አዲስ አበባ፡– ለጋ ወጣቶች የአልኮል መጠጥ ተፅዕኖ ውስጥ እንዳይወድቁ ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ነድፎ እየሠራ መሆኑን ዲያጆ ሜታ የመጠጥ አምራች ኩባንያ አስታወቀ።
ዲያጆ ሜታ የመጠጥ አምራች ኩባንያ ከ ”ኩልንግውድ ለርኒንግ” ጋር በመተባበር ፕሮግራሙን በአዲስ አበባ በሚገኙ 22 ትምህርት ቤቶችም ውስጥ እየሠራ መሆኑና በዚህም ከ15 ሺ በላይ ተማሪዎችን መድረስ መቻሉን ገልጿል።ፕሮግራሙ ስማሽድ ተብሎ የተሰየመና በኢትዮጵያም ውስጥ ጥረት ለህይወት ኢትዮጵያ ተብሎ በሚጠራ ተቋም አማካይነት እየተተገበረ መሆኑም ተጠቅሷል።
የጥረት ለህይወት ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ አለማየሁ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት ፕሮግራሙ ወጣቶችን ከአልኮል ጉዳቶች በመጠበቅ ጥሩ ውጤት እያስመዘገ ነው።አልኮል በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶችን የአዕምሯዊ እንዲሁም አካላዊ ጉዳት ሊያደርስ ከመቻሉም በላይ ተማሪዎች በትምህርት፣በቤተሰባዊ እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እንዳለውም አክለዋል።
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ከፍተኛ ኤክስፐርት ወይዘሮ ፍሬህይወት አሰፋ በበኩላቸው ድርጅቶቹ ይህንን ፕሮግራም ቀርጸው መሥራታቸውን አድንቀው ቢሮውም ተባባሪ በመሆን በለጋ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች የአልኮል ሱሰኛና ጉዳተኛ እንዳይሆኑ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ባለሙያዋ እንዳሉት ትምህርት ቢሮ በተለይ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት አሰጣጥን ዳግም በመፈተሸ ጤነኛ እና ብቁ ትውልድን ለማፍራት በአትኩሮት እንደሚሠራም ጠቅሰዋል።የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ስቴፈን ኔሬነስቴይን “የስማሽ” ፕሮግራም በተማሪዎች ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።የቲያትር ተውኔቶቹ ተማሪዎች በአልኮል መጠጦች ላይ ያላቸው አስተሳሰብና ባህሪ ዙሪያ መልካም ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ የሚገኝ ሲሆን ይሄም ተማሪዎች በፕሮግራሙ ሂደት በሚሰጡት ግብረ መልስ መረዳት መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም ተማሪዎች በራስ መተማመናቸው እንዲያድግና በአቻዎቻቸው ተገፋፍተው ለአልኮል መጠጥ እንዳይዳረጉ ከማድረጉም በተጨማሪ ፕሮግራሙ የተተገበረባቸው ትምህርት ቤቶች በራሳቸው የአልኮል መጠጦች ጉዳትን ለተማሪዎቻቸው የሚያስተምሩበት አቅም መገንባት መቻቸውን ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
አብርሃም ተወልደ