የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጀርመን አገር በህክምና ሲረዱ ቆይተው ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት አገራቸውን በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ ከፕሬዚዳንትነት ከወረዱ በኋላ በ1997 ዓ.ም በተደረገው አገራዊ ምርጫ በደንቢ ዶሎ በግል ተወዳድረው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ነበሩ፡፡ ዶክተር ነጋሶ በጀርመን ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው እዚያው ያረፉ ሲሆን፣ አስክሬናቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ስርዓተ ቀብራቸው እንደሚፈፀም ይጠበቃል፡፡
የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው የገለፁ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ ብሔራዊ ኮሚቴ የሚቋቋም ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮችን በየጊዜዉ እንደሚገለፅ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ባወጣው የሀዘን መግለጫ ጠቅሷል፡፡
የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባወጡት መግለጫ፤ ሀገራቸውን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉትን ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ አለም በሞት መለየት አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ነጋሶ በዘመናቸው ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በታማኝነት እና በቅንነት ያገለገሉ ባለውለታ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈት አስመልክቶ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የፌደራል መስሪያ ቤቶች የሀዘን መግለጫ አውጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈት አስመልክቶ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም