አዲስ አበባ፡- የክርስትና እምነቱ ተከታዮች የትንሳኤ በዓል ሲያከብሩ ከጥላቻና ግጭት በመራቅ ፣ለሰላም፣ ሀገር አንድነት በጋራ ለመስራት በማሰብ፣የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ መሆን እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የትንሳኤን በዓል አስመልክቶ በአስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ በገጠርና በከተማ፣ በውጭ ሀገር የሀገር ዳር ድንበር ለማስከበር ለቆሙ፣ በህመም ምክንያት በፀበልና በህክምና ላይ ለሚገኙ፣ በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች በሙሉ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።
ፓትርያርኩ እንዳሉት፤ የጌታ በዓለ ስቅለትና በዓለ ትንሳኤ የሚያስተምረው በመንፈሳዊ ሕግ ሁሉን ድል ማድረግ እንደሚቻል ነው። የሰው መደበኛ ጠላት ሕግን መጣስ ነው። ሕግ ከተጣሰ ኃጥያት ይመጣል። ኃጥያት ከመጣ ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየት ይመጣል። ስለሆነም ከበዓለ ስቅለቱ ትልቅ ትምህርት ወስደን ሰብዓዊና መንፈሳዊ ሞራላችንን በሕግ፣ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በሰላምና በዕምነት በመገንባት ከዕርስ በርስ ግጭት መራቅ ይኖርብናል ።
ሀገርን ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅና የበለፀገች ሀገርን ለመፍጠር ዛሬ የሀገራችን ወቅታዊና አንገብጋቢ ነገሮች ሆነው የሚታዩትን የጭፍን ጥላቻ፣ ራስ ወዳድነት፣ ለኔ ብቻ ይድላኝ ባይነት፣ በጥርጣሬ ዓይን መተያየት፣ አለመተማመን፣ መጨካከን፣ አንዱ ለሌላው ስጋት መሆንን ሙሉ ለሙሉ ከጭንቅላታችን ማስወጣት ስንችል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የተራቡና የተጠሙ ወገኖቻችንን ካለን በማካፈል አብረው በልተው፣ ጠጥተውና ተደስተው እንዲውሉ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ግዴታ መሆኑን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፍኤል በበኩላቸው፣ መልካም ክርስቲያን ክፋትን አሸንፎ መልካም ሥራ የሚሠራ ነው ብለዋል። ‹‹እግዚአብሄር ሞቶ ያዳነውን ህዝብ ማፈናቀል ከእምነት ውጪ የሆነ ነገር ነው።
የሁሉም እምነት እንደሚያስተምረው ከፈጣሪ ቀጥሎ ሰውን ሁሉ እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚለውን መሪ ቃል በመከተል እርስ በርሳችን ይቅር ተባብለን ካልተዋደድንና ካልተዛዘንን የትንሳኤው ክብር ዋጋ ያጣል›› በማለት ምክራቸውን ሰጥተዋል።
የትንሳኤ በአል ስናከብር ልክ እንደቀደምት ክርስቲያኖች ሁሉ በተለይም በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ተፈናቅለው ላሉ ወገኖቻችን፣ ለችግረኞች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ረዳትና አስታዋሽ ላጡ ያለንን በመስጠትና በማካፈል መሆን አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ፣ “ጥል ክርክርን ታነሳለች፣ ፍቅር ግን ሃጢያትን ሁሉ ትከድናለች”፤ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ በሆነችው ሀገራችን ብዘሃነትንና ልዩነትን እንደ ውበታችን ጸጋ ተቀብለን በሰላም፣ በመከባበር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፈሪሀ እግዚአብሄር አብሮ ለመኖር መትጋት ይገባል ብለዋል።
ይህን በዓል በምናከብርበት ወቅት ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነት እያሰብን፣ኑሮ የከበዳቸውን ወገኖች በተለይም ወላጅ ዘመድ የሌላቸውን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አዛውንቶችንና ህመምተኞችን በማገዝና በመደገፍ ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ እንደገለጹት ፣ ከክርስቶስ ሕመማትም ሆነ ስቅለት እውነተኛ ፍቅርን አስመልክቶ በርካታ ቁም ነገሮችን መቅሰም እንችላለን፡፡እነዚህ ቁም ነገሮች በግልም ሆነ በአገር ደረጃ በብዙ ይጠቅሙናል።“
በአሁኑ ጊዜ እንደ አገር ብርቱ ተስፋና ስጋት ከፊታችን ተደቅኗል” ያሉት ፓስተር ጻድቁ፣ ተስፋዎቻችን በሥራ የምንደርስባቸው ሲሆኑ፣ ስጋቶቻችንን ግን ወደ መልካም ተስፋ የምንለውጠው እርስ በእርሳችን በመደማመጥ፣ በመፈቃቀድና አንዱ የአንዱን በደል ባለመቁጠር መሆኑን ተናግረዋል።
“ቂምና በቀል ሁሌም ጥፋትን እንጅ ሰላምን አያመጣም፡፡በቀለኛውም ተበቃዩም አብረው የሚወድቁበትን ገደል እንጂ ተደጋግፈው ከማጥ የሚወጡበትን አቅጣጫ አያመላክትም” ያሉት ፓስተር ጻድቁ፣ በትንሳኤው ዕለትም ሆነ በሌሎች ቀናት ድሆችን እንድናስብ፣ ህሙማንን እንጎበኝ፣ አቅመ ደካሞችን እናስታውስና ለተጨነቁም እንራራ በማለት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም
ሞገስ ፀጋዬ