አዲስ አበባ፡- የተዛባ የፖለቲካ አስተሳሰብንና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን በመፍታት የወጣቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። በ70/30 የቤት ግንባታ ለ210 ሺህ የመዲናዋ ወጣቶች የስራ እድል በቅርቡ ይፈጠራል ተብሏል።
‹‹ምክንያታዊ ወጣት ለአዲስ አበባ ብልፅግና›› በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የነበረው የወጣቶች ውይይት በትናንትናው ዕለት ሲጠቃለል ከንቲባ አዳነች፤ በሰላም፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካ ጉዳዮችና በስራ እድል ፈጠራ ከወጣቶች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የተዛባ የፖለቲካ አስተሳስብና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን በየደረጃው በመፍታት ወጣቶች በሁሉ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል። ከንቲባዋ አክለውም ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን በሁሉም ዘርፍ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግና ለውጡን ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመዲናዋ ለሚኖሩ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፤ በ70/30 የቤት ግንባታ ለ210 ሺህ የመዲናዋ ወጣቶች የስራ እድል በቅርቡ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በመዲናዋ በስራ እድል ፈጠራ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ኮሚቴ በማዋቀር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ወጣቱ ምክንያታዊ ሆኖ የመጣውን ለውጥ በማስቀጠልና ጠንክሮ በመስራት ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚ እድገት በመደገፍ የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለትውልድ ማስተላለፍ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፤ በተለያየ ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስትሮች የኢቨስትመንት ቦታና መሰረተ ልማት በማሟላት ለወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጥሩ እየተሰራ ነው ብለዋል፡ በተጨማሪም የስራ እድል ተፈጥሮላቸው በተለያየ የስራ ዘርፍ ተሰማርተው ባሉ ወጣቶች ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ወጣቱ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በስራ እድል ፈጠራ ያነሳቸውን ችግሮች በመፍታት ለውጡን ለማስቀጠልና ወጣቱን በሁሉ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተማ አስተዳድሩ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፤ መንግስት በአስተዳደር መዋቅር ለወጣቶች ሰፊ እድል በመስጠት ወጣቱን በፖለቲካው ዘርፍና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።
ታደሠ ብናልፈውና ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም