በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ለነገ የሚተው የቤት ስራ አይደለም:: ለነዚህ ዜጎች የሚደረጉ ድጋፎች የገንዘብ፣ ቁሳቁስ፤ እንዲሁም ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊና አእምሯዊ ሊሆኑ ይችላሉ::በተለይም ሴቶችና ህፃናት በእንዲህ አይነት ችግሮች ውስጥ ሲገኙ ደግሞ ድጋፉ ፈጥኖ እንዲደርስ ማድረግ ግድ ነው::
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑን በአዳማ መልካ አዳማ ሆቴል ይሄን ታሳቢ ያደረገ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥተል:: ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም በዘለቀው የስልጠና መርሐ ግብር መክፈቻ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንደተናገሩት፣ ስልጠናው ዘርፈ ብዙ ዓላማ ያለው ሲሆን በዋናነት የስነ ልቦና፤ የማህበራዊ እና የአእምሮ ጤና ድጋፍ አገልግሎቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ የታሰበ ነው::
በዘርፉ የሚታየውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት እንደሚቀርፍ ጠቁመዋል:: የተቀናጀና በእውቀት ላይ የተመሠረተ የድጋፍ አገልግሎት መስጠት ያስችላልም ብለዋል:: ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር ማለሙንም አንስተዋል:: ይህ ስልጠና የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሲሆን በዋነኛነትም በጾታዊ ጥቃት ምላሽ አሰጣጥ፣ በአዕምሮ ጤና፣ በማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ እንዲሁም በህጻናት ጉዳይ አያያዝ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል:: ስልጠናው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ባገኘው ድጋፍ በትግራይ፤ በአፋር፤ በኦሮሚያ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በግጭት ምክንያት የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ለማቋቋም የነደፈው የአምስት ዓመት ፕሮጀክት የትግበራ እንቅስቃሴ አካልም ነው::
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የጤና ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ይሄው ስልጠና በጦርነት ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የተቀናጀ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ስልጠናው ጾታዊ ጥቃትን መከላከልና ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግንም ታሳቢ እንዳደረገ ተናግረዋል:: ስልጠናው የተሰጠው ለሐይማኖት አባቶችና ለታዋቂ ግለሰቦች ሲሆን የማህበራዊና የአእምሮ ጤና ባለሞያዎችም በስፋት ተሳትፈውበታል::
በስልጠናው ተካፋይ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ ብያና ዋኬኖ፣ የመጡት ከምዕራብ ወለጋ ነጆ ወረዳ ነው:: የወረዳው ማህበረሰብ አስተባባሪም ናቸው:: ወረዳው ከፍተኛ ተፈናቃይ ያለበት ሲሆን፣ 15ሺ667 ተፈናቃይ አባ ወራ መኖሩን ይናገራሉ:: ከነዚህም የሴቶች ቁጥር 5 ሺ 569 ሲሆን የህፃናትና ታዳጊዎችም ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ:: ‹‹ለመፈናቀል የዳረገን ግጭት መነሻ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ጋር የሚያዋስን ድንበር ነበር›› በማለት የሚያስታውሱት ብያና ይሄው ችግር ስር እየሰደደ መጥቶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በመድረስ በርካቶችን ከቀያቸው ሊያፈናቅላቸው እንደበቃ ይገልፃሉ::
በዚህ መካከል በርካታ ሴቶችና ህፃናትም ለተለያየ ጥቃት መዳረጋቸውን ያወሳሉ:: በማንኛውም ችግር ወቅት ከሌላው ሕብረተሰብ በተለየ ሁኔታ ሴቶችና ህፃናት ለኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ችግሮች መጋለጣቸውንና ለእነሱም ፈጥኖ መድረስ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል:: 17 ወረዳ ባለው በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ500 ሺህ ሕዝብ በላይ ከቀየው መፈናቀሉን የሚጠቁሙ መረጃዎች እንዳሉ የጠቀሱት እኚህ አባት፣ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን መገመት እንደሚቻልም ይናገራሉ::
ከቄለም ወለጋ ደንቢዶሎ የመጡት የስልጠናው ተሳታፊ አቶ ደሳለኝ ታፈሰ፣ በአካባቢው በተፈጠረ ችግር ነዋሪው መፈናቀል ብቻ ሳይሆን የተለያየ ችግር እንደ ደረሰበት አስረድተዋል:: በዚህም ህፃናት እናትና አባታቸውን አጥተዋል፣ ቤተሰብ ተለያይቷል፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎችም በግጭቱ ሞተዋል:: ከዚህ ውስጥ የቤተሰብ ኃላፊ በመሆናቸውና በተለያየ ምክንያት መሸሽ የማይችሉት ሴት ተጎጂዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው::
ስልጠናው የሞቱትን ባይመልስም በሕይወት ያሉትን ችግር ይፈታል ብለው ያምናሉ:: ጉዳቱን በፀጋ ተቀብለው ለዳግም ሕይወት የመነሳሳት አቅም ከመፍጠር ጀምሮ ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ ይረዳቸዋል የሚል ሀሳብም አላቸው:: ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ ከአልባሳት ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁስና የምግብ አቅርቦት ድጋፍ በማድረግ እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል::
በምዕራብ ሸዋ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ የሥራ ሂደት መሪ የሆኑት አሰልጣኝ አስካለች ቀነአ እንደሚሉት፣ ስልጠናው የተዘጋጀው በነሱ አካባቢና በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የሰላም ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ችግሩን ተቋቁመው በትንሽ ድጋፍ ችግሩን ማለፍ እንዲችሉ ለማድረግ ነው:: ‹‹ሴቶች በሰላሙ እጦት ተደፍረዋል፤ ቤት ንብረታቸውን ተቀምተዋል:: ከኢኮኖሚና ከአካል በላይ በእእምሮና ስነልቦናቸው ላይ ከፍተኛ ችግር ደርሶባቸዋል›› ያሉት አሰልጣኝ አስካለች፣ እሳቸው የሚሰጡት ስልጠናም ይሄን ችግር መቅረፍና ሴቶች ከችግሩ እንዲያገግሙ ማስቻልን ያካትታል:: ከሚሰጧቸው ስልጠናዎች ዓይነትም የአእምሮ ጤና እና የስነ አእምሮና ማህበራዊ ድጋፍ (Mental Health and Pscho social Support)፣ የሴቶችና ህፃናት ጥቃትን እንዴት አድርጎ መምራት፣ ማስተናገድና ወደነበሩት እንዲመለሱ የሚያደርጉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው::
አሰልጣኝዋ ስልጠናውን ከመስጠታቸው ቀደም ብሎ ሰልጣኞቹ በጉዳዮቹ ላይ ቀደም ብለው ምን ያህል ዕውቀት እንዳላቸው በዚያው የስልጠና ሂደት የሚገመገምበት ሁኔታ እንደነበረም አሰልጣኟ ተናግረዋል:: ሰልጣኞች ከስልጠናው ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ግንዛቤ መጨበጣቸውን የሚያረጋግጥ ፈተና እንደወሰዱም አክለዋል::
‹‹በአብዛኛው በአእምሮ ጤና ላይ ስለምንሰራ ያገኙት ልምድና ዕውቀት ምን ያህል ያግዛቸዋል ብለን እንገመግማለን›› ያሉት አሰልጣኟ፣ ስልጠናው ሴቶችን ጨምሮ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ወደ ጤናቸው እንዲመለሱ ያስችላል ብለው ያምናሉ:: በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ተጎጂ የሆኑ ሰዎች አብዛኞቹ ተስፋ ስለቆረጡና በደረሰባቸው ችግር አእምሯቸው ስለተጎዳ ምንም መነሳሳት እንደሌላቸው የጠቆሙት አሰልጣኟ፣ ስልጠናው አእምሯቸውን ለሥራም ሆነ ለማንኛውም ዝግጁ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሎ እንደታመነበት ያስረዳሉ:: ስልጠናው በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎች ተሰጥቶም ሴቶች ወደ አምራችነትና ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው እንዲመለሱ በማድረግ የተሻለ ውጤት ማምጣቱ ታይቷል:: በኦሮሚያ ክልል ባሉ ተጎጂ ሴቶች ላይም ከስልጠናው በኋላ ይሄው ሁኔታ ይመጣል ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል::
ሲስተር ካሰች ለታ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመጣች ሲሆን ስልጠናውን ከሰጡ ባለሙያዎችም አንዷ ናት:: ሲስተር ካሰች ስልጠናውን የሰጠችው በአእምሮ ጤና ላይ ሲሆን ስልጠናው በሴቶችና ህፃናት ላይ በሰላም እጦት ከደረሰው ችግር አንፃር አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን ታስረዳለች:: እንደ ምክንያት የምታነሳውም ሴቶች፤ ህፃናትና፤ አቅመ ደካማ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአደጋው ሲጋለጡ በርካታ ችግሮች የሚደርሱባቸው መሆኑን ነው:: ከሚደርስባቸው ችግር አንዱና ዋንኛው የስነ ልቦና ችግር መሆኑንም ታወሳለች:: የአእምሮና አካላዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚደርስባቸው መሆኑንም ታክላለች::ከዚህ ችግር ውስጥ ወጥተው ወደ ቀድሞው ማንነታቸውና ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማስቻል ስልጠና መስጠት ወሳኝ መሆኑንም ትጠቁማለች::
‹‹ተጎጂዎቹ አካላቸውም ሆነ አእምሯቸው ጤናማ ካልሆነ ምርታማ መሆን አይችሉም:: ምርታማ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞም ድህነት ይመጣባቸዋል›› ስትልም ለሚመለከታቸው አካላት በየደረጃው ስልጠናውን መስጠት በሕብረተሰብ ክፍሎቹ ላይ በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ችግር እንደሚቀርፍ ታምኖበትና ከተሞክሮም ታይቶ ስልጠናው እንደተሰጠ ትናገራለች:: የስልጠናው ዓላማ ተጎጂዎቹ ሴቶች በአጠቃላይም የሕብረተሰብ ክፍሎች በጉዳቱ ምክንያት የደረሰባቸውን ጠባሳ አስወግዶ ትክክለኛ አቋም ያላቸው ምርታማ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን ተናግራለች::
‹‹በግጭት ወይም በጦርነትና ይሄን ተከትሎ ከሚመጣ መፈናቀል ጋር የተደፈሩ፤ የተደበደቡና አካላቸው የጎደለ ሴቶች ይኖራሉ:: እነዚህ ጉዳቶች ደግሞ የአእምሮ በሽታ ያመጣሉ›› የምትለው ሲስተር ካሰች፣ ሰልጣኞቹ በስልጠናው ባገኙት ዕውቀት በመታገዝ የተጎጂዎቹን ችግር እየለዩ ለመፍታት መሰል ስልጠናዎች ያስፈልጓቸዋል ብላ ታምናለች:: ስልጠናው ሰልጣኞቹ የሚችሉትን የሴቶቹን አእምሮ ህመም ለይተው እንዲያክሙ የማይችሉትን ደግሞ በጊዜ ወደ ሌላ ሕክምና ተቋም እንዲልኩ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም አክላለች::
እንደ ሲስተር ካሰች ገለፃ፣ በስልጠናው የስነ ልቦና ባለሙያዎችን መካፈላቸው በፊናቸው የስነ ልቦና ምክር እየሰጡ ተጎጂዎቹ ካለባቸው ችግር ወጥተው ጤናማ ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲመሩም ያግዛል በዚህም ችግሮች ፈጥነው ይቀረፋሉ የሚል ተስፋ አላት:: ስልጠናውን ‹ወቅታዊ፤ አስፈላጊና አንገብጋቢ› ስትል ገልፃዋለች:: በተለያየ ጤና ድርጅት የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች በብዛት ላይኖሩ እንደሚችሉ የምትጠቁመው ሲስተር ካሰች፣ ስልጠናውን የወሰዱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በስልጠናው በመታገዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች እንዲያግዙ የሚያስችል መሆኑንም ትናገራለች:: ለአብነትም የስነልቦና ባለሙያዎች ምክር ለሚያስፈልጋቸው ምክር በመለገስ፤ ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ነርሶችና ብዙ ባለሙያዎች ስላሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ለይተው ሕክምና እንዲሰጡ ያደርጋል::
በዚህ የአእምሮ ህመም ምልክት የሚታይባቸውን ሴቶች መርዳት ያስችላል:: በተለያየ ምክንያት አእምሯቸው የተጎዳ ሴቶች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው ቀድሞ እንደነበረው አይሆንም:: ስልጠናው ተጎጂ ሴቶችን እንዲሁም አጠቃላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማነሳሳትና በማነቃቃት የማቋቋም ሥራ መሥራት እንደሚያስችልም ታብራራለች:: የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው በዋነኛነት በአዕምሮ ጤና፣ በጾታዊ ጥቃት ምላሽ አሰጣጥ፣ በማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ እንዲሁም በህጻናት ጉዳይ አያያዝ ላይ ማተኮሩንም ትጠቁማለች:: የስልጠናው የመጨረሻ ግብም ተጎጂዎቹን ከገቡበት ችግር በማውጣት ወደ አምራች፣ ጤናማ፤ ሠላማዊና ምርታማ ማድረግ እንደሆነም አስተያያቷን ሰጥታለች::
ሰው ሠራሽ ጦርነትም ሆነ የተፈጥሮ ችግርና ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ይልቅ ሴቶችን የበለጠ ተጎጂ እንደሚያደርጉ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ:: ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል የነበረ ጦርነትን አስመልክቶ በክልሉ የተደረገ ጥናት የሚያሳየውም ይሄንኑ የሴቶችን ይበልጥ ለችግር ተጋላጭነት ነው:: መደፈር፤ መገደል፤ የንብረት ውድመት፤ ዝርፊያ፤ መፈናቀልና በዚህ ወቅትም ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጥ የበለጠ በሴቶች ላይ ደርሷል:: በጦርነት ከተጎዱ የሕብብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ቁጥራቸው በእጅጉ የላቀ ሲሆን በጥናቱ እንደተመለከተው ከ409 ሺ በላይ ሴቶች ተጎጂ ናቸው:: ከ263 ሺ በላይ ደግሞ ህፃናት እንደሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2015