ሀገር ከምትታፈርባቸው ሁነቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የጠንካራ መከላከያ ሠራዊት መኖር ቀዳሚው ነው። የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ሉዓላዊነት በሚመለከት ከሰሞኑ የክልል ልዩ ኃይሎች በመደበኛ የሠራዊት አደረጃጀት ውስጥ እንዲካተቱ የሚያደርግ የትግበራ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል።
በዚህም መሠረት ከመንግሥት በኩል የተለያዩ መግለጫዎች ወጥተዋል። በክልሎች በ“ልዩ ኃይል” ስያሜ የተደራጁ ኃይሎች ወደ ተለያዩና መደበኛ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያትና ዓላማ የሀገርን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አንጻር መሆኑ መተማመን ላይ ተደርሷል። ከዚህ በዘለለም የሠራዊትን ቁመና ከማጠናከር አኳያ የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅ እንደሆነ የተለያዩ የፌደራል እና የክልል ተቋማት ባለስልጣናት መግለጫዎች ጠቁመዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት ሕገ መንግሥቱ እውቅና ያልሰጠው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሲነሱ የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎችንም ለመመለስ እንደሆነ ፤የልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች መግባት ሀገርን አንድ ከማድረግና ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ አንጻር የላቀ ዋጋ እንደሚኖረው ተገልጿል። የክልሎችን ልዩ ኃይሎች ሁኔታ፣ ወደ መደበኛው የመዋሓዱን አካሄድ፣ ዓላማና ትግበራውን አስመልክቶ ከመንግሥት በኩል ተከታታይ መግለጫ ወጥቷል፤ ከዚህ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መግለጫ አንዱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመግለጫቸው “ለጋራ ጥቅም ሲባል የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅር ይገባሉ። ከዚህ በኋላ ክልሎች የፖሊስ ኃይላቸውን አጠናክረው ወንጀልን በመከላከልና የአካባቢ ፀጥታን በማስከበር ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ከየትኛውም ኃይል የሚሰነዘር፣ የሀገርን ድንበር ሕልውናና ሉዓላዊነት የሚዳፈር ኃይል ሲነሳ ደግሞ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ ይወስዳል። ለዚህ የሚሆን አደረጃጀትም በተግባር ላይ ውሏል” ማለታቸው ይታወሳል።
“የክልሎች ፉክክርና ውድድር በልዩ ኃይል ግንባታ ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ልማትና በዲሞክራሲ እሳቤ ላይ ይሆናል” ያሉ ሲሆን “የሚመለከታቸው ተቋማትና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ የውሳኔውን ሀገራዊ ፋይዳና የሚያስገኘውን ዘላቂ ጥቅም ከግምት በማስገባት ለተግባራዊነቱ ርብርብ” እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈው እንደነበር አይዘነጋም።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ጄነራል አበባው ታደሰ ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅልን የምንፈልገው በሀገሪቱ የፀጥታ ኃይል እንዲገነባ ሕገመንግሥቱ የሚፈቅደው መከላከያ ሠራዊትን፣ ፌደራል ፖሊስን እና ለክልል መደበኛ ፖሊስ ነው” ሲል ተናግረዋል።
የክልል ልዩ ኃይሎች የክልል ፀጥታን ይጠብቁ ነበር። ከመከላከያ ጋር በመሆን ሕይወታቸውን ገብረዋል፤ ቆስለዋል፣ ደምተዋል። ይህም ሆኖ ግን ከሕገመንግሥት አንጻር ሕጋዊ አይደሉም።“ከዚህ በዘለለ የልዩ ኃይል መዋቅር ብሔር ተኮር ነው። ስር የሰደደውንና ሀገር አቀፍ የሆነውን አብሮነት ይሸረሽረዋል” ሲሉም ስለ ክልል ልዩ ኃይል ሁኔታ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ የጄኔራሉ ማብራሪያም ልዩ ኃይልን በተመለከተ የሚነሱ አንዳንድ የሕዝብ ጥያቄዎች እግረመንገዳቸውን ምላሽ አግኝተዋል።
አፈጻጸሙን በተመለከተ ሁሉንም እኩል ከማደራጀት ጎን ለጎን በጥንቃቄም እንደሚሠራ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። “አንደኛው ክልል ልዩ ኃይል እንዲኖረው ሌላኛው ክልል ልዩ ኃይል እንዳይኖረው አናደርግም። ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ አይታሰብም” ሲሉ በቀላል ቋንቋ ብዥታችንን አጥርተውልናል።
ስለትግራይ ክልል የትጥቅ አፈታት ያነሱ ሲሆን እንደማንኛውም ክልል መደበኛ ፖሊስ ብቻ እንደሚኖረው በመግለጽ ሀገር ለመገንባት ያለን አማራጭ ሕገመንግሥቱን በተከተለ አሠራር የመከላከያ ሠራዊት መገንባት ብቻ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
የክልል ልዩ ኃይል ኢትዮጵያዊነትን አደብዝዞ አንድን ብሔር ብቻ ያገነነ ለኦሮሞ እሞታለሁ፣ ለአማራ እንዲህ እሆናለሁ በሚል የተያዘ ነው ያሉት ጄኔራሉ፣ እንዲህ ከመሰለው እኔነት ለመውጣት ሁሉን ያማከለ ኅብረ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት መገንባት ቀዳሚው ይሆናል ሲሉ በስፋት አብራርተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ተመሳሳይ መግለጫ ፤ በሀገሪቱ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት እንደሌለ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “የክልል ልዩ ኃይሎች እንደገና በመደራጀታቸው ኅብረ ብሔራዊ የሆነ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም ይገነባል” ብለዋል ፣ ልዩ ኃይል አደረጃጀት በክልሎች መካከል በስጋት መተያየትን ሊያስከትል እንደሚችል በመጠቆም ፤ ይህንን ችግር ለመፍታት መፍትሔው በአዲስ አደረጃጀት ወደ ሕገመንግሥታዊነት ማምጣትን እንደሆነም ጠቁመዋል።
የክልል ልዩ ኃይልን በሚመለከት ሁሉንም የመንግሥት መግለጫዎች ብናስተውል አንድ ዓይነት ይዘት ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። የሁሉም ዓላማና ተልዕኮ ጠንካራ ሀገርና ሕዝብ ከመፍጠር አኳያ የሚታዩ ናቸው። አሁን ባለው የፀጥታ ሁኔታና የሀገር ስጋት “የክልል ልዩ ኃይል” የሚለውን ከፋፋይ እሳቤ ትተን መከላከያ ሠራዊትን አጠንክሮ በሁሉም ረገድ ምላሽ የሚሰጥ የጦር ሠራዊት መገንባት ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም ነው።
እንደ ሕዝብ የምንጠይቀው ጥያቄ ይኖራል። ካለው ነባራዊ ሁኔታ “ለሀገራችን ምንድነው የሚጠቅማት?” ብለን ስንጠይቅ ሁለት መልሶችን እናገኛለን። የመጀመሪያው የተጠናከረ መከላከያ ሠራዊት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከመከላከያ ጎን የቆመ ሕዝብና በፌደራል ደረጃ በተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የታቀፈ ኃይል የሚሉት ናቸው።
እነዚህን ሁለት እውነቶች ማረፊያቸው ሀገርና ሉዓላዊነት ነው። መከላከያ ሠራዊት ጠንክሮና በልጽጎ አስተማማኝ ደጀን እንዲሆን የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያየ የፀጥታ ተቋም መውረድ ቀዳሚው መስፈርት ነው። ቀጣዩ መስፈርት ወደ ሕዝብ የሚወርድ ነው።
በሀገር ፍቅርና በኅብረብሔራዊ አንድነት ከተገነባው ሠራዊት ጎን በመቆም ሕዝብ አለኝታነቱን ማሳየት ለሀገር ሉዓላዊነት የሚከፈል የዜግነት እዳ ሆኖ ወደ እያንዳንዳችን ይመጣል። ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት፣ መከላከያ ሠራዊት ለሀገር በሚል ቁርኝት ውስጥ ነው የምንፈልገው ነጻነትና ሉዓላዊነት የሚመጣው።
ከእውነታው የራቁ አንዳንድ የሚናፈሱ ወሬዎች አይጠፉም። ከእውነት ጎን ውሸት ሁሌም አለ። እውነቱ ከታማኝ ልቦች የፈለቀ ሀገርና ሕዝብን አንድ የሚያደርግ ሲሆን ውሸቱ ደግሞ የሀገርን አንድነትና እድገት ከማይፈልጉ ኃይሎች የመነጨ እንደሆነ ትርክቱ በራሱ ይናገራል።
የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ የተፈጠረው ውዥንብርም መነሻው ይሄን መሰሉ ሁለት አይነት መልክ የፈጠረው ነው። ኃላፊነት እንዳለበት አንድ አካል መንግሥት እውነቱን ለሕዝብ በማሳወቅ ላይ ይገኛል። ሕዝብ የወሬኞችን አሉባልታ ትቶ በሚበጀውና ለሀገርን በሚጠቅመው እውነት ላይ በንቃት ሲሳተፍ ነው የጋራ ትሩፋት የሚሰጠን።
ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ የልዩ ኃይልን መልሶ ማደራጀትን በተመለከተ ቀደም ብሎ የወጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መግለጫ ይሄን የወሬኞች አሉባልታ የነካ ነበር። “ከጊዜያዊ መፍትሔ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም” ሲል የተነሳው የጠቅላዩ መግለጫ “ሳይገባቸው የሚቃወሙትን ለማስረዳትና ለማሳመን ጥረት እናደርጋለን፣ ሆን ብለው የአፍራሽነት ሚና በሚጫወቱት ላይ ደግሞ ተገቢውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እንወስዳለን” ብለው ነበር።
ከዚህ እውነት በመነሳት ውዥንብር ፈጣሪዎች ወደ እውነቱ እንዲመጡ መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ከዚህ ባለፈ ተደናብረው ሰው የሚያደናብሩ የክፋት ወዳጆች እነሱ ስለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ተጠያቂ እንዲሆኑ መሥራት ሁለተኛው ኃላፊነታችን ነው።
አንድነት አስፈሪነት እንደሆነ የገባንን ያክል ምንም ነገር ገብቶናል አንልም። በአንድነት ተራምደን ነው ዛሬ ላይ የምንኮራባቸውን ሀገራዊ ድሎች ያስመዘገብነው። አሁንም በተሻለ ሀሳብ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር የተሻለ የመከላከያ አደረጃጀት ያስፈልገናል።
የትግበራ አቅጣጫው ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በላቀ የተሻለች ለማድረግ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ቢሆንም፤ ከዚህ በተጓዳኝ ሠራዊቱን በኢኮኖሚ፣ በትጥቅ፣ በስነልቦናና በመሳሰሉት አቅም ለመፍጠርም እንደሆነ ተጠቁሟል። የትግበራ አደረጃጀቱ ማረፊያው ሀገርና ሉዓላዊነት ነው።
ሉዓላዊነታችን ያለው አንድነታችን በመሠረተው መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ነው። እንደ ሀገር ደክመን እንደ ክልል ብንበረታ ፋይዳ የለውም። ክልል እኔነት ነው። ሀገር ግን የአንድነትና የኅብረብሔራዊነት ጥብቆ ናት። ያማርነው በልካችን የተሠራውን “ሀገር” የሚሉትን ቡሉኮ ለብሰን ነው።
አንድነታችን ሀገር ካልሰጠን፣ ወንድማማችነታችን ሕዝብ ካላደረገን “ኢትዮጵያዊ” የሚለው ቅፅል የሚገባን አይሆንም። አንድነት ጠንስሶ የጠመቀው ሁላችንም የምንጎነጨው የጋራ ማዕድ ያስፈልገናል። ልክ ሀገር ለመሥራት ከዚህም ከዛም እንደተዋጣው መከላከያ ሠራዊት፣ ከዚህም ከዛም እንደተሰባሰቡት ልዩ ኃይሎች ጠንካራ ማንነት ያሻናል።
እንደሀገር ዓላማችንን ለማስፈጸም ሁላችንንም የሚያግባባ አንድ የሆነ እውነት ያስፈልገናል። የተነሳሁበት መነሻ ጽሑፍ ለሀገርና ሕዝብ ሉዓላዊነት በመንግሥት የታመነ፣ በብዙ ጥናት የተፈተሸ እውነት ነው። ይሄን ለማረጋገጥ ደግሞ የትግበራው አዋጅ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ያለውን፣ የመንግሥትን መግለጫም ሆነ የአገር ወዳድ ዜጎችን አስተያየት ማየቱ ብቻ በቂ ነው።
ልክ እንደመንግሥት ሁሉ ሕዝብም ሊያምንበት ይገባል። ማመን ብቻ አይደለም ለትግበራውም ይሁንታውን ማሳየት ይጠበቅበታል። በአንድ ሀገር ላይ መንግሥትና ሕዝብን አንድ የሚያደርጉ እንጂ የሚያከራክሩና ረብሻ የሚፈጠሩ ሀሳቦች ሩቅ አይወስዱንም።
የክልል ልዩ ኃይሎች ጉዳይ የጋራ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን የትግበራ ሂደቱ ከመንግሥት በኩል ቢመጣም አስፈጻሚው የሕዝብ (ሕዝባዊ) ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጉዳዩ የጋራ ጉዳያችን ስለሆነ ነው። የክልል ልዩ ኃይሎች ከነትጥቃቸው መከላከያን ሲቀላቀሉ፣ በፌደራል ፖሊስ እና በክልል ፖሊስነት ሲሠሩ ወንጀልን ከመከላከልና ጸጥታን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን አስተማማኝ ሰላም እየፈጠርን ነው ማለት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ከውጪ ሆነው ለሚያዩን ተንኳሽ ሀገራትም ማንነታችንን ለማሳየት ጥሩ ዕድል ይሰጠናል።
ከዚህ ረገድ ያለን ምርጫ አንድ ብቻ ሲሆን፤ እሱም በተቀመጠው የመንግሥት አቅጣጫ የልዩ ኃይል አባላት እንደየፍላጎታቸው ወደሚፈልጉት የጸጥታ ተቋም በመቀላቀል የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ማስቻል፤ እንዲሁም፣ ጠንካራ ሠራዊት በመገንባት ጠንካራዋን ኢትዮጵያ ለዓለም ማስተዋወቅ ነው።
ይሄን አደረጃጀት በብዙ መንገድ ልናየው እንችላለን። ሕገመንግሥትን የመጠበቁ ተግባር እንዳለ ሆኖ በክልል ልዩ ኃይል በኩል ክፍፍል ያበጀውን ኢትዮጵያዊነት ወደ አንድ መመለስ አንዱ ሲሆን፣ ከዚህ በተጓዳኝ አስፈሪና የተጠናከረ መከላከያ ሠራዊት በመገንባት ከየትኛውም ወገን የሚሰነዘርብንን ጥቃት መመከት መቻል ሌላው በረከቱ ነው።
ከዚህ ውጪ ሌሎች ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠነክሩ፣ እንደ ኅብረትና ወንድማማችነት አይነት፣ አንድነትና ሰላም የሚያመጡ በረከቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው፣ በፌደራል ደረጃ መሰባሰቡና ውሕደቱ በኢኮኖሚ ረገድም የላቀ አበርክቶ እንዳለው በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል። ከዚህ ባለፈ በታደሰና በጎለበተ የጦር ኃይል አቅም ራሳችንን ለተቀረው ዓለም የምናስተዋውቅበት መድረክም መሆን ይችላል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም