሩ ላይ የእኔነት ስሜት ተሰምቶት ከሌሎች ወገኖቹ ተቀራርቦ ለልማት እንዲሠራ፤ እንዲተባበር መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ በነገራችን ላይ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን በሚገባ ቢወጡ ኖሮ በዚህ ትውልድ ላይ ብዙ ነገር መሥራት በቻሉ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእምነት አባቶች በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ በመሆኑ ስርነቀል የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስችላል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ፉክክራችን ደሃ በማዳን ቢሆን ኖሮ የት በደረስን ነበር። ደረቅ ስብከት ከመስበክ ይልቅ በተግባር አርአያ መሆን ቢችሉ የሕዝቡን ቀልብ ሊይዙ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለወጣቶች የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህ?
ኡስታዝ ኑሩ፡- ወጣቱ የበጎ ሥራ መሪ ተዋናይ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ደግሞ የመንግሥት እገዛ ይፈልጋል። ከሁሉ በላይ ግን ቤተእምነቶቻችን ወጣቱ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወጣቱ ከራሱ አልፎ ለወገን አለኝታ ከማድረግ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን በሚገባ ተወጥተዋል ብዬ አላምንም። በአንድ ጁምአና የሰንበት ቀን ብቻ ትልቅ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ወጣቱን በሚያገኙበት አጋጣሚ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ከልባቸው ሊሠሩ ይገባል፡፡ ወጣቱን በትክክለኛ መንገድ ካስተማሩት አይደለም ገንዘቡን ሕይወቱን ይሰጣል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ በየእምነት ተቋሙ የተጎሳቆሉ ወገኖችን እያዩ ከንፈር መምጠጥ ሃገር አይለውጥም፤ ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚረዱበትና ከድህነት የሚወጡበት መንገድ የእምነት ተቋማቱ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻለ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት አይቻልም፤ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ከተጠያቂነት አናመልጥም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ኡስታዝ ኑሩ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም